ኢትዮጵያውያን የእርስ በርስ ትስስራቸው የጠነከረ፣ አብሮነታቸው እንዳይበጣጠስ ሆኖ የተገመደ፣ የተለያየ ቦታና ዘመን ላይ ሆነው ስነ ልቦናዊ ጥምረታቸው በጉልህ የሚታይ ድንቅ ህዝቦች ናቸው፡ ፡ ይህ ጥምረታቸው በኪነ ጥበብ ጎልቶ እና ደምቆ ይታያል፡፡
የአንዱ ባህል ለሌላው ውበት የአንዱ ውበት ለሌላው ሞገስም ነው።ይሄ ባህላዊ ትስስር በአንድነት ሲታይ ደግሞ ልዩ ኢትዮጵያዊ የሆነ ህብር አለው። ዛሬ በኪነ ጥበብ አምዳችን የባህላዊ ሙዚቃ መሳሪያዎቻችን እና ሙዚቃዎቻችን የሚያመሳስላቸውን ጉዳይ በመፈተሽ ለማህበራዊ ትስስራችን መጠናከር ያላቸውን ጉልህ ሚና እንዳስሳለን፡፡
የባህላዊ ሙዚቃ መሳሪያዎቹ አሰራር፣ሙዚቃ አከዋወንና መሰል ጉዳዮች አንዱ ማህበረሰባችን ከሌላው የቀረበ ኪነ ጥበባዊ ግንኙነት እንዳለው ማሳያ ነው፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ የሀገራችን ክፍል በሙዚቃዊ ምት የሚፈጠረው የአንገት እንቅስቃሴ፣ በትከሻ ድለቃና የደረት እን ቅጥቅጥ ፣ የወገብ እቅስቃሴን ተመልክተን ፣የእግር ጭፈራ ስናገኝ ሙሉ የሆነ የሰው አካል በጥበብ ሲዋሀድ እናይበታለን፡፡
ኢትዮጵያ በልጆችዋ የጥበብ ጌጥ ሙሉ የሆነች፤ አንዱ ክፍሏ በሌላው ሙሉ የሚሆን ትስስራዊ የውበት ፈርጥ፤ ውበትዋ ተዛንቆ በአንድነት ሲቀርብ ልዩ ግርማ የሚያላብስ፤ ሀገረ ሰባዊ ሙዚቃና የሙዚቃ መሳሪያዎቻችን አንድነትን ፣ የእርስ በርስ ትስስራችንና ድንቅ እሴቶቻችንን የሚያጎሉ ናቸው፡፡
ሀገራዊ ጥበባትን በወጉ አጥንተን ለጠቀሜታ ማዋሉ ላይ ዘንግተን እንጂ ኢትዮጵያ በጠቢባን ልጆችዋ ለዓለም የሚተርፍ የበዛ የጥበብ ውጤቶች አፍርታለች፡፡ባህላዊ ሙዚቃና መሳሪያዎቹ ለዚህ አበይት ምስክር ናቸው፡፡ዛሬ ላይ ትኩረት ተነፍጓቸው ሊሰጡት የሚችሉት ፋይዳ የለዘበ ቢመስልም በሀገር ልጅ ከአገሬው የተሰሩ ናቸውና ለኢትዮጵያውያን ልዩ ትርጉም አላቸው፡፡
በተለያዩ ባህላዊ ሙዚቃዎች ላይ ምርምር ያደረገው፤ በእንጦጦ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ የሙዚቃ ተመራማሪና መምህር አቶ ሰለሞን ገብረ ዮሐንስ እንደሚለው የኢትዮጵያውያን አብሮነትና የባህል መወራረስ የፈጠረው ማህበረሰባዊ ጥምረት ብዙ ማሳያ ስለመሆኑ አጥብቆ ያምናል፡፡ በባህላዊ ሙዚቃዎቻችን ላይ እያደረገ ያለው ጥናት በቅርበት ይህንን እንዲረዳ አድርጎታል፡፡
ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያ የሚሰራበት ቁስ መመሳሰል፣ የክዋኔው መቀራረብ፣ ባህላዊ ሙዚ ቃው ባህልን በመግለጽ መመሳሰሉ፣በህብረ ድምጽ መዜማቸው፣ ባህላዊ ሙዚቃዎቹ በመሪ ወይም «ኮንዳክተር» መመራታቸው የሚያቀራርባቸው ተመ ሳስሎነት መሆኑን ባጠናው ውጤት ማረጋገጡን ይናገ ራል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥት በበርታ ብሔረሰብ ውስጥ የሚገኘው ዙንባራ፣ የደራሼው ፊላ ፣ የዳውሮው የሙዚቃ መሳሪያ ዲንካ ዋሽንትና መሰል የሙዚቃ መሳሪያዎቻችን ለመስራት የሚጠቀሙበት ቁስ አንድ መሆን የመሳሪያዎቹ ድምፅ አወጣጥና አፈጣጠር በየራሳቸው የሚገለጹበት ቀለም እና ምት ቢኖረውም በድምጽ አወጣጥና ድምፀት ተመሳሳይነታቸው ሌላው ማሳያ ነው፡፡ አቶ ሰለሞን ይህ ጥምረት እንዲሁ በአጋጣሚ የተፈጠረ ሳይሆን የጠበቀ ስነ ልቦናዊ ቁርኝት የፈጠረው ስለመሆኑ አስረግጦ ይናገራል፡፡
ብዙ ጥናት የተካሄደባቸው ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎችና ሙዚቃዎቻችን ትኩረት ተሰጥቶ ጥናትና ምርምር ቢካሄድባቸው ለእርስ በርስ ትስስራችን ምቹ መደላደል መፍጠር እንደሚችሉም ያምናል፡፡ በደርግ ዘመን በፖለቲካ ርዕዮት ዓለም ምክንያት ወደ ሩሲያ ሄደው ሙዚቃን እንዲያጠኑ የተላኩት ኢትዮጵያውያን፤ የምዕራቡ ዓለም የሙዚቃ ስልት አጥንተው ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ የተማሩትን ስልት እና የሙዚቃ ባህል ከማስረጻቸው ባለፈ ለባህላዊ ሙዚቃና ሀገረሰባዊ ጥበቦች ትኩረት መስጠት እንዳልቻሉ ይገልጻሉ፡፡
በሀገራችን የሙዚቃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚሰጡ ባህላዊ የሙዚቃ ትምህርቶች በቁጥር ማነስ ለዚህ በማሳያነት ይጠቅሳሉ፡፡ ለባህላዊ ሙዚቃ መሳሪያዎቻችን ትኩረት ተሰጥቶ መጠናትና ያላቸውን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ተገንዝቦ የሚሻሻሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ሀገራዊ ኃላፊነትን መወጣት መሆኑ ልብ ይሏል፡፡
ሰለሞንና መሰል የሀገረሰብ ሙዚቃ ላይ ጥናት የሚያደርጉ ባለሙያዎች በራስ ተነሳሽነት ካልሆነ በቀር ድጋፍ የሚያደርግላቸው መንግሥታዊም ሆነ ሌላ ድርጅት አለመኖሩ ጉዳዩ ምን ያህል ችላ እንደተባለ ማሳያ ነው፡፡ ሀገራት ማህበራዊ ትስስራቸውን የሚያጎለብቱት በፈጠሩት ጥበብ ነውና እኛም ሀገረሰባዊ ጥበቦችን ተጠቅመን ሀገራዊ መግባባትን በሚፈጥር መልኩ መገልገሉ ችላ ልንለው የማይገባን ጉዳይ ነው፡፡ ሀገራዊ የሙዚቃ ጥበብ ማጥናት የሚያስገኘው ፋይዳ የጎላ መሆኑን የሚናገረው የሙዚቃ መምህርና ተመራማሪው ሰለሞን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙትን በርታዎች ባህላዊ ሙዚቃ ዙንባራን ይጠቅሳል፡፡
የበርታ ብሄረሰብ ባህላዊ ሙዚቃ ዙንባራ ከአዝናኝነቱ እና ማህበረሰባው ባህልን ከመግለጽ ከፍ ባለ መልኩ የዴሞክራሲ ፅንሰ ሀሳብ በውስጡ ያቀፈና መቻቻልንና አብሮነትን ለማጠናከር የሚረዳ መሆኑን ይገልጻል፡፡ በየዓመቱ በሚካሄድ «ዙንባራ ሀበሽ» በተባለ ባህላዊ ሙዚቃ ውድድር ላይ የትንፋሽ ሙዚቃ መሳሪያ የሆነውን ዙንባራ አንዱ ቀበሌ ከሌላው ጋር ውድድር ይደረግበታል፡፡ በዚህ ውድድር አሸናፊ የሚሆነው ለብዙ ሰዓት ሳያቋርጥ የሙዚቃ መሳሪያውን የተጫወተው ወገን ሲሆን ከተሸናነፉ በኋላ አብሮ የመመገብና ከምግቡ ፍጻሜ መልካም ግንኙነት የሚያጠናክሩ ውይይቶች ማድረግ የሁነቱ አንድ አካል ነው፡፡
በዚህ ውይይት አካባቢያዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ይፈተሻሉ፤ ውይይት ተደርጎባቸው በጋራ መግባባት ይጠናቀቃል፡፡ ይህ ሀገረሰባዊ ጥበብ ያስገኘው መልካም ገፅታ ነው፡፡ ይሄ ለበርታዎች ዙንባራ የፈጠረላቸው መልካም ገጠመኝ ነው፡፡ በሌላኛው የሀገራችን ክፍል የሚገኙት የየም ብሔ ረሰብ በመስቀል በዓል የሚያቀርቡት «ፊንፊ» የተሰኘው ሙዚቃቸው ለእርስ በርስ ግንኙነታቸው ትልቅ አጋጣሚ ፈጥሮላቸው ያልፋል፡፡ የየም ብሄረሰብ ከፊንፊ ዓመታዊ ክብረ በዓል በኋላ ተሰብስበው በዓመቱ ውስጥ ባጋጠማቸው ማህበራዊ ችግር ላይ ይወያያሉ፡፡በዚህ ወቅት ሰውን የበደለ፣ያለአግባብ የሰውን ንብረት ያወደመና የሰረቀ በግልጽ ቀርቦ በደሉን ተናዞ ይቅርታ ይጠይቃል።
ሀገረሰባዊ ጥበብና ሙዚቃዎች ያላቸውን ፋይዳ ተረድቶ ማህበረሰቡ እንዲጠቀምባቸው ጥልቅ ጥናትና ምርምር ማድረግ ወሳኝ ነው፡፡የሙዚቃ ትምህርት ቤቶችም ለሀገረሰባዊ ሙዚቃዎች ትኩረት ቢሰጡ አንድም ማህበረሰባችን ያለውን የረቀቀ ጥበብ ማየት ያስችላል፡፡በሌላ በኩል ደግሞ የእርስበርስ ትስስርና አብሮነትን በማጠናከሩ በኩል ያላቸውን ሚና ጥቅም ላይ ማዋል ያስችላል፡፡
ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎች ራሳችንን በመግለፅ፣በጎ እሴቶቻችንን በማጎልበትና ለጥበብ ያለንን ትልቅ ቦታ ለማሳወቅ የጎላ ድርሻ ይወስዳሉ፡፡በተለይ አሁን ያለንበትን ነባራዊ ሁኔታ ለመለወጥ የእርስ በርስ ግንኙነታችንን ለማጠናከር ትልቅ ድርሻ ያበረክታሉ፡፡ ያላቸውን ተመሳስሎ፣አፈጣጠርና መቀራረብ የእርስ በርስ ስነ ልቦናዊ ጥምረታችን አመላካች ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/2011
በተገኝ ብሩ