አገራችን በማይገባትና በማይመጥናት ሁኔታ ውስጥ እያለፈች ነው። ፅንፍ ይዞ ዘዋሪውም በዝቷል። በእንደዚህ አይነት ከባድ ጊዜ እንደ አገር፤ እንደ ህዝብ ማሰብ ይጠበቃል። ከአካባቢያዊነት፤ ከዘረኝነት ባለፈ አርቆ የሚያይ ሰውም እጅጉኑ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ብሄር፤ ዘር፤ የምንላቸው ሁሉ የሚኖሩት አገር ሰላም ስትሆንና አገር ስትቀጥል ነው። ትውልድ ቦታ፤ ብሔር፤ ሰፈር የምንላቸው ሁሉ የሚኖሩት በአገር ውስጥ ስለሆነ የአገር ህልውና ተናጋ ማለት የእነዚህ ጉዳዮች መኖር ጥያቄ ውስጥ ይገባል።
በመሆኑም ብሔሬን እወዳለሁ ዘሬን እፈልጋለሁ የሚል ሁሉ የአገር ደህንነት አደጋ ውስጥ እንዳይገባ የሚችለውን ብቻ ሳይሆን የማይችለውን መሞከር አለበት። ብሔር፤ ዘር ከአገር ጋር የተሰናሰሉ ነገሮች ናቸው። የእነዚህ ሁሉ አቃፊ ደግሞ ኢትዮጵያ ናት። ኢትዮጵያ እናት ስትሆን አማራ ፤ኦሮሞ፤ ትግሬ፤ ጉራጌ፤ ……ወዘተ በእሷ ስር ያሉ ልጆቿ ናቸው። በመኖሯ የኖሩ በእናትነቷ የተፈጠሩ። በመሆኑም እናት ደህና ስትሆን የልጆቿ ደህንነት ይጠበቃል። የልጆቿ ሰላም ዋስትና የእናታቸው መኖር ነውና።
አሁን አገራችን ላይ እየሆነ ያለው ግን በተቃራኒው ነው። ይህቺ በብዙሐን ደምና አጥንት የቆመች፣ ብዙ ህይወት የተከፈለባት፣ በብዙ መስዋእትነት የቆመች አገር በጥቂቶች ቅድሚያ እየተሰጣት አይደለም። ከዚያ ይልቅ ልጆቿን ለመከፋፈል የሚደረገው ጥረት እጅጉኑ በርትቷል። ብዙው ሰው እየሆነ ያለው መከራና ስቃይ የሚሰማው፣ ትውልድ ቦታው ላይ ሲደርስና የእሱ ብሔር ላይ ሲፈፀም ብቻ ነው። የአንድ ኢትዮጵያ ልጅ መሆን ቀርቷል ሰብአዊነት ውሃ በልቶታል። እይታችን በጣም ጠቧል። እንደ አገር ማሰብ አቅቶናል አንድ የሚያደርገን መለኮታዊ ኃይል ካላገኘን በስተቀር ተራርቀናል።
ይበልጡኑ የሚያሳዝነው ደግሞ በዚህቹ በአገራችን በኢትዮጵያ ስም በዓለም አደባባይም ሆነ በአገራችን ከፍተኛ የእውቅና ማማ ላይ የተቀመጡ፣ በብዙ ያከበርናቸው ታዋቂ ሰዎች (public figures)፤ የጥበቡ አለም ሰዎች፤ ምሁራን፤ ፖለቲከኞች ፤ አትሌቶች፤ በተለያዩ ዘርፎች እውቅናን የተጎናጸፉ ኢትዮጵያውያን በዚህ ቁርጥ ሰአት ኢትዮጵያን ዘንግተው የመጡበትን ብሔር ወክለው ጽንፈኛ ንግግር ሲናገሩና ዘረኝነትን ሲሰብኩ ማየት የሚያም ነገር ነው።
ያስተማራቸው፣ ብዙ ዋጋ የከፈለላቸውን፣እውቅና የሰጣቸውን በብዙ ያከበራቸውን ሕዝብ ውለታውን የሚመልሱለት ልዩነትን የሚያሰፋ መርዛማ ምላሳቸውን በመዘርጋት ሆኗል። እነዚህ ታዋቂ ሰዎች በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች በተመቸ እና በተደላደለ ሁኔታ ውስጥ እየኖሩ እዚህ ያለው ወገናቸው ጉዳይ ሳያሳስባቸው ህዝቡን የሚያራርቅ የጥላቻ ንግግር ይልኩልናል። የደረሱበት የእውቅና ማማ ላይ የወጡት አገር ሰላም በነበረችበት በዚያ ወቅት መሆኑን ረስተውታል። ባይታደሉ እንጂ እውቅናቸውን፣ ተቀባይነታቸውን ለዚህ ግዜ ነበር መጠቀም የነበረባቸው። ያላቸውን ተሰሚነት በመጠቀም እንዴት ለችግራችን መፍትሄ ማበጀት እንዳለብን፣ ከልዩነታችን ይልቅ የሚጎላውን አንድነታችንን፣ ከጉራማይሌነት ይልቅ የሚመሳሰለውን ተፈጥሯችንን በማንሳት ለሰላም አስተዋጽኦ ማድረግ ነበረባቸው።
እነሱ ግን ከዚህ ይልቅ ጦርነቱ እንዲባባስ፤ ዘረኝነቱ ስር እንዲሰድ ነገር እያወሱ ታሪክ እያጣቀሱ አገር እንድትበታተን የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ ነው። የእንደነዚህ አይነቶቹን ከንቱ ስራ ስመለከት ወደ አዕምሮዬ የምትመጣው ሻለቃ አትሌት ደራርቱ ቱሉ ናት። ደራርቱን አብዛኛውን ጊዜ የጀግንነት፤ የድል፤ የጥንካሬ ማሳያ ናት ብለው ብዙዎች ይገልጿታል። ለእኔ ደግሞ የእናት አገር ተምሳሌት ትሆንብኛለች። ፡ ርህራሄዋ የእናት፤ ጥንካሬዋ የኢትዮጵያ፣ ደግነቷ የእናት ጀግንነቷ ደግሞ የአገር ማሳያ ነው። ስለደራርቱ ብዙ ማለት ይቻላል በተለይ ደግሞ አገራችን አሁን ባለችበት ሁኔታ ደራርቱ አስር ብትሆን ብዬ አስባለሁ። የደራርቱ አይነት ልብ ያላቸው ጥቂት ሰዎች ቢኖሩ ለምነው ያስታርቁን ነበር፤ ሰላም ያመጡልን ነበር።
ደራርቱ ልቧ የተለየ ነው እሷ የሁሉም ናት ሁሉም ደግሞ የእሷ። ዘር፣ ፖለቲካ፣ ኃይማኖት እሷ ዘንድ ቦታ የላቸውም። ደራርቱ ጋር ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ሰው መሆን ብቻ ነው። እሷ እርቀ ሰላም እንዲመጣ ብዙ ለምናለች። ብዙ ሞክራለች ግን ብቻዋን ሆነች። እሷን የሚያሳስባት የእናቶች እንባ የህጻናት መሪር ለቅሶ ነው። ስለፖለቲካ ቢጠየቁ ምንም ማብራሪያ መስጠት የማይችሉ የጦርነቱ ገፈጥ ቀማሾች፣ በረሀብ የሚገረፉት እነሱ ናቸው። የእሷ ጭንቀት በሄደችበት የምትናገረውም የምታስተላልፈውም መልእክት ይህ ነው። ስለነዚህ ፍትህ አልባ ነፍሶች። በተገኘችበት መድረክ ሁሉ ስለሴቶች፣ ስለህጻናት ስትሉ ሰላም አውርዱ ብላ በእንባ ለምናለች።
በዚህ አገር በብርቱ በተፈተነችበት ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ፣ ሲሉ የነበሩ ሁሉ ዘራቸው በልጦባቸው ኢትዮጵያን በካዱበት በዚህ ከባድ ጊዜ ሰው ሆና የተገኘች ምርጥ ኢትዮጵያዊት ሴት ናት። እንኳን ሙሉ ኢትዮጵያ በችግርና በጦርነት እየታመሰች ቀርቶ፣ የግለሰቦችን ህመም እንኳን እንደራሷ የምትቆጥር መልካም ሴት ናት።
አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታማ ምን ያህል አሟት ይሆን?። ደራርቱ እናት ናት የርህራሄ ጥግ እሷ አገር ናት የደግነት ሙላት። እንኳን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የተፈናቀሉ፤ የተራቡ ምስኪኖች አይታ፣ እንኳን ያለ በቂ ምክንያት በጦርነቱ ህይወቱ የሚያልፍ ወጣት አይታ የአገሯ ባንዲራ ሲውለበለብ ስታይ እንባዋን መግታት አትችልም። የኢትዮጵያ ነገር አይሆንላትም።
ተመኘሁ ደራርቱ አስር ብትሆን ብዬ። የፍቅር ልብ ያለው አገር የሚሰማው ጥቂት ሰው ቢኖረን ብዬ። የፖለቲካ ልዩነት ከሰው ልጅ ክቡር ህይወት አይበልጥም። ምክንያቱ ደግሞ ፖለቲካዊ አመለካከትንም ተግባራዊ የሚያደርጉበት ሰው ያስፈልጋል። ህዝብ ያስፈልጋል። የፖለቲካ ትግልም ቢሆን የሚታገሉለት ህዝብ እያለቀ ትርጉም አይኖረውም። ህዝብ በችግር እና በጦርነት እያለቀ ትግሉ ለማን ነው?።
በቅድሚያ ህዝብ የመኖር ዋስትናው ሊጠበቅለት ይገባል።ምክንያቱም ህግም፣ ህገመንግስትም፣ መንግስትም የሚኖረው ህዝብ ሲኖር ነው። ለማስተዳደር የሚተዳደር (ህዝብ) ሰው መኖር አለበት። ጦርነቱ ኢትዮጵያን ብዙ ኪሳራ ውስጥ ከቷታል። ከጦርነቱ ባለፈ አሁን ላይ አገራችን ላይ የተፈጠረው የኑሮ ውድነት ውጥረትም የጦርነቱ ውጤት ነው። ታድያ ጦርነቱ ማብቃት እንዳለበት፣ ከጦርነት ትርፍ እንደሌለ፣ ከጦርነት ተጠቃሚ እንደሌለ ሁላችን በተግባር አይተነዋል። ሁሉም ሰው ጋር ይህ ሀሳብ መፈጠር አለበት። ይህን ግንዛቤ በመፍጠር ደግሞ ታዋቂ ሰዎች የበለጠ ውጤታማ ይሆናሉ።
አሉ እንጂ መማር መደንቆር የሆነባቸው፣ ከስማቸው ፊት እነሱን የማይገልጽ ግብራቸውን የማይመጥን ግዙፍ ማእረግ ተሸክመው ለጥፋት ሲያሴሩ የሚውሉ። ከተማሩ፣ ብዙ ዋጋ ተከፍሎላቸው እዚህ ከደረሱ በኋላ ህዝባቸውን የረሱ። አገር በብዙ ፈተና ውስጥ በወደቀችበት በዚህ ወቅት ብዙ ተዛዝበናል። አገር ወዴት እያመራች ነው? እጣ ፈንታዋ ምንድነው? የሚለው ያላሳሰባቸው።
አገርን ከማረጋጋት ለሰላም የድርሻን ከማድረግ ይልቅ ዘረኝነትን መስበክ እንደ ጀግንነት ተያይዘውታል። ምሁራን ከሚባሉ ሰዎች ይህን መስማት በጣም ያሳፍራል። አገር በውስጥና በውጪ ጠላቶች እንደዚህ በተጨነቀችበት በዚህ ወቅት ከአካባቢያዊ አስተሳሰብ ወጥቶ እንደ አገር ማሰብ ያስፈልጋል። አንዳንድ ምሁራን ነን ባዮች እንደዚህ ብዬ ነበር፣ ይህ እንደሚመጣ ቀድሜ አውቅ ነበር፣ እያሉ በአገር ላይ ያሟረቱት ክፉ ሀሳብ እውን በመሆኑ ጉራቸውን እየቸረቸሩ፣ በየማህበራዊ ሚዲያውና በየሚዲያው የሚናገሩትን ቤት ይቁጠራቸው። ብዙ ታዋቂ ሰዎች ከሚጠበቅባቸው ደረጃ ወርደው የተገኙበት አጋጣሚ የሚያሳዝን ነው።
ሲሆን ሲሆን በሰው ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት ተጠቅመው ህዝቡን አንድ ማድረግ ማስተሳሰር ኢትዮጵያዊነትን ከፍ አድርገው ማሳየት ነበረባቸው። ታዋቂዎቹ እውቅናውን ያገኙት አገር ሰላም በነበረችበት ወቅት መሆኑን ረስተውታል ምሁራኖቹም እንደዛው። እውቅናም ዝናም የሚኖሩት አገር ሰላም ስትሆን ነው። ከእያንዳንዱ ዜጋ የሚጠበቀው ለሁሉም የሚበጅ አገር የሚያስቀጥል ሀሳብ ማንሳት ነው። ጦርነት ለማንም እንደማይጠቅም በተደጋጋሚ አይተናል። ጦርነት የሚጨምርልን ምንም ነገር የለም የሠራነውን ከማጥፋት፣የገነባነውን ከማውደም በቀር። ኢትዮጵያ በዚህ ጦርነት ምን ያህል እንዳጣች ምን ያህል እንደወደመች በተግባር አይተነዋል። ለመስራት በጣም ብዙ አመታት የወሰዱብንን ነገሮች በጥቂት ወራት አጥተናቸዋል ፈርሰዋልም ያህል እንደወደመች ወድመዋል ወደኋላ ነው የተመለስነው።
መስራት እንደማፍረስ ቀላል አይደለም ለዓመታት የገነባነውን በምን ያህል ጊዜ ደግሞ እንዳጠፋነው አይተናል። ከምንም በላይ ደግሞ በምንም የማይተካው ክቡሩ የሠው ልጅ ህይወት በምንም ልንመልሰው የማንችለው ውድ ነገር። ሊያውም ወጣቱ ኃይል፣ አገር ላይ ብዙ ነገር መፍጠር የሚችል ለውጥ ማምጣት፣ መቀየር የሚችለውን፣ ያለ በቂ ምክንያት ለመናገር እንኳን በማይመች የእርስ በእርስ ጦርነት ያጣነው ይህ በጣም ያሳዝናል።
ለምሳሌ የኪነጥበብ ሰዎች ከተለያዩ ብሔሮች የተውጣጡ እንደመሆናቸው ጽንፍ ይዘው ዘረኝነትን ከማቀንቀን ይልቅ፣ ኪነ-ጥበብ ለማህበረሰቡ ትርታ ቅርብ እንደመሆኗ በሙዚቃውም፤ በድራማውም፤ በስነጽሁፉም፣ በተለያዩ የጥበብ ስራዎች፣ ከትግራይ የወጣው ጥበበኛ የትግራይ ህዝብን፣ ከአማራው የወጣው አማራውን፣ ጉራጌውም፣ ኦሮሞውም……. ሌሎቹም ብሔሮች እንዲሁ ከሚለያየን ይልቅ የሚያመሳስለን እንደሚበዛ፣ ከሚያራርቀን ይልቅ የሚያቀራርበን እንደሚልቅ፣ በመንገር ፖለቲካ ጊዜያዊ ችግር እንደሆነ ደግሞም እንደሚፈታ ኢትዮጵያዊ ግን ሁልጊዜ አንድ መሆን እንዳለበት በማስገንዘብ ሕዝብን ማረጋጋት፣ ወደ ቀድሞ መከባበሩና መፈቃቀሩ እንዲመለስ በማድረግ ለውጥ ማምጣት ይቻላል።
ጦርነት እንደማይጠቅም ኪሳራ እንጂ ትርፍ እንደሌለው ማህበረሰቡ ከተረዳ፣ ከዘረኝነት አስተሳሰብ ወጥቶ ኢትዮጵያ ማለት ከጀመረ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ በሰላም እንጂ በጦርነት እንደማትቆም ከተገነዘበ፣ ጦርነቱን መቃወም ይጀምራል።
ጦርነት አሰቃቂ ነገር ነው ከጦርነት ተጠቃሚ የለም። በጦርነቱ ተሳትፈው የሚሞቱትን ተተን በዚህ ሳቢያ በረሀብ የሚሞቱ ህጻናትን፣ ምስኪን እናቶችን ማሰብ እንዴት ያቅተናል። ልጇን የምታበላው አጥታ የምታለቅስ እናት ጉዳይ መኖርን ያስጠላል፤ በረሀብ ሙሉ ሰውነቱ አልቆ የራስ ቅሉ ብቻ የቀረ አጥንቶቹ የሚቆጠሩ ህጻን መመልከት እጅግ ልብ ይሰብራል። ታፍሮ ተከብሮ ከሚኖርበት ቀዬ ቤተሰቡን ይዞ የተፈናቀለ ምንም ሊያደርግላቸው ባለመቻሉ ተስፋ የቆረጠ አባወራ ማየት ለአእምሮ ይከብዳል።
አንድ ቦታ ላይ የተሰበሰበ ከሰማይ የሚወርድ መናን የሚጠብቅ ምስኪን የተራበ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ማየት የልብ ስብራቱ መቼም አይድንም። የአገሬ ህዝብ ያሳዝናል። በቅጡ እንኳን በማይረዳው ፖለቲካ በሚሉት ጉድ ምክንያት ሜዳ የወደቀ የአገሬ ገበሬ ልብ ይነካል። ታድያ ይህን ሁሉ መአት አይቶ ስለሰላም እንደመማለድ ለሰላም አስተዋጽኦ እንደማድረግ ጦርነት እንዲቀጥል በለው፣ ጨርሰው፣ እያሉ መለፈፍ ምን ይሉታል። ስለ ሰላም መናገር ካልቻላችሁ ቢያንስ ዝም በሉ ጥላቻን አትናገሩ፤ ጦርነቱን አታበረታቱ፤ እልቂትን አትደግፉ።
የሰላም ዋጋ እንዲገባን ከዚህ የባሰ ምንም ነገር ሊፈጠር አይችልም። ምሁራን፣ የኪነጥበብ ሰዎች፣ በተለያየ ዘርፉ እውቅና ያላችሁ ተጽእኖ መፍጠር የምትችሉ። እባካችሁን በተራበች እናት ቦታ ሆናችሁ አስቡ ርቦት በሚያለቅስ ጨቅላ፤ መኖሪያ ቤቱ ወድሞበት ስደት የወጣ አባወራ፣ በረሀብ የሞተ ልጅን የመቅበር ስሜቱን ለመረዳት ሞክሩ። ከእናንተ የሚጠበቀው የፍቅር ሀሳብ ነው። የአንድነት ሀሳብ ነው። መልእክታችሁ ብዙ ሰው ጋር የመድረስ እድል አለው።ብዙዎችን የመለወጥ አቅም አለው። ስለዚህ ከዘረኝነት አስተሳሰብ ወጥታችሁ ፍቅርን ስበኩ አንድነትን ተናገሩ። በህይወታችሁ የማይፀፅታችሁን ነገር አድርጉ። ኢትዮጵያ መቼም አትፈርስም፣ጊዜ ይወስድ ይሆናል እንጂ ሕዝብም ተለያይቶ አይቀርም።
ይህም ቀን ያልፍና የሚያናቁረን ነገር ሁሉ ገለል ይላል። ይህ የተፈጥሮ ህግ ነው። እንኳን ህዝብ ይቅርና ፖለቲከኞቹ ራሳቸው የሚያግባባቸው ሀሳብ ላይ ሲደርሱ መታረቃቸው አይቀርም። እናንተ ግን በህይወታችሁ የማታፍሩበትን ታሪክ አስቀምጡ። ሠላም !
በአክበረት ታደለ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 29 ቀን 2014 ዓ.ም