ከስድስት ዓመታት ቀደም ብሎ ነው፤ ወጣቱ ተማሪ ምንተስኖት የምሬ የመሰናዶ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተመድቦ ወደዛው ያቀናው። ታድያ በግቢው ትምህርቱን በአግባቡ የመማርና የትምህርት ዘመኑ ሲጠናቀቅ ከግቢው ተመርቆ ለመውጣት ብቻ አልነበረም ያቀደው። ይልቁንም ቀደም ብሎ በነበረው የተማሪነት ዘመኑ «በምትመደቡበት ግቢ ንባብን በተመለከተ አንድ ነገር አድርጉ» የሚል አደራ ከመምህሩ ተቀብሎ ነበርና እሱንም ከልቡ ሰንቋል።
እናም እንዲህ አደረገ፤ ወደ ተመደበበት ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሲያመራ ከአልባሳትና አንዳንድ ቁሳቁሶች ባለፈ በእጁ ያሉትንና ያነበባቸውን መጻሕፍት ሸከፈ። ከተማሪዎች መኝታ ክፍል ወይም ዶርም መካከል ምንተስኖት የተገኘበት ክፍል በር ላይም «መጽሐፍ ማንበብ ለምትፈልጉ ከዚህ መዋስ ትችላላችሁ» የሚል መልዕክት ያለው ወረቀት ለጠፈ። ይህን ያዩ ተማሪዎች በሩን አንኳኩተው መጻሕፍት እየተዋሱ ማንበብ፤ አንብበው ሲመልሱ ደግሞ ከመጽሐፉ ባገኙት ሃሳብ ዙሪያ ሰብሰብ ብለው መነጋገር ጀመሩ።
በዚህ መሰረት ብዙዎች ወደዚህ ዶርም እግራቸው ይመላለስ ቀጠለ። በመጻሕፍት ውሰትና ንባብ፤ ከሃሳብ ልውውጥ የተሻገረ ወዳጅነት ተፈጠረ። የመጀመሪያው የትምህርት ዓመት ተጠናቅቆ ክረምት ሲመጣና መለያየት ግድ ሲል፤ ምንተስኖት ይዟቸው የነበረውን መጻሕፍት ሁሉ ማንበብ ለሚፈልጉቱ አከፋፈለ። ተማሪዎቹም ክረምቱ አልቆ ለትምህርት ዳግም ጎንደር ሲገናኙ ከተዋሱት ተጨማሪ ሌሎች መጻሕፍትን ይዘው እንዲመጡ ተስማሙ። እንዲህ እንዲህ እያለ ነው እንግዲህ ዛሬ ላይ ልናወሳ የወደድነው ማኅበር የተመሠረተው፤ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሳንኮፋ የአንባብያን ማኅበር።
ይህን ደግሞ ያጫወተን በማኅበሩ የቤተመጻሕፍት ክፍል ኃላፊ ወጣት ኢዮብ መስፍን ነው። ኢዮብ ማን ነው? ኢዮብ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሦስተኛ ዓመት የፊዝዮ ቴራፒ ተማሪ ነው። ወደማኅበሩ የተቀላቀለበትን ሁኔታም ያስታውሳል። መጀመሪያ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ግቢ ሲገባ መጻሕፍትን በነጻ የሚያስነብቡ ተማሪዎች መኖራቸውን በማወቁ የተሰማውንም ደስታ እንዲሁ አይረሳውም። በዚህ ስሜት ወደ ማኅበሩ ቀረበ። እርሱም በበኩሉ አስቀድሞ በሚኖርበት አዋሽ መልካሳ አካባቢ ‹የነገው ተስፋ› የሚባል ቤተመጻሕፍት ያስተባብር ስለነበር ለመጻሕፍት አዲስ ባለመሆኑ አልተቸገረም።
የማግዘው ካለ እንካችሁ ብሎ የሳንኮፋ አባልና አገልጋይ ሆነ። ሳንኮፋ የአንባብያን ማኅበር እንደ ኢዮብ ያሉ በመጻሕፍት በኩል የተለያዩ ሃሳቦችን ሸምተው ራሳቸውን የሚያልቁ ወጣቶች እንቅስቃሴ ማሳያ ነው። በዚህ በኩል ‹የአንባቢ ያለህ!› ተብሎ በሚጮህበት፤ በወዲያ ‹ጊዜ አጠረን› በሚባልበት ወቅት ሳንኮፋ የአንባብያን ማኅበር በህክምና ተማሪዎች ግቢ ውስጥ እየተንቀሳቀስ ይገኛል። ብዙ ንባብ ከመጠየቁ የተነሳ ፋታ አያገኙም የሚባልላቸው የህክምና ተማሪዎች ጊዜ ሰጥተው ከታሪክ፣ ከልብወለድ፣ ከፍልስፍና፣ ከሥነ ግጥም ዓለማት የሚቀስሙበትን ሰዓት ከመመደብ አልቦዘኑም።
ስለማኅበሩ አሁንም ጥቂት እንበል፤ ወጣት ኢዮብ እንደነገረን ከሆነ ስያሜውን ከምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ጋና ወስዷል። ሳንኮፋ የሚለው ቃል የወፍ ምልክት ያለው ሲሆን፤ ወፊቱ ወደፊት የምትሄድ ነገር ግን ራሷን ወደኋላ የመለሰች ናት። የምልክቱ ተምሳሌት ወይም የቃሉ ትርጉሙ ‹ወደኋላ ተመልሰህ አግኝ› የሚል ዓይነት ሲሆን፤ ማኅበሩም ‹የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ› በሚል አገርኛ አባባል ተርጉሞ ለስም መርጦታል። ኢዮብ አለ፤ «በአገራችን ብዙ ጠቃሚ የሆኑ ታሪኮች አሉን፤ ግን አሁን ላይ የራሳችንን እያየንና እየመረመርን አይደለም ያለነው። ሳናኮፋ የሚለውን ቃል ለዛ ነው የተመረጠው።»
በዚህ መሰረት የኋላውን ለማወቅና ለመረዳት ደግሞ መጻሕፍት ተመራጭ ሆነው ተገኙ። ሳንኮፋ አንዴ ከሌሎች ማኅበራት ጋር ተዳብሎ ሲሠራ፤ ቀጥሎ የተማሪዎች መመገቢያ አካባቢ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቶ በ2008 ዓ.ም ወርሃ ሐምሌ ላይ በህክምና ትምህርት ግቢ ውስጥ የተወሰነ ቦታ አገኘ። የሳንኮፋ አንባብያን ሁለት ክፍል ቤት በርከት ያሉ መጻሕፍት በስርዓት የተቀመጡባቸው ሁለት መደርደሪያዎችን ይዛለች። ተምሳሌትነታቸው የሚጎላ የጥበብ ሰዎችና አንጋፎች ምስሎቻቸው ዙሪያውን በክፍሉ ግድግዳ ላይ ተለጥፎ ይታያል። የመጻሕፍት ውሰትና መሰል አገልግሎቶችን ለመስጠት ክፍሏ ከምሽት ከ12፡00 እስከ 3፡00 ሰዓት ክፍት ትሆናለች። አገልግሎቱን ለመስጠትም ከአባላቱ መካከል በተራ ሁሉም ይገኛሉ።
ከፈተና ጋር ሲሆን ጫና የሚበዛባቸውና መስዋ ዕትነት የሚከፈልበት ጊዜ መኖሩንም ኢዮብ ይጠቅ ሳል። ከዚህ ባለፈ የሥነጽሑፍ ምሽቶች በማኅበሩ ይዘጋጃል። ሳምንታዊ የመጻሕፍት ላይ ውይይቶችና የምክክር መድረኮችም እንዲሁ ይካሄዳሉ። ከዚህ ባለፈ ቤተመጻሕፍቱ ከተደራጀ በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ (ወመዘክር) 450 የሚጠጉ መጻሕፍትን እንዲሁም የቆዩ ጋዜጦችን ጥራዝ ለማኅበሩ እንዳበረከተ ኢዮብ ይገልጻል። የመጻሕፍቱ ቁጥር እየጨመረ፣ የማሰባሰብ ሥራውም እየተጠናከረ የአባላት ምዝገባ ተጀምሮ እንቅስቃሴው የበለጠ ደመቀ። ባለሁለት ክፍሏ የሳንኮፋ አንባብያን ቤት ሁሉን አባላት በአንድ ጊዜ መቀበል ባትችልም እንኳ የተሰነቀባት ህልምና የየእለት እንቅስቃሴዋ ግን እየላቀ ሄደ። ይህንንም ተከትሎ 2009ዓ.ም ክረምት ላይ ዓመታዊው የመጻሕፍት አውደ ርዕይና ሽያጭ ሳምንት የሆነው ንባብ ለሕይወት ላይ ለመሳተፍ ዕድል አገኘ፤ ሳንኮፋ የአንባብያን ማኅበር። ትጋታቸው ላልቀነሰው እንደ ኢዮብ ላሉት የሳንኮፋ ወጣቶች ይህ ብዙ በሮችን የከፈተ አጋጣሚ ነበር። ማኅበሩ አሁን ላይ በቁጥር 700 በላይ አባላት አሉት። ሁሉም ንባቡ ላይ በንቃት ይሳተፋሉ ማለት ባይቻልም የበለጠ በተሠራ ቁጥር ብዙዎችን የበለጠ ማቅረብ እንደሚቻል ኢዮብ ይጠቅሳል። አባላት ለማኅበራቸው በየወሩ አምስት ብር ያዋጣሉ። እንደ ቀደመው ጊዜም በክረምት ወራት መጻሕፍትን የተዋሱ እንደሆነ፤ ለትምህርት ዳግም ሲሰባሰቡ መጻሕፍትን ጨምረው ያመጣሉ።
ልክ እንደ ሳንኮፋ ሁሉ በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመሳሳይ እንቅስቃሴዎችን የሚያደርጉ ስለመኖራቸው ኢዮብ ነግሮናል። ለምሳሌም በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ‹ፍኖተ አእምሮ› የሚባል ቤተመጻሕፍት አለ ይለናል። ይህም በግቢው የህግ ተማሪዎች የተቋቋመ ነው። እንደዛው ሁሉ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሴቶች ላይ አተኩሮ በመሥራት ጀምሮ የንባቡን ሥራም አካትቶ በመንቀሳቀስ ላይ ያለ ‹መራሂት› የተሰኘ የንባብ ማኅበር እንዳለ ይጠቅሳል። በተለያየ አጋጣሚ እነዚህ ማኅበራት ተገናኝተው ታድያ ሃሳብ ተለዋውጠዋል፤ ተነጋግረዋል። ኢዮብን ስለ ሳንኮፋ ዓላማና የወደፊት እቅድ ጠይቀነው ነበር።
እንደሚለው ከሆነ ለሳንኮፋ መመሥረት ምክንያት የሆነውና ‹በምትሄዱበት ሁሉ ንባብ ላይ አንድ ነገር ሥሩ› የሚል ንግግር አሁንም ቀጥሏል። ሰው ከአገሩ እስካልወጣ ድረስ ኑሮውን ባደረገበት ከተማ፤ አገሩ በዛ ናት። ከኢዮብ ንግግር ቃል በቃል ልዋስ፤ እርሱ እንዲህ አለ፣ «ጎንደር እስካለን ጎንደር ኢትዮጵያችን ነች። እናም ሁሉም ቦታ በዚህ መሰረት መሠራትና መነበብ አለበት። እኛም ያለንን ሃሳብ ማጋራት እፈልጋለን። አሁን ንባብ ላይ እየሠራን ያለነው ከላይ ወደታች ነው።» አያይዞም ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር እስከ አንደኛ ደረጃና መዋዕለ ሕጻናት ድረስ ካሉ መምህራን ጋር ውይይት ለማድረግ ታቅዷል ይላል። ጎንደር ላይ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር እንዴት እንሥራ በሚለው ላይ ተወያይተውም የንባብ ክበባትን ከማብዛትና ከማጠናከር በተጓዳኝ ‹የንባብ ባህል› የሚል የትምህርት ዓይነት ተጨምሮ እንዲካተት ለማድረግም ሃሳብ አለ። «ይህ ከሆነና ከታች ጀምሮ ከሠራን ሁሉም በደረጃው እየተስተካከለ ይመጣል።»
ኢዮብ እንዳለው። የሳንኮፋ መሪ ሃሳብ እንዲህ ነው፤ ‹እናንብብ፣ እንለወጥ፣ እናካፍል› ማኅበሩም እንዲህ ባለ አካሄድ ነውና በሁለት እግሩ የቆመው የሄደበትን ጥርጊያ መንገድ በዚህ መሰረት ለሌሎች እያካፈለ ይገኛል። ይህም ለማድረግ፤ እንደ ኢዮብ ገለጻ ከተማሪዎቹ ጥረት በተጓዳኝ ‹እናንብብ› ያሉትን ተማሪዎቹን ‹በርቱ!› ከማለት አልፎ ሥራቸውን አይቶ በብዙ መልክ ትብብርና ድጋፍ ለሚያደርገው የጎንደር ዩኒቨርሲቲም ምስጋን ያስፈልጋል። «አሁን ባለንበት ጊዜ ከወቀሳ ለመዳን ያለው ዕድል ራስን በራስ መጠቀም ነው። ይህ ትውልድ ይወቀሳል እንጂ እንዲያነብ ምን ይደረግለት አይባልም። አሁን ላይ በከተሞች እንኳ ብዙ የሕዝብ ቤተመጻሕፍት የሉም። ታድያ ከምንወቀስ ራሳችንን ማዳን አለብንና ይህን ሠርተናል፤ ይህንን ለመሥራትም መርጠናል።
ይህም በጥቂቱም ቢሆን እየተሳካልን ነው» አለ፤ ኢዮብ። ተማሪ ተስፋዬ ወይሳ የፊዚዮ ቴራፒ አራተኛ ዓመት ተማሪ ሲሆን፤ አሁን ላይ የሳንኮፋ አንባብያን ማህበር ሊቀመንበር በመሆን እያገለገለ ይገኛል። እርሱ እንደሚለው በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ ተማሪዎች የሃሳብ ሰዎች ሊሆኑ ይገባል። እናም ለዚህ ደግሞ የንባብ ጥቅም ያለጥርጥር የሚጠቀስ ነው። «ማንበብ ዓለምን መመልከቻ መነጽር ነው።» የሚለው የማኅበሩ ሊቀመንበር ተማሪ ተስፋዬ፤ ከዚህ በኋላም ማኅበሩ ማንበብ ግዴታ የሚሆንበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ለማድረግ ይሞክራል፤ ይህን በሚያጸና ሥራ ላይም ትኩረት ይደረጋል። ለዚህም የመጀመሪውም እርምጃ በግቢ ቆይታቸው መጻሕፍትን ሲያነቡ የቆዩ ተማሪዎች ተመርቀው ሲወጡ ሃሳቡን ወደሚደርሱበት ቦታ እንዲያደርሱትና በኢትዮጵያ የተለያዩ ሳንኮፋዎች፤ የንባብ ክበባት እንዲቋቋሙ ማድረግ ነው ይላል።
እናብቃ! ከምክንያታዊነት ተፋትቶ፣ ጊዜ ተርፎት ዱላና ድንጋይ ለማንሳት የሚያንገራግር ወጣት በየጊዜው እያየን ነው። ‹ቀድሞ ነበር እንጂ…» ይሉት የራሳችን ተረት ካልተተረተብን በቀር፤ አሁንም ወጣቱ ልብ እንዲገዛና ከቀልቡ እንዲሆን ለማድረግ ብዙ አይረፍድም። መጻሕፍት ሲታከሉበት ደግሞ እልፍ ሃሳቦችን ማስተናገድ የሚችል ሰፊ አእምሮና ዝግጁ ልብ ስለሚፈጠር፤ የተሻለ ነገር አስረክቡን የሚሉ ሳይሆኑ የተሻለ ነገር ራሳቸው የሚፈጥሩ ወጣቶችን ማግኘት ይቻላል። ለሁሉም ግን ይቅናን። ሰላም!
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/2011
በሊድያ ተስፋዬ