የወልዲያው ጉብል
የጁ- ‹‹የእግዜር መሀል እጁ›› ከሚባልበት መሀል ወልዲያ ተወልደው አድገዋል። በእሳቸው ዘመን ‹‹ህይወት እንዳሁኑ አልከበደም። ‹‹ቀላልና መልካም ነበር›› ይላሉ። አቶ ዮሀንስ ሀይሉ። የዛኔ ያሻቸውን አላጡም። የፈለጉት ጉዳይ ከእጃቸው የራቀ አልነበረም።
የወልዲያው ዮሀንስ ልጅነታቸውን በየጁና አካባቢው በደስታ ቦርቀውበታል። ዕድያሜቸው ከፍ ማለት ሲጀምር ደግሞ ከትውልድ አገራቸው የጁ መራቅ ፈለጉ። በወቅቱ እሳቸውን መሰል እኩዮቻቸው ከከተማ ዘልቀው ህይወታቸውን እንደሚቀይሩ ያውቁ ነበር። እናም ዮሀንስ የእነሱን መንገድ ሊከተሉ አማራቸው። ያሰቡት አልቀረም። አንድ ቀን ጓዛቸውን ሸክፈው ተነሱ።
ወቅቱ የአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን ነበር። በንጉሱ ጊዜ እንደአሁኑ ከተማ አልሰፋም፣ ህዝብ አልበዛም። የእሳቸው ዘመዶች በአዲስ አበባ ይኖራሉ። አክስቶቻቸው እንግዳውን ጉብል ለመቀበል ፊታቸውን አያዞሩም። ይህን አሳምረው የሚያውቁት አፍላው ዮሀንስ በእርግጠኝነት ጉዞ ጀመሩ። የጁ ወልዲያን ተሰናብተው፣ ደሴ ኮምቦልቻን አልፈው፣ ከሸዋ ምድር ሲደርሱ እግራቸው ከደብረብርሀን አላለፈም። ደብረብርሀን የወታደሮች ካምፕ መኖሩን ሰምተዋል። ‹‹ጠባሴ›› ከተባለው ስፍራ ደርሰው ወደካምፑ አመሩ።
የጦር ካምፑ ሰዎች ወጣቱን ዮሀንስ አልገፏቸውም። በበጎ ተቀብለው ለእሳቸው የሚሆን ስራ ሰጧቸው። ልጅነት ከፍላጎት ተዳምሮ ጥረታቸው ሲጎላ የጦር ካምፑ ቋሚ ተቀጣሪ ሆኑ። በየወሩም ደሞዝ ይከፈላቸው ያዘ።
ዮሀንስ ‹‹እንጀራዬ›› ብለው በያዙት መተዳዳሪያ ራስን ማገዝ አወቁበት። ወጣትነት፣ ከአፍላ ጉልበት ታክሎ የጦር ካምፑ ቆይታ በጥንካሬ ተገፋ። ዓመታት እየጨመሩ፣ ጊዜው መክነፍ፣ መንጎድ ያዘ። እንደዋዛ አስራስምንት የስራ ዓመታት ተቆጠሩ።
1953 ዓ.ም አዲስ አበባ
አስራስምንት ዓመታትን በጠባሴ የጦር ካምፕ ያሳለፉት አቶ ዮሀንስ 1953 ዓ.ም ሲጀመር አዲስ አበባ መግባት አማራቸው። አዲስ አበባ ከደብረብርሀን ቅርብ በመሆኑ በመንገድ ብዛት አልደከሙም። በከተማው ደርሰው ነዋሪውን መሰሉ። እንግዳው ጥቂት ቀናት ቆይተው አዲስ ስራ ተገኘላቸው። ዕድላቸው መልካም፣ እግራቸው እርጥብ ሆነ። ያገኙት ስራ ከጃንሆይ ዕልፍኝ፣ ከቤተመንግስቱ አደረሳቸው።
ራስ መስፍን ስለሺ ዮሀንስን ገነተ ልዑል ቤተመንግሥት ባስገቧቸው ጊዜ ውስጣቸው በደስታ ተሞላ። ለስራ ፈላጊው ቤተመንግስት ይሉት እውነት አዲስ የሚባል ህይወት ነው። እሳቸው ከዚህ ቀድሞ በእንዲህ አይነቱ ልማድ አላለፉም። ስራውን በደስታ ተቀበሉ። ጥቂት ቆዩና ወደእዮቤልዩ ቤተመንግስት ተዛወሩ።
በቤተመንግስቱ እንደሌላው ዘው፣ ሰተት ተብሎ አይገባም። ስፍራው የራሱ በሆነ ንጉሳዊ ስርዓት ይመራል። በውስጡ የሚመላለሱ እንግዶች ተራ የሚባሉ አይደሉም። ገቢ ወጪው ሁሉ ለንጉሱና ቤተሰቦቻቸው፣ ለባለሟሎቻው ጭምር ‹‹ ለጥ ›› እያለ እጅ ይነሳል።
ዮሀንስና 1953 ዓ.ም በቤተመንግስት ሲገናኙ ወቅቱ ፈታኝ የሚባል አጋጣሚን ፈጠረ። የንጉሱን ሥርዓት አጥብቀው የሚቃወሙ ኃይሎች መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ ሞከሩ። የታህሳሱ ግርግር የፈጠረው ነውጥ እሳቸውን ጨምሮ ለመላ ኢትዮጵያውን ታላቅ ትኩረት ሳበ። ወንድማማቾቹ ገርማሜና መንግስቱ ንዋይ ለውጥ ሽተው ታሪክ ሊቀይሩ መነሳታቸው ደምቆና ጎልቶ ተሰማ።
ከጊዚያት በኋላ የታህሳሱ ግርግር በመንግስት ኃይሎች መክሸፉ ታወጀ። አገር ተረጋግቶ ህይወት እንደቀድሞው ቀጠለ። በወቅቱ አቶ ዮሀንስ በቤተመንግስቱ በተሰጣቸው የመዝገብ ቤት ስራ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ነበር። የዛኔ በግቢው የሚካሄደው ስርዓት በእጅጉ ይለያል። በዙፋን ችሎት የሚዘጋጀው ግብር በሶስት አይነት ደረጃ የተከፈለ ነው።
በመጀመሪያው ደረጃ የንጉሳውያን ቤተሰቦችና አቻዎቻቸው ሲቀመጡ በሁለተኛውና ሶስተኛው ደረጃ ደግሞ መካከለኞቹና ተከታዮቻቸው ይሰየሙ ነበር። በተመሳሳይም በማዕድ ገበታ ላይ የነበረው ስርዓት በደረጃ የተለየና በወጉ የተወሰነ እንደነበር ያስታውሳሉ።
በወቅቱ ዮሀንስ ከጃንሆይ ዓይን ቢገቡ የተለየ ሞገስ አገኙ። በተሰጣቸው ደረጃ ከገበታው እየታደሙ፣ ከሚቸራቸው ስጦታ በረከቱን እያገኙ በደስታ ዘለቁ። ጃንሆይ ዮሀንስን ባዩዋቸው ጊዜ የፍቅራቸውን ሊያደርጉላቸው አልሰሰቱም። በፉሪ፣ አጋሮና ጅማ ከተሞች የነበሩ ሰፋፊ ይዞታዎችን በጋሻ መሬት አስለክተው አበርከቱላቸው።
የዛኔ የልጅነት ዕድሜ ታክሎበት ስለነገ መጨነቅን አያውቁትም። ቦታውን ሸጠውና ለውጠው የመጠቀም ሀሳብ አልነበራቸውምና በዕድሉ አልተጠቀሙም። ስጦታዎቻቸውን በምስጋና እየተቀበሉ የቤተመንግስት ህይወታቸውን ቀጠሉ።
1966 ዓ.ም የአብዮቱ ፍንዳታ
አሁን በአገረ ኢትዮጵያ ሥር ነቀል ለውጥ አስፈልጓል። ሥርአቱን በሚቃወሙ አብዮታውያን ግፊት መስከረም 2 ቀን 1966 ዓም አብዮቱ ፈነዳ። ድንገቴው የመንግስት ለውጥ የብዙዎችን ህይወት ቀያየረ። ንጉሱ ከዙፋናቸው እንደወረዱ ዮሀንስን መሰል ሰራተኞች ከቤተመንግስቱ ሊለቁ ግድ ሆነ።
ዮሀንስ አሁንም ጎበዝ ጎልማሳ ናቸው። ያሉበት ዕድሜ ሰርቶ ለመግባት፣ ሮጦ ለማደር ብቁ ነው። ከጃንሆይ የተበረከተላቸው ጥቂት የማይባል ጋሻ መሬት እንደተበላ ዕቁብ ሆኗል። ደርግ ‹‹መሬት ለአራሹ›› ሲል ባወጣው አዋጅ የእሳቸውን ጨምሮ የበርካቶች ሀብት ንብረት ተነጥቋል።
እስከዛሬ ከንጉሱ በስጦታ የተበረከተላቸው ጋሻ መሬት ከእጃቸው አልገባም። አሁን ከስም በቀር ያተረፉት የለም። ደግነቱ ለአንገታቸው ማስገቢያ፣ የቀበሌ ቤት አላጡም። ከለውጡ በኋላ ስራ መፈለግ የጀመሩት ዮሀንስ አንድቀን የልባቸውን መሻት ሞላ። አውራ ጎዳና ይባል ከነበረው መስሪያቤት ተቀጠሩና ደሞዝተኛ ሆኑ።
ስራቸው ከበርካቶች ጋር ያገናኛል። የዛኔ ከአንድሺህ አምስት መቶ በላይ ሰራተኞችን ያስተዳድሩና ይመሩ ነበር። ዮሀንስ ረጅሙን ዓመታት በመስሪያቤት አሳለፉ፡ በኃላፊነት የተሰጣቸውን እየከወኑ፣ በታዛዥነት ግዴታቸውን እየተወጡ የስራ ዓለም ቆይታቸውን አጠናቀቁ። ዕድሜያቸው ደርሶ በጡረታ ሲሰናበቱ በውስጣቸው የኖረው የመስራት ፍላጎት አልቀዘቀዘም።
ከጡረታ ማግስት …
ገና በአፍላ ዕድሜ ካገራቸው የወጡት ዮሀንስ ዓመታትን በስራ ዓለም ቆይተው በጡረታ ተሰናብተዋል። አሁን ዕድሜያቸው ጨምሯል፡ የቀድሞው መልክና ቁመና ከእሳቸው ጋር አይደለም። እንደቀድሞው ባይሆኑም ለስንፍና እጅ አልሰጡም። ከመስራት ፍላጎት ጋር ኑሮን ሊጋፈጡ ስራ መፈለግ ይዘዋል።
ለጡረታ የሚሰጣቸው ገንዘብ እዚህ ግባ አይባልም። ኑሮ ሲጨምር ህይወት መክበድ ይዟል። ይህ እውነት በዙሪያቸው ያለው ዮሀንስ ገቢያቸውን ከወጪ እያዛመዱ ደጋግመው አሰቡ። ከጎናቸው ማንም የለም። ትዳር ይዘው ቤተሰብ አልመሰረቱም። ጎጆ ቀልሰው ወግ ማዕረግ አላዩም። አንዳንዴ አንዳንድ ሁኔታዎች በዓይናቸው ውል እያሉ ይፈትኗቸዋል። ያም ሆኖ ብቸኝነት ብቻውን አልበገራቸውም።
ትዳር በማምሻ
ዕድሜ …
ዮሀንስ በጡረታ ተሰናብተው ከቤት ውለዋል። መሮጥ ለማይሠለቻቸው ብርቱ ያለስራ መቀመጡ እያስጨነቃቸው ነው። ይህ አጋጣሚ ግን መልካም ዕድል ያመጣ ይመስላል። ለአዛውንቱ አባት ጎናቸውን የምታሞቅ፣ ቤታቸውን የምታደምቅ ግራጎን ተገኝታለች። ይህ እውነት እስከዛሬ ትዳር ይሉትን ላልሞከሩት ሰው ታላቅ ለውጥ ሆኗል።
በዮሀንስ ህይወት ብቸኝነት ተወግዷል። ከሆቴል መብላት፣ ከውጭ አምሽቶ መግባት በነበር ተረስቷል። አሁን በቤት ያለችው ወይዘሮ ስለ ጓዳዋ ታስባለች፣ ስለባሏ ትጨነቃለች። ጥንዶቹ የዕድሜ አቻዎች አይደሉም። ያም ሆኖ ተሳስበው፣ ተከባብረው ይኖራሉ። አሁን ለዓመታት ተዘግቶ የኖረው ቤት ወግ ደርሶታል። እንደሌሎች በር ተከፍቶ ይውላል። ዝምታ የዋጠው ጎጆ ቤተዘመድ ይጎበኘዋል፣ ወዳጅ ጎረቤት ያየዋል።
በዮሀንስ ኑሮ አዲስ ምዕራፍ እየተጀመረ ነው። ጡረተኛው አባወራ የማምሻ ዕድሜያቸው ሌላ በረከት አስከትሏል። ህይወታቸው በልጅ ስጦታ ታድሷል። የትዳራቸው ፍሬ፣ ወንድ ልጅ አሳቅፏቸዋል። አዛውንቱ አባት ኑሮን እንደ አዲስ ይመሩት ያጣጣሙት ይዘዋል።
ዓመታትን የዘለቀው ትዳር በልጅ በረከት ሲታደስ የኑሮ ትርጉሙ ተለየ። ዮሀንስ ስለልጃቸው ያስቡ ይጨነቁ ያዙ። አሁን ሌላ ነፍስ ቤታቸውን ተቀላቅሏል። ለጨቅላውና ለጎጇቸው ተጨማሪ ገቢ ያሻል። በእርግጥ ጥቂት የጡረታ አበል ከኪሳቸው ይደርሳል። ይህ ብቻ ግን በቂ አይሆንም። ይህን ያወቁት አዛውንት በዝምታ አልተቀመጡም። ለባለጉዳዮች ጉዳይ ማስፈጸም ጀምረዋል።
ጥቂት ቆየና የባለቤታቸው ጤና አሳሳቢ ሆነ። የጨቅላው እናት ሆስፒታል መመላስ ያዙ። እያደር ሰላም የነሳቸው ህመም ከአልጋ ማዋል ጀመረ። ከሰሞኑ የሆነው ግን ከሌላው ቀን ተለየ። ወይዘሮዋ በእጅጉ ታመዋል፡ ሁኔታቸው አስጊ እየሆነ ነው። ብዙዎች ስለሳቸው ያስባሉ፣ ይጨነቃሉ። የተፈራው አልቀረም። የአቶ ዮሀንስ ባለቤት በህይወት ወደቤታቸው አልተመለሱም። ጨቅላ ልጃቸውን ትተው፤ ቤት ትዳራቸውን አራግፈው እሰከወዲያኛው አሸለቡ፤
ህይወት በሌላ ገጽ
ዛሬ እንደትናንቱ አልሆነም። ህይወት በሌላ መልክ ተቀይሯል። የጎጆው ድባብ ዝምታ ውጦታል። የአዛውንቱን ትዳር ሞት ፈቶታል። አባወራው የማምሻው ዓለማቸው እንደጅማሬው አልሰመረም። አሁን በቤቱ የወይዘሮዋ ድምጽ የለም። የትንሹ ልጅ ሳቅና ለቅሶ አይሰማም። ዮሀንስ ግራ ገብቷቸዋል። አንድዬ ልጃቸው ከአያቱ እጅ ገብቷል። ብቸኝነት፣ ሀዘንና ብሶት ከቧቸዋል።
ህይወት እየከበደ፣ ኑሮ እያሻቀበ ነው። ትልቁ ሰው ከሆቴል መብላት ጀምረዋል። ውለው ሲገቡ በፈገግታ የሚቀበላቸው የለም። ድምጻቸው ቢጠፋ፣ በወጡበት ቢቀሩ አስታዋሽ የላቸውም። በየቀኑ የባለጉዳዮችን ዶሴ ይዘው ይወጣሉ። ለሰሩበት ጥቂት ይከፈላቸዋል። የሚያገኙትን ገንዘብ በዕለት ይጎርሱበታል። ሲነጋ ለሌላ ስራ ዓይናቸው ይማትራል። ካገኙ ለኪሳቸው አያጡም።
ከሀምሳ አራት ዓመት በላይ የኖሩበት የአራት ኪሎ ሰፈር ለልማት ተፈልጎ መነሳት ጀምሯል። የዮሀንስ የቀበሌ ቤት ከመፍረስ አልዳነም። እሳቸውም እንደሌሎቹ ምትክ ቤት አግኝተው ከስፍራው ለቀዋል። ይህ መሆኑ አዛውንቱን አላስጨነቀም። የግለሰብ ቤት ተከራይተዋል። የተጠየቁትን ክፍያ አሟልተው የጋራ ቤቱን ተረክበዋል።
እርጅና ብቻህን ‹‹ ና ››
ህይወት በብቸኝነት ቀጥሏል። ዮሀንስ እንደቀድሞው አይደሉም። ዕድሜያቸው ገፍቷል። አካላቸው ደክሟል። እያሰለሰ የሚያስታውሳቸው ሕመም ጤና እየነሳቸው ነው። በአንድ ወቅት ያጋጠማቸው የመኪና አደጋ ጉዳት ቀን ቆጥሮ ይሰማቸው ይዟል። በህክምና ስህተት ‹‹ጠፍቷል›› የሚሉት አንድ ዓይናቸው ታሟል። ሲራመዱ በዝግታ ነው። አካባቢውን ከለቀቁ ወዲህ የሞካከሩት የቤት ኪራይ ምቾት የለውም።
ቦሌ ቡልቡላ የተሰጣቸውን ቤት አልፎ አልፎ ያዩታል። ቤቱ ቢከራይ ገቢው ይጦራቸዋል። ቢቆይ ደግሞ ለልጃቸው ይሆናል። ልጁ አሁንም አያቶቹ ዘንድ እየኖረ ይማራል። ከእሳቸው አንዳች አይፈልግም። ዮሀንስ ዛሬም ከህይወት ግብግብ ይዘዋል። ዕድሜቸው ቢገፋም፣ እጅ መስጠት አይሹም። መቀመጥ ይሉትን አይወዱም። ቢደክማቸውም ይዞራሉ። ባይሰሩም ገንዘብ ያስፈልጋቸዋል። ለመኖር መብላት አለባቸው።
ያመኑት ፈረሰ…
አሁን መውጣት መውረዱ አዝሏቸዋል። በተሰጣቸው ቤት ባይኖሩም መጠቀም እንዳለባቸው ያምናሉ። በቤቱ ጉዳይ የልባቸውን እንዳይደርስ ዕድሜቸው ፈተና ሆኗል። እንዲያም ቢሆን መፍትሄ አላጡም። ለውጣውረዱ ወኪል ቢኖራቸው የሀሳባቸው ይሞላል። ዮሀንስ አውጥተው አውርደው ከአንድ ሰው ደረሱ። ለውክልና ያሰቧት የቅርብ ጓደኛቸውን ልጅ ሆነ። ይህች ሴት እንደሳቸው ሆና የሀሳባቸውን ትከውናለች። በቤቱ በሚኖረው ጉዳይ ሁሉ ውክልናውን ትወስዳለች።
አቶ ዮሀንስ በሙሉ አመኔታ በእጃቸው ያለውን ዶሴ ለተወካያቸው አስረከቡ፡፤ ወኪሏ ለቤቱ እንደሳቸው ልትሆን ቃል ገብታ ኃላፊነቱን ወሰደች። ጊዚያት ተቆጠሩ። ዮሀንስ፡ አሁን ስለ ቤቱ ማሰብ ትተዋል። ለዕለት ጉርሳቸው አላጡም። ለኪሳቸው የሚተርፍ ጥቂት ገንዘብ ከእጃቸው ይገባል።
አንድ ቀን ዮሀንስ ድንገት ለጆሯቸው የደረሰውን እውነት ማመን ተሳናቸው፡፤ የሚሰሙት ሁሉ ሀሰት ቢመስላቸው በርካቶችን ደጋግመው ጠየቁ። የሁሉም ምላሽ አንድ ሆነ። የባልንጀራቸው ልጅ፣ በዕምነት የሰጧትን ቤት በውክልናዋ ተጠቅማ ሸጣዋለች። የሰሙትን ባለማመን ያመኗትን ሴት በፍለጋ አሰሱ። አላገኝዋትም።
እንደዋዘ ከእጃቸው የተነጠቀውን ሀብታቸውን እያሰቡ በትካዜ አንገት ደፉ። ውስጣቸው አረረ፣ ሀዘናቸው ከፋ። በእጃቸው የቀረ አንዳች ሰነድ ያለመኖሩን አሰቡ። ሁሉንም በህጋዊ ውክልና በህገወጥ ሂደት ተዘርፈዋል። ዕድሜቸውን አሰቡት። ሸምግለዋል። ለሩጫ የሚተርፍ፣ ለሙግት የሚበረታ ጉልበት ከእሳቸው የለም። ተወካያቸውን አጥብቀው ፈለጓት፣ አስፈለጓት። የግል ቤቷን ሸጣ ከአካባቢው መራቋ ተነገራቸው። ቆይተው የእሳቸው ኮንዶሚኒየም ከተለያዩ ሰዎች አርፎ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ስለመሸጡ አወቁ። አንዳች ማድረግ አልቻሉም። ከእንግዲህ ጥርሰ የሌለው አንበሳ ሆነዋል።
ኑሮን በእንክርት…
ዛሬ አቶ ዮሀንስ ኑሮ በእጅጉ ከብዷቸዋል። ከጎናቸው ወዳጅ ዘመድ የለም። በእጃቸው ጥሪት አልተረፈም። ከእንግዲህ ተከራይተው መኖር አይችሉም። ከሆነላቸው በቀን አንዴ ይጎርሳሉ። ሁሌም በአንድ አይነት ልብስ ይታያሉ። ጥቁር ካፖርታቸው የሩቅ መለያቸው ነው።
ዛሬ ላይ ቆመው ትናንትን ያስባሉ። ቀድሞ በሳንቲም የሚመገቡበት ቤት አሁን በመቶብሮች ይጠየቃል። መኖሪያ ማደሪያ የላቸውም። ለነፍስ ያሉ በሚቸሯቸው ገንዘብ ከቤርጎ አድረው ጎናቸውን ያሳርፋሉ። አንዳንዴ ከአውቶቡስ ፌርማታ ለማደር ጋደም ይላሉ። ትናንት የሚያውቋቸው አንዳንዶች ስለሳቸው ግድ ባላቸው ጊዜ ከእነሱ ጥግ እንዲያድሩ ይፈቅዱላቸዋል። ቆፍጣናው ዮሀንስ እጅን ለልመና መዘርጋት ሞታቸው ነው። ገንዘብ ሲሰጧቸው ይበሳጫሉ፣ ቁጣ ቁጣ ይላቸዋል።
ክረምቱ ደረሰ – ቤት ያላችሁ ግቡ
ሽማግሌው ኑሮ በእጅጉ ከብዷቸዋል። አንድዬ ልጃቸው ኮሌጅ ተምሮ መመረቁን ያውቃሉ። ስራ ባለመያዙ ለችግራቸው አልደረሰም። አሁን ሰኔ ግም ሊል ክረምቱ ሊመጣ ነው። ቤት የለሹ ዮሀንስ ዝናቡ፣ ብርዱ ያሳስባቸዋል። ነገ የሚሆነውን አያውቁም። የዕድሜ ጫና፣ የሰዎች ክፋትና ያለባቸው ችግር ከጎዳና ሊገፈትራቸው አሰፍስፏል።
አሁን ዮሀንስ ተመልካች ዓይኖችን ይሻሉ። በቀን አንዴ ብቻ ለሚጠቀሙት እህልውሀ፣ ለሚያድሩበት ቤርጎ ይከፍሉት የላቸውም። ጎዳና እየወጡ ነው። አጥተዋል፣ ነጥተዋል። እንዲህ ለመኖር ለሚውተረተሩት አዛውንት እጆቻችን ይረባረቡ። ‹‹አለንዎ›› እንበላቸው። የአገር ባለውለታ ናቸውና።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2014