የጉራጌ ምድር ያበቀለቻቸው የ‹‹እነሞር›› ፍሬዎች በለምለሙ መስክ ሲቦርቁ ይውላሉ። በእንሰት ተክል ከተከበቡ ውብ ጎጆዎች ብቅ የሚሉ ህጻናት ሁሌም ወዘናቸው ያምራል። ትኩስ ወተት እየተጎነጩ ፣ቆጮ በአይቤ፣ ሲበሉ። አድገዋል።
እነሞር ባለ አረንጓዴው መሬት፣ ድንቅ የጉራጌ ምድር። በአካባቢው ተወልደው ያደጉ አብዛኞች በትጋታቸው ማደር ልምዳቸው ነው። ከእነዚህ መሀል በርካቶቹ ከሰፈር መንደራቸውን ርቀው መውጣት ብርቃቸው አይደለም። እነዚህ እንጀራ ፈላጊዎች በየደረሱበት ስራን አይንቁም። ጫማ አሳምረው (ሊስትሮ) ተብለው ይኖራሉ። በጉልበታቸው ለፍተው፣ በላብ ወዘናቸው ያድራሉ።
የእነሞሩ እንግዳ… 1964 ዓም
ተማም ሀሰን በዕድሜው ገና ልጅ ነው። እነሞር ተወልዶ ሲያድግ ልጅነቱን ያሳለፈው እንደእኩዮቹ ፈንድቆ ነበር። ወላጅ አባቱ የአዲስ አበባን ህይወት አሳምረው ያውቃሉ። የበግ ቆዳ መሸጥ መተዳደሪያቸው ነው። ለልጃቸው እሱን መሰሎች ከከተማ ዘልቀው በኑሮ መለወጣቸውን ሲነግሩት ቆይተዋል። ተማም ትንሽ ልጅ ቢሆንም እንደማንኛውም የጉራጌ ልጆች ሮጦ ማደር እንደማያቅተው ያውቃሉ።
የተማም አባት አንድ ማለዳ የትንሹ ልጃቸውን እጅ ይዘው ከመንደራቸው ራቁ። እስከ ወልቂጤ በእግር ተጉዘው ወልቂጤ ሲደርሱ የመኪና ትኬት ቆርጠው ወንበር ይዘው ተቀመጡ። አፍታ ሳይቆይ ተሳፋሪዎች መኪናውን ሞሉት። ጉዞ ወደ አዲስ አበባ።
ትንሹ ልጅ ከዚህ በፊት አውቶቡስ ይሉትን ተሳፍሮ አያውቅም። ከአባቱ ጋር ራቅ ብሎ መሄዱ በእጅጉ አስደስቶታል። በጉዞው እየተዝናና ፣ በሚያየው ሁሉ እየተደነቀ መንገዱን ገፋው። ጥቂት ከተሞች ወደኋላ እያለፉ፣ ሜዳ ጫካው እየራቀ ጉዞው ቀጠለ። አባትና ልጅ ወደ ደማቋ አዲስ አበባ ሲደርሱ ትንሹ ተማም በግርምት ተሞላ ። እሱ ከሚያውቃት የእነሞር መንደር የበለጠ ሌላ ስፍራ እንዳለ አያውቅም። እጁን በአፉ ጭኖ ዙሪያውን በአድናቆት ቃኘ። ከተማውን ጥሎት ከመጣው ቀዬ እያዛመደ በሚያየው እውነት ተደመመ።
አዲስ አበባ የገባው ትንሹ እንግዳ ውሎ ሳያድር ስራ ተገኘለት። እንደሌሎቹ የአገሩ ልጆች ጫማ ሊጠርግ ቡሩሽ ከቀለም ይዞ ከመንገድ ወጣ። ልጅነቱን ያዩ፣ ቅልጥፍናው ያስደነቃቸው ሁሉ ጫማቸውን ያሳምር ዘንድ ደንበኞች ሆኑለት። አባት የልጃቸውን ብርታት ባዩ ጊዜ ልባቸው ረጋ። ከእንግዲህ ራሱን ለመቻል መንገዱን ጀምሯል። ዛሬን ከሰራ ነገ ባለሱቅ ነው። ነጋዴ ሆኖ ብር ይቆጥራል።ሀብት ይዞ ለሌሎች ይተርፋል።
ተማም ጥቂት ጊዜ በሊስትሮው እንደሰራ ልጅነቱ አሸነፈው። በቀን የሚያገኘውን ሳንቲም ይዞ ወደሱቅ መመላለስ ልምዱ ሆነ።ብስኩት እየገዛ የሚገምጥበት የቀን ገቢው እንደታሰበው ቁም ነገር አልሰራም። አባት በድርጊቱ ተበሳጩ። ስለሱ ያሰቡት የነገ ህልም እንደማይዘልቅ ገባቸው። ያለስራ እንዲቀመጥ አልፈቀዱም። የሊስትሮ ዕቃውን አስጥለው ከሰው ቤት አስቀጠሩት።
የሶስት ብሩ ደሞዝተኛ …
ከአንድ መኖሪያ ቤት በጭሎነት የተቀጠረው ተማም ቤት እየጠበቀ የታዘዘውን ይሰራል። ለጉልበቱ ዋጋ በወር ሶስት ብር የሚከፍሉት ባልና ሚስት የመንግሥት ሰራተኞች ናቸው። ጥንዶቹ ጠዋት ወጥተው ማታ ይመለሳሉ። አጋጣሚ ሆኖ የተማም አሰሪዎች ከጎረቤቶቻቸው ጋር ሰላም የላቸውም፡፤ በየምክንያቱ፣ በየሰበቡ ሲጣሉ ዓመታትን ዘልቀዋል።
አንድቀን የተማም አሰሪዎች ስራ ውለው ወደ ቤት ተመለሱ። ወይዘሮዋ ሁሌም እንደሚያደርጉት ግቢውን አለፉና ድመታቸውን ደጋግመው ተጣሩ። የዛን ቀን የሚወዷት ውሮ እንደልማዷ አልሆነችም። ወትሮ ሮጣ ትመጣ እንዳልነበር በዝምታ ተዋጠች። የልምዳቸውን ያጡት ወይዘሮ በተማም ላይ እንዳፈጠጡ ስለ ድመታቸውን ጠየቁ፤ በቂ መልስ አላገኙም።
ሴትዬዋ ዙሪያ ገባውን እየቃኙ ደጋግመው ተጣሩ። ጥቂት ቆይቶ ድመቷ አንድ እግሯን አንጠላጥላ እያነከሰች ብቅ አለች። ዓይናቸውን ማመን አልቻሉም። እንደልጅ የሚያሳድጓት ድመታቸው በእጅጉ ተጎድታለች። ፊታቸው በንዴት ተለዋወጠ። ይህን ያደረጉት ጠበኛ ጎረቤቶቻቸው እንደሆኑ ገባቸው።
እመቤቲቱ አፍታ አልቆዩም። ተማም ላይ ዱላ ያወርዱበት ያዙ። ጥበቃውን በወጉ አልተወጣም ያሉት ወይዘሮ ፈጣን እርምጃ ወሰዱበት። ትንሹ ጭሎ በአስቸኳይ ቤታቸውን ለቆ እንዲወጣ ትዕዛዝ ተሰጠው። በድመቷ ሰበብ እህል ውሀው ያለቀው ተማም ከስራው ተባረረ። በዓይኑ ዕንባ እንደሞላ አባቱ ወደሚገኙበት በግ ተራ ደርሶ የሆነውን ሁሉ አወጋቸው።
የዛኔ የእነተማም ዘመዶች ዛሬ ተወካዮች ምክር ቤት በተሰራበት ሜዳ ላይ በጎች ይነግዱ ነበር። እነሱን ጨምሮ ወላጅ አባቱ የሆነውን በሰሙ ጊዜ ወደ ሊስትሮነት ስራው እንዲመለስ መከሩ። ተማም የተገዛለትን የሊስትሮ ዕቃ ይዞ ጫማ ማሳመሩን ቀጠለ። ልጅነቱን በስራ መግፋት የያዘው ህጻን ሲያመቸው ከሰው ቤት እየሰራ፣ አንዳንዴም ለሆቴሎች ሰሀን እያጠበ ኑሮ ቀጠለ።
የአፄው ስርዓት ተገርስሶ አዲስ መንግሥት በተሾመ ጊዜ ትንሹ ተማም ራሱን ለማገዝ በታላቅ ልፋት ይታትር ያዘ። አገር በአብዮትና አብዮተኞች ለውጥ መልኳ ሲቀየር የአፍላነት ግዜው እየጀመረ ነበር። እሱም ለራሱ ህይወት ለውጥን ፈላጊ ሆኖ በአማራጮች ሁሉ ሮጠ። ዕድሜው ሲጨምር ብስለት ታከለበት። ልጅነቱ እየራቀው ሲሄድ የቆመበትን፣ ያለበትን ጊዜ አሰበው። ወታደር፣ ሆኖ ዳር ድንበር ማስከበርን ተመኘ።
1973 ዓ.ም ተማም የውስጡን ፍላጎት ሊሞላ ከሁርሶ ወታደራዊ ማስልጠኛ ተገኘ። የዛኔ እሱን መሰል ልጅ እግሮች ምልምል ወታደር ለመሆን ቁርጠኞች ነበሩ።በውሰጣቸው ያደረው የአገር ፍቅር፣ ከአፍላ ስሜት፣ተዳምሮ ብቃታቸውን ሊያሳዩ የፈጠኑ ፣ ግዳጅ ለመቀበል የተዘጋጁ ናቸው።
የስልጠናው ቆይታ በጥንካሬ እንደተቋጨ ተማም ብቁ ወታደር ሆኖ ለግዳጅ ተዘጋጀ። 1974 ዓ.ም ። የቀይ ኮከብ ዘመቻ የታወጀበት ታሪካዊ ጊዜ። ትንሹ ወታደርና መሰሎቹ ከጊዜው መልክ ሊገናኙ ግድ ያላቸው ወቅት ሆነ። የኤርትራ ምድር አፍላዎቹን ወታደሮች ለመቀበል እጇቿን ዘርግታለቸ፣ጦርነቱ ተፋፍሟል፣በየቦታው ቅስቀሳና አፈሳው ጦፏል።
ዘማቹ ተማም ከኤርትራ ተራራዎችና ምሽጎች የሚሰጠውን ወታደራዊ ትዕዛዝ እየተቀበለ ግዳጁን መወጣት ያዘ። አንዳንዴ ጦርነቱ ሲግም የልጅነት ልቡ ይደነግጣል። ቤተሰቦቹን እያሰበ፣አስተዳደጉን እያስታወሰ ይቆዝማል።ያም ሆኖ የቆመበትን ዓላማ ፈጽሞ አይዘነጋም። አሁን ድንበር ጠባቂ ጀግና ወታደር ነው።አገሩን ከጠላት ሊጠብቅ ደጀን ሆኖ ዘብ ቆሟል፡፤
የኤርትራው ጦርነት ተፋፍሞ ቀጥሏል።በርካቶች ከጎኑ በክብር ይወድቃሉ። ሌሎች ጀግኖች ቆስለው እየደሙ፣ አካላቸውን ያጣሉ። ተማም ከዚህ ዕጣ ፈንታ አላመለጠም። ከአንድም ሶስት ጊዜ በተኩስ ልውውጡ ቁሰለኛ ሆኖ ተጎዳ ።
አስር አለቃው በቁርጥ ቀን…
ወታደሩ ተማም የቆይታ ጊዜው የአስር አለቅነት ማዕረግን አልብሶታል። እየቆሰለና እያገገመም የግንባር ግዳጁን ቀጥሏል። ውጊያው አላባራም። አሁንም ሺዎች እየተሰዉ ሺዎች ይወድቃሉ ። በ1982 ዓ.ም የተካሄደው ጦርነት ግን በእጅጉ የከበደ ሆነ።በአውደ ውጊያው የተሳተፈው ተማም በድጋሚ እግሩን ተመቶ ቆሰለ። ሁኔታው እንደ ቀድሞ አይነት ጉዳት አልሆነም።
የደቀመሀሪው የምሽግ ውስጥ ውጊያ የበርካቶችን ህይወት ነጠቀ። የሳዋ ምድር የተማምን የግራ እግር አሳጣው። በጓደኞቹ አግላይነት እስትንፋሱ አስመራ የደረሰው ቁስለኛ ከሆስፒታል ገብቶ ከአልጋ ላይ ዋለ።ጉዳቱን ያስተዋሉ ሀኪሞች እግሩ በአስቸኳይ እንዲቆረጥ ከውሳኔ ደረሱ። ተማም ይህን ሲሰማ ‹‹እምቢኝ፣ አሻፈረኝ›› ሲል ተቃወመ።
አዲስ አበባ እንዲላክ የወሰነው የህክምና ቦርድ ተማምን ለቀጣዩ ሂደት አመቻቸው። ቁስለኛው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እንደደረሰ ዕጣ ፈንታው ከቀደመው ውሳኔ አላለፈም። እግሩ ከጉልበቱ በታች ሊቆረጥ ግድ ሆኖ የታሰበው ተፈጸመ። እንዲህ በሆነ ሰሞን ኢህአዴግ መላ አገሪቱን ተቆጣጥሮ አዲስ አበባ ደረሰ። ይህኔ ተማምን መሰል የቀድሞ ወታደሮች ህይወት ከፈተና ወደቀ። ወያኔ ወታደሮቹን በጠላትነት ፈርጆ ‹‹እንጃላችሁ›› አላቸው። ‹‹አላውቃቸሁም›› የተባሉ ሁሉ ከከፋ ችግራቸው ጋር ከስንብት መዝገብ ሰፈሩ።
ቁስለኛው ተማም አሁን እንደቀድሞው አይደለም ። ሙሉ አካሉን አጥቷል። የልጅነት ዕድሜውን ከፍሏል። ዛሬ ሮጦ መስራት አይቻለውም። ተስፋ መቁረጥ ከቦታል ።ርሀብ ጥማት ፈትኖታል።ትናንት በወደቀላት አገሩ ቁራሽ እንጀራን ተነፍጎ ለከፋ ችግር ተጋልጧል።
የወቅቱ ሀይሎች በርካቶችን በእርዳታ ስንዴ ሲሸኙ እነተማምን በቀይ መስቀል አማካኝነት ከታጠቅ ጦር ሰፈር ወስደው አሰፈሯቸው።ይህን ተከትሎ ደብረዘይት የቀድሞ ጀግኖች አምባ የተላከው ተማም የሰው ሰራሽ እግር ተገጥሞለት ከማዕከሉ ግቢ ተሰናበተ።
የቀድሞ ወታደሩ ትካዜ..
ሰውዬው ከዓመታት በፊት የልጅነት ዕድሜቸውን ባሳለፉበት መሀል አራትኪሎ ተገኝተዋል። ይህ አካባቢ ለእሳቸው መኖሪያቸው ብቻ አይደለም። የህይወትን ጅማሬን አይተውበታል። ከልጅነት እስከ ጉልምስና አልፈውበታል፣ አራት ኪሎ ለእሳቸው አግኝተው የሰሩበት፣አፍሰው የበተኑበት፣ልዩ ሰፈር ነው።
ዛሬ ከአራት ኪሎ ጋር የተገናኙት በሙሉ አካላቸው አይደለም። ስለህይወታቸው አጥብቀው ይጨነቃሉ። ክራንቻቸውን ደገፍ እንዳሉ ስለኑሯቸው ያስባሉ።በእጃቸው አንዳች ሳንቲም የለም። ለጎናቸው ማረፊያን አላገኙም። የቀድሞው ወታደር አቶ ተማም……በትካዜ ተውጠዋል።
ከቀናት በአንዱ ቀን አንድ ልበ ደግ ተማም ካሉበት ደርሶ የክብደት መለኪያ ሚዛንን ‹‹እነሆ›› አላቸው። ስራ ወዳዱ ሰው ውለው አላደሩም። ከመንገድ ዳር ይዘውት ተቀመጡ። በርካቶች ከሚዛኑ እየወጡ ዋጋውን ይከፍሏቸው ያዙ። ተማም ሚዛኑ ገንዘብ ቢያመጣላቸው ተጨማሪ ገቢን ፈጠሩ። ባለ ጀብሎ ሆኑ። ማስቲካ ከረሜላ እየሸጡ ደንበኞችን አበዙ።
አሁን አቶ ተማም ገንዘብ መያዝን አውቀዋል። ስለነገው ህይወታቸው በሰፊው እያቀዱ ነው። ዕቁብ ጀምረዋል። ዕቁብተኞቹ የሰጧቸውን ሰድስት መቶ ብር ብር ባንክ አላስገቡም። ለጀመሩት የጀብሎ ስራ በቂ አቅርቦት አሟልተው ንግዱን አስፋፉ። የጀብሎው ንግድ እንጀራቸው ሆኖም ህይወታቸውን ይመራ ያዘ።
የግራ ጎንን ፍለጋ ..
ተማም የጎዳናው ላይ ስራቸው ከብዙዎች ያውላቸዋል።ጥረታቸውን የሚያስተውሉ ደንበኞቻቸው ከእሳቸው ለመግዛት አይቦዝኑም። የጦር ጉዳታቸውን የሚያውቁም ጠጋ ብለው ያበረቷቸዋል። ተማም አሁን ብቸኝነት ይሰማቸው ጀምሯል። ከጎናቸው የምትጣመር፣ከእንጀራቸው የምትካፈል አጋር ቢያገኙ አይጠሉም። ያሰቡት አልቀረም።አንድቀን ለእሳቸው የተጻፈችው ወይዘሮ የትዳር አጋራቸው ልትሆን ፈቀደች። ተማም ስለማንነቷ አጣሩ። የእነሞር ፍሬ የጉራጌ ልጅ ሆና አገኙዋት ።በእጅጉ ተደሰቱ።ደግመው፣ደጋግመው እንጋባ አሏት። ትዳር ፈላጊዋ እመቤት አልተግደረደረችም። ከእሳቸው ሆና የግራ ጎናቸውን ልትሆን ወደደች። ጥንዶች ሆኑ።ጎጆ ቀለሱ።ሁለት ልጆች አፈሩ።
ጡሩንባ ነፊው..
የትናንቱ ብርቱ ተማም ዛሬ የኔ ይሉት ማረፊያ የላቸውም። በአቅማቸው በተከራዩት ትንሽ ቤት ውለው ያድሩበታል። የአካባቢው ዕድር ጡሩንባ ነፊዎችን በፈለገ ጊዜ ከሌሎች ጋር ተወዳደሩ ።ፈተናውን አልወደቁም። ዕድር ቤቱን እየጠበቁ ያለ ኪራይ ሊኖሩበት ዕድል ተሰጣቸው። ቤቱን ተረከቡ። በመንደሩ ለቅሶ ባጋጠመ ጊዜ ባለአንድ እግሩ ጠባቂ ሌት ከጅብ እየተጋፉ፣ ጡሩንባውን ይነፋሉ። ቀን ከጀብሏቸው ውለው ማታ ከቤታቸው ያርፋሉ።
አሁን ልጆች እያደጉ ፣ኑሮ እየተወደደ ነው። ህይወት ባለበት አይቀጥልም። ለውጥ ያስፈልጋል፤ይህ እውነት የሚያሳስባቸው ጥንዶች ለልጆቻቸው መጪ ዕድል አጥብቀው ይጨነቃሉ፤ኑሯቸውን በሚያገኙት የቀን ገቢ ብቻ መምራቱ ከብዷቸዋል። ባልና ሚስቱ ጊዜ ወስደው መከሩ፣ተማከሩ። ጀብሎውን ከሚሸጡበት አንድ ጥግ ባዶ ስፍራ አለ። በዚህ ቦታ የጀበና ቡና ቢያቀርቡ ኑሯቸው እንደሚደጎም አሰቡና ወሰኑ ። ፈጥነው ቦታውን አዘጋጁት።የቡና ዕቃውን አሟልተው ሽያጩን ጀመሩ። ጎን ለጎን ለድንኳን የሚሆን የወረቀት ጉዝጓዝ እየሸጡ ኑሯቸውን ቀጠሉ።
በጥንዶቹ ዘንድ የኔ የሚባል ድርሻ የለም። በእኩል ቆመው በአንድ ይሰራሉ። አቶ ተማም ቡናውን ቆልተው ሲኒውን ያቀርቡና በእርጋታ ይቀዳሉ። የዕጣኑ ጭስ በመልካም መዓዛው ደንበኞችን ይጠራል። ለቡና ቁርሱ ብስኩትና አምባሻ አይጠፋም። ወይዘሮዋ የጎደለውን እያዩ ደንበኞችን ያስተናግዳሉ። በቤቱ ሁሌም ትህትናና መልካም መስተንግዶ ተለምዷል።
አንዳንዴ አቶ ተማም ኑሮ ሲጫናቸው ይከፋሉ። በቸገራቸው ጊዜ የውስጥን የሚረዳ ወዳጅ ዘመድ በቅርብ የለም። ጤና ሲጓደልና ድካም ሲበረታ ትካዜ ይገባቸዋል። ልጆች አሳድጎ ለማስተማር የኑሮ ውድነት ይፈትናል። መርካቶ ደርሶ ዕቃ ለማምጣት ጉልበት ይጠይቃል፣የአካል ጉዳታቸው ከሌሎች ተጋፍቶ ትራንስፖርት የሚያስይዝ አይደለም። ያም ሆኖ ከሌሊቱ አስር ሰአት ጀምሮ ከቤታቸው ወጥተው ስራቸው ላይ ይገኛሉ።
አንዳንዴ ልጆቻቸው ክራንች ይዘው እንዲታዩባቸው አይሹም። እነሱ የአባታቸውን ችግር ሌሎች እንዲያውቁት አይፈልጉም። እሳቸው ግን ክራንቹ የሁልግዜ ምርኩዛቸው ነው። አቅም ቢፈቅድና አጋዥ ቢያገኙ በሞተር የሚሰራውን መጓጓዣ ይመኛሉ።
አስር አለቃ ተማም የዕለት እንጀራቸው የሆነው ቦታ ዳያስፖራዎች ይመጣሉ በሚል ሰበብ ፈርሶባቸዋል። የዛኔ በእጅጉ ከፍቷቸው ነበር። አሁንም ቢሆን እንደነገሩ የተሸፈነው ከለላ ክረምቱን የሚያሳልፋቸው አይደለም። የሚሰሩበት ዕቃና ንብረትም በተደጋጋሚ ተዘርፎባቸው ያውቃል። ከዓመታት በፊት በጥበቃ ያገኙት የዕድር ቤትም በልማት ምክንያት ፈርሷል። ዛሬ ግን የካ አባዶ በደረሳቸው ኮንዶሚኒየም ከነቤተሰባቸው ይኖራሉ።
ከጀብሎ ስራ አንስቶ ሰላሳ ሦስት ዓመታትን የሰሩበት የመንገድ ዳር ቦታ ለተማም ባለውለተኛቸው ሆኖ ዘልቋል። እዚህ ቦታ እንዳሉ ትዳር ይዘው፣ልጆች ወልደው ዓመታትን ገፍተዋል። እንዲህ ለመኖር ብዙ የታተሩት የአገር ባለውለታ አሁንም አንድ እግራቸው አይዝልም፣ ሻካራ እጆቻቸው አይሰንፉም። በጥረት ዛሬን ያሳድራሉ። በድካም ነገን ያሻግራሉ።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ግንቦት 20/2014