– በውድድሩ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ቡድን ተሸኝቷል
ለ22ኛ ጊዜ በሞሪሽየስ በሚካሄደው የአፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን የሚወክለው የአትሌቲክስ ልዑካን ቡድን እሁድ ምሽት በአራራት ሆቴል ተሸኝቷል። ልኡካን ቡድኑ ትናንት ወደ ሞሪሽየስ አቅንቶም በሰላም መድረሱን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አሳውቋል፡፡
በሽኝት መርኃ ግብሩ ላይ የቡድኑ የአንድ ወር የሆቴል ቆይታውን በተመለከተ አትሌቶች፣ አሰልጣኞችና የቴክኒክ ቡድን መሪው አቶ አሰፋ በቀለ በየተራ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ እና የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በመርሃግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር በማድረግም ለቡድኑ የሥራ መመሪያና የመልካም ምኞት መግለጫ መልእክት አስተላልፈዋል። የቡድኑ ተወካዮችም የአገር መለያና ምልክት የሆነውን ሰንደቅ አላማ ከታላቅ አደራ ጋር ከክብር እንግዶችና ከፌዴሬሽኑ አመራሮች እጅ ተረክበዋል።
በ2020 በአልጄሪያ አዘጋጅነት ሊካሄድ የነበረው የአፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ለሁለት አመት ከተራዘመ በኋላ ዘንድሮ አዘጋጅ አገር ተቀይሮ በሞሪሺየስ ከነገ ጀምሮ ለተከታታይ አራት ቀናት ይካሄዳል። ኢትዮጵያ በዚህ ቻምፒዮና ጥሩ ውጤት አስመዝግባ ለመመለስ ከሃምሳ በላይ አትሌቶችን ከአንድ ወር በላይ ስታዘጋጅ መቆየቷን ከፌዴሬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ በዚህም ከሜዳ ተግባራት ውድድሮች ጀምሮ፣ በአጭርና መካከለኛ፣በሦስት ሺ ሜትር መሰናክል እንዲሁም በረጅምር ርቀት ውድድሮች በሁለቱም ፆታ ጠንካራ ተፎካካሪና ውጤታማ የሚሆኑ አትሌቶችን ወደ ውድድሩ ስፍራ መጓዛቸው ታውቋል፡፡
በአፍሪካ ትልቁ በሆነው የአትሌቲክስ መድረክ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሃምሳ በላይ አገራት የሚሳተፉ ሲሆን በተለያዩ ውድድሮች በርካታ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ቀዳሚ ሆነው ለማጠናቀቅ ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
በዚህ ቻምፒዮና በሃያ ሶስት የውድድር አይነቶች አርባ አምስት ፉክክሮች የሚስተናገዱ ሲሆን ሃያ ሁለት በወንዶች መካከል፣ ሃያ ሁለት በሴቶች መካከልና አንድ የአስር ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር በድብልቅ ጾታ ፉክክር የሚደረግ ይሆናል።
ከሜዳ ተግባራት ውድድሮች በተጨማሪ በሩጫ ውድድር ከአጭር እስከ ረጅም ርቀት የተለያዩ ፉክክሮችን የሚያስተናግደው ይህ ቻምፒዮና በአፍሪካ ታላላቅ አትሌቶች በብዛት ባይሳተፉበትም በርካታ ተስፋ የተጣለባቸው ወጣት አትሌቶች አገራቸውን በመጪው ክረምት በአሜሪካ ፖርት ላንድ ኦሪገን በሚካሄደው የአለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ለመወከል ራሳቸውን ያሳዩበታል ተብሎ ይጠበቃል። በተለይም በአለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና አገራቸውን ለመወከል በተለያዩ ርቀቶች ሚኒማ እስካሁን ማሟላት ያልቻሉ አትሌቶች በዚህ ውድድር የሚያስመዘግቡት ሰአት ወደ ታላቁ ውድድር ስለሚመራቸው ጠንካራ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። በተለያዩ የአጭር ርቀት እንዲሁም የሜዳ ተግባራት ውድድሮች በአለም ቻምፒዮና ለመሳተፍ ሚኒማ ማሟላት ዘወትር የሚከብዳቸው እንደ ኢትዮጵያውያ ያሉ አገራት በዚህ ቻምፒዮና በለስ ከቀናቸው በአዳዲስ የውድድር አይነቶች ሚኒማ አሟልተው በአለም ቻምፒዮና አዲስ የተሳትፎ ታሪክ ለመጻፍ እድላቸውን ይሞክራሉ።
የአፍሪካ አትሌቲክስ መዲና በመባል የምትሞካሸው ሞሪሽየስ ይህን የአፍሪካ ታላቅ የአትሌቲክስ መድረክ ለማሰናዳት በቂ ዝግጅት ያደረገች ሲሆን እኤአ በ2019 የገነባችው ኮት ደ ኦር ብሔራዊ ሁለገብ ስቴድየም እንግዶቹን ይቀበላል። ሞሪሽየስ የአፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮናን እኤአ በ1992 እና በ2006 በስኬት ማስተናገዷ የዘንድሮው ቻምፒዮና ከአልጄሪያ ተነጥቆ የአዘጋጅነት እድሉ እንዲሰጣት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2014