ባለፈው ሳምንት ህትመታችን ወፈፌው ይልቃል አዲሴ፣ እንደዚህ ቀደሙ በሌሊቱ ተነስቶ በሰፈራችን ከሚገኘው ዋርካ ስር ቆሞ እየጮኸ እያለ ከአራቱም አቅጣጫ የይልቃል አዲሴን ጩኸት እንደ መጽሐፍ ለማንበብ የሰፈራችን እና የእድራችን ሰዎች መሰባሰባቸውን አውግተናችሁ ነበር። በወቅቱም የይልቃል አዲሴን ንግግር በጥሞና እያዳመጡ እያለ አብሿሙ ክንፈ ጉደታ የይልቃል አዲሴን ንግግር ማቋረጡን እና የአብሿሙን የክንፈ ጉደታ ጥያቄ መጠየቁን እንዲሁም የወፈፌውን ይልቃል አዲሴን ምላሽ ለቀጣይ ሳምንት ይዘን እንደምንቀርብ ቃል ገብተን ነበር። በገባነው ቃል መሰረት የአብሿሙን የክንፈ ጉደታ ጥያቄ እና የወፈፌውን ይልቃል አዲሴን ምላሽ እነሆ ብለናል፤ መልካም ንባብ ።
አብሿሙ ክንፈ ጉደታ፣ ይልቃል አዲሴን የጠየቀው በሰፈራችን ለዘመናት የቆየው የችግር ቋጠሮ መፍታት ያልተቻለው ለምንድን ነው ? የሚል ነው ። ይልቃል አዲሴም የተጠየቀውን ጥያቄ ለመመለስ ጉሮሮውን እየሞረደ …. «በሰፈራችን ለዘመናት የቆየው የችግር ቋጠሮ መፍታት ያልተቻለበት አብይ ምክንያት ያልቀደሱ ቀዳሾች መበራከት ነው! » አለ እና ንግግሩን ቀጠለ …
ቀዳሾች በቅድስናቸው ሌላውን ለመባረክ ከመፈለጋቸው እና ከማሰባቸው በፊት ራሳቸውን አስባርከው የተቀደሱ ሊሆኑ ይገባል። ራስን በእርኩስ መንፈስ አስክሮ በእርኩስ መንፈስ ባቡር አሳፍሮ እየሸመጠጡ እድራችንን እና ሰፈራችንን ለመባረክ ሌት ተቀን እየሰራሁ ነው ማለት ፌዝ ነው ።
ከሰሞኑ ስለበጀት ጉድለት እና ኑሮ ውድነት በስፋት ሲወራ እየሰማን ነው። የሚገርመው ስለበጀት ጉድለቱ እና ኑሮ ውድነቱ የሚያወራን ሰው የሚነዳውን መኪና ፣ የሚመገባቸውን የምግብ አይነቶች ፣ የሚለብሳቸውን ልብሶች፣ የሚጫማቸውን ጫማዎች ወዘተ በአንክሮ ስንመለከት በሰፈራችን እና በእድራችን ላጋጠመን የበጀት ጉድለት ዐብይ ተዋናኙ ራሱ መሆኑን በግልጽ እንድንመለከት ያደርገናል። ሳይቀደሱ መቀደስ ማለት ይህም አይደል?!!
ከቀዳሾች ጋር ተያይዞ በሰፈራችን እና በእድራችን ለዘመናት ሲነገር የሚኖር ለሌብነት ሽፋን የሚሰጥ አባባል አለ፤ «ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል» የሚል። ይህ አባባል ሳይቀደሱ ቀዳሽ ነን ለሚሉ ህገወጦች ስልጣናቸውን መከታ አድርገው የሰፈራችንን እና የእድራችንን ሀብት እንዲሰርቁ በአዋጅ ያልታወጀ የህግ እውቅና ሲሰጥ ኖሯል። እስካሁን ከእንደዚህ አይነት ቀዳሾች እና አስቀዳሾች ሰፈራቸን እና እድራችን መገላገል ባለመቻሉ ለዘመናት ሰፈራችንን ሲፈታተኑ የኖሩ ያልተፈቱ ቋጠሮዎችን እንዳይፈቱ አድርጎ እያጠበቃቸው ይገኛል።
ቀዳሾች ለዘመናት በሰፈራችን እና በእድራችን እየተስተዋሉ የዘለቁ እና ሰፈራችንን ወደፊት አላራምድ ያሉ ያልተፈቱ ቋጠሮዎችን ከልብ ለመፍታት ከፈለጉ በመጀመሪያ ደረጃ ሶስት ነገሮችን እንደመርህ እንዲከተሉ እመክራለሁ።
አንደኛው እራስን ማወቅ ( self-knowledge) ነው። ይህ ማለት አንድ ሰው ራሱን እኔ ማን ነኝ ብሎ መጠየቅ መቻል እንዳለበት የሚያሳይ ከችግር የመውጫ ጥበብ ነው ። በእኔ ማን ነኝ ውስጥ ደግሞ ሰዎች ደካማ እና ጠንካራ ጎናቸውን አንድ በአንድ በዝርዝር ለይተው ማስቀመጥ ይጠበቅባቸዋል።
«እኔ ማን ነኝ» ከሚለው ጽንሰ ሃሳብ ጋር ተያይዞ የእኛን ሰፈር እና እድር የሚመሩ ፣ ለመምራት የሚራኮቱ ተፎካካሪዎች ፣ ወግ አሳላጮች እና ጥሩንባ ነፊዎች ዋነኛው እና ትልቁ ችግራቸው የሰፈራችንን እና እድራችንን ደካማ እና ጠንካራ ጎኑን ለይተው አለማወቃቸው ነው፤ ከዚህም ባለፈ የራሳቸውንም ደካማ እና ጠንካራ ጎን አንድ በአንድ ለይተው አለመገንዘባቸው ነው ። ለዚህ በርካታ አመክንዮዎችን መደርድር ይቻላል። ግን ሁሉን ቢያወሩት ሆድ ባዶ ስለሚቀር ትቸዋለሁ።
የኑሮ ውድነቱ የሰፈራችንን ሰዎች በጋለ ምጣድ ላይ እንደተጣደ ቂቤ አቅልጦ መሄጃ አሳጥቶ እያንተከተካቸው እንደሆነ እየታየ ለችግሩ መፈጠር በቀዳሾች፣ ለመቀደስ በሚፎካከሩ ሃይላት ፣ በወግ አሳላጮች እና በጡሩምባ ነፊዎች የሚሰጡት ምክንያቶች መሬት ላይ ከእውነታው ጋር የሚጣጣሙ አይደሉም። ሁሌም የተለመደ ዲስኩር ምክንያት …… ስግብግብ ነጋዴዎች ፣ የአለም አቀፉ ኢኮኖሚያዊ ጫና ፣ወዘተ ይሉሃል ። በእርግጥ ለተፈጠረው የኑሮ ውድነት እና የበጀት ጉድለት ስግብግብ ነጋዴዎች ፣ የአለም አቀፉ ኢኮኖሚያዊ ጫና ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ አያጠራጥርም። ግን ለተደጋጋጋሚ ችግሮች ከወሬ በዘለለ ሁነኛ መፍትሄ መስጠት ያስፈልጋል። ካልሆነ ግን ሁሌም ስግብግብ ነጋዴዎች፣ የአለም አቀፉ ኢኮኖሚያዊ ጫና እያሉ የተለመዱ ምክንያቶችን መደርደር ቀዳሾችን እንደ ድስኩራም የሚያሳይ እና የሚያስንቅም ነው ።
ሁነኛ መፍትሄ ለመስጠት ደግሞ የሰፈራችን እና የእድራችን ደካማ ጎኖች ምንድን ናቸው? የቀዳሾች፣ ለመቀደስ በሚፎካከሩ ሃይላት ፣ የወግ አሳላጮች እና የጡሩምባ ነፊዎች እንዲሁም የተቀዳሹ ደካማና ጠንካራ ጎን ምንድን ነው ? ብሎ ለይቶና ነቅሶ ማውጣት ያስፈልጋል።
ሰዎች የራሳቸውን ደካማ እና ጠንካራ ጎን ለይተው ካወቁ ደግሞ ቀጣዩ እርምጃ የሚሆነው ራስን አምኖ መቀበል የሚለውን ሁለተኛውን ራስን ከችግር የማውጫ መርህ ነው ። ሰዎች የራሳቸውን ጠንካራ እና ደካማ ጎን በዝርዝር ከለዩ በኋላ ጠንካራ እና ደካማ ጎናቸውን የእኔ ነው ብሎ አምኖ መቀበል ያስፈልጋል ።
የአብዛኛዎቹ የሰፈራችን ቀዳሾች እና ተቀዳሾች ግን ይህን ከችግር መውጫ መርህ ለመቀበል ከኮሶ በላይ ሲመራቸው ፤ ከኮምጣጤ በላይ ሲጎመዝዛቸው እያየን ነው ።እንዴት ሰው ራሱን አምኖ መቀበል ያቅተዋል ? ደካማ ከሆንኩ በቃ ደካማ ነኝ! ድክመቴን አምኜ ስላተቀበልኩ ብቻ ጠንካራ መሆን አልችልም። ጠንካራ ከሆንኩ በቃ ጠንካራ ነኝ ! ሰዎች ደካማ ነህ ቢሉኝ እንኳን ደካማ ልሆን አልችልም ። ምክንያቱም ስራዬ ምስክር ነውና ! ስለዚህ ሰው እንዴት ራሱን ይዋሻል ? ራሱን የዋሸ ሰው እንዴት ሌሎች እንዲያምኑት ይፈልጋል?
ራሱን አምኖ የተቀበለ ሰው ጠንካራ ጎኑን እንደ ጠናካራ ጎኑ በመያዝ ከአለበት ደረጃ ወርዶ ላለመገኘት ጠንክሮ ይሰራል። ደካማ ከሆነም ደግሞ ደካማ ጎኑን ለማሻሻል የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቅሞ ድክመቱን ለወደፊት ስኬቱ መስፈንጠሪያ ቦርድ አድርጎ ይጠቀማል። ደካማ ጎኑን ለማሻሻል የሌሎችን ተሞክሮዎች በመቅሰም ሌሎች ከደረሱበት ለመድረስ በርትቶ እንዲሰራም ያደርገዋል።
ራሱን አምኖ የማይቀበል ከሆነ እና ደካማ ጎኑን የማያውቅ ከሆነ ችግሩን ድል ለመንሳት እና ስኬትን ለማምጣት ወደ ፊት ለመስፈንጠር ሚያደርገውን ጥረት በሙሉ በችግር የተተበተበ ያደርገዋል። እንደዚህ አይነት ሰዎች አደርጋቸዋለሁ ብለው ለህዝብ የሚገባቸው ቃለ ማሃላዎች መፈጽም ይሳናቸዋል። የገቡትን ቃል እንፈጽም ቢሉ እንኳን ውሃን በወንፊት ለመያዝ እንደሚሞከር ሰው ክንቱ ድካም ይደክማሉ።
ሌላው ሁሉም ቀዳሾች በመርህ ደረጃ ሊቀበሉት የሚገባው ሶስተኛው አብይ ጉዳይ ደግሞ ለራሳችን የምንሰጠው ዋጋ (self-esteem) የሚባለውን ነገር ነው። ይህ የችግር መውጫ መርህ ለራሳችን የምንሰጠው ዋጋ ካለን ብቃት ጋር የተስተካከለ መሆን እንደሚገባው ያስገነዝባል ። ሰው ጠንካራ ጎኑን እና ደካማ ጎኑን ለይቶ ከተገነዘበ በኋላ ራሱን አምኖ መቀበል አለበት ። ራሱን አምኖ የተቀበለ ሰው ደግሞ ጥንካሬውን እና ድክምቱን በሚገባ የሚያገናዝብ ስለሆነ ለራሱ የሚሰጠው ዋጋ ካለው ብቃት ጋር ተመጣጣኝ እንዲሆን ያደርገዋል።
ማንም ሰው ለራሱ ካለው ጥንካሬ የያነሰ ዋጋ ሊሰጥ አይገባም ። ሰውየው ካለው ጥንካሬ በላይም ለራሱ ዋጋ ከሰጠ ችግር ይኖረዋል። ስለዚህ የሰፈራችን ቀዳሾች እና አስቀዳሾች ለራሳቸው የሚሰጡት ዋጋ ካላቸው ብቃት ጋር ተመጣጣኝ የሚሆን ከሆነ በሰፈራችን እና በእድራችን ውስጥ የሁለተናዊ መሻሻል ማነቆ የሆኑ ቋጠሮዎችን በቀላሉ መፍታት ያስችላቸዋል።
ከላይ የተጠቀሱት መርሆች የማንከተል ከሆነ ግን በችግር ላይ ችግር በቋጠሮ ላይ ቋጠሮዎችን እየጨመርን የወደፊት በሚመጣው ሀገር ተረካቢ ትውልድ ሊፈታው የማይችል የችግር ድሪቶ ጥለን እንደምናልፍ ማወቅ ይኖርብናል። ይህ ደግሞ የእኛን ትውልድ ለታሪክ ተወቃሽነት ያበቃል።
ስለሆነም የተቋጠረውን ቋጠሮ ለመፍታት ከተፈለገ ቋጠሮውን ለመፍታት ግንባር ቀደም ቦታውን የያዙ ቀዳሾች እና ወደ ፊትም ቦታውን ለመያዝ የሚፎካከር ሃይሎች፣ ጡርንባ ነፊዎች እና ወግ አሳላጮች ከላይ በተጠቀሱት መርሆች ሊቀደሱ እና ሊባረኩ ይገባል።
ለዘመናት የቆዩትን የችግር ችንካሮች ከስር ለመንቀል ከላይ ከተጠቀሱት መርሆች በተጨማሪ የእድራችንና የሰፈራችን መሪዎች ፣ ተፎካካሪ ሃይሎች ፣ ወግ አሳላጮች እና ጡርምባ ነፊዎች እንዲሁም አስቀዳሾች ሊከተሏቸው የሚገቡ ሌሎች ከችግር የመውጫ ጥበቦችም አሉ። ከእነኝህ መካከል አንደኛው Civility (polite way of acting towards the other) የሚባለው ነው ።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የእድራችንና የሰፈራችን መሪዎች፣ ተፎካካሪዎች ወግ አሳላጮች እና ጡሩምባ ነፊዎች የሚያደርጉትን እንያንዳንዱ ንግግር እና ድርጊት ከጉራ እና ከትዕቢት ይልቅ ፈገግታን የተላበሰ መሆን ይገባዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ ቀደሾች እና አስቀዳሾች በመገናኛ ብዙኃን ወይም በሌሎች አማራጮች ለህዝብ የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች በትዕቢት የተሞሉ እና ሀገር አፍራሽ ናቸው ። እነኝህን ቀዳሾች እና አስቀዳሾች ለምን እንደዚህ ታድርጋለህ? ሲባሉ ምን ያገባህ የሚል መለስ መስጠጥ ይቀናቸዋል። ይህ ትክክል አይደለም። እንደዚህ አይነት የትዕቢት ንግሮች የእድራችንና የሰፈራችን አባላት ልብ ከማሻከሩም ባለፈ ለዘመናት ተቋጥሮ አልፈታ ባለው ችግር ላይ ሌላ የችግር ቋጠሮ ይጨምራል።
ስለሆነም የእድራችንና የሰፈራችን መሪዎች ፣ ተፎካካሪ ሃይሎች ፣ ወግ አሳላጮች እና ጡርምባ ነፊዎች በእያንዳንዱ እርምጃችሁ እና ንግግራችሁ ከትዕቢት እና ንቀት ይልቅ ቅንነት እና ፈገግታ የተሞላ ንግግር ብታደርጉ መልካም ነው ።
ሌላው የእድራችንና የሰፈራችን መሪዎች ፣ ተፎካካሪ ሃይሎች ፣ ወግ አሳላጮች እና ጡርምባ ነፊዎች ሊከተሉት የሚገባው ነገር Open mindedness ወይም (the interest to listen the ideas of the other) የሚለውን ነው ።
ሰዎች ስለሚናገሩት ነገር ጆሮ ሰጥቶ ማዳመጥ ያስፈልጋል። የራስ መላጣ እና የራስ ነውር ለባለቤቱ አይታይም እንዲሉ ብልህ ቀዳሾች እና አስቀዳሾች በተቃራኒ ጎራ የቆሙ ሰዎች የሚነግሯቸውን ህጸጾች በቅንነት ይቀበሉታል ። በነገራችን ላይ ይህ ህጸጽን በደስታ የመቀበል ልምድ አንዱ የስልጣኔ መገለጫም ነው ።
ነገር ግን ህጸጻችንን ሲነግሩን ህጸጽ የነገሩን ሰዎች እንደጠላት መቁጠር እና እኔ ከምለው ውጭ ሌላው ምን ያውቃል ፤ ምንስ አገባው ብሎ መታበይ ለዘመናት በሰፈራችን እና በእድራችን የሚስተዋሉ የችግር ቋጠሮዎችን ከመደረት በስተቀር ሌላ ትርፍ የለውም ። ለሰፈራችን ህልውና መደላድል አንድም ስንዝር አስተዋጾ ማበርከት አይችልም ። ስለሆነም የሰፈራችንን የችግር ቋጠሮዎች ለመፍታት Open minded የሆነ የሰፈር እና የእድር መሪ ፣ ተፎካካሪ ሃይል፣ ወሬ አሳላጭ እና ጡሩምባ ነፊ ያስፈልገናል።
ከሰሞኑ የሰፈራችን መሪዎች እንደተናገሩት የሰፈራችን እና እድራችን አመታዊ በጀት በርካታ በጀት ጉድለት አጋጥሞታል። ለዚህ የበጀት ጉድለት የዳረገን ዐብይ ምክንያት ደግሞ በሰፈራችን እና በእድራችን ውስጥ የተደረገው ጦርነት መሆኑን በጀት አቅራቢው አስረድተዋል። ለጦርነቱ መነሻ ደግሞ አለመደማመጥ መሆኑን ለመገንዘብ የግድ የፖለቲካ ሊቅ መሆን አይሻም ። አሁን በተለያዩ የሰፈራችን እና የእድራችን አካባቢዎች የሚታዩ አለመግባባቶች በስፋት እየተስተዋለ ነው ። እነኝህ አለመግባባቶች ደግሞ በአግባቡ ተደማምጠን የማንፋታ ከሆነ ምን አልባትም ከዚህ ቀደሙ ከምናውቃቸው የባሱ አውዳሚ ጦርነቶችን ሊያስከትሉ ይችላሉ። ይህ ደግሞ በሃገር በጀት ላይ ከሚፈጥረው ጫና ባለፈ ሰዎችን ሞት እና ስደት መዳረጉ አይቀርም ። ይህ ደግሞ አይደለም በጀት እጥረት፤ በጀት መዳሚ አካልም ያሳጣናል። ስለዚህ በየአካባቢው የሚነሱ አለመግባባቶችን ምክንያታቸው ምን እንደሆነ በማዳመጥ በአግባቡ መፍታት ያስፈልጋል ባይ ነኝ ።
ሌላው የሰፈር እና የእድር መሪዎቻችን ፣ ተፎካካሪ ሃይሎች ፣ ወግ አሳላጮች እና ጡሩምባ ነፊዎች ሊከተሉት የሚገባው ነገር ፣ Civic mindedness ወይም (give priority for common good than private interest) የሚለውን ነው ።
ይህ ማለት ሁሉም የሰፈራችን እና የእድራችን አባላት እንዲሁም የሰፈራችን እና የእድራችን መሪዎች ፣ተፎካካሪ ሃይሎች፣ ወግ አሳላጮች እና ጡሩምባ ነፊዎች ከራሳቸው ጥቅም ይልቅ ሰፈራችን እና እድራችን ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው የሚያስገነዝብ የጥሩ ዜጋ መገለጫ ነው ።
አሁን አሁን በሰፈራችን እና በእድራችን የሚስተዋለው ነገር እጅጉን አሳሳቢ ነው ። ከሰፈራችን ህልውና ይልቅ ራሳቸውን የሚያስቀድሙ የሰፈራችን እና የእድራችን መሪዎች ፣ተፎካካሪ ሃይሎች ፣ ወግ አሳላጮች እና ጡሩምባ ነፊዎች እየተባራከቱ ነው ። ይህ ደግሞ የሰፈራችን እና የእድራችን የችግር ቋጠሮዎች ይበልጡኑ ያጠነክራቸው እንደሆን እንጂ ከችግር መውጫ መንገድ አመካለች አለመሆኑን ለአቅመ አዳም እና ሄዋን ያልደረሱ ህጻናት እንኳን የሚረዱት ሃቅ ነው ። ስለሆነም የሰፈራችን እና የእድራችንን የዘመናት የችግር ቋጠሮ ለመፍታት ከመቸውም ጊዜ በላይ ለጋራ ጥቅም ቅድሚያ እንስጥ ብሎ ንግግሩን ወፈፌው ይልቃል ሲጨርስ ስብሰባውን ሲታደም የነበረው ህዝብ ጥሩ ትምህርት ማግኘታቸውን ለማሳየት ይልቃል አዲሴን በጭብጨባ ሸኙት ።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ሰኔ 2 ቀን 2014 ዓ.ም