ደራሲ፡- ማረኝ ኃይለማርያም
ዘውግ፡- ሙዚቃዊ ቴአትር
የሚታይበት ቀንና ቦታ፡- ረቡዕ ምሽት 11፡00 በሀገር ፍቅር ቴአትር
አዘጋጅ – ዮሃንስ አፈወርቅ
ብዙ ባይባሉም የቴአትር ትምህርት ክፍል ያላቸው ዩኒቨርሲቲዎች አሉን። የቴአትር ትምህርት ክፍል ለምን በጥቂት ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ይሰጣል? የሚለው ጥያቄ ተደጋግሞ ቢነሳም ዋናው ጥያቄ ግን ከዚህ በላይ ነው። እየሰጡ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎችስ ምን አስገኙ? ኪነ ጥበቡ ላይ ምን ጨመሩ? የቴአትር ማሳያ አዳራሾቻችንስ ምን ያህል ናቸው? ከቴአትር ትምህርት ክፍል የወጡ ተማሪዎች የት ደረሱ? ምን ሰሩ? የሚሉት ጥያቄዎች ‹‹ለምን ቴአትር የሚያስተምሩ ዩኒቨርሲቲዎች አነሱ?›› የሚለውን ጥያቄ ያስረሱናል።
ራሳቸው ተማሪዎች ደግሞ የሚያነሱት ሌላ ሀሳብ አለ። ከቴአትር ትምህርት ክፍል ተመርቆ ወጥቶ ሥራ ላይ መሰማራት ከባድ ነው። ምንም እንኳን ችግሩ በሁሉም የትምህርት ክፍል ላይ ያለ ቢሆንም በተለይ በዚህኛው ግን ይብስበታል ነው የሚሉት። ለዚህም ነው እንደ ጋዜጠኝነት ባሉ ተዛማጅ የትምህርት ክፍሎች ሥራ ሲፈልጉ ይታያል።
ቴአትር ከሌላው የትምህርት ክፍል ይለያል። ሌላው የትምህርት ክፍል ሳይንስነቱ ይበልጣል፤ ቴአትር ግን ተሰጥዖን የሚጠይቅ ነው። ይህን ትምህርት የሚማሩ ልጆች ከሌላው የሚለዩት፤ የተሻለ ቅጥር አለው፣ የተሻለ ደመወዝ አለው ብለው የሚገቡ አይደሉም፤ የተፈጥሮ ዝንባሌያቸውንና የነፍስ ጥሪያቸውን ይዘው የሚሄዱ ናቸው። የዚህ ሙያ ፍቅር ስለበለጠባቸው ነው።
እንደዚህም ሆኖ ግን ተመርቀው ከወጡ በኋላ ይማረራሉ፤ የሚማረሩት ያን በጉጉት ሲጠብቁት የነበረውን የጥበብ ፍቅራቸውን መወጣት ባለመቻላቸው ነው። የሚቸገሩት ደግሞ የተመቻቸ ሁኔታ ባለመኖሩ ነው። በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ውስጥ ሆነው በቅርብ የተመረቁ ወጣቶች አንድ ቴአትር ሰርተዋል። ሁኔታዎች ቢመቻቹ ወጣቶች መሥራት እንደሚችሉ ያሳያል ማለት ነው። ቴአትሩን እናስተዋውቃችሁ። ዋና ጉዳዩ በሰላም ላይ የሚያተኩር ሙዚቃዊ አስቂኝ ቴአትር ነው።
ቴአትሩ «ሰፈረ ጎድጓዳ» የሚል ርዕስ ተሰጥቶታል። ጎድጓዳ የሰፈር ስም መሆኑ ነው። የዚህ ጎድጓዳ የሚባለው ሰፈር ወጣቶች «ቦዘኔ» በሚለው ቃል የሚጠሩ ናቸው።በቃ አካባቢውን መበጥበጥ ነው።ቤታቸውን ለመምራትና ልጆቻቸውን ለማሳደግ ሥራ ላይ ብቻ የሚያተኩሩ ሰዎችን ይበጠብጣሉ፤ የማይስማሙባቸው ነገሮች ይበዛሉ።
የቴአትሩ መልዕክትም ላለመስማማት እንኳን መስማማት እንደሚያስፈልግ ማሳየት ነው። በቴአትሩ ውስጥ ሌሎች ንዑሳን ጭብጦችንም ማውጣት ይቻላል። ፍቅር አለ፣ ማህበራዊ ጉዳይ አለ፣ ፖለቲካ አለ። በቴአትሩ ውስጥ የሚነሱ ሀሳቦች ሌላ ሀሳብም ለማንሳት የሚገፋፉ ናቸው። እንግዲህ እነዚህ ወጣቶች ያን ሁሉ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳይ አስተውለውት ነበር ማለት ነው።
የአገሪቱን ነባራዊና ወቅታዊ ሁኔታ በትኩረት ተከታትለውታል ማለት ነው። ይሄ ደግሞ ወጣቱ ፈዟል የሚለውን ሀሜትም ሀሜት ሆኖ እንዲቀር ያደርጋል። ለምን ቢባል በዚያ ቴአትር ውስጥ ያሉ ሀሳቦች የአገሪቱን ሁኔታ በትኩረት እንዳስተዋሉ ያሳያልና! ይህን ቴአትር የሰሩት በቅርብ የተመረቁ ወጣትና ጀማሪ የቴአትር ተመራቂዎች ናቸው። ከወልቂጤና ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የተመረቁ ወጣቶች ‹‹ገና ቴአትርና መልቲ ሚዲያ›› የሚል ኩባንያ አቋቋሙ። ዓላማቸውም ‹‹አይ የቴአትር ወርቃማ ዘመንማ አለፈ፤ ከዚህ በኋላ ቴአትር አይሰራም!›› የሚለውን ሀሜት በማክሸፍ አለማለፉን ለማሳየት ነው። ከዚህ በኋላ ለሚመጡ አዳዲስ ወጣቶችም ተስፋ ማሳየት ነው።ከደራሲው ጀምሮ ተዋናዮችም የመጀመሪያቸው ነው።
እንደሚታወቀው ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲ ከተመረቁ በኋላ ከዚያ ዩኒቨርሲቲ ጋር ያላቸው ግንኙነት እዚያው ላይ ያልቃል። የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ግን ‹‹ይህን አላደርግም›› ብሏቸዋል። ብዙ ነገር አብሯቸው ሊሰራ ‹‹አይዟችሁ!›› ብሏቸዋል።
ወደ ቴአትሩ እንመለስ!
ቴአትሩ አስቂኝ ሙዚቃዊ ቴአትር ነው።«ቁም ነገሩን ቀልድ አልሸፈነውም ወይ?» የሚል ጥያቄ አንስቼለት ከደራሲው ማረኝ ኃይለማርያም ጋር ተጨዋውተን ነበር። ቁም ነገሩን ቀልዱ እንደማይሸፍነው ነው የሚያምን። እንዲያው በደረቁ ቢሆን ምክር ነው ሚሆነው! በዚያ ላይ የወጣቶቹ (የገጸ ባህሪያቱ ማለት ነው) እና የሰፈሩ ዓውድም ለቀልድ ያስገድዳል። በነገራችን ላይ በቴአትሩ ውስጥ ለቀልድ ተብለው የሚነገሩ ቃላት ያስቁ እንጂ የሚተነተን ሀሳብ የያዙ ናቸው። ይሄ ደግሞ እንደተመልካቹ ይወሰናል። አንድ ነገር ግን እንመን! ቴአትርና ፊልም የሰሪውን ብቻ ሳይሆን የተመልካችም ጥበብ ይጠይቃል። አንዳንዱ ሀሳቡ ለሳቅ ብቻ ተብሎ የገባ ይመስለዋል፤ አንዳንዱ ደግሞ ከተነገረበት ዓውድ ተነስቶ ሌላ ትርጉም ይሰጠዋል። በእርግጥ የኪነ ጥበብ ሥራ በባህሪው ለትርጉም ተጋላጭ ነው። በሰፈረ ጉድጓዳ ቴአትር ውስጥ ያሉ የቀልድ ቃላትም እንዲህ ናቸው፤ በውስጣቸው ዘርፈ ብዙ ሀሳብ የያዙ።
በቴአትሩ ውስጥ ‹‹ነውር›› ሊባሉ የሚችሉ አንዳንድ ቃላት አሉ። ነውርነታቸው ከጾታዊ ግንኙነት ጋር የተያያዘ ነው። እነዚያን ቃላት ማስወጣት ነበረባቸው ለማለት ደግሞ ከኪነ ጥበብ ባህሪ ጋር አይሄድም። ለምሳሌ ገጸ ባህሪያቱ ‹‹ቦዘኔ›› የሚባለው አይነት ናቸው። በወጣትነት ዕድሜ ውስጥ ጨዋ የሚባሉትም ሳይቀር እርስበርስ ሲያወሩ እንደወረደ ነው። እንዲያውም ቴአትሩ ውስጥ ያን ያህል እንደወረደ የሚባል ነገር የለውም። ኪነ ጥበብ ደግሞ ለስብከት ብቻ ተብሎ አይሰራምና የወጣቶች ዓውድ ያስገድዳቸዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ እንደወረደ መናገርም ኪነ ጥበብ አይደለም። ለምሳሌ የመራቢያ አካል ክፍልን እንደወረደ መናገር ነውርነቱ ብቻ ሳይሆን ኪነ ጥበባዊ አገላለጽም አይኖረውም። ለምሳሌ ከዚሁ ቴአትር ውስጥ አንድ ጥበባዊ አገላለጽ ልጥቀስ። ከሰፈረ ጎድጓድ ሴቶች አንደኛዋ ባለሱቁን በእርግጫ የመራቢያ አካሉን ትመታውና በጸና ያመዋል። ‹‹ዘሬን መተካት አልችልም›› እያለም ያለቃቅሳል፤ ሌላ ቀን ሲገናኙ ‹‹የዚያን ቀን እኮ የመታሽኝ በጣም አመመኝ›› ሲላት ‹‹ልድገምልህ?›› ብላ እግሯን ታነሳለች። ይህኔም ባለሱቁ ‹‹አሁን እንኳን ቦታ ቀይረናል›› ይላታል።
እንዳልኳችሁ ኪነ ጥበብ ለትርጉም ተጋላጭ ነው። በዚህ ውስጥ ግን አንድ ነገር በቅኔ ተነግሯል። የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት። ‹‹ቦታ ቀይረናል›› የሚለው ቃል ከቀልድነቱና ከአስቂኝነቱ በተጨማሪ ይሄን ትርጉም ይይዛል። ዘሩን መተካት ካልቻለ እንዲህ ሊሆን ነው ማለት ነው። በዚህ ውስጥ እንግዲህ በማረሚያ ቤቶች ውስጥ ይደረግ ነበር የተባለውን አጸያፊ ድርጊትም እናገኘዋለን ማለት ነው። በቴአትሩ ዋና ጭብጥ የሰላምን አስፈላጊነት ነው የምናየው።
የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታም ያሳየናል። ነጋዴዎች፣ የቀን ሠራተኞች፣ በአነስተኛም ይሁን በትልቅ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ፀብ እንዳይፈጠር ሲጥሩ፣ ሲመክሩ ሲዘክሩ ቦዘኔዎች ግን የጡንቻንና የጠብን አስፈላጊነት ያሳያሉ። በቅሚያና በዝርፊያ ያምናሉ።
ሌላም እውነት አለ። እነዚያ ወደቅሚያና ዝርፊያ የገቡ ወጣቶች መገፋትና መበደል ነው ወደዚያ ያስገባቸው። ፍትሕ አጥተው ነው ጡንቻ ማፈርጠም የጀመሩት። በዚያ ሁሉ ወከባ ውስጥ ግን ሽማግሌዎችና ሰላም ፈላጊዎች ያሸንፋሉ።
ተግዳሮቶች
ልምድ አላቸው የሚባሉት የዘርፉ ሰዎች ጀማሪዎችን የማበረታታት ባህሉ የለም። ገና ስክሪፕቱን እንኳን ሳያዩት አይችሉም በሚል እምነት ያልፏቸዋል። ተመልካቹም ‹‹ምን አለ›› ሳይሆን ‹‹እነማን አሉ›› ብሎ ስለሚሄድ ስጋቱ ነበረባቸው።
ሌላው መሰረታዊ ችግር መለማመጃ ቦታ ነው። የቀበሌና የወረዳ ቦታ እንኳን ሲገኝ አለማማጆች እዚያ መውረድ ፈቃደኛ አይሆኑም። የሚሰሩት ወጣቶችም ከክፍለ ሀገር የመጡ ስለሆኑ በብዙ ነገር ይቸገራሉ። የትራንስፖርት እንኳን ለመክፈል ስለሚቸገሩ ይሄም አንዱ ፈተና ነበር። እንግዲህ የአገራችን የጥበብ ሥራ እየወረደ ነው የሚል ሁሉ እንደነዚህ ዓይነቶችን ማገዝ አለበት!
አዲስ ዘመን መጋቢት 14/2011
ዋለልኝ አየለ