ወጣት ትኩስ ሃይል ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ ይህ ትኩስ ሃይል በብዛት የሚገኝባት አገር ናት። ይህ ሃይል ጥቅም ላይ እስካልዋለ ድረስ ግን ቁጥር ብቻ ነው የሚሆነው። የአገር እድገት ሲታሰብም ወጣቱን በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በስፋት ማሳተፍ ያስፈልጋል። ለወጣቱ የስራ እድል መፍጠርም የግድ ይላል።
ይህን ማድረግ ካልተቻለ ግን ወጣቱ ሃይል ለማህበረሰብ፣ ለአገርና ለመንግስት መልሶ ስጋት መሆኑ አይቀርም። በተለይ ደግሞ የወጣት ስራ አጥ ቁጥር ማሻቀብ ቁጣን ቀስቅሶ በመንግስት ላይ ድንጋይ ለመወርወር ይጋብዛል። ይህ ትኩስ ሃይል በአግባቡ ስራ ላይ ባለመዋሉ አገሪቷንም በርካታ ገቢ ያሳጣታል። ለዚህም ነው በወጣቶች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት አስፈላጊ ነው የሚባለው።
በአሁኑ ጊዜ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በየአመቱ ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። ይህ ሁሉ የተማረ ወጣት ታዲያ ሁሉም ተቀጥሮ ይሰራል ማለት አይደለም። ተቀጥሮ ለመስራት እንኳን ውድድሩ ቀላል አይሆንም። ከዚህ አኳያ ወጣቱ በራሱ ስራን ፈጥሮ መስራት መልመድ አለበት። መንግስትም ወጣቶች የራሳቸውን ስራ ፈጥረው እንዲሰሩ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይኖርበታል።
የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ይታወቃል። ህዝቡ በጦርነት ውስጥ አልፏል። ድርቅ፣ መፈናቀል፣ ሞትና የቤት ንብረት ውድመት ተከስቷል። የኑሮ ውድነቱ ጨምሯል። የፖለቲካ ትኩሳቱ ጦዟል። አገሪቷም በፈተና ውስጥ ትገኛለች። ወጣቱ ደግሞ የዚህ ፈተና አንዱ አካል ነውና በዚህ ወቅት ከወጣቱ ብዙ ነገር ይጠበቃል። ለመሆኑ በዚህ የፈተና ወቅት ከወጣቱ ምን ይጠበቃል? ፈተናዎችንስ እንዴት ማለፍ ይኖርበታል?
ወይዘሪት ሌሲ በላይ ኮንሰርቲየም ዩዝ ዴቨሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን ኢን ኢትዮጵያ የተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ድርጅቱ ከአምስት ክልሎች ማለትም አዲስ አበባ፣ አማራ፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ ኦሮሚያና ትግራይ በተውጣጡ የወጣት ድርጅቶች በ2005 ዓ.ም ተቋቁሟል።
በ2005 ዓ.ም በወጣቶች ስነ ተዋልዶ ጤና ላይ ያተኮረ ሲምፖዚየም በባህርዳር ከተማ ተካሂዶ ነበር። በዚሁ ሲምፖዚየም ላይ በአብዛኛው የሚወራው ስለወጣትና ስነ ተዋልዶ ጤና ነበር። ሆኖም በዚህ ሲምፖዚየም ላይ ወጣቱን ህብረተሰብ ወክሎ የሚናገር አካል አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ሌሎች ሰዎች ነበሩ ስለወጣቶች ሲያወሩ የነበሩት።
በጊዜው በሲምፖዚየሙ ላይ የተገኙት ወጣቶች ስለኛ ለምን እናንተ ትናገራላችሁ ስለኛው እኛው እንናነገር በሚል አነሳሽነት ድርጅቱ ሊቋቋም ችሏል። የድርጅቱ ዋነኛ አላማውም የወጣት ህብረት በመፍጠር ወጣት መርና ወጣት ተኮር ድርጅቶች አንድ ላይ ሆነው በተለያዩ ወደ አስራ ሶስት ጉዳዮች ላይ በጋራ ይሰራሉ።
ከነዚህ ጉዳዮች ውስጥም የስነ ተዋልዶ ጤና፣ ወጣቶችን ማብቃት፣ ስራ አጥነትና ስደት ይገኙበታል። ድርጅቱ በዋናነት የሚሰራው ግን በጋራ መስራትን መፍጠርና እነዚህን ወጣት ተኮር ድርጅቶችን የማብቃትና ማበረታታት ነው።
እንደ ወይዘሪት ሌሲ ገለፃ የድርጅቱ ዋነኛ ስራ ትግበራ ላይ ሳይሆን ወጣት ተኮር ድርጅቶችን ወደ አንድ የማምጣትና እነርሱ የሚሰሩትን ሥራ ወደ ፖሊሲ ቀይሮ የማስረፅ ነው። ከዚህ አንፃር በወጣቶች ህብረት ምክር ቤት በኩል በተለይ በአገራዊ ምክክር መድረኩ ወጣቶች በምን መልኩ መሳተፍ እንዳለባቸውና ምን ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አብሮ በመወያየትና ለወጣቱ ድምፅ በመሆን ስራዎችን እየሰራ ይገኛል።
ድርጅቱ በወጣቱ በኩል ያለውን ጉዳይ ለመሸፈንና ድምፅ ለማሰማት ብሎም በጋራ ለመስራት ባሉ ፕሮግራሞች ላይ ይካፈላል። የድርጅቱ አባል የሆኑ ወጣቶችን በተለያዩ መድረኮች በመላክና ድምፃቸውን እንዲያሰሙ በማድረግ የራሳቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱም እያደረገም ይገኛል።
ድርጅቱ ከዚህ በፊት በ2012 ዓ.ም ምርጫ ሊካሄድ ሲል ፕሮጀክቶችን ቀርጾ የተለያዩ ውይይቶች በወጣቶች በኩል ይካሄድ ነበር። ወጣቱ እንዴት አድርጎ ድምፁን ማሰማት እንዳለበትና በተለይ ወጣት ሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ በዲሞክራሲ ላይ ያለው አስተዋጽኦ ለማሳደግ ሴቶች ምን ማድረግ እንዳለባቸውና ግጭትን እንዴት ማስወገድ እንደሚኖርባቸው የተለያዩ ርእሶችን በማንሳት ወጣቶች ውይይት ሲያካሂዱ ነበር።
ይህ ውይይት እንዲሰረፅና በአመራር ላይ ያሉ ሰዎች በምርጫና የተለያዩ ስራዎች ላይ እንዲሳተፉ የማድረግ፣ ወጣቶች ራሳቸውን በምርጫ እጩ ተወዳዳሪ አድርገው እንዲቀርቡ የማድረግና ይህንን እንደሚችሉ የማሳወቅ ስራዎችንም ድርጅቱ ሲሰራ ቆይቷል።
አሁንም በተመሳሳይ ድርጅቱ ከወቅታዊ አገራዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ወጣቶች የራሳችን ድርሻ ነው ብለው ግጭቶችን በተለያዩ መንገድ ማስወገድ እንዲችሉና ይህንኑ ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ወደ አንድ የማምጣትና የማቀናጀት ስራዎችን እየሰራ ይገኛል። በተለይ ደግሞ ወጣት ተኮር ከሆኑ ድርጅቶች ጋር አጋርነት በመፍጠር በወቅታዊ አገራዊ ሁኔታ ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የማብቃት ስራዎችንም እያከናወነ ነው።
በአገራዊ የምክክር መድረኩ ላይ ወጣቶች ተሳታፊ ሆነው ሃሳባቸውን እንዲያቀርቡ ድርጅቱ ከወጣቶች ምክር ቤት ጋር በተለያዩ መድረኮች ላይ በተደጋጋሚ ተገናኝቶ ተወያይቷል። በአገራዊ ምክክሩ የድርጅቱና የወጣቱ ድርሻ ምን እንደሆነም ጠይቋል። በወጣቶች ዙሪያ የሚሰሩ ድርጅቶች በአገራዊ ምክክሩ በምን መልኩ መሳተፍ እንደሚችሉም አውርቷል። ጉዳዩ አገር አቀፍ በመሆኑ በየአካባቢው ያሉትን ወጣቶች በአገራዊ ምክክሩ ተደራሽ ማድረግ ይቻላል።
ከዚህ አንፃር ድርጅቱ ከአገራዊ የምክክር መድረኩ ጋር በተያያዘ ወጣቶች ተሳታፊ ሆነው ሃሳባቸውን እንዲያካፍሉ እንደ ድልድይ ሆኖ ያገለግላል። ወጣቶች እነሱን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑም ያነቃቃል። ሁኔታዎችንም ያመቻቻል።
ወይዘሪት ሌሲ እንደሚሉት ከሰሞኑ ከወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ጋር በተገናኘ ለአባል የወጣት ተኮር ድርጅቶች በጉትጎታና ተሟጋችነት ዙሪያ ሥልጠናዎች ሲሰጡ ነበር። ወጣቶች ፀብና አምባጓሮ አስነስተው ፍላጎታቸውን ለማሳካት ከመጣር ይልቅ ከግጭት የፀዱ መንገዶችን በመከተል ድምፃቸውን ማስማት እንደሚችሉ ከዚህ ስልጠና ተምረዋል።
በሰላማዊ መንገድ ወጣቶች ድምፃቸውን በማሰማት የመንግስትን ፖሊሲ ማስቀየርና መንግስት ላይም ተፅእኖ ማሳደር እንደሚችሉም ተረድተዋል። የጉትጎታና ሙግት ጉዳይ ደግሞ በኢትዮጵያ ብዙም ያልታወቀ በመሆኑ ሁሉም አባል የወጣት ድርጅቶች ስልጠናውን እንዲያገኙ ተደርጓል።
በሌላ በኩል ደግሞ የድርጅቱ ዋነኛ ራዕይ ወጣቱ የግጭቶች ሰለባና የጥፋት ሃይሎች መሳሪያ እንዳይሆን በመሆኑ በዚህ ላይ ትልቅ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል። በተለይ ደግሞ ድርጅቱ ራሱን የሚያውቅና በራሱ መወሰን የሚችል ወጣት እንዲፈጠር አበክሮ ይሰራል።
ይህ ስራ ሲሰራ ታዲያ ወጣቱን ወደ ግጭትና ለጥፋት ሃይሎች መጠቀሚያ የሚያመሩት ምክንያቶችን መለየት ያስፈልጋል። ምክንያቶቹ ግን በርካቶች ሊሆኑ ይችላሉ። ለአብነትም ስራ አጥነትን መጥቀስ ይቻላል። ወጣቱ ስራ አጥ ባይሆን ኖሮ የማንም መጠቀሚያ አይሆንም። ገንዘብ ለማግኘትም ሆነ በተለያዩ ጉዳዮች ምክንያት ወጣቶች የነዚህ የጥፋት ሃይሎች መጠቀሚያ ሲሆንም ይታያል።
ከዚህ አንፃር ድርጅቱ ወጣቱ የጥፋት ሃይሎች መጠቀሚያ ወደሆነበት መነሻ ምክንያቶቹ እየሄደ በጉዳዩ ላይ ፕሮጀክት ቀርጾ እነዚህ ችግሮች እንዳይፈጠሩ በራሱም ሆነ በአባል ድርጅቶቹ በኩል ይሰራባቸዋል። ራሱን የሚያውቅ፣ ድንጋይ የማያነሳና ለመብቱ የሚከራከር ወጣት እንዲፈጠርም ይሰራል።
ከወጣቶች ጋር በተገናኘ ድርጅቱ ለሚያከናውናቸው ስራዎች ሁሉ ዋነኛ ባለድርሻ አካል መንግስት ነው። በተለይ ደግሞ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመሆን የተለያዩ ስራዎች በጋራ ይሰራሉ። በዚህም የወጣቶች ካውንስል እየተቋቋመም ነበር። ካውንስሉ ሲቋቋም ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በመቀራረብ ወጣቶችን የሚመለከቱ ጉዳዮችን በማነሳት በጋራ ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል። በጤና ዘርፍም ከጤና ሚንስቴር ጋር ተመሳሳይ ስራዎች ተሰርተዋል።
ከዚህ ባለፈ ሁሉም ወጣት ባለበት ቦታ ላይና በተሰማራበት የሙያ መስክ ትክክለኛውን ነገር ማድረግ ይጠበቅበታል። አስፈላጊ ካልሆኑ ጉዳዮች ራሱን በማራቅ በሚጠቅሙት ላይ ብቻ ማተኮር ይገባዋል። የችግሮች ምንጭ ላይ አተኩሮ መስራት ከተቻለም ዘለቄታ ያለው መፍትሄ ማምጣት ይቻላል።
አልያ ግን አብዛኛውን ጊዜ የችግሮች ውጤት ላይ ቢሰራም ነገም መልሶ ችግሩ ሊከሰት ስለሚችል የችግሩ ምንጭ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ይሻላል። ይህም ኋላ ለሚመጣው ትውልድ መንገድ ለመጥረግ ያስችላል። በአገር ላይም ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት ያስችላል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2014