የአምቦ – ወሊሶ መንገድ ፕሮጀክትን በመጪው ዓመት ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ ፦ በኦሮሚያ ክልል የደቡብ ምዕራብ ሸዋ እና የምዕራብ ሸዋ ዞኖችን የሚያገናኘውን የአምቦ-ወሊሶ የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ እስከ 2018 ዓ.ም አጋማሽ አጠናቆ ለማስረከብ እየተሠራ መሆኑን መከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ አስታውቀዋል።

የአምቦ-ወሊሶ መንገድ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ የማነህ ከበደ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ 64 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የአምቦ ወሊሶ የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ አፈጻጸም 49 በመቶ ደርሷል። የመንገዱን አስፓልት ማንጠፍ ሥራ በ2017 ዓ.ም መጨረሻ፤ አጠቃላይ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታው በ2018 ዓ.ም አጋማሽ አጠናቆ ለማስረከብ እየሠራ ነው።

የፕሮጀክት ግንባታው በ2008 ዓ.ም መጀመሩን አስታውሰው፤ በወቅቱ የመንገድ ፕሮጀክቱን ኤልሳሜክስ የተባለ የስፔን ተቋራጭ በሦስት ዓመት ውስጥ ግንባታውን ሠርቶ ለማስረከብ ውል ገብቶ ሲሠራ ቆይቷል፤ ሥራውን ውል በገባበት የጊዜ ገደብ ባለማከናወኑ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የተቋራጩን ውል ማቋረጡን ገልጸዋል፡፡

በ2011 ዓ.ም መከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ፕሮጀክቱን መረከቡን አስታውሰው፤ ኢንተርፕራይዙ የመንገድ ፕሮጀክቱን በ2013 ዓ.ም በሦስት ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ ውል ተገብቶ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ድርጅታቸው የመንገድ ግንባታውን በፍጥነት በማከናወን በተቀመጠለት ጊዜ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ጥረት ቢደረግም በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታው ሊዘገይ ችሏል ብለዋል።

እንደ አቶ የማነህ ማብራሪያ፣ የመንገድ ግንባታው ለመዘግየቱ በዋናነት ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ የካሣ ክፍያ መዘግየት፣ የዋጋ ንረትና የግንባታ ግብዓት አቅርቦት እና ተያያዥ ችግሮች በግንባታ ሂደቱ ላይ ቀላል የማይባል አሉታዊ ተፅዕኖዎችን አሳድረዋል፡፡ ይህም ቢሆን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ክፍያውን እስኪፈጽም ሥራው መቆም ስለሌለበት ክፍያውን በመፈጸም ሥራዎች እንዲቀጥሉ ለማድረግ ተሞክሯል።

ከዚህ በተጨማሪ ከአካባቢው ነዋሪዎች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከአመራሩ ጋር እየተገናኘን ከግብዓት አቅርቦት ጋር በተያያዘ ያሉትን ችግሮች በመመካከር በትብብር ለመፍታት እየሠራን እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በፕሮጀክቱ አጠቃላይ 64 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህ ውስጥ እስካሁን 46 ኪሎ ሜትር መንገድ አስፓልት ተሠርቷል። የሚቀረው 18 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ በ2017 ዓ.ም መጨረሻ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ እየተሠራ እንደሚገኝ፤ የመንገድ ዳር መፋሰሻውን ጨምሮ አጠቃላይ የመንገድ ፕሮጀክቱ በ2018 ዓ.ም አጋማሽ እንደሚጠናቀቅ አስታውቀዋል።

የመንገድ ፕሮጀክቱ ለረጅም ጊዜ በመጓተቱ በአካባቢው ኅብረተሰብ ላይ የተፈጠረ የልማት ጥያቄ መኖሩን አንስተው፤ ተቋራጩ የኅብረተሰቡን ቅሬታ ለመፍታት በፍጥነት አጠናቆ ለማስረከብ እየሠራ መሆኑን አመልክተው፤ ኅብረተሰቡ ፕሮጀክቱ እስኪጠናቀቅ አብሮነቱን እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል። በ2008 ዓ.ም የአምቦ-ወሊሶ መንገድ ፕሮጀክት ሲጀመር በአንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ለማጠናቀቅ በጀት ተይዞ እንደነበር አመልክተው፤ አሁን ላይ በጀቱ ተከልሶ አጠቃላይ የፕሮጀክቱ ወጪ ወደ ሦስት ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ከፍ ብሏል። የበጀት ክለሳው በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ታምኖበት መሻሻሉንም ጠቁመዋል፡፡

ዳንኤል ዘነበ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ታኅሣሥ 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You