ገና ሲገባ ጀምሮ ታሪክ ይናገራል ይሉሃል እንዲህ ነው። የአካባቢው ማህበረሰብ ማንነት በዙሪያው ባሉ የተለያዩ ታሪካዊ ቅርሶች ይገለጻል። ዙሪያ ገባውን ገደላማ ስፍራ አልፈው፤ በሜዳው ቦርቀው ማርያም ቤተክርስቲያን ቅጽር ግቢ ሲዘልቁ የሚሰማዎት ስሜት የተለየ ነው።የአየሩ ነፋሻማነት፣ የማህበረሰቡ አቀባበልና ባህላዊ የፍትህ ስርዓቱ ሁሉ ያስደምማል። በባህላቸው ጥፋት የሰራ ሰው ብቻ አይደለም የሚፈረድበት፤ ቅጣት የሚጣልበት። ግኡዙ አካል ሳይቀር ጥፋት ከሰራ በሰንሰለት ይታሰራል።
ለዚህ ደግሞ ማሳያ የሆኑ ሁለት ነገሮች ለታሪክነት ተቀምጠዋል። የመጀመሪያው በቤተክርስቲያኑ መግቢያ ላይ እንደጅብራ ተገትሮ የሚታየው ትልቅ ድንጋይ ሲሆን፤ ከተራራ ላይ ወርዶ የሰው ነብስ በማጥፋቱ በሰንሰለት ታስሮ ዓመታትን በዚያ ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዲያሳልፍ ተፈርዶበታል። ድንጋዩ የታሰረበት ዓመት ከመቶ ያላነሱ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት ወደ ውስጥ እየዘለቀ በአፈር ከመሸፈኑ ባሻገር ምንም አልተነካም።
ግን ጥበቃ ስላልተደረገለት ደግሞ አልጌ ወርሶት ምን ያህል ስፋትና ክብደት እንዳለው ለማወቅ ያስቸግራል። ሌላኛው የታሪክ ምስክር ደግሞ መቶ ዓመታትን ያስቆጠረው ለቤተክርስቲያን መስሪያ ተብሎ ከርቀት የመጣው እንጨት ነው። ይህም እንደድንጋዩ ሁሉ በሰንሰለት ታስሮ ተቀመጧል። ይህ እንጨት ደግሞ ተሸክሞት ያመጣውን ሰው በመግደሉ የተነሳ ነው ቅጣት የተጣለበት ይላሉ የአካባቢው ተወላጆች። እንጨቱ ከመቶ ዓመት በላይ በዚያ የተቀመጠ በመሆኑ በስብሷል።
ግን እስከዛሬ ያልጠፋበት ምክንያት የጥንት ቤቶች ሲሰሩ ምን ዓይነት ጠንካራ እንጨት መምረጥ እንደሚችሉ ይነግረናል። ከዚያ አለፍ ሲባል ደግሞ እን ጨቱን ማሰራቸው መግደል ከባድ ወንጀል መሆኑን ያስተምራል። ይህ አመለካከትና ባህል በማህበረሰቡ ዘንድ አሁንም አለ ። ጥፋት ያጠፋ ይቀጣል፤ እኩል ቅጣት መሰጠት ያስፈልጋል ብለው የሚያምኑ መሆኑን ነው ያጫወቱን።
ለማንምና ለምንም አይነት ስህተት እኩል ፍርድ መስጠት ይገባል የሚል ሀሳብ አላቸው። «ይህ የባህል ባለቤት ማን ነው?» ካላችሁ በደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ጊንጪን አለፍ ብለን ያሉትን ከተሞች አቋርጠን 12ኪሎ ሜትር ኮረኮንቹን ይዘን ስንገባ በምናገኛት የደንዲ ወረዳ ውስጥ ነው። በከተማዋ እንብርት ላይ ፊታውራሪ ሀብተጊወርጊስ ዲነግዴ ቤተክርስቲያን ለመስራት መሰረት ጥለውበታል። ቤተክርስቲያኗ በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ቦታዎች እንደተተከለችም ይነገርላታል።
የዛሬ ቦታዋን ያገኘችው ከዛሬ መቶ ዓመት በፊት እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ። ቤተክርስቲያኑ እንዲጠናቀቅ ያደረጉት የፊታውራሪው ባለቤት ናቸው። በዙሪያዋ ዋናው ቤተክርስቲያን እስኪጠናቀቅና ታቦታቱ ወደዚያ እስኪገቡ የሚቀመጥበት ሦስት ባለሁለት ፎቅቤቶች ይታያሉ፤ አንደኛው ውስጥ የፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ባለቤት ትኖርበት እንደነበር ሰምተናል። ከመቶ ዓመት በላይ የሆናቸው ሦስት ታሪ ካዊ ፎቅ ቤቶችም በዙሪያው እንዳሉና ምንም እንዳልተነኩ በዓይናችን ማየት ችለናል። ይሁንና እነዚህም ቢሆኑ እንክብካቤ እንደሚያስፈልጋቸው ተናጋሪ አያሻውም። ምክንያቱም አንድ ቀን ታሪ ካቸውን ሳይተውሉን ሊወድቁ ይችላሉ።
ወደዋናው ቤተክርስቲያን ስንመለስ በንብ የሚጠበቅ ነው፤ በአካባቢው አንድ ጥፋት ከተሰራ ንቡ ወርዶ ይናደፋል። ስለዚህ በዚያ ስፍራ የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ምንም መጥፎ ነገር ለማድረግ አይደፍሩም። ስምንት ማዕዘናትን የያዘው ይህ ቤተክርስቲያን የራሱ የሆነ የአሰራር ጥበብን የተከተለ ሲሆን፤ በርከት ያሉ መስኮቶች አሉት። በአንዱ ማዕዘን ብቻ ከሶስት ያላነሱ መስኮቶች ይታዩበታል።
ውበቱ ይበልጥ የሚጎላው ደግሞ ወደ ቤተመቅደሱ ሲዘለቅ ነው። እጅግ በሚያምሩ የጥንት ስዕሎች ተሞልቷል። የስዕሎቹ አቀማመጥም ሆነ አሳሳል የራሱ የሆነ ባህልን የተከተለ ነው፤ የጥንቱን የቤተክርስቲያናት የአሳሳል ስልት የያዘ ነው። ይህ ሲባልም በጣም ጥንታዊ ናቸው በተባሉ ቦታዎች ስንሄድ እን ደምናየው አይነት።
በቅድስቱ መግቢያ ላይ መቀ መጥ ያለባቸው፤ በሴቶች፤ በወንዶችና በካህናት መግቢያ ላይ መቀመጥና መሰራት ያለባቸው ስዕሎች ልዩነት ሳይኖራቸው በአግባቡ በግርግዳዎቹ ላይ ተሰርተዋል። ይህ ደግሞ ጥንታዊነቱን በትክክል እንዲናገር አድርጎታል። «ከአዲስ ዓለም ማርያም በወቅቱ አንቱታን ያተረፉ ሰዓልያን ተመርጠው መጥተው ነው እንዲህ ውብ የሆኑ የእጅ ጥበባቸውን በግርግዳዎቹ ላይ ያኖሩት።
ጣሪያው ብቻ ሲቀር ሙሉ ቅድስቱ በስዕላት የተሞሉ ናቸው። ግን ማንም የማያየውና እንደቅርስ የማይወስደው በመሆኑ ዝናብ እያፈሰሰበት ወደመበላሸቱ ደረጃ ደርሷል።» ያሉን የአካባቢው ነዋሪ አቶ ዳመነ ሀይሉ ናቸው። በተለይም የአካባቢው ገበሬ በወቅቱ በጉልበቱ ነበርና አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያደርገው በቂ እንክብካቤ ሊደረግለት አልተቻለም። ከአካባቢው ተወላጆች ገንዘብ በማሰባሰብ በመጠኑም ቢሆን በዙሪያው የተለያዩ የአገልግሎት መስጫ ቤቶችን ለማሰራት መቻሉን የሚያነሱት አቶ ዳመነ፤ እነዚህ ስዕሎች ባሉበት ሳይንቀሳቀሱ በባለሙያ መታየትና መሰራት ካልቻሉ ቅርስ ነታቸው መጥፋቱ አይቀርም።
አሁን ባለው ሁኔታ ደግሞ ለአገልጋይ ካህናት ክፍያ እንኳን ለመክፈል የአካባቢው ማህበረሰብ ተቸግሯል። ስለሆነም የሚመለከተው አካል ለዚህ ታሪካዊ ቅርስ ዛሬ ይድረስ ይላሉ። ስዕላቶቹ በእውቅ ሰዓልያን እንደተሳሉ የሚታወቀው አቧራ ከመልበሱ ውጪ ቀለማቸው ምንም ያልተነካ መሆኑ ነው። በተጨማሪም በሚ ወርድባቸው ዝናብ አማካኝነት ለመላጥ ችለዋል እንጂ ምንነታቸው አልተደበቀም። በተለይም ከእምነቱ ውጪ የተሳሉ ስዕሎች በእጅጉ የሚማርኩና በሌሎች ቦታዎች የሚገኙ አይመስሉም።
ለአ ብነትም እንደአካባቢው ተወላጆች ማብራሪያ ቅጃቸው በድረ ገጾችና በተለያዩ ቦታዎች ቢኖርም ዋናው የፎቶ ስዕል መገኛቸው በዚያ የሆኑ እንደ ፊታውራሪ ሀብተጊወርጊስ ዲነግዴ ዓይነት ስዕሎች ይገኙበታል። በዚህም ይህ ታሪካዊ ስዕል ከማንም የበለጠ ዛሬ ሊሰራለት እንደሚገባ ሁሉንም ጎብኝ ተማጽነዋል።
የቤተክርስቲያኑ ስዕላት የኢትዮጵያ ስነጥበብ ትውፊት ባልተቋረጠ መልኩ ከትውልድ ትውልድ በቅብብሎሽ የተሻገረባቸው ለመሆኑ ማሳያ ነው። ምን ያህል ርቀት እንደተጓዘም በሚገባ ያመላክታል። ምክንያቱም የኢትዮጵያ መልክአምድራዊ ሁኔታና የአኗኗር ዘዬአቸው በሚገባ በስዕሎቹ የተቀመጠበት ነው። ልዩ የቀለም አጣጣላቸውም እንዲሁ ባህላዊ መለያቸውን ይዘው ቀጥለዋል። ግን ማንም ስላላያቸው እንክብካቤ ጎሏቸዋል። ታሪካዊ ይዞታቸውንም እየለቀቁ ነው።
የደንዲ ነዋሪዎች ባህላቸውን ፣ የአባቶቻቸውን ታሪክ የማሳወቅ ፍላጎት እና ተነሳሽነትም አላቸው። ይህንንም ሲያደርጉ በሚያውቁት ታሪክ ላይ ተንተርሰው ብቻ ነው። ስለ ቅርሱ ምንነትና አገልግሎቱ የሚያስረዳ አካል ቢኖራቸው ደግሞ ከዚህ የበለጠ ለታሪክ ተቆርቋሪ ይሆናሉ የሚል እምነት አለ።
ነገር ግን የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊዎች አካባቢውን እንብዛም ስለማያስታውሱት እንደነዚህ ዓይነት የኢትዮጵያዊነት መገለጫ የሆኑ ታሪካዊ ቦታዎችን እንኳን መጠበቅ ተስኗቸዋል። «ከአቅም በላይ ሆነና ከዚህ በላይ መጓዝ አልቻልንም፤ የአባቶቻችን ቅርስ ሳንንከባከበው ሊጠፋብን ነው። በዚህ ቦታ የወረዳው የምክር ቤት አባል፤ የቀበሌው አስተዳዳሪ ሆኜ ሳገለግል የተለያዩ ተግባራትን ለመፈጸም ሞክሪያለሁ። ግን ከወሬ ያለፈ ነገር አላገኘሁም። ይህ ደግሞ ልቤን ሰብሮታል።
ማንም በጄ ብሎ ወደሥራው ሊገባና ቅርሳችንን ሊታደግልን ባለመቻሉ ተስፋ ቆርጫለሁ» ሲሉ የነገሩን የአካባቢው ተወላጅ አቶ ገዛኸኝ ግዛው ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ የተራራው ከፍታ 1350ጫማ ነው። መንገድ የሚገኘው ደግሞ ይህንን ተራራ አቋርጦ በመሄድ ሲሆን፤ ያንን በጫካና በተራራ የተከበበ ምድር ወደ መንገድ ለመቀየር እጅግ ያዳግታል።
በተለይ ለአካባቢው ሰው ፈታኝ ነው። ይሁንና ከአካባቢው ተወላጆች ገንዘብ በማሰባሰብ በጥቂቱም ቢሆን መንገድ እንዲኖር ጥረት ተደርጓል። ለነፍሴ ያለችም አንዲት የአካባቢው ተወላጅ ተራራውን ሰንጥቃ የአገሬው ሰው ከእግር ጉዞ እንዲተርፍ ጥርጊያ መንገድ አሰርታለች። ይህንን ተከትሎ እንኳን ቅርሶቹን ላስተዋውቅ የሚል የመንግሥት አካል አልተገኘም።
የአካባቢው ማህበረሰብ አንድ እርምጃ ሲራመድ መንግሥት ካልደገፈው የአካባቢው ማህበረሰብ ተስፋ ይቆርጣል ያሉት አቶ ገዛኸኝ፤ አሁን በፈረስ እንጂ በመኪና ለመግባት በጣም ያስፈራል። ምክንያቱም በደንብ የተስተካከለ መንገድ የለም። በዚህም በከበሩና ጥንታዊ በሆኑ ስዕሎች የተዋበውን የማርያምን ቤተክርስቲያን ለታሪክ ማቆየት ተስኖናል። ጫካ የነበረውን መግቢያ ቀዳዳ እንዲኖር ለማድረግ በጠጠር ከመሙላት ያለፈ ሥራ መስራት አይቻለንምና አሁንም ለታሪካዊ ቤቶቻችን ሲባል መንግሥት ሊያየን ይገባል።
በአመራር ለውጥ ምክንያት ታሪክ ሊጠፋ አይገባውምና ልብ ይባል ሲሉ ተማፅነዋል። በቀደመው ጊዜ መንግሥታት ልዩና የግዞት ቦታ ይሆናል ብለው ከመረጡት መካከል ደንዲ አንዱ ነው። ምክንያቱም በተራራ መሃል መኪና አይገባም፤ ሰውም ይኖርበታል ተብሎ የሚታሰብበት ቦታ አይደለም። አገረ ገዥው እንኳን ግዞተኞችን ሊጠይቁ ሲሄድ መንገዱ በሰው ጉልበት እየተጠረገላቸው ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ በላንድሮቨር መኪና የገቡባትን መንገድ ነው ዛሬ ላይ የአካባቢው ነዋሪ የሆነች ሴት አስጠርጋ መንገድ ለማድረግ የጣረችው።
ማህበረሰቡ የተቻለውን ቢያደርግም የመንግሥት እገዛ አልታከለበትም። የታሪክ ተወቃሽ ላለመሆን በመንግሥት በኩል እየሰራ ያለው አካል የሚገባውን ማድረግ ይኖርበታል። የአካባቢው ተወላጆችም ቢሆኑ ከመንግሥት ጎን በመሆን ታሪኩንና ባህሉን በማሳወቅ ዙሪያ መስራት ይገባል። እኛ በአንድ አጋጣሚ ማለትም በቅርስ ዙሪያ በሚሰሩ ማህበራት አማካኝነት ወደቦታው ባናቀና የማየቱ ዕድል አይኖረንም። እኛም ታሪክን ጠብቆ ባለማቆየት በባህሉ ተቀጪ እንዳንሆን እንፍጠን።ጥፋት ሰውን መግደል ብቻ ሳይሆን ታሪክንም መግደል ነውና ተወቃሽ ትውልድ ላለመሆን እንጣር።
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/2011
በጽጌረዳ ጫንያለው