ኢትዮጵያ በምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ አገራት መካከል በተካሄደው የወጣቶች አትሌቲክስ ቻምፒዮና በርካታ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ በቀዳሚነት አጠናቃለች። ዘንድሮ ለ4ኛ ጊዜ በታንዛኒያ ዳሬሰላም በተካሄደው ቻምፒዮና የቀጣናው አገራት ዕድሜያቸው ከ20 እና ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ተተኪ አትሌቶችን አሳትፈዋል። 27 አትሌቶችን በቻምፒዮናው ያሳተፈችው ኢትዮጵያ በሩጫ ውድድሮች ከ100 ሜትር ጀምሮ እስከ 5ሺ ሜትር እንዲሁም በሜዳ ተግባራት በጥቅሉ በ20 የውድድር ዓይነቶች በሁለቱም ጾታ ተካፍላ ሃያ ሁለት ሜዳሊያዎችን ማሸነፍ ችላለች።
ለሁለት ቀናት በተካሄደው ውድድር በሁለቱም የዕድሜ ደረጃዎች ኢትዮጵያ 17 የወርቅ፣ 3የብር እና 2የነሃስ በድምሩ 22 ሜዳሊያዎችን አፍሳለች። በተጨማሪም ኢትዮጵያ በቻምፒዮናው ሁለት ዲፕሎማዎችን በማስመዝገብ በውድድሩ ላይ ከፍተኛ ብልጫ በማሳየት በደረጃ ሰንጠረዡ በቀዳሚነት መቀመጥ ችላለች። ስኬታማው የኢትዮጵያ ልኡካን ቡድን እሁድ ማለዳ ውድድሩን አጠናቆ ወደ ሃገሩ ሲመለስም በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ አቀባበል ተደርጎለታል። በአቀባበሉም ላይ በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት ገዛኸኝ አበራ፣ የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትና የፌዴሬሽኑ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
አትሌቶቹ ባስመዘገቡት ውጤት መሠረትም የማበረታቻ ገንዘብ ሽልማት በዕለቱ የክብር እንግዳ አምባሳደር መስፍን ቸርነትና በአትሌት ገዛኸኝ አበራ እንደተበረከተ ፌዴሬሽኑ ያደረሰን መረጃ ያመላክታል። የቡድኑን አጠቃላይ ቆይታ በማስመልከትም በምስራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት እና በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ ገለጻ ተደርጓል። በዚህም ቡድኑ በቆይታው የምግብ፣ የትራንስፖርትና የማረፊያ ችግር ገጥሞት የነበረ ቢሆንም በኢትዮጵያዊ ወኔ ለድል የበቃ በመሆኑ አድናቆት እንደሚገባው ተናግራለች።
የተገኘው ውጤት ታሪካዊ መሆኑን እና ቻምፒዮናውም ለቀጣዩ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ተስፋ ሰጪ መሆኑን የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ገዛኸኝ አበራ ገልጿል። ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር መስፍን ቸርነት በበኩላቸው ለቡድኑ አባላት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት በማስተላለፍ ‹‹የኢትዮጵያ የነገ ተተኪዎች የሆናችሁትን እናንተን ስለምትጠብቅ ጠንክራችሁ ስሩ›› በማለት ያሳሰቡ ሲሆን፤ ድሉ ከመቼውም በላይ አነቃቂና ታሪካዊ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2014