ወይዘሮዋ ከባለቤታቸውና ከልጆቻቸው ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው በቀይ ባህር ዳርቻ ሽር ብትን ብለዋል። ከምጽዋ ወደብ ላይ መልህቃቸውን ጥለው የቆሙ መርከቦች እና ጀልባዎች እየተመለከቱ ተንሸራሽረዋል። ጀልባዎቹን ማዕበል ወዲህ ወዲህ ሲላጋቸው አይተዋል። ከባህሩ ዳር ያለው ትርምስ በአዕምሯቸው ውል እያለ ትውስታው ከፊታቸው እንደ ደራሽ ጎርፍ ድርስ ምልስ እያለ ያስቸግራቸዋል። ዛሬም ደረስ በዓይነ ህሊናቸው እየተመላለሰባቸው ቀይ ባህርን ይናፍቃሉ።
ከባለቤታቸው ጋር ሆነው የአስመራ ‹‹ሜሎቲ›› ቢራ በ40 ሣንቲም የተጎነጩበት፤ በትልቁ ጠርሙስ አምቦ ውሃ አንድ ብር፤ ለስላሳ በ50 ሳንቲም ጭልጥ አድርገው የጠጡበት ጊዜ ከአይነ ህሊናቸው አልተፋቀም። ይህን ሲያስታውሱ ወትሮውንም ከቀይ ባህር ጋር ያላቸውን ትዝታ ይብስ ያንርባቸዋል።
ደራሲው ‹‹ያመጣል መንገድ፤ ይወስዳል መንገድ እንዳለው›› ብዙ ርቀው ከተጓዙበት ተመልሰው መጥተዋል። ብዙ ወደፊት ተራምደው በእውንም ሆነ በህልም ዓለም ወደኋላ አፈግፍገዋል። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓቶች ሲለዋወጡ በተስፋና በትዝብት ተመልክተዋል። ስኬት ሲመኙ ሲርቃቸው፤ ኑሮን ሲገፉት ኑሮም ሲገፋቸው፤ ወዳጅ የነበረው ጠላት፤ ጠላት የነበረውም ወዳጅ ሆኖ ሲቧቀሱ፤ ሲሞጋገሱ በብሌናቸው አይተው «ወይ መኖር ደጉ!» ብለው እጃቸውን ከአፋቸው ላይ ጭነዋል። በመቆጣት፣ በመደሰት፣ በመፀፀት እና በብዙ ዝብርቅርቅ ስሜቶች ውስጥ ሆነው ሕይወትን መርተዋል። አሁንም ያው እንዲሁ በትዝታ ወላፈን፤ በትናንትና ዛሬ መሃከል ሆነው ነገን አሻግረው ለማየት ይጓጓሉ።
የባህር ኃይሉ የትዳር አጋራቸው አለባበስ እና ተክለ ቁመና ዛሬም ከፊታቸው ድቅን ይልባቸዋል። የወታደራዊ ሠላምታ ልውውጡ አይረሳቸውም። አገር ተጋድሎ እና ጣፈጩ የትዳር ሕይወት ለዓመታት ጉስቁልና ካዳረጋቸው የኑሮ ውጣ ውረድ ጋር አያሰቡ ይተክዛሉ። እንዲሁ ደግሞ እጅ አልሰጥ ባይነታቸው ከወደቁበት አንስቶ ወደ ላይ ከፍ ያደረጋቸውን ሁኔታ እያሰቡ የኋሊት በሃሳብ ይማስናሉ። ይብከነከናሉ፣ ይናፍቃሉ፣ ይስቃሉ፣ ይተክዛሉ። በመሆንና ባለመሆን መካከል እርሳቸው ያላዩት ነገር እንደሌለ ሲያስቡት «እርሱ ሰጠ እርሱ ነሳ» የሚለውን መንፈሳዊ ቃል እያሰቡ ፈጣሪያቸውን ያመሰግናሉ።
ወይዘሮ ትበርህ አጽበሃ ይባላሉ። ሽረ እንደስላሴ ነው የተወለዱት። ዕድሜያቸው በ60ዎቹ መጀመሪያው ላይ እንደሆነ ይገምታሉ እንጂ በትክክል የተወለዱበትን ቀን አያስታውሱም። በ13 ዓመታቸው ነበር ወደ ምጽዋ አጎታቸው ዘንድ ያቀኑት። ጃንሆይ መስከረም 02 ቀን 1967 ዓ.ም ከስልጣን ወርደው እርሳቸው መስከረም 26 ቀን 1967 ዓ.ም የመጀመሪያ ልጃቸውን እንደወለዱ ያስታውሳሉ።
አዲስ አበባ ሲገቡ መሰረተ ትምህርት ተምረዋል። በ1970 ዓ.ም ምጽዋ ላይ ጦርነት ሲካሄድ፤ ህዝብ እንደ ቆሎ ሲረግፍና ገሚሱ ደግሞ በሱዳን ሲሰደድ ያስታውሳሉ። «ከገጠር እስከ ከተማ የነበረው ጦርነቱ አሰቃቂ ነበር» ሲሉ ያኔ የነበረውን አስቸጋሪ ወቅት ያስታውሳሉ። በጦርነቱም የተነሳ ምጽዋን ለመልቀቅ መገደዳቸው እንደእግር እሳት ያንገበግባቸዋል። የባለቤታቸው የትውልድ አገር አዲስ አበባ ገዳም ሰፈር ነበር። የሁለትና ሦስት ዓመት ልጆቻቸውን ይዘው ከምጽዋ 22 ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ ወደ አዲስ አበባ መጡ።
ባለቤታቸው የባህር ኃይል አባል ሲሆኑ፤ ደመወዛቸው 90 ብር ነበር። ያኔ ኑሮው ጥሩ ስለነበር ወታደር ለአገሩ ከማሰብ ውጭ ብዙም ቅንጦት አያምረውም። ከምፅዋ ሁለት ልጆች ይዘው ተመልሰዋል፤ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላም ደግሞ ሁለት የአብራካቸውን ክፋዮች አግኝተዋል። ከባለቤቴ ጋር ‹‹ናይት ክበብ›› የተዝናናሁት ትዝ ሲለኝ እንባዬ ይቀድማል ይላሉ። ወደ አዲስ አበባ ከመጡ 40 ዓመት ደፈኑ።
አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ባለቤታቸው ለትምህርት ወደ ራሺያ አቀኑ። የባህርና ትራንዚት ትምህርት ተምረው መጡ። ከዚያም በባህርና ትራንዚት አገልግሎት ድርጅት ተቀጠሩ። ትንሽ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰርተው እንደገና ለትምህርት ወደ ኮርያ አቀኑ። እስከዚያች ሰዓት ድረስ ቤታቸው ሞልቶ፤ ሁሉ ነገር የፍሰሃ ነበር። ዳሩ ግን ከኮሪያ ከተመለሱ በኋላ ባለቤታቸው የእዕምሮ እክል ገጠማቸው። ትንሽ ቆይተው ትዳራቸው ተበተነ። ፍቺው ከተፈፀመ ከ27 ዓመታት በኋላ የፍቅር አጋራቸውን፤ የልጆች አባታቸውን እስከመጨረሻው ተሰናበቱ።
ወይዘሮ ትበርህ 1980ዓ.ም ወዲህ ልጆቻቸውን ለማሳደግ ያላቸውን ጥሪት በሙሉ አጥተዋል። የአንገት እና የጆሮ ወርቃቸውን፤ አደባባይ ሲወጡ መዋቢያቸውን በየተራ ሸጠዋል። ከአንድ ኩንታል ስንዴ ውስጥ አፈርና እንክርዳዱን እየለዩ አስር ብር ተከፍሏቸዋል፤ በዚህ ስራ አንድ ዓመት ከስድስት ወር ሰርተዋል። ሦስት ዓመት በሰው ቤት እንጀራ ጋግረዋል፤ ጉሊት ቁጭ ብለው ቲማቲምና ድንች ቸርችረዋል። ሦስት ዓመት ደግሞ ፒያሳ ገዳም ሰፈር በሚባለው አካባቢ በቀን አሥራ ስድስት ብር እየተከፈላቸው የቀን ስራ ሠርተዋል። የሚለብሱትን አጥተው ከጓደኞቻቸው ልብስ ተመፅውተዋል፤ ደረቅ ሽንብራ ቆርጥመው ስድስት ቀናትን አሳልፈዋል። ሁለትና ሶስት መልክ አውጥተው ልጆቻቸውን ለማሳደግ ጥረዋል። ከብዙ ጉስቁልና በኋላ የቀን ሥራ እየሰሩ ጥበብ ኢትዮጵያ የሚባል ድርጅት ውስጥ ገቡ።
በ10 ክፍለ ከተሞች በሚገኙ የመንግሥት መስሪያ ቤቶችና ድርጅቶች እየተዟዟሩ ልመና ይቁም፤ ቆሻሻ እናጽዳ ብለው ለፍፈዋል። ከዚያም ከሴቶች ጋር ሆነው 10 ሳንቲም መቆጠብ ጀመሩ። ከዚያም ይህ ድርጅት 200 አዲስ ልሳን ጋዜጦችን አስይዟው በየከፍለ ከተሞቹ እየዞሩ ይሸጡ ነበር። እንዲህ እያሉ ጋዜጣ እያዞሩ መሸጥ ቋሚ እንጀራቸው ሆነ። ሌሊት እንጀራ ጋግረው፤ ሊነጋ ሲል የሰሌን ኮፍያቸውን ከአናታቸው ላይ ጣል አድረገው ወደ መርካቶ ያዘግማሉ።
ጋዜጣውን በጀርባቸው ተሸክመው ወደ ፒያሳ ከፍታ ይወጣሉ፤ ወደ መርካቶም ቁልቁለት ወረድ ብለው ጋዜጣቸውን ያከፋፍላሉ። ደንበኞቻቸውን በትክክል ይህን ያክል ናቸው ብለው አያውቋቸውም። በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ከጋዜጣ አንባቢ ደንበኝነትም በላይ ወዳጅ ዘመድ አፍርተዋል። ለዚህም ማሳያ አለኝ የሚሉት ወይዘሮ ትበርህ፤ የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ በወጣላቸው ጊዜ የመርካቶ ደንበኞቻቻው 15 ሺህ ብር ሰብስበው ሰጥተዋቸዋል።
ወይዘሮ ትበርህ «መማር ብቻ ሳይሆን፤ በተገኘው ሥራና መስመር ሌት ተቀን መሥራት ይገባል» ይላሉ። ሰው ከሥራ ካልተገናኘ ከድህነት መላቀቅ አይቻልም የሚል እምነት አላቸው። እርሳቸው ያለፉበትን ውጣ ውረድ እያስታወሱ ጋዜጣ አንባቢውንም ማስታወቂያ ስራ ፈላጊውንም «ይቅናህ» ይላሉ። ‹‹ምነው ምርቃት አበዙ›› ብሎ ለሚጠይቃቸው «ደንበኛ ክቡር ነው፤ መልካም ምኞት በረከት ነው» የሚል ምላሽ አላቸው።
ትልቅ ነገር ተመኝተው፤ ደግሞ በፈጣሪ እርዳታ አሳክተዋል። ከ1997 ዓ.ም ጀምረው ቁጠባን ስራዬ ብለው ተያይዘውታል። በ10ኛው ዙር የጋራ መኖሪያ ቤት እጣ ሲወጣ ባለ ሁለት መኝታ ቤት ደረሳቸው። በየወሩ 3ሺ411 ብር የኮንዲሚኒየም ክፍያ አለባቸው። በአሁኑ ወቅት በራሳቸው ቤት ከልጆቻቸው ጋር ይኖራሉ። ቀድሞ ፒያሳ ገዳም ሰፈር አካባቢ በቀበሌ ቤት 10 ብር ይከፍሉ ነበር። ግን የጋራ መኖሪያ ቤት ደርሷቸው መብራት እና ውሃ እንደገባ ቤት እያለኝ ከኔ የባሰ ድሃ ይኑርበት ብለው ለሚመለከተው አካል አስረክበው ወጥተዋል። በአሁኑ ወቅትም ፒያሳና መርካቶ እየኳተኑ ጋዜጦችን ይሸጣሉ።
አሁን አቅማቸው ደክሟል ቋሚ የመሥሪያ ቦታ ይፈልጋሉ። የካ አባዶ ሁለት ሜትር በሁለት ሜትር ለስራ ቦታ ቢሰጣቸውም አካባቢው ብዙ አንባቢ ባለመኖሩ መሃል ከተማን ይሻሉ። ፍቅር እንዳለ ፀብ አለ የሚሉት ወይዘሮዋ ትበርህ «ፍራቻ አልፈጠረብኝም፤ ቂምም አልወድም ባይሆን ወዲያውኑ ተቧቅሼ ነገሩን ብረሳ እመርጣለሁ» ይላሉ።
«የነካኝን ግን በቦክስ ስነቀንቀው፤ ልክ ሳስገባው እረካለሁ» የሚሉት እኚህ እናት፤ የተመጠነ ምግብና መጠጥም ያስደስታቸዋል። ባያበዙም ቢራ እንደነፍሳቸው ይወዳሉ። ዱለትና ጥብስ ደግሞ ለእርሳቸው ከልባቸው የሚወዱት ምግብ ነው። ከለበሱም ሽቅርቅር ማለት ደስ ይላቸዋል። ዛሬ ኑሮ ተጭኗቸው፤ ሕይወት ተመሰቃቅ ሎባቸው ወደ መደበኛ መንገዱ ሊመልሱ በሚለፉበት ዘመን ሆነ እንጂ፤ ያኔ አስመራ ሆነው ዝንጥ፣ ቁንጥንጥ የሚሉ ሸጋ ወይዘሮ ናቸው። ማህበራዊ ሕይወታቸውም አስደሳችና በሰዎች የተከበበ እንደነበር ያስታውሳሉ። ግን ባለቤታቸው ባህር ኃይልን ሲሰናበቱ ቆይተውም ሲሞቱ፤ ነገሮች መለወጣቸው ያስቆጫቸዋል።
አዲስ አበባ ሲመጡ በተራው ኑሮ ተገለበጠባቸው። የደስታውና በሰው የመከበቡ ነገር ተቀየረባቸው። መቼም ይህን ኑሮ ለመግፋት በስንቱ ተገፍተው፤ እርሳቸውም ስንቱን የሕይወት ውጣ ውረድ እንደገፉት መገመቱ ብዙም አይከብድም። ኖሯቸውም ባይሄዱም የምጽዋ ትዝታ ዛሬም አልወጣላቸውም።
ጊዜ ደጉ ብዙ ያሳያል የሚሉት እኝህ እናት፤ ልክ እንደ እናታቸው ረጅም እድሜ ይመኛሉ። እናታቸው በ108 ዓመታቸው ነው ያረፉት። አቅም ስላጡ እንጂ ዘመዶቻቸውን ሁሌም ቢጠይቁ ምኞታቸው ነው። እስካሁን ሽሬእንደስላሴ የሄዱት ሦስት ጊዜ ብቻ ነው።
በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የነበረው ፀብ ረግቦ ሠላም መውረዱ በጣም ትልቅ ደስታ ፈጥሮላቸዋል። ጊዜ አግኝተው ወደ ምጽዋ ሄደው አየሯን ማግ ማግ አድርገው፤ ከዱሮ ትውስታቸው ጋር በምፅዋ ወደብ አጠገብ ሆነው ዱሮ ባለቤታቸው ይዘንጡባቸው ይዝናኑባቸው፤ ይሰሩባቸው በነበረው አካባቢ ቢገኙ፤ በትዝታ ባህር ቢመላለሱ ምርጫቸው ነው።ማን ያውቃል? ነገም ሌላ ቀን ነውና ያሰቡት ተሳክቶላቸው እንዲህ በአይናቸው ላይ ውል የምትለውን ምፅዋን ይጎበኟት ይሆናል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 14/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር