አዲስ አበባ፡- የወጣቶችን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ታስቦ በ2009 ዓ.ም በመንግሥት የተመደበው 10 ቢሊዮን ብር የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ በአስፈፃሚ አካላት ቅንጅት አለመኖር የታለመለትን አላማ ማሳካት እንዳልተቻለ የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሚኒስቴሩ የወጣቶች ማሳተፍና የሥራ ዕድል ፈጠራ ባለሙያ አቶ ብርሃኑ ፋንታዬ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ የሚፈለገውን አላማ እንዳያሳካ ያደረገው የአስፈጻሚ አካላት የቅንጅት አለመኖር፣ ወጣቱን ውጤታማ በሆኑ የሥራ መስኮች አለማሰማራትና የክልሎች አፈጻጸም አነስተኛ መሆን ነው፡፡
«ክልሎች ተዘዋዋሪ ፈንዱ ስኬታማ እንዲሆንትኩረት ሰጥተው አልሠሩም» ያሉት አቶ ብርሃኑ፤ በጥናት ላይ የተመሰረተ የወጣቶች ፍላጎትና አዋጭ የሥራ መስክ ተመርጦ መተግበር ሲገባው በተቋማት መካከል ተናቦ ባለመሠራቱ የሚፈለገውን ውጤት ማግኘት እንዳላስቻለ አንስተዋል።
አካባቢን መሰረት ያደረገ ተግባር አለመከወኑና ሥልጠና በመስጠት ወደ ሥራ አለመገባቱ እንዲሁም ምቹ የሆነ የብድር አገልግሎት አለመኖሩ አላማው ግቡን እንዳይመታ እንዳደረገው ገልጸዋል። ወደሥራ የገቡት ወጣቶች በቂ ክትትልና ድጋፍ አለማግኘታቸውም አንዱ ችግር መሆኑን ተናግረዋል።
የገንዘብ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሃጂ ኢብሳ እንደገለጹት፤ ለክልሎች የተመደበው ገንዘብ በወቅቱ ተለቋል። ከዚያ ያለፈውን ሥራ የሚከታተሉትና ቁጥጥር ማድረግ ያለባቸው ራሳቸው ክልሎቹ ናቸው። ተዘዋዋሪ ፈንዱ ለታለመለት አላማ እንዲውል ደግሞ በፌዴራል ደረጃ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና በክልል ደግሞ ርዕሰ መስተዳድሮቹ እንዲመሩት ተደርጓል።
ሆኖም ክልሎች ለወጣቶች ስኬታማነት ተቀናጅተውና ኃላፊነት ተሰምቷቸው ካልሰሩ ችግሩ መፈጠሩ አይቀርም። ለክልሎች ከተመደበው ገንዘብ 91ነጥብ3 በመቶ ወይም 9 ቢሊዮን 125 ሚሊዮን 757 ሺ 385 ነጥብ24 ብር መልቀቁን ገልጸው፤ ገንዘቡ ለታለመለት አላማ መዋል አለመዋሉን መከታተልና ቁጥጥር ማድረግ የክልሎቹ ድርሻ እንደሆነ አስረድተዋል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የሥራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕርይዞች ልማት ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ተሰማ በበኩላቸው፤ በክልሎችና በፌዴራል ደረጃ ባለው የአሰራርና የቅንጅት ችግር ምክንያት ክልሎቹ በጀቱን በወቅቱ እንዳያገኙ እንቅፋት እንደሆነባቸው ገልጸዋል። ወጣቶቹን ለማደራጀት የወጡ መስፈርቶች አስቸጋሪ መሆን፤ ወጣቶቹ ሥራ ከመጀመራቸው በፊት ተገቢውን ሥልጠና አለማግኘታቸው ተዘዋዋሪ ፈንዱ የታለመለትን ግብ እንዳይመታ አድርጓል ብለዋል።
በወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ 700 ኢንተርፕራይዞችና ከ4000 በላይ ወጣቶች ተሳታፊ ቢሆኑም ኢንተርፕራይዞቹ ውጤታማ እንዳልሆኑ የሚያነሱት አቶ ፍቃዱ፤ ወጣቶችን ለማደራጀት የተቀመጠው አሰራር ወጣቶቹ በሚፈልጉት መልክ እንዳይደራጁና የፈለጉትን ሥራ እንዳይሠሩ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።
ወጣት ሚኬሎ ተስፋዬ፤ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ጎፋ ሰፈር ከሦስት ጓደኞቹ ጋር ተደራጅቶ የፈለገውን አይነት ሥራ ለመሥራትና ለመለወጥ፣ ለሌሎች የሥራ እድል ለመፈጠር አላማው አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም ብዙ ፈተና እየገጠመው መሆኑን ገልጿል። ለመደራጀት የተቀመጠው መስፈርት ብድር ማግኘት እንዳላስቻላቸው ጠቅሶም ከጓደኞቹ ጋር ተለያይተው መለወጥ ያልቻሉበትን ሥራ በመሥራት ላይ መሆናቸውን ተናግሯል።
«ምቹ ሁኔታ ቢፈጠርልን ተደራጅተን የተሻለ ውጤት ማስመዘገብ እንችል ነበር» ያለው ወጣት ሚኬሎ አሁን እየሠሩ ባሉት ሥራ የተሰጣቸውን ብድር እንኳን ለመመለስ እንዳልቻሉ ጠቅሷል። «ክልሎች ተዘዋዋሪ ፈንዱ ስኬታማ እንዲሆን ትኩረት ሰጥተው አልሠሩም» ያሉት አቶ ብርሃኑ በጥናት ላይ የተመሰረተ የወጣቶች ፍላጎትና አዋጭ የሥራ መስክ ተመርጦ መተግበር ሲገባው በተቋማት መካከል ተናቦ አለመሥራት የሚፈለገውን ውጤት ማግኘት እንዳላስቻለ ይገልጻሉ፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 15/2011
በተገኝ ብሩ