የሦስት መንግሥታት ታሪክ አዘል መጽሐፍ መሆናቸውን ከጉሮሮአቸው የሚፈልቁት ቃላቶች ይናገራሉ። ህገ መንግሥቱ እንዴት ተረቀቀ? እነማን አገልግለውበት አለፉ?፤ እነማንስ ጥሩ ሥራ ሠሩ? ወዘተ… የሚሉትን ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ ሰውም ከእርሳቸው ውጪ የዓይን እማኝ ያለ አይመስልም።
አብጠርጥረው በነበሩባቸው ጊዜያት የነበሩ ክንውኖችን ይተርካሉ። እኝህ ሰው ሦስት መንግሥታትን አማክረዋል፤ በሦስቱም መንግሥታት በተረቀቀ ህገ መንግሥት ውስጥ ተሳታፊ ሆነዋል። በመምህርነት፣ በተመራማሪነትና በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይም የሠሩ ናቸው።
ለሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ መመስረት ትልቁን አሻራቸውን ያሳረፉ፤ የሸሪዓ ህግም በአገር ውስጥ እንዲተገበር ያደረጉ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል። ሁለት የተለያዩ መጽሐፎችንና ሙያዊ መጣጥፎችንም ጽፈዋል። በአሁኑ ጊዜ የህገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አባል ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ። የዛሬው የህይወት እንዲህ ናት እንግዳችን ዶክተር ፋሲል ናሆም። ሦስት መንግሥታትን ሳያስቀይም ያገለገሉበት ተሞክሯቸው ብዙ ልምድን ያጋራልና ይድረስ ለአንባቢያን ስንል አቀረብነው።
የአስመራው ዝማም
ከሰባ ስድስት ዓመት በፊት ነው ለቤተሰቡ መኩሪያ የሆነው አንድ ህፃን ቤተሰቡን የተ ቀላቀለው። እስከ አስር ዓመቱ ድረስም ከኤርትራዋ ዋና ከተማ አስመራ አልተነቃነቀም። በዚሁ ቦታ እንደአካባቢው ህፃን ዳዴ ብሎ አደገ፤ በሜዳው ቦረቀ፤ ኳስ ተጫወተ፤ አለፍ ሲልም ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ሽር ሽር በተራራዎቹ ላይ አደረገ። ትምህርት ቤትም ተቀላቀለ።
«ልጅነቴ በደስታ የተሞላ ነበር። ቤተሰቤ በፍቅርና በመተሳሰብ አሳድገውኛል። በመካከለኛ ገቢ የሚተዳደሩ ቢሆኑም ሊሟላልኝ የሚገባውን ነገር ነፍገውኝ አያውቁም። ሁለቱም በመንግሥት ተቀጥረው በመሥራታቸው ደግሞ የልጅ አስተዳደግን በሚገባ ያውቁበታል። ያው እኔ የማስታውሰው እናቴን ብቻ ቢሆንም» ሲሉ ያጫወቱን የትናንቱ ህፃን የዛሬው አዛውንት ዶክተር ፋሲል ናቸው። በልጅነታቸው በቤተክርስቲያን በዝማሬ (በኳዬር) ውስጥ ያገለግሉ ነበር። ስለዚህም እሁድን አብልጠው ይወዷታል። እሁድ ለልጅነታቸው ማስታወሻና የደስታ ስሜት መግለጫ ቀን ናት። በልጅነታቸው ዝምተኛና ሥርዓት ያለው ልጅ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በእነዚህ መድረኮች ላይ እንዲሳተፉ መደረጉ በንግግር የተሻሉ እንዲሆኑ እድል ሰጥቷቸዋል።
ሀቀኛ እንዲሆኑም አግዟቸዋል። ልጆች በጨዋታ መካከል ይጣላሉ። እርሳቸው ግን ከጓደኞቻቸው ጋር በፍቅር ለማሳለፍ ያስቻላቸው ይህ እንደሆነ ይናገራሉ። በባህሪያቸው ምስጉንና ጠንቃቃ፤ ያመኑበትን ሀሳብ ግብ ሳያደርሱ የማያቆሙ በመሆናቸው የክፍል ጓደኞቻቸው «ፊሊያስ ፎግ» እያሉ ይጠሯቸው እንደነበር የሚያስታውሱት ዶክተር ፋሲል፤ ፊሊያስ ፎክ አንድ መጽሀፍ ላይ ያለ ገጸባህሪ ነው። ረጋ ያለ፣ ጠንቃቃና ዓለምን በ80 ቀናት የዞረ እንዲሁም ያሰበውን የሚፈጽም ነው ይላሉ።
ከዚህ አኳያም ይመስላል ማንኛውም ልጅ መሆን የሚፈልገውን ሲመርጥ እርሳቸውም አንድ ነገር መሆን እንደሚፈልጉ ያስቀመጡት። በልጅነታቸው በህክምናው ዘርፍ ዶክተር መሆንን ይመኙ ነበር። ምክንያታቸው ደግሞ እናታቸው ናት። እናታቸው አዋላጅ ነርስ በመሆ ናቸው ሰዎችን ሲረዱ ማየታቸው ያስደስታቸዋል። በዚያ ላይ ቤቱ ሁልጊዜ የህክምና ጉዳይ የሚ ወራበትና የሚተገበርበትም ጭምር ነው። እናታቸው በቤት ሳይኖሩ እንኳን ለጎረቤት የተለያየ እገዛ የሚያደርጉት እርሳቸው ነበሩ። ይህ ደግሞ ሙያውን አጥብቀው እንዲወዱት አደረጋቸው።
ከፕሪንቺፔ እስከ አሜሪካ
ትምህርታቸውን «ሀ» ያሉት በዚያው በትውልድ ቀያቸው አስመራ ነው፤ «ፕሪንችፔ» በሚባል የጣሊያን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት። ለአምስት ዓመታት በዚህ ቆይተዋል። አስተማሪዎቻቸው ደግሞ በአብዛኞቹ ሴቶች በመሆናቸው በሥነ ምግባርም ሆነ በውጤታማነት የተሻለ ተማሪ እንዲሆኑ አግዟቸዋል። ከወንዶቹ ይልቅ ሴቶች ለተማሪዎች ቅርብ ናቸው የሚሉት ባለታሪኩ፤ በእንክብካቤ ጭምር ማስተማር ያውቁበታል። በዚህም ውጤታማና ሥነምግባር ያለው ተማሪ ለመሆን በቅቻለሁ። ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ የደረጃ ተማሪ የሆኑትም በዚህ ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ። የእናታቸው አዋላጅ ነርስ መሆን እርሳቸውን በአንድ ቦታ እንዳይማሩ አድርጓቸዋል። ከአምስተኛ ክፍል በኋላ ጉዞ ወደ ሌላኛዋ የኤርትራ ትንሽ ከተማ «ሰንአፈ» እንዲያደርጉም አስገድዷቸዋል።
በዚህ ሳያበቃም እስከአምስተኛ ክፍል በነበረው የትምህርት ቆይታቸው ሙሉ ትምህርቱን በጣ ሊያንኛ በመከታተላቸው የተነሳ ሌላ ቋንቋ እን ዳይችሉ ሆነዋልና ለሌላ ቋንቋ ራሳቸውን ማዘጋጀት ሌላ ፈተና ሆኖባቸው። በዚህ ቦታ መማር የሚቻለው በአማርኛ፣ በትግሪኛና በአረብኛ ቋንቋ ነው። ስለዚህ ይህንን ቋንቋ ምንም ስለማያውቁ ከአምስተኛ ክፍል ወደ ሦስተኛ ክፍል ዝቅ እንዲሉ ተደረጉ። ዶክተር ፋሲል፤ በጣም ጎበዝ ተማሪ ናቸውና ሦስተኛ ክፍል የገቡበትን ቋንቋ በዓመት ውስጥ አጠናቀው አምስተኛ ክፍል ለመግባት ችለዋል። ቀጣዩን የትምህርት ክፍል የተማሩት ደግሞ እንዲሁ ሌላ አካባቢ በመሄድ ነበር። አዲግራት አግአዚ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት። በዚህ ትምህርት ቤት ሌላ ቋንቋ ማለትም እንግሊዝኛን ለምደዋል። በዓመት ውስጥም ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍልን አጠናቀዋል። ከዘጠኝ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል የተማሩት ደግሞ «ኢትዮጵያን ኢቫንጄሊካል ኮሌጅ» ተብሎ በግል ደረጃ በሚሲዮናዊያን አማካኝነት በተቋቋመው ትምህርት ቤት ሲሆን፤ መገኛው ደብረዘይት ነው። አዳሪ ትምህርት ቤት በመሆኑ ብዙውን ነገር በዚያ እያገኙ ነው የተማሩት። ይህ ደግሞ ጠንካራ ተማሪ አደረጋቸው።
ታዋቂነታቸው ጨመረ፣ የኮሌጁ የተማሪዎች ፕሬዚዳንት እስከመሆን ደረሱ። በቀጣይ ጉዞው ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ሆነ። በዚህ ኮሌጅ የልጅነት ህልማቸውን ለማሳካት የመጀመሪያ ጥረታቸው ያደረጉት ሳይንስ ትምህርት ክፍል መግባት ነው። ምክንያቱም በወቅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የህክምና ትምህርት አይሰጥም። እናም ለአንድ ዓመት ከህክምናው ጋር ምንም ያልተገናኘ ትምህርት ተማሩ።
ፍላጎታቸው ባለመሳካቱም ትምህርቱን ለማቋረጥ ተገደዱ። ምን ማጥናት እንዳለባቸው ሲያሰላስሉም ታሪክና ቋንቋ ጥሩ እንደሆነ በማመናቸው ወደእዚያ የትምህርት መስክ ገቡ። በበፊቱ አርት ፋካሊቲ በአሁኑ የማህበራዊ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ገብተው ትምህርቱን መከታተል ጀመሩ። ግን በዚህም ብዙ መቆየት አልቻሉም። ከዓመታት ትምህርት በኋላ ዳግም የትምህርት መስካቸውን ወደ ህግ አዛወሩ።
በጣሊያንኛ ቋንቋ የተጻፉ ብዙ ማጣቀሻ መጽሀፍት በዩኒቨርሲቲው በመገኘቱ ይህ ምር ጫቸው የተሻለ እንደሆነ አምነውም ቀጠሉበት። በህግ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውንም በማዕረግ ተመረቁ። ከዚያ ቀጣዩ የትምህርት ክትትላቸው ወደ አሜሪካ የሚወስዳቸው ሲሆን፤ «የይል ዩኒቨርሲቲ» በተባለ የህግ ትምህርት ቤት ገቡ። በዚህም ጉብዝናቸው ሳይቀንስ ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ያዙ። ይህ አጋጣሚ ደግሞ ከቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን ጋር እንዲማሩ እንዳገዛቸው አጫውተውናል። ከዚያ የተለያዩ ሥልጠናዎችን ከመውሰድ ባለፈ ትምህርታቸውን አልቀጠሉም።
ህግን በሥራ
የማዕረግ ተመራቂ በመሆናቸው ዩኒቨርሲቲው ሊለቃቸው አልፈለገምና በዚያው ቀርተው እን ዲያስተምሩ ሲፈቅድ ሥራቸውን ጀመሩ። ይህ ደግሞ በተማሩበት ትምህርት ቤት እንዲቆዩ አድርጓቸዋል። የተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎችን በመቀያየር ለ12 ዓመት አገልግለዋል። ከመማር ማስተማሩ ውጪ ደግሞ የኢትዮጵያ የህግ መጽሄት ዋና አዘጋጅም በመሆን ሠርተውበታል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የህግ አማካሪም ነበሩ።
ደርግ ሲገባ ደግሞ ህገመንግሥት ማርቀቅ በመፈለጉ ከዩኒቨርሲቲው አምስት ሰዎች ተመ ርጠው «የብሔረሰብ ኢንስቲትዩት» የሚባል ተቋቋመና ወደዚያ እንዲሠሩ ተወሰዱ። በዚያም ዓመታትን ሠሩ። ሥራው ሲጀመር ግማሽ ቀን እያስተማሩ ግማሽ ቀን እንዲሠሩ ነበር። ሆኖም ሥራው በመክበዱ የተነሳ ሙሉ ጊዜያቸውን በዚያ እንዲያሳልፉ ሆነዋል። እርሳቸው ይህንን አልጠሉትም። ምክንያቱም እየተማርኩበት ነው ብለው ያምናሉ።
ይሁንና ይህ የለፉበት ህገመንግሥት ተግባራዊ ባለመሆኑ ቅር ብሏቸዋል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ከጎረቤት አገራት ጋር እየተለዋወጡ እንዲያስተምሩ በሚያደርግበት ወቅት ደግሞ ለሁለት መንፈቅ ዓመት (ተርም) ያህል ሱዳን ውስጥ «ካርቱም ዩኒቨርሲቲ» በመሄድ እንዲያስተምሩ ከተመረጡ መምህራን መካከል አንዱ እንደነበሩ ያስታውሳሉ።
እንዳውም «ይህ ጊዜ ያስተማርኩበት ብቻ አይደለም፤ የተማርኩበትም ጭምር ነው» ይላሉ። ምክንያታቸው የሸሪዓ ህግን በአግባቡ አውቀው መምጣታቸውና በአገራቸው ህጉ እንዲረቀቅና አሰራሮች እንዲኖሩ ማስቻላቸው ነው። በህጉ ላይ በተለይ ቁርአን ሲተረጎም አራት የሆኑ የአተረጓጎም ስልቶችን እንዲያውቁ የሆኑት በዚህ እድል በመሆኑ ማስተማር ሳይሆን መማርንም አይቼበታለሁ ይላሉ።
ሌላው ሠራሁበት ያሉት የየክልሉን ቋንቋ የሚችል ዳኛ በአገሪቱ ውስጥ ባለመኖሩ እነዚህን ዳኞች ለማሠልጠን ከአካባቢው መምህራን በመመልመል በቋንቋው የመዳኘትን ሥራን ለመፍጠር በተመሰረተው የዛሬው ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በእነርሱ ጊዜ የተቋቋመው «የሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ» መስራችም ፕሬዚዳንትም የሆኑበት ቦታ ነው።
ሌላው የሥራ ጊዜያቸው ፍትሀ ብሔሩ ያሉበትን ችግሮች ለማሻሻል ሲባል «የፍትህና የህግ ምርምር ኢንስቲትዩት» እንዲቋቋም ሲደረግ ከአቃቃሚዎች መካከል አንዱ በመሆን የእርሳቸው ተሳትፎ ትልቅ ነበር። በዲንነትም ለስምንት ዓመታት አገልግለዋል። ቀጣዩ ሥራ በህገ መንግሥት ላይ የሚያወያይ አካል ሲቋቋም እርሳቸውም ተመራጭ ነበሩና የተለያዩ ተግባራትን ከውነዋል።
ይህንን ሁሉ ሲያደርጉ ግን በሙሉ ቀን ተግባር አልነበረም። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ በመሆንም ጭምር እየሠሩ እንደነበር አጫውተውናል። ዶክተር ፋሲል፤ ከትምህርት ቤት ጀምሮ ትልልቅ ኃላፊነቶችን የሚወስዱ በዚያም ምስጉን የሆኑ ሠራተኛ ለመሆናቸው ሥራቸው ያመላክታል። በዚህ በኢህአዴግ ዘመነ መንግሥት እንኳን ከህግ ሙያቸው ሳይለዩ 27 ዓመታት ሠርተዋል። በኢህአዴግ ዘመን ሠራሁ ከሚሉት ውስጥ ዋነኛው «በእሥራኤል ያለውን የኢትዮጵያ ንብረት» ማስመለሳቸውን ነው። በኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ቴባ ከሚባል የግል መድኃኒት አምራች ድርጅት ጋር ውል ይገባና በአገር ውስጥ ሥራው ይጀመራል።
ይሁንና ደርግ ሲገባ የቴባን ንብረት ሙሉ ለሙሉ ወርሶ አልሰጥም ይላል። ይሄ ደግሞ ድርጅቱን አስቆጣውና ኢትዮጵያን ከሰሰ። በዚህም የድርጅቱ ባለቤት እሥራኤላዊ በመሆኑና ደርግ ምላሽ ሳይሰጥ በመቆየቱ ለአፈጻጸም እሥራኤል አገር ከፍተኛ ፍርድቤት የኢህአዴግ መንግሥት ይጠራል። በዚህም የተወሰነው የኢትዮጵያ ንብረት ተሸጦ እንዲከፈል ነበር። ኢህአዴግ ግን ይህ እንዲሆን አልፈለገምና እርሳቸውን ልኮ እንዲደራደሩ አደረገ።
በዚህም እንግዳችንም ሳያፍሩ ንብረቱ እንዳይነካ ማድረግ ቻሉ። ከዚያ አልፎም እርዳታ እንዲያደርጉ በማሳመን ከ250 ሺህ ዶላር በላይ የሚያወጣ መድኃኒት ለኢትዮጵያ ድጋፍ ሊደረግ እንደቻለ አውግተውናል። ዶክተር ፋሲል ይህንና የመሳሰሉ ትልልቅ ለአገር የሚበጁ አበርክቶዎችን አድርገዋል። ሦስት ጠቅላይ ሚኒስትሮችን፤ ሦስት መንግሥት ያረቀቁትን ህግ በማስተግበርና በማማከርም ያገለገሉ ናቸው። ዛሬ ደግሞ «ህገመንግሥቱ በተለየ መንገድ ሊቃኝ ይችላል። ስለዚህም ብዙ መሠራት አለብኝ» ሲሉ በህግ አጣሪ ጉባኤ ውስጥ አባል በመሆን እየሠሩ ይገኛሉ። የተለያዩ የህግ ጉዳዮችን ያማክራሉ።
የፖለቲካ ተሳትፎ
«እኔ የፖለቲካ ሰው አይደለሁም። የሙያ ሰው ነኝ። እና ሙያዊ የሆነ ምክር በተለይ ህገ መንግሥትን በተመለከተ ህገ መንግሥታዊ ሥርዓትን ከማስፈን አንጻር ሦስቱንም ማለትም የአፄ ኃይለሥላሴን፣ የደርግንና የኢህአዴግን መንግሥታት ሳማክር ቆይቻለሁ። የማማክረው ግን ከህገ መንግሥት አንጻር ነው። ህገ መንግሥት በምልበት ጊዜ በእኔ እምነት መንግሥት የህዝብን መብት ከመጠበቅ እና ከማስጠበቅ ሌላ ኃላፊነት የለበትም። የማንኛውም መንግሥት ትልቁ ዋናው መሰረታዊው ኃላፊነት ሰብዓዊ መብትን ማክበርና ማስከበር ነው» ይላሉ። ማንኛውም መንግሥት ወደ ኋላ ተሄዶ ሲታይ ጥንካሬውና ድክመቱን ዘርዝሮ ማየት ይቻላል።
እናም የኢህአዴግ ጥንካሬ ከደርግ ውድቀት በኋላ ህገ መንግሥት ያስፈልጋል ብሎ መነሳቱና ይህን ህገ መንግሥት በተቻለ መጠን ተግባራዊ ለማድረግ መሞከሩ ነው። ኢህአዴግ በራሱ አመለካከት ነው ሲሄድበት የነበረው የሚለው ትክክል ነው። ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ማስተዳደር የጀመረው የአብዛኛውን ገጠር ህዝብ አመለካከት ይዞ ነው።
ኢህአዴግ ዲሞክራቲክ ነው ብሎ መናገር አይቻልም። ግን ዴሞክራሲ ሥራ ላይ መዋል አለበት ብሎ የሚያምን አካል እንደሆነም ፖለቲካዊ አንድምታውን ያነሳሉ። «ህገ መንግሥት የእግዜአብሔር ቃል አይደ ለም። ህዝብ ይህ ይሻለናል የሚላቸው ሃሳቦች ያሉበት ሰነድና እናት ህግ ነው።
እናም በየዘመኑ አሰራሩን አይቶ ዛሬ በደረስንበት ደረጃ በዚህ መልክ ከምንሠራ በዚህኛው መልክ ይሻላል ብሎ ማሰቡ ጠቀሜታ አለው» ይላሉ። አሁን በሥራ ላይ ያለው ህገ መንግሥት መሰረታዊ ግቦችን የያዘ ነው። አንደኛ ሰላም፣ ሁለተኛ ዴሞክራሲና ሦስተኛ ደግሞ ልማት ናቸው። ህገ መንግሥቱ ከሩብ ምዕተ ዓመት በኋላ እንደገና ውስጡን መፈተሽና እኛ ዛሬ ከደረስንበት ሁኔታ ምን ማሻሻል እንችላለን ብሎ መነሳቱ ይጠቅማልና አሁን ያለው መንግሥት ይህንን መመልከት ይገባዋል ሲሉ ይናገራሉ።
የሦስቱ መንግሥታት ህገመንግሥት
ጣሊያንኛ፣ ትግሪኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ አማርኛና እንግሊዝኛ ቋንቋዎችን አቀላጥፈው የሚናገሩትና በከፊልም ቢሆን የሲውዲን ቋንቋ እንደሚችሉ የሚገልጹት ዶክተር ፋሲል፤ የመንግሥታት ልዩነት በህገመንግሥት ዙሪያ ብዙ ልዩነት እንደሌለው ይጠቅሳሉ። ምክንያቱም መጀመሪያ ሲሠራ የአን ድን ማህበረሰብ ታሪክ፣ ራዕዩ፣ ፍላጎት፣ ዛሬ ያ ህብረተሰብ የት ነው ያለው የሚለው ታይቶ ነው። ከዚያ ከታሪኩ ተነስቶ መገዛት የሚፈልገው በየትኛው ሥርዓት እንደሆነ ይቀመጣል።
ሰው ስብዕናው፣ መብቱና ግዴታው ምን ሊሆን ይገባል የሚለውም በጥልቀት ይዳሰሳል። ስለዚህ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች በሚገባ ስለሚቃኙ ልዩነቱ እንብዛም አይደለም። ዶ/ር ፋሲል ናሆም፤ ጽጌረዳ ጫንያለው የኢትዮጵያ ህጎች ከተለያዩ ምንጮች የተወሰዱ ናቸው የሚሉት ባለታሪኩ፤ ፍትሃ ነገሥቱ፣ ኢትዮጵያዊ አመለካከቱ፣ የውርስ ህጉ የተካተተበት ነው። ፍትሀ ብሔሩ ከሞላ ጎደል ከፈረንሳይ ሲወሰድ፤ የውርስ ህጉ ከጀርመን፣ የወንጀል ህጉ ደግሞ ከፈረንሳይና ከሲውዝ፣ ሥነ ሥርዓቱ ደግሞ ከእንግሊዝ … ወዘተ እያለ ይቀጥላል። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያዊነት መልክ እንዲኖረው ተደርጎ ስለሚተገበር ልዩነቶች እንዳይሰፉ ያደርገዋል ባይ ናቸው። በኢትዮጵያ ውስጥ ዋናው ችግር በተለያዩ ጊዜያት ውስጥ ከፖለቲካው ጀምሮ የነበረን ማስቀጠል አለመቻል ነው። ሁልጊዜ በሁሉም ነገር አዲስ ነገር መጀመር ምርጫ ይደረጋል። ይህ ደግሞ ብዙ ጉልበትን፤ በጀትም ያስወጣል።
ይህም መሆኑ የእያንዳንዱ ሥርዓት የራሱ ክፍተት ቢኖረውም ጥቅም እንዳለው መታየት እንዳይችል አድርጓል። የፊውዳል ሥርዓትን እርግፍ አድርጎ መተው ትክክል አይደለም። ይልቁንም ጥቅሙን ማየት ላይ መተኮር አለበት። መሰረት የተጣለበትን ሥርዓት ማሻሻል ላይ እንጂ እርግፍ አድርጎ መተውና እንደአዲስ መጀመር አያዋጣም። እናም የሥርዓቱን ድክመት በአዲስ አስተሳሰብ በመሙላት ወደ ፊት መገስገስ እንደሚገባ ይናገራሉ።
ገጠመኝ
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ልዩ አማካሪ በነበሩበት ወቅት ነው ይህ የሆነው። የተጻፈው ከአንድ ሀኪም ነበር። በጥቁር አንበሳ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ውስጥ ተቀጥሮ ከሚሠራ። ዝርዝሩ የሚለው «ደመወዜ ይህን ያህል ነው። በወር ውስጥ የማወጣው ደግሞ ይህንን ነው። ስለሆነም ሲደመር ከሚበቃኝ በላይ እየከፈላችሁኝ በመሆኑ እንድትወስዱልኝ ወይም እንድትቀንሱልኝ እፈልጋለሁ» ይላል። በዚህ ግራ የተጋቡት ፕሬዚዳንቱም እርሳቸውን ያማክሯቸዋል። ወቅቱ ደግሞ በዩኒቨርሲቲው መምህራን ዘንድ ደመወዝ ይጨመርልኝ የሚባልበት ጊዜ ነበር። ይህ ሁለቱ ጥያቄ ያልተስማማላቸው ባለታሪካችንም ሰውዬውን ለማማከር ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አቀኑ።
ማንነታቸውን ከተናገሩ በኋላ ለምን ይህንን እንዳለም ጠየቁት። የእርሱ ምላሽ ግን «የተለየ ነገር የለኝም» የሚል ነው። እርሳቸው ዩኒቨርሲቲው ይህንን የመቀነስ መብት የለውም። ተፈራርመን በዚህ ደመወዝ እንዲሠሩ ተግባብተናልና ይህንን መሻር አንችልም። ስለሆነም እርሶ የማይፈልጉት ከሆነ እየተቀበሉ ለድሃ ይስጡት ሲሉ ምላሽ ሰጡ። እርሱም በጣም በመበሳጨት «ሥራዬን ልሥራ ወይስ እየዞርኩ ልስጥ። የተለየ ሥራ ጨመራችሁብኝ» ሲል የመለሰላቸውን መልስ መቼም አይረሱትም።
በጎነት ያገናኘው ትዳር
ባለቤታቸው ሲውዲናዊት ናት። የሲውዲን ሚሲዮናውያን ትምህርት ቤት ውስጥ ለአንድ ዓመት የትምህርት አገልግሎት በነፃ ለመስጠት ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣች ነው የተዋወቋት። መነሻቸው ግን የእርሷ መምጣት ብቻ አልነበረም። የበጎ ተግባር እንቅስቃሴያቸው ነው ከበጎ አድራጊ የዛሬ ባለቤታቸው ጋር ያስተሳሰራቸው። በወቅቱ እርሳቸው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እየተማሩ ነበር። ሆኖም የተማሩበት ትምህርት ቤት በጎ ተግባር አለቀቃቸውምና ለአንድ ተማሪ በቋሚነት የሚማርበትን ትምህርት ቤት ለማመቻቸት ኃላፊዎችን ለማነጋገር ይመላለሱ ጀመር። በቦታው ደግሞ እርሷን ዘወትር ያገኟታል።
ልባቸውም ይደነግጥላታል። እርሷም ብትሆን ስለእርሳቸው ምንነት በሚገባ ከነባሩ የትምህርት ቤቱ አመራር ዘንድ ትሰማ ነበርና ልቧ ሳይከጅላቸው አልቀረም። በዚህም ትውውቃቸው ጠነከረ። የሁለቱም ውስጥ ምላሽ በአወንታ ታጀበና በትዳር አስተሳሰራቸው። ትዳሩም 50ዓመታትን ዘለቀ። ዛሬ የሦስት ሴት ልጆች አባትና እናት ሆነዋል። የልጅ ልጆችም አይተዋል። ሁለቱ ልጆቻቸው በህክምናው ዘርፍ ተሰማርተው የሚሠሩ ሲሆን፤ አንደኛዋ ልጃቸው ደግሞ ኢኮኖሚክስ አጥንታ በአገር ውስጥ እየሠራች ትገኛለች።
መልዕክት
ዛሬ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ወጣት ነው። በዚህ ወጣት ህዝብ ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል። ወጣቱ ምን ይፈልጋልና በምን መልክ ነው መደገፍ ያለበት የሚለው መሰረታዊ የመንግሥት የቤት ሥራ መሆን አለበት። ከትምህርት፣ ከስራና ለኑሮ መሟላት ከሚያስፈልጉት ጉዳዮች ዋና ትኩረቱ ሊሆን ይገባል። ይህ ደግሞ አልፎ አልፎ የሚሰራ ሳይሆን ቀጣይነት ያለው ሥራ የሚጠይቅ ነው። የእኩልነት ጉዳይም መታሰብ አለበት። የብሄር ብሄረሰቦች፣ የጾታ፣ የሃይማኖት፤ ከተሜና ገጠሬ ሁሉም በእኩልነት መስተናገድ አለባቸው።
አገልግሎቶቹ ተደራሽ፣ አድሎ የሌለበትና ፍትሀዊና ፈጣን ማድረግ ላይም መንግስት መስራት ይኖርበታል። ማገልገል የማይችሉ ሰዎችን ከአንዱ ወንበር አንስቶ ሌላ ወንበር ማስቀመጥ ሳይሆን ሊያገለግሉ በሚችሉ ብቃትና እውቀቱ ባላቸው ሰዎች ብቻ ነው መተካት ያለባቸው።ለዚህም ዛሬ ያለው ለውጥ መልካም ጅማሮ መሆኑን ያስረዳሉ። ከዓለም ወደ ኋላ እንዳንቀር ከማን እናንሳለን የሚለው መሰረታዊ አስተሳሰብ በህዝቡ ውስጥ እንዲሰርጽ በትምህርትም ሆነ በመገናኛ ብዙኃን መሰራት አለበት። ይህን ለማድረግ አሰራሮቻችን በሙሉ ቀልጣፋ ወቅታዊና ግልጽ መሆን አለባቸው የመጨረሻ መልዕክታቸው ነው። እንግዳችን የበርካታ ታሪክ ባለቤት ቢሆኑም ጊዜ ገድቦናልና ሀሳባችንን በዚህ ቋጨን። ሰላም!
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/2011
በጽጌረዳ ጫንያለው