ወፈፌው ይልቃል አዲሴ ዛሬም እንደዚህ ቀደሙ በሌሊቱ ተነስቶ በሰፈራችን ከሚገኘው ዋርካ ስር ቆሞ ይጮሃል። የይልቃል አዲዜን ጩኸት እንደ መጽሐፍ ማንበብ የጀመሩ የሰፈራችን እና የእድራችን ሰዎች የይልቃልን ንግግር ለመስማት በዋርካው ሰር ተሰባሰቡ።
ይልቃል ንግግሩን የጀመረው … ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የእድራችንን እና የሰፈራችንን ህልውና የሚፈታተኑ ጋሬጣዎችን እና እንቅፋቶችን በሰከነ እና በሰለጠነ መንገድ እየተነጋገርን እና እየተወያየን በመደማመጥ ከመፍታት ይልቅ ስሜታዊነታችን ጎልቶ እየወጣ እርስ በርስ ለመጠፋፋት ስንቋምጥ ይታያል። ይህን የሚመለከት ማንም የሰፈራችን እና የእድራችን አባል እውነት እኛ የአክሱም ስልጣኔ ወራሾች፣ የላልይበላ የአጥንት ክፋዮች፣ የሐረር ግንብ አናጺዎች፣ የአደዋ ድል ባለቤቶች የጥቁር ነፃነት ምሳሌዎች የሆኑ የአባቶቻችን ልጆች ነን ወይ ? ብሎ ራሱን እንዲጠይቅ ይገደዳል በሚል ነው።
ይልቃል ንግግሩን ቀጥሎ …መደማመጥ በነጋዴው እና በሸማቹ፣ መደማመጥ በፖለቲከኞች ፣ በሚዲያዎች፣ በአገር ውስጥና በውጭ በሚኖሩ የእድራችን እና የሰፈራችን ሰዎች፣ በተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች እና ጎሳዎች መካከል እንደሰማይ እየራቀን መምጣቱን እየተመለከትን ነው። እነኝህ አካላት መደማመጥ ተሳናቸው ማለት ደግሞ የእድራችንን እና የሰፈራችንን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለመተንበይ የግድ ነብይ መሆንን አያሻም። በአገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት እና አካባቢዎች የሚስተዋሉ የሰላም መደፍረስ፣ የሰዎች መሞት እና መፈናቀል ደግሞ ለዚህ ዋነኛ ማሳያዎች ናቸው።
መደማመጥ የችግሮች ሁሉ መፍቻ ቁልፍ ነው። መደማመጥ የትዕቢተኞችን የጥፋት ድግስ የሚያሽር ዓይነተኛ መድኃኒት ነው። መደማመጥ የሌለበት የፖለቲካዊ ፣ ሃይማኖታዊ፣ ብሔረሰባዊ ልዩነት አደገኛ ነው። ዓይንን ጨፍኖ ገድልን ለመሻገር እንደመሞከር ነው። መደማመጥ የሌለበት ፖለቲካ ዓይንን ጨፍኖ መስታወት እንደመመልከትም ነው። ስለሆነም ለእድራችን እና ለሰፈራችን ህልውና ሲባል ሁሉም የእድራችን እና የሰፈራችን ሰዎች ልዩነታቸውን አቻችለው እየተደማመጡ እና እየተናበቡ መሄድ ያስፈልጋል ባይ ነኝ።
ይልቃል አዲሴ የመደማመጥ ማነስ የሚያስከትለውን መዘዝ እና የመደማማጥ እና መግባባት መቻል ደግሞ የሚያስገኘውን ትርፍ በሁለት ተረቶች ላሳያችሁ ሲል ለተሰበሰበው ሰው ገልጾ …..ንግግሩን ለመቀጠል ጉሮሮውን እየሞረደ ተረት አንድን ጀመረ።
ተረት አንድ … አለመደማመጥ እና መዘዙ
በአንድ ወቅት በአንድ ስፍራ የሚኖር ቤተሰብ ነበር። በቤተሰቡ ውስጥ አንድ አባወራና ባለቤቱ ከሴት ልጃቸው ጋር ይኖሩ ነበር። ነገር ግን የሦስቱም ጆሮ ከፍ ያለ ድምጽን ካልሆነ በስተቀር ዝቅ ያለ ድምጽን ለመስማት ይቸገሩ ነበር። በሌላ አነጋገር «ጆሮአቸውን ያከራክራቸው» ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን አመሻሽ ላይ አባወራው አህያውን ውሃ ማጠጣት ፈልጎ ወደ ወንዝ ይዟት ወረደ። ወንዙ አጠገብ እንደደረሰም ሌሎች ብዙ እረኞች ከብቶቻቸውን ውሃ ያጠጡ ነበር። እነእርሱም «ሰማህ አንተ ሰው? ከብቶቻችን እየጠጡ ነው። ያንተ ግን አህያ ስለሆነች ከብቶቻችን ከጠጡ በኋላ ትጠጣለች» አሉት። ምክንያቱም አንድ አህያን ከሌሎች እንሰሳት የሚለይ ባህሪ አለ …ወንዝ ባገኘች ቁጥር መሽናት እና ውሃን በሽንቷ መበከል።
ቆይ መጀመሪያ ከብቶቻችን ይጠጡ የተባለው ባለ አህያ ጆሮውን ያከራክረው ስለነበር «ይቅርታ አህያዬ የሚሸጥ አይደለም።» አላቸው።
እነርሱም «ሰውየው ምን ነካው?» ብለው አሰቡ። እንዲህም አሉት «ያንተ አህያ ቢሸጥ ባይሸጥ ግድ የለንም። ከከብቶቻችን ቀድሞ እንዳይጠጣ ነው የምንፈልገው።»
ሰውየውም ቀና ብሎ አይቷቸው «የምናገረውን አትሰሙም እንዴ? አህያዬ አይሸጥም!!! አልኳችሁ እኮ።» ብሎ ይመልስላቸዋል።እረኞቹም «ሰውየው እብድ ነው?» ብለው አስበው ዝም አሉት።
አህያውንም ውሃ አጠጥቶ ወደ ቤቱ ተመለሰ። ሰውየው ቤቱ እንደደረሰም ወደ ኩሽና ሄዶ ሚስቱን እንዲህ አላት «ይገርምሻል! አህያችንን ውሃ ለማጠጣት እንደሄድኩ ቁጥራቸው በርከት ያሉ ነጋዴዎችን ወንዙ ዳር አግኝቼ ነበር። ነጋዴዎችም ‘አህያህን ካልሸጥክልን’ ብለው አስቸግረውኝ ነበር። እኔም አልሰማ ሲሉኝ ጊዜ ተበሳጭቼ አህያዬ የሚሸጥ አለመሆኑን ነገርኳቸው።» ሚስቱም ቀና ብላ አይታው ምንም ሳትሰማው እንዲህ አለችው «እንግዲያውማ ልትፈታኝ ከወሰንክ አንድም ቀን ካንተ ጋር ማደር ስለማልፈልግ ወደ ቤተሰቦቼ እሄዳለሁ።»
ትታውም ልትሄድ ዕቃዎቿን እየሰበሰበች እያለች ልጃቸው ወደ ቤት ስትገባ ሚስትየው ልጃቸውን ቀና ብላ እየተመለከተች እና በንዴት እየተንተከተከች «ይገርምሻል! ከእነዚያ ብዙ የትዳር አመታት በኋላ አባትሽ ሂጂልኝ! አልፈልግሽም! አለኝ እኮ» አለቻት።
ልጅቷም እናቷ ያለቻትን ሳትሰማ የሃፍረት ፈገግታ አሳይታ እና እየተኮረመመች እናቷን እና አባቷን ቀና ብላ እያየች እንግዲህ «እናንተ ወላጆቼ ናችሁ። ልትድሩኝ ከፈለጋችሁ በሃሳባችሁ እስማማለሁ።» አለቻቸው ይባላል። የዚህ ተረት መልዕክትም ሰው የሚሰማው መስማት የሚፈልገውን ነገር ብቻ እንደሆነ ያሳየናል። ይህ ደግሞ አሁን ላይ የሰፈራችን እና የእድራችንን ህልውና በግልጽ እየተፈታተነ ያለው ክፉ መንፈስ ነው።
ይልቃል አዲሴ ቀጠለ …
ተረት ሁለት …መደማመጥ እና መግባባት
በድሮ ጊዜ በመነጋገር አይደለም በጥቅሻ የሚግባቡ ባል እና ሚስት ነበሩ። ከዕለታት አንድቀን ባል እና ሚስት የድኩላ ስጋ ያምራቸዋል። ድኩላ ለማጥመድም ከቤታቸው በትንሽ ኪሎ ርቀት ወደሚገኝ ጫካ ያመራሉ። ጫካው ላይ እንደደረሱም የድኩላ ወጥመድም ያጠምዳሉ። በበነጋታው አቶ ባል ወጥመዱን ወደ አጠመዱበት ጫካ ሲሄድ ያጠመዱት ወጥመድ ድኩላ ይዞ ያገኘዋል። አቶ ባልም በሆነው ነገር ተደስቶ ሚስቱን ይጠራታል። ሚስትም የባሏን ጥሪ ሰምታ አቤት ትለዋለች። አቶ ባልም ያጠመድነው ወጥመድ ድኩላ ይዟል ብሎ በግልጽ ቢነግራት የሰፈራቸው ሰዎች ከድኩላው ስጋ አካፍሉን ሊላቸው ሆነ። አቶ ባልም አንድ ዘዴ በመዘየድ ከቤታቸው በርቀት ከሚገኘው ጫካ ውስጥ ሆኖ ሚስቱን ምን ቢላት ጥሩነው .. እንትን ባልንበት እንትን ገባበት። እንትን አምጭልኝ፤ እንትን እልበት። አንችም ነይልኝ እንትን ትይልኝ ይላታል። ሚስትም እንትን ባልንበት እንትን ገባበት የሚለው ንግግር ባጠመድነው ወጥመድ ድኩላ ተይዟል። እንትን አምጭልኝ እንትን እንልበት ሲላትም፤ ቢለዋ አምጭልኝ ቆዳውን የምገፍበት እና ስጋውን የምበልትበት መሆኑን እና አንችም ነይልኝ እንትን ትይልኝ ሲል ደግሞ ቆዳውን ስገፍ እና ስጋውን ስበለት እርዳታሽ ያስፈልግኛል መሆኑ ገብቷት በፍጥነት ወደጫካው ቢላዋ ይዛለት ተፈተለከች።
በዚህም ድኩላውን ያለማንም ተቀናቃኝ አርደው ስጋውን ወደ ቤታቸው መውሰድ ቻሉ ይባላል። ምን አለበት እኛም እንደዚህ በጥቅሻ መግባባት ቢያቅተን እንኳን በደንብ ተነጋግረን ስለምን መግባባት ብንችል።
ከጥቂት አመታት በፊት አሜሪካ እና መሰል የሰፈራችን እና የእድራችን ታሪካዊ ጠላቶች እንትን ባልንበት እንትን ገባበት እንትን አንምጭልኝ እንትን እልበት ዓይነት ዘዴን ተከትለው በራሳችን ሰፈር እና እድር ውስጥ የሚገኙ የነዋይ ሴሰኞችን ተጠቅመው በምስጢር እና በጥቅሻ ሰፈራችንን እና እድራችንን ለማጥፋት ይጥሩ ነበር። አሜሪካ እና መሰል የሰፈራችን እና የእድራችን ታሪካዊ ጠላቶች ሆኑ የእነሱ አሽከር የነበሩት በሰፈራችን እና በእድራችን የሚገኙ የነዋይ ሴሰኞች የሚያደርጉት አኩይ ተግባር እንዳይጋለጥ በመስጋት እያንዳንዱን የጥፋት እርምጃቸውን በጥንቃቄ ይከውኑ ነበር።
አሁን አሁን ግን እያየለ መምጣቱን እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅመው የሰፈራችንን እና የእድራችንን ሰዎች ከመጤፍ ባለመቁጠር እንደፈለጉ ይፈነጩበት ይዘዋል። አሁን ላይ በሰፈራችን እና በእድራችን ያለው አለመደማመጥ ዋናው መነሻ ደግሞ አሜሪካ እና በገንዘብ የገዛቻቸው የነዋይ ሴሰኞች ሃይማኖትን፣ ጎሳን፣ ፖለቲካን፣ ንግድን ወዘተ መሠረት አድርገው የፈጠሩት የቁስል ሽንቁር ማመርቀዙ ነው ።
በእኛ አለመደማመጥ እና መጣላት ታሪካዊ ጠላቶቻችን ብዙ ያተርፋሉ። በነገራችን ላይ በእኛ አለመደማመጥ እነሱ የሚከስሩ ቢሆን ኖሮ አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በባሌም በቦሌም ብለው እንድንስማማ ያደርጉን ነበር።
ሮበርት ሙጋቤ እንደተናገሩት የሚወሳ አንድ አባባል አለ… «ሴቶች በሙሉ የኤድስ መድኃኒት እስኪገኝ ድረስ የግብረ ስጋ ግንኙነት (Sex) አንፈጽምም ብለው ቢያምጹ ኖሮ ወንዶች በ30 ቀናት ውስጥ መድኃኒቱን ባገኙት ነበር።» ይህንን አባባል ወደ ሰፈራችን እና እድራችን ነባራዊ ሁኔታ አምጥተን ተግባራዊ ብናደርገው ሰፈራችንን እና እድራችንን ከጥፋት የምንታደገው ይመስለኛል። እንዴት አትሉም? እየውላችሁ የሰፈራችን እና የእድራችን ሰዎች የሃይማኖትን፣ የጎሳን፣ የፖለቲካ..ወዘተ የአመለካከት ልዩነቶችን አቻችለው መደማመጥ ቢጀምሩ እና አንድነታቸውን ቢያጠናክሩ ኖሮ አንደኛ በሰፈራችን እና በእድራችን ውስጥ የሚገኙ የአሜሪካ ቅጥረኛ የነዋይ ሴሰኛ ባንዳዎችን ልክ ማስገባት ይቻል ነበር። ሁለተኛ አሜሪካ እና ታሪካዊ ጠላቶቻችን ቢያንስ ቢያንስ የሰፈራችንን እና የእድራችንን ነዋሪዎች እንደሰው የሚሰጡት ክብር ይኖር ነበር።
ዳሩ ምን ዋጋ አለው ! የእኛ ሰፈር ሰዎች አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ጠላቶቻችን የሚናገሯትን እያንዳንዷን አባባል እንደ ቅዱስ መጽሐፍት ቃላቶች ወስደው የሚያስተጋቡ እና በተግባር ላይ የሚያውሉ ሃይላት በሰፈራችን እና በእድራችን ሰዎች እንደ አዋቂ ይቆጠራሉ። እነኝህ አላዋቂዎችም ራሳቸውን እንደ አዋቂ ቆጥረው ይኮፈሳሉ። እኛ ካልነው ውጪ ማንንም አንሰማም ይላሉ። ይህ አካሄድ ጠላቶቻችን እኛን ለማጥፋት አንገታችን ውስጥ ያጠለቁትን የጥፋት ገመድ ሸምቀቆ በገዛ እጃችን እንደመሳብ ነው። ይህን ስል በአመክንዮ እንጂ እንዲሁ በግብዝነት ስላለመሆኑ በአንድ ሮበርት ሙጋቤ አባባል ላሳያችሁ።
«ዓለም አፍሪካን በድላታለች… ከአውሮፓ አንድ ነጭ ወደ አፍሪካ ከመጣ የውጭ ዜጋ ጎብኚ ይባላል። ከአፍሪካ አንድ አፍሪካዊ ወደ አውሮፓ ከሄደ ግን ሕገ ወጥ ስደተኛ ይባላል። በቡድን ነጮች ወደ አፍሪካ ከመጡ ቱሪስት ይባላሉ። በብዛት አፍሪካውያን ወደ አውሮፓ ከሄዱ ደግሞ ስደተኞች ይባለሉ። ነጮች አፍሪካ ውስጥ መጥተው የአፍሪካውያን አሠሪ ይሆናሉ። አፍሪካውያን አውሮፓ ሄደውም የነጮች ሠራተኛ ነው የሚሆኑት» ይህን አስተሳሰብ እኛም ከነጮች ተቀብለን የማብራሪያ መዓት እናዥጎደጉዳለን። እንደምሁርም ስንቆጠርበት ይታያል። ከዚህ በላይ ነጮች ባጠመዱት ወጥመድ ገብቶ መበላት ከየት ይመጣል።
ኧረ ጎበዝ ! አሜሪካ እና መሰል የሰፈራችን እና የእድራችን ታሪካዊ ጠላቶች ተባልተን ሳንጠፋ አሁኑኑ እንደማመጥ። አለበለዚያ ሰፈራችን እና እድራችን «ወደ ነበረበት» መቀየሩ የማይቀር ነው። ብሎ ንግግሩን ሳይጨርስ አብሿሙ ክንፈ ጉደታ፤ ይልቃል አዲሴ እንዲመልስለት የፈለገው ጥያቄ ስለነበረው ጥያቄውን ለመጠየቅ እጁን በማውጣት ንግግሩን አቋረጠው።
የአብሿሙን ክንፈ ጉደታ ጥያቄ እና የይልቃል አዲሴን መልስ በሚቀጥለው ዝግጅታችን ይዘን እንቀርባለን እስከዚያው አለመደማመጥ ከወለዳቸው የጥፋት ጋሬጣ ይጠብቀን። ሰላም!!!
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ግንቦት 18 ቀን 2014 ዓ.ም