ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ እንደሚያስረዳው፤ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የቧንቧ ውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑት በ1893 ዓ.ም ነበር። ይህም የአፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥት የውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ በሆነ ሰባት ዓመታት ቆይቶ ነው። የቧንቧ ውሃ አገልገሎት መጀመርን ተከትሎ አገልግሎቱን ማን ይስጠው የሚለውን መልስ መሻትም ግድ ነበር። በመጀመሪያ የሥራ ሚኒስቴር በመባል ይታወቅ የነበረው መስሪያ ቤት ይህን ኃላፊነት ሲወጣ ቆየ። ከጣሊያን ወረራ በኋላ በ1934 ዓ.ም የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት እንደገና ሲዋቀር ደግሞ «የውሃ ማደራጃ ዋና መስሪያ ቤት» በሚል ስያሜ እንደ አንድ የሥራ ክፍል የውሃ አገልግሎት የሚሰጥ ክፍል ተቋቋመ።
የገፈርሣ ግድብና ማጣሪያ ጣቢያ፣ የለገዳዲ ግድብና ማጣሪያ ጣቢያ እንዲሁም የድሬ ግድብ ከፍተኛ ውሃ የማምረት አቅም ያላቸው የውሃ ምንጮች ናቸው። በተጨማሪም ጉድጓዶችና ሌሎች የከርሠ ምድር ምንጮች ከፍተኛ የሆነ ውሃ የማምረት አቅም ያላቸው ሲሆን የአዲስ አበባን ውሃ ጥም በመቁረጥ ባለውለታዎች ናቸው።
እነዚህ የታሪክ ሂደቶች ታልፈው፤ በሂደት የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በአዋጅ ቁጥር 68/1963 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ፤ በድጋሚ በአዋጅ ቁጥር 10/87 በአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን መቋቋሚያ አዋጅ መሰረት ተቋቋመ። ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአዋጅ ቁጥር 10/87 በተሰጠው ስልጣን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የውሃና ፍሳሽ አገልግሎቶችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የውሃ መገኛዎችን በመጠቀም እና የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓትን በመዘርጋት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ከአዲስ አበባ ከተማ ፈጣን ዕድገት ጋር የሚመጣጠን የንፁህ ውሃ አቅርቦት እና የዘመናዊ ፍሳሽ ማስወገጃ አገልግሎት ለከተማዋ ነዋሪ በበቂና በአስተማማኝ ሁኔታ ተደራሽ ለማድረግ በርከት ያሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን በማዋቀር ለህብረተሰቡ አስፈላጊውን አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።
በዛሬው ዕትማችንም የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የውሃ ደንበኞች ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሞገስ አርጋው የተቋሙን አሠራር አስመልክቶ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ያደረጉትን ቆይታ ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፡- ባለስልጣኑ በአሁኑ ወቅት ምን ያህል ደንበኞች አሉት?
አቶ ሞገስ፡- ደንበኞቻችንን የውሃ እና ፍሳሽ ብሎ በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል። በአሁኑ ወቅት ከውሃ አኳያ ወይንም ውሃ ቆጣሪ በቤታቸው የተገጠመላቸው 600ሺ ደንበኞች አሉ። ከፍሳሽ አኳያ ወይንም በዘመናዊ መንገድ መስመር ተዘርግቶ ፍሳሽ የሚያስወግዱ ደንበኞች ደግሞ 198ሺ በላይ የሚሆኑ ናቸው። ይህ ቁጥር በየጊዜው አዳዲስ ደንበኞች እየመጡ ሲሄድ ቁጥሩ እየጨመረ የሚሄድ ነው። አሁን ባለስልጣኑ የሚያውቀው ቁጥር ግን ከላይ የገለፅኩት ነው።
አዲስ ዘመን፡- የባለስልጣኑን አገልግሎት ለማግኘት የሚሹ ደንበኞች ፍላጎትና ዕድገት ምን ይመስላል?
አቶ ሞገስ፡– የደንበኞችን ፍላጎት በሁለቱም መንገድ ነጣጥሎ ማየት ይገባል። ከውሃ ቆጣሪ ፍላጎት አኳያ ራሱን የቻለ ታሪክ አለው። የዘመናዊ ፍሳሽ መስመር መጠቀምም ራሱ የተለየ ባህሪ አለው። ንፁህ ውሃ ለማግኘት ከሚጠይቁት ከመሃል ከተማ ነዋሪዎች አኳያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ነው። ይህም በየጊዜው ጠይቀው ምላሽ ያገኙ ናቸው። በሌላ ጎኑ በጋራ መኖሪያ ቤቶችና ማስፋፊያ አካባቢዎች ከፍተኛ ፍላጎት አለ። በመሆኑም በመሃል ከተማ እና በማስፋፊያ አካባቢ ያለው በድምር ሲታይ ግን የደንበኞች ፍላጎት እየጨመረ ነው።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ በየዓመቱ ከ10ሺ እስከ 15ሺ የውሃ ቆጣሪዎች ይቀጠላሉ። የሪል ስቴቶችም የዚሁ ተጠቃሚ ናቸው። ባለስልጣኑ 1962 ዓ.ም ሲቋቋም ፍሳሽ ቆጣሪ ቅጥያ ዕድገት በጣም አዝጋሚ ነው። ፍሳሽ አገልግሎት በስፋት ሲሰጥ የነበረውና አሁንም ድረስ ፍሳሽ ማንሻ በተሽከርካሪዎች ነው። በዚህም ደንበኞቻችን ሁለት ዓይነት ባህሪ አላቸው። አንደኛው በተሽከርካሪ አገልግሎት የሚያገኙ ሲሆን ሁለተኛው ግን ከቤታቸው ቀጥታ የፍሳሽ መስመር የሚዘረጋላቸውና ከመስመሩ ጋር የሚገናኙ ናቸው። በአፍሪካ ቀዳሚ ከሆኑት የፍሳሽ ማጠራቀሚያዎች አንዱ የሆነው የቃሊቲ ፍሳሽ ማጠራቀሚያም ለዚህ ሥራ መሳካት ትልቅ ጥቅም አለው። ሁለቱንም ስንመለከት ፍሳሽ በመስመር መጠቀሙ ፍላጎት እያደገ ነው። ለዚህም የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ በመሥራታችን እየተሻሻለ ነው። ሌላው ትልልቅ ህንፃዎች እና መሃል ከተማ ያለው በተሽከርካሪ ብቻ ተደራሽ መሆን አስቸጋሪ ስለሚሆን ወደዚህ እየገቡ ነው። በዚህም ባለፉት ሦስት ዓመት ከ60ሺ ወደ 198ሺ አድጓል። እየቀነሰ የመጣው በተሽከርካሪ ፍሳሽ ይነሳልን የሚለው ጥያቄ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት ከመኖሪያ ቤት ውጭ የመክፈል አቅማቸው የተሻሉ የምንላቸውን ደንበኞች ለሦስተኛ አካላት አሳልፈን (out sorce) አድርገናል። ሌላው የቀነሰበት ምክንያት ዘመናዊ ፍሳሽ ማስወገጃ በበራቸው ላይ የሚያልፍ ነዋሪዎች በአስገዳጅ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ ከዋና መስመር ጋር እያገናኙ ነው። በዚህም በሂደት የዘመናዊ መስመር እየተጠቀሙ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በፍሳሽ አወጋገድ ከደንበኞችና ከተማዋ ነዋሪዎች ፍላጎት አኳያ የባለስልጣኑ ምላሽ አሰጣጥና አፈፃፀም እንዴት ይለካል?
አቶ ሞገስ፡- የፍሳሽ ሥራችን ለዘመናት የተረሳ ጉዳይ ነበር። የመጀመሪያው ነገር ተቋሙ ከተመሠረተ ጀምሮ ሲሰራበት የነበረው ውሃ ምርትና ስርጭት ላይ ያተኮረ ነበር። በወቅቱ ለዚህም በቂ ምክንያት ነበር። የከተማው በጀት ለመንገድ፣ መብራት፣ ለውሃ ስርጭት የተወሰነ ስለነበር በወቅቱ ፍሳሽ ማንሳት ሥራውና ዘመናዊ ፍሳሽ አወጋገድ ላይ ብዙ ትኩረት አልተሰጠም ነበር። ሽፋኑም እስከ 2010 ዓ.ም 15 እስከ 19 ከመቶ ብቻ ነበር። በእርግጥ በቀላሉ በመንግስት በጀት ብቻም የሚመለስ አይደለም። ይህ የሚያሳየው ለበርካታ ዓመታት የተዘነጋ ነበር።
የፍሳሽ መሰረት ልማት ከውሃ መሰረተ ልማት ያልተናነሰ እንዲያውም በበለጠ መልኩ በጀት የሚፈልግና በቴክኒኩም ብዙ ነገር የሚጠይቅ ነው። ይሁንና ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ የከተማው ዕድገት ከትንንሽ ቤቶች ተነስቶ በጣም ግዙፍ ህንፃዎች እየተበራከቱ ነው። እነዚህንም በተሽከርካሪ የፍሳሽ አወጋገድ ማስተናገድ አይቻልም። ለአብነት ሲግናል አካባቢ ለሚገኙ መኖሪያዎች በቋሚነት መኪና ተመድቦ ነበር ፍሳሽ የሚያስወግደው። ከተማዋ ንፁህ ለምን አልሆነም የሚል ጥያቄ በብዛት ይነሳል። ግን ዘመናዊ ቆሻሻ አወጋገድ ከሌለ ለጥያቄው መልስ ማግኘት አይቻልም። ለዚህ ምላሽ ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀትና ዘመናዊ ፍሳሽ መስመር በመገንባት የሚመለስ ነው። ይህን ታሳቢ በማድረግም ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በተሠራው ሥራ ሽፋኑ ወደ 30 ከመቶ የደረሰ ሲሆን በተያዘው በጀት ዓመት ደግሞ 32 ከመቶ የማድረስ ዕቅድ ተይዟል።
ይህ ሲሠራ ብዙ ፈተና ነበር። ህብረተሰቡ ዘመናዊ ፍሳሽ አወጋገድን ለመጠቀም ያለው ፍላጎት ዝቅተኛ ነው። ሕብረተሰቡ ይህን ለመጠቀም አሁንም ፈተና ነው። ግን ወደ አሰራር ለመግባት ባለስልጣኑ በርካታ አመቺ መንገዶችን እየተከተለ ነው። ሁለተኛው ፈተና የከተማው ልማት ፊትና ኋላ በመሆኑ መናበብ አልተቻለም። አንዳንዶቹ ቀድመው ሲሄዱ ሌሎች እንደ አዲስ አሁን እየጀመሩ ነው። ከተማዋ ከልማት አንፃር በፕላን ላይ ተንተርሳ ከጅምሩ ባለመሠራቱ ፈተናዎች በርክተዋል። በዚህም የተነሳ ወሰን ማስከበር ስራው እስካሁንም ከፍተኛ ፈተና ሆኗል።
አዲስ ዘመን፡- የወሰን ማስከበር ስራውና አንዱ ሌላው የሚወቅስበት ጊዜ መቼ ያበቃል?
አቶ ሞገስ፡- መጀመሪያ መታወቅ ያለበት የተቋማትን ስልጣንና ተግባር ነው። መገናኛ ብዙሃንም ሆኑ ህብረተሰቡ ሊረዱት የሚገባው እያንዳንዱ ተቋም ተልዕኮ ምን እንደሆነ ነው። ይህን በሚገባ ባለመለየት አንዱ ባጠፋው ሌላው ይወቀሳል። ለአብነት መብራት፣ ውሃና ቴሌ ሥራቸው መሬት ላይ ነው የሚከናወነው። ከእነዚህ ጋር በጋራ መስራት የሚያስችለን መንገድ አለ።
በተለይም አዳዲስ ሰፈሮችና ማስፋፊያ አካባቢዎች በመነጋርና በመመካከር መስራት ይቻላል። ነገር ግን ሌሎች መሰረተ ልማቶች ቀድመው በሰሩበት ቦታ እኛ እንደ አዲስ ስንገባ ያልተናበበ ሥራ ሊኖር ይችላል። አሁንም አንዱ ተቋም ከሌላው ቀድሞ ቢገባ በቢ.ፒ.አር የተቀመጠ አሰራር ስላለ መናበብ ይቻላል።
ሌላው መናበቡን አስቸጋሪ የሚያደርገው የአገሪቱ አቅም ሲሆን፤ ፕላንና ህጋዊ የሰነድ ማረጋገጫ ከሌላቸው ስራው አስቸጋሪ ይሆናል። የአገሪቱ አቅም ውስን መሆን ፈተና ነው። በአፄ ኃይለሥላሴ ጊዜ የተዘረጉ መስመሮች አሁንም አገልግሎት እየሰጡ ነው። ይህን መቀየር ይገባል። ለዚህ ታዲያ በመንግስት በጀት ብቻ የሚከናወን ሳይሆን ሌሎች አጋዥ አካላትም ድጋፍ ይፈልጋል። ሌላው ባለስልጣኑ ውሃ ለማስገባት ጉድጓድ ተቆፍሮ የሚቀመጥ ከሆነ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሆነን እየፈታን ነው።
ብዙ ችግሮችን በመነጋገር እየፈታን ነው። ነገር ግን አልፎ አልፎ የተወሰኑ ችግሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይገመታል። ይሁንና ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው እውነተኛ ጥያቄዎች የሉም ወይ ከሆነ መልሱ አለ ነው። እነዚህን በሂደት የምንፈታው ነው። የሆነው ሆኖ በማንኛውም አካል ችግር ቢኖርም ወይም ቢፈጥርም እንደ ከተማ አስተዳደር ስለሆነ ለመፍትሄውም በጋራ እየሰራን ነው። ይህን የሚያቀናጅ አካል አለ። ከዚህ በዘለለ ከነዋሪዎች ጋር ፎረም ስላለን ችግራችንን በቀላሉ ለመፍታት እያስቻለን ነው። ጠቅለል ሲደረግ ግን ከዓመታት በፊት የነበሩ እሰጣ ገባዎች በአሁኑ ወቅት በብዙ እጥፍ እየቀነሱ ነው። ውሃና ፍሳሽ፣ ቤቶች እና መብራት አንዱ ከሌላኛው በጣም የተሳሰሩ ስለሆኑ ተናበን ለመሥራት እንገደዳለን።
አዲስ ዘመን፡- የደንበኞችን ፍላጎት ለማወቅ የዳሰሳ ጥናት ታካሂዳላችሁ፤ ደንበኞቻችሁ እናንተን እንዴት ይገልጿችኋል?
አቶ ሞገስ፡- ደንበኞችን ነባራዊ ፍላጎት ስንመለከት፤ አንደኛው እንደነዋሪ 24 ሰዓት ውሃ የማግኘት ፍላጎት አለ። ሌላኛው በአሁኑ ወቅት ውሃ በከተማዋ ውስጥ በብዛት በሬሽን መሆኑ ይታወቃል። በሣምንት ሦስት ቀን የሚያገኙ ከሆነ በሣምንት አራት ቀን የማግኘት ፍላጎት አለ። ሳምንቱን ሙሉ ውሃ የሚያገኙ ካሉም ምንም ሳይነካ ከሳምንት ሳምንት ማግኘት የሚፈልጉ አሉ። እነዚህን ፍላጎቶች በደንብ እናውቃለን፤ ጥናትም ሳይደረግ ይታወቃል። ነገር ግን ህብረተሰቡ የሚፈልገው ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ማግኘት ይፈልጋል። እኛም ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንዲያገኝ እንፈልጋለን። አሁን የሚመረተው እና የሚሰራጨው ውሃ መጠን ይታወቃል። በአቅርቦትና ፍላጎት መካከል አለመመጣጠን አለ።
በመብራት መቆራረጥ ከሚመረተው ውሃ እስከ 25 ከመቶ ይባክናል። የውሃ ጉዳይ ቀላል አይደለም። ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች አሉት። የሆነው ሆኖ ግን የተመረተው ውሃ ህብረተሰቡ ዘንድ ፍትሃዊ ሆኖ መድረሱ ነው። እኛ እዚህ የሚገጥመን ፈተና ውሃ ከተመረተ በኋላ የራሱ ሂደቶች አሉ። አንዳንዱ በግራቪቲ ሲሄድ፤ ሌላው በፓምፕ ይሄዳል። በዚህ ወቅት መብራት ከተቆራረጠ የተለመደው ፈረቃ ይዛባል። ይህ አንዱ የመልካም አስተዳደር እጦት ምንጭ ነው፤ ደግሞ ትክክል ነው።
አዲስ ዘመን፡- በባለስልጣኑ እይታ በሬሽን የሚሰራጨው ውሃ አሰራሩ ፍትሐዊ ነው?
አቶ ሞገስ፡- ፍትሐዊነቱ መቶ በመቶ የተረጋገጠ ነው አንልም። ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች አሉ። መብራት ይጠፋል፤ አንዳንዴ ደግሞ መስመር ይሰበራል። አልፎ አልፎ ሥራችን በሦስተኛ ወገን ስለሚሠራም ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ይህን ህብረተሰቡ ይገነዘባል። እኛ በውሃ መስመር ዝርጋታና ቁፋሮ፣ በፍሳሽ መስመር ዝርጋታ እስከ 10ሺ ለሚሆኑ ወጣቶች ሥራ ፈጥረናል። አሰራራችን በሰው ሃይል የሚሰራ ስለሆነ ክፍተቶች አሉ። በዋናነት ግን የተመረተው ውሃ ወደየትም አይሄድም።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ አካባቢዎች ውሃ ያለመቆራረጥ ሲያገኙ የሌሎች ደግሞ ጥያቄ በሚያስነሳ መንገድ የሚቆራረጠው ለምንድን ነው?
አቶ ሞገስ፡- በሁለት መንገድ ማየት ጥሩ ነው። 24 ሰዓት ውሃ የሚያገኙ ስድስት ወረዳዎች አሉ። ከዚህ ውጭ በፈረቃ ነው። ሌላው በአንድ አካባቢ ከመንገድ ቀኝ እና ግራ ሆነው አንዱ ውሃ ሲያገኝ ሌላው አያገኝም። ይህ የሆነው ከተማችን የውሃ መገኛ በተለያየ ቦታ እና መንገድ ነው። የሚመራውም በሰው ነው። አንዳንዴ ህብረተሰቡ ውሃ እንዲያገኝ ብለን ብዙ አሰራር እንከተላለን። ቴክኒካል ነገሮችን አስተካክለን ነው ውሃ የምናሰራጨው። ሌላው ቀርቶ በአንድ መስመር ላይ ሆነው አንዱ ደንበኛ ውሃ ሲያገኝ ሌላው ደንበኛ ውሃ ላያገኝ ይችላል። ይህ የሚሆነው ‹‹ጌትቫልቭ›› ሲዘጋ እንኳን ካለማየት ሊመነጭ ይችላል። ሌላው የቆየ የብረት መስመር እየዛገ ሲመጣ ውሃ መስመሩን ይዘጋል። ይህን ችግር ለማቃለል ደንበኞቻችን ውሃ መስመሩን እንዲቀይሩ እንመክራለን። ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ ሰራተኞቻችን ችግር ሊኖርባቸው እንደሚችል ይታመናል። ከተማችን ውስጥ የውሃውን ስርጭት ፍትሃዊ ለማድረግ የተገጠሙ 112 በላይ ቫልቮች አሉ። አልፎ አልፎ ስርቆት ያጋጥመናል ይህም የውሃ ስርጭቱ ላይ እክል ይፈጥራል። ይህን ለማረም ህብረተሰቡ መተባበር አለበት። ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶችን በብዛት በመክፈት ለደንበኞች ጥያቄ ለመመለስ እየሰራን ነው።
አዲስ ዘመን፡- እውነት ደንበኞችን ከመጉላላት ለመታደግ አዳዲስ አሰራር ተዘርግቷል?
አቶ ሞገስ፡- አዎ! ለምሳሌ ቅርንጫፎቻችሁ ተደራሽ አይደሉም የሚል ጥያቄ ነበር። በዚህም አራት ቅርንጫፍ ተጨምሮ አዲስ አበባን በ12 ቅርንጫፍ ለመምራት ጥናት ተጠናቋል። እስከ 2010 የነበረው ከ42 የመሰብሰቢያ ማዕከላት በአሁኑ ወቅት ወደ 350 አድጓል። አገልግሎት አሰጣጡም ኋላቀር ነው የሚል ወቀሳ ነበር። ለክፍያ ይሰለፉ የነበሩትን ጫና ለማቃለል በአንድ ዓመት አምስት የክፍያ አማራጮችን ጀምረናል። ዊንዶ ሰርቪስ፣ ኢንተርናል ባንኪንግ፣ ሲቢኢ ብር፣ ኢድማርክ አካውንት እና ሞባይል ባንኪንግን ወደ ሥራ አስገብተናል። ይህ ትልቅ ለውጥ ነው።
ሌላኛው የንባብ ጥራት ችግር አለ በሚል ሕብረተሰቡ ቅሬታ ነበረው። ይህን ሙሉ ለሙሉ ለማቃለል በቢቢነስ ፕላን ተካቶ አንድ አንባቢ ሲመጣ በአምስት ሜትር ርቀት ቆጣሪውን ማንበብ ይችላል። ይህ ተሰርቶ ግን ሙሉ ለሙሉ ከስህተት የፀዳ ነው የሚል መከራከሪያ የለም። ሆኖም በቀጣይ ችግሮችን በስፋት ለማቃለል ስትራቴጂካሊ ለማቃለል እንሠራለን።
የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድም ላይ ቀደም ሲል ከ30 ሜትር ርቀት በላይ ከሆነ ማስተናገድ አስቸጋሪ ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን ይህን ችግር ለማቃለል እስከ 150 ሜትር ርቀት አገልግሎት የሚሰጡ 90 ተሽከርካሪዎች እስከ ሐምሌ ድረስ ወደ አገር ውስጥ ይገባሉ። በአጠቃላይ ባለስልጣኑ በአጭርና ረጅም ጊዜ ውስጥ የሕብረተሰቡን ጥያቄዎች ለመመለስ እየሠራ ሲሆን ከተማ አስተዳደሩም አስፈላጊውን ትኩረት ሰጥቷል። በርካታ ሥራዎቻችንም ‹‹አውት ሶርስ›› አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡- በከተማዋ የመጠጥ ውሃ ለጓሮ አትክልትና ለመኪና እጥበት እየዋለ ነው። መጠጥ ውሃ በፈረቃ በሆነበት ከተማ ይህ አግባብ ነው?
አቶ ሞገስ፡- በከተማው የውሃ አቅርቦትና ፍላጎት የተጣጣመ አይደለም። ይህን የሚያባብሱ ሁኔታዎች አሉ። አንደኛው ህገ ወጥ የውሃ አጠቃቀም ነው። ሌላው ትልልቅ ሮቶ መሬት ውስጥ በመቅበር ውሀ መጥለፍ ‹‹ሃይጃክ›› ያደርጋሉ። ይህ በፈረቃ ውሃ ማግኘት ያለባቸው ነዋሪዎች ውሃ ሳያገኙ ይቀራሉ። መጠጥ ውሃን ከመጠጥ ውጭ ለሌላ አገልግሎት መጠቀም ይስተዋላል።
ትልቁ ችግር መንግስታዊ ሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ንፁህ የመጠጥ ውሃን ለግንባታ አገልግሎት ይጠቀማሉ። አቅም ያላቸው ትልልቅ ሆቴሎች ግቢያቸውን ለማስዋብና ለዕፀዋት ንፁህ ውሃ ይጠቀማሉ። እኛ ከ2010 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ የመጠጥ ውሃ ለሌላ አገልግሎት እንዳይውል ህግ አውጥተናል። ግን ህንፃ የሚገነባ ሰው ምን ያድርግ ለሚለው ምላሽ ከፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ አጣርተን የምናስወጣው በንጽህናው ከመጠጥ ውሃ ያልተናነሰ ውሃ ወደ ወንዞች እየተለቀቀ ነው። በመሆኑም ለመኪና እጥበትና ግንባታ አገልግሎት የሚውልበት ሁኔታ አመቻችተናል። ነገር ግን ከ2010 ዓ.ም በፊት ውሃ ቆጣሪ የገባላቸውና የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው መኪና አጣቢዎች ንፁህ ውሃውን እየተጠቀሙ ነው። ከዚያን በኋላ ግን ይህ አሰራር ቆሟል፤ አዳዲስ ጥያቄዎችም ዝግ ናቸው። እኛ አገር ውሃ በጣም ርካሽ ስለሆነ እንጂ እንደ ሌላው አገልግሎት ውድ ቢሆን የሥራ ዕድል ፈጠራ የሚለው አይታሰብም።
አዲስ ዘመን፡- ሆቴሎችን ጨምሮ በርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የከርሰ ምድር ውሃ አውጥተው እንዲጠቀሙ አቅጣጫ ተቀምጦ ነበር። ይህን በማይተገብሩት ላይ ዕርምጃ እየተወሰደ ነው?
አቶ ሞገስ፡- ወደዚህ ያስገባን ችግሩ እንጂ እንደ አሰራር ማስገደድ አይቻልም። ከተማውን፣ መንግስትና ተቋሙን ከማገዝ አኳያ እንጂ በአሰራር ጉድጓድ እንዲቆፍር አንድ ሆቴል አይገደድም። ውሃ ከየትም አምጥቶ ማቅረብ ያለበት ባለስልጣኑ ነው። አንደኛው የባለስልጣኑ የገቢ ምንጭ ከውሃ ሽያጭ ስለሆነ ነው። ወጪና ገቢ አመጣጥኖ መምራት እንጂ ይህ ሥራዎችን በሙሉ ለሌላ አሳልፎ መስጠት አሠራር ሆኖ መቀጠል የለበትም። ውሃ እና ፍሳሽ ከአጠቃላይ ገቢው 80 ከመቶ የሚገኘው ከውሃ ሽያጭ ነው። ሌላው ይህን በፍርድ ቤት መክሰስ አንችልም። ሦስተኛው ጉዳይ ከጤና አኳያም ይህ አሰራር ብዙ ስለማይመከር ይህ አስገዳጅ መሆን አለበት የሚል አቋም የለም። ይህ አሰራር የከተማውን አሁናዊ ችግር ለማቃለል የሚያግዝ ነው። ይህ በሂደት የሚቆም ነው።
አዲስ ዘመን፡- የባለስልጣኑ አገልግሎት አሰጣጥ፣ የደንበኛና መንግስት ፍላጎት እንዲጣጣም ምን አይነት አሰራሮች ተቀይሰዋል?
አቶ ሞገስ፡- የመጀመሪያው አገልግሎት አሰጣጥና የተቋሙን ተልዕኮ ለማሳካት የተቋሙን የማስፈፀም አቅም ማሳደግ ነው። ቴክኖሎጂ የዚህ አካል ነው። መሰረታዊው ነገር መዋቅራዊ አደረጃጀት ማስተካከል ይፈልጋል። 600ሺ በላይ ደንበኞችን ይዞ ውሃ አምርቶ፣ መስመር ዘርግቶ አሰራጭቶ እና ገቢ ሰብስቦ ደንበኛን አስደስታለሁ ማለት ከባድ ነው። በመሆኑም አሰራሮችን ማዘመን ይገባል በሚል አሰራር መዋቅራዊ ማስተካከያዎች ተደርገዋል።
ችግሮችን ለማስተካከል የውጭ አገራትን ተሞክሮ በመቅሰም ወደ ተግባር ተገብቷል። ቴክኖሎጂዎችን መተግበር ተጀምሯል። አይቻሉም የሚባሉ አጀንዳዎች ተዘግተው እንደሚቻል አሳይተናል። አሰራሮችን በየጊዜው እያዘመንን ነው። አዋጅ፣ ደንብና መመሪያዎችም ተሻሽለዋል። ለምሳሌ አርሶ አደሮች እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ውሃ አያገኙም ነበር። ይህን እና መሰል አሰራሮችን የህዝብን ፍላጎትና የመንግስትን አሰራር በማክበር እየሰራን ነው። ቴክኖሎጂ ተኮር አሰራሮች በብዛት እየተተገበሩ ነው። የፋይናንስ አሰራራችን አውቶሜትድ ሆኗል። አሰራራችን በሲስተም የተደገፈ ነው። የካዳስተር ሲስተማችን ከአንድ ዓመት በኋላ ይጠናቀቃል። በርካታ አሰራሮቻችን በቴክኖሎጂ የታገዙ እንዲሆኑ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ነን። ጥያቄዎችን ለመመለስ ተቋሙ ግልጽ ቢዝነስ ፕላን አለው።
አዲስ ዘመን፡- የተቋሙ አንኳር ችግሮች ምንድን ናቸው?
አቶ ሞገስ፡- የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ግብዓቶች የሚገቡት ከውጭ አገር ነው። በዚህም ውጭ ምንዛሪ እጥረት አለ። ከዚህ በተጨማሪ ቁጥራቸው ከ100ሺ በላይ ደንበኞች ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት ለመክፍል ዝግጁ ያልሆኑ ናቸው። ሌላው ሥራ ትተን ቆጣሪ ለመቁረጥ እንሄዳለን። በዓመት እስከ 54ሺ ቆጣሪ ቆርጠናል። ይህ ትልቅ ፈተና ነው። ውሃ በጣም ርካሽ ታሪፍ ነው። አንድ ሜትር ኪዩብ ውሃ ለማምረት 30 ብር እናወጣለን፤ ለህዝብ የምናቀርበው ግን በ2 ብር ከ40 ሳንቲም ነው። ተቋሙ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች አሉ። ጥቂት ደንበኞች ምናልባትም ከ20 እስከ 25 በመቶ ደንበኞች በሚፈጥሩት ችግር ተቋሙ በፋይናንስ እጥረት እንዲፈተንም ምክንያት ሆኗል። በመሆኑም በዚህ ላይ የመገናኛ ብዙሃን የጠራ መረጃ ይዘው እንዲያግዙን እንፈልጋለን።
አዲስ ዘመን፡- የዝግጅት ክፍላችን እንግዳ ሆነው ለባለስልጣኑ ያቀረብናቸውን ጥያቄዎች ምላሽ ስለሰጡ እናመሰግናለን።
አቶ ሞገስ፡- እኔም የተቋማችንን አሰራር በተመለከተ ለህዝቡ መረጃ ስለምትሰጡ እናመስግናለን።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2014