የዓለም የቅርስ ቀን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) አማካኝነት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሚያዚያ 18 በየዓመቱ ይከበራል። ይህ በዓል በዘመናት ሂደት ውስጥ የሰው ልጅ ያሳረፈውን የስልጣኔ አሻራና ሃብት ለመጠበቅ፣ ለማልማትና ለማስተዋወቅ ከመዋሉም በላይ ለትውልድ ለማስተላለፍና ለሃብቶቹ የሚሰጠውን ክብር ከፍ ለማድረግ ልዩ አጋጣሚን እንደሚፈጥር ይታመንበታል። በተለይ የቀደሙት ትውልዶች አኗኗር፣ ስልጣኔና እውቀት ምን ይመስል እንደነበር ምስክር የሚሆኑ ቁሳዊና ባህላዊ ሃብቶችን ለማስተዋወቅ ቀኑ ከወትሮው በተለየ አስፈላጊ ይሆናል።
ኢትዮጵያ በዓለም ስልጣኔ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ካበረከቱ አገራት ተርታ በቀዳሚነት ትጠቀሳለች። የባህል፣ የታሪክ፣ የአገረ መንግስት ምስረታና የጥንታዊ ስልጣኔ ምስክር የሆኑ አስደናቂ ቅርሶች፣ ሙዚየሞችና ልዩ ልዩ ታሪካዊ ሃብቶች መገኛም ጭምር ነች። በዚህ ምክንያት አርኪዮሎጂስቶች፣ ጎብኚዎችና በቱሪዝም፣ ጥናትና ምርምር ዘርፍ ላይ ፍላጎት ያላቸው ቡድኖችና ግለሰቦች በልዩ ሁኔታ ትኩረት ያደርጉባታል። ይሁን እንጂ የጥንታዊ ስልጣኔና ጥንታዊ ሃብቶች መገኛነቷን ያህል በመላው ዓለም ሃብቶቹን ለማስተዋወቅ፣ ለማልማትና ከዚያም የሚገኘውን ምጣኔ ሃብት በሚፈለገው መጠን ተጠቃሚ ስትሆን አይታይም።
ለዚህ እንደ ችግር ተደርጎ የሚወሰደው ቀደም ባሉት ጊዜያት መንግስት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ በስፋት ያለመስራትና ጠቀሜታውን ያለማጉላት ነበር። ከዚያም ባለፈ የባህል፣ የታሪክና የስልጣኔ ምስክር ተደርገው የሚጠቀሱ በመላው አገሪቱ የሚገኙ ሃብቶችን በእውቀትና በልዩ ጥንቃቄ የመምራት ችግር እንደነበርም ይታመናል።
አሁን በስልጣን ላይ ያለው አዲስ መንግስት ችግሩን ተገንዝቦ የቱሪዝም ዘርፉን በልዩ ትኩረት እና ጥንቃቄ ለመምራት ወስኖ እየሰራ ነው። ከአምስቱ ዋና ዋና ዘርፎች መካከል አንደኛው እንዳደረገውና የታሪክ፣ የባህል፣ የቅርስ ጉዳዮችን የሚጠቀልለው ቱሪዝም በሁሉም አቅጣጫ እምርታ እንዲያሳይ የአደረጃጀት ለውጥ ማድረጉን አሳውቆ መስራት ውስጥ ከገባ ወራት ተቆጥረዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ለዘመናት ተጠብቀው የቆዩት ቅርሶችን ከሚያስተዳድረው፣ ከሚጠብቀውና ከሚያለማው የቱሪዝም ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናት ጥበቃ ባለስልጣን ነው። ይህ መስሪያ ቤት በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በሚዳሰስ (ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀስ) እንዲሁም በማይዳሰሱ የባህልና የመንፈሳዊ ቅርሶች ዙሪያ ያሉ ማናቸውንም ቅርሶች ጠብቆ ለትውልድ የማሻገር ኃላፊነት አለበት። ከዚያ ባለፈ በመላው ዓለም እንዲታወቁና የቱሪስት መስህብ ከመሆን አልፈው ለአገር የምጣኔ ሃብት የጀርባ አጥንት እንዲሆኑ ኃላፊነት የተሰጠው መስሪያ ቤት እንደሆነ ይታወቃል።
ከእነዚህ ተግባርና ግዴታዎቹ መካከል ቀዳሚ የሆነው ዜጎችም ሆኑ ዓለም አቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ ውስጥ ስላሉ የማይዳሰሱና የሚዳሰሱ ቅርሶች የማስተዋወቅ፣ ግንዛቤ የመፍጠርና ሁሉም ጥበቃ እንዲያደርጉለት የማድረግ ኃላፊነት ለመወጣት የተለያዩ ስልቶችን ነድፎ እየሰራ መሆኑን መስሪያ ቤቱ አስታውቋል።
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ለዝግጅት ክፍላችን ባደረሱን መረጃ መሰረት ይህንን ግብ ለማሳካት በልዩ ሁኔታ ለመጀመሪያ ጊዜ “የቅርስ ቀን” በአገር አቀፍ ደረጃ ማክበር ይጀመራል። የሚከበርበት ቁርጥ ቀን ይፋ ባይደረግም ይህ ሁነት በይፋ በየአመቱ ሲከበር በኢትዮጵያ ለሚገኙ ቅርሶች ልዩ ትኩረት ለመስጠትና ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው እንዲጎላ ለማድረግ ሰፊ እድል የሚፈጥር እንደሆነ ይናገራሉ።
“ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የቅርስ ቀንን በግንዛቤ ፈጠራና በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ታከብራለች” ያሉት የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር፤ እስካሁን ሲከበር የቆየው የሙዚየም ቀን ተብሎ እንደነበር ይናገራሉ። ኢትዮጵያ በአይነትም በርካታ የቅርስ ሀብት ያላት በመሆኑና የቅርስ ቀንን ማክበር ስላለባት ቀኑን ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነም ይገልጻሉ። አገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገቡ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት እንደመሆኗ፤ የቅርስ ቀኑን ከማክበር ባሻገር ቅርሶች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የሚኖረው ማህበረሰብ የቅርሶችን ደህንነት እንዲጠበቅ የሚያስችል የግንዛቤ ፈጠራ በመስራት በተለያዩ የንቅናቄ መርሃ ግብሮች እንደሚከበር ነው ያስታወቁት።
በዓለም ላይ ያሉ በቅርስነት የተመዘገቡ ኃብቶች በተገቢው መልኩ የሚተዋወቁት አገራት በሚገነቧቸው ጠንካራ የግንኙነት መስመሮች እንደሆነ ይታወቃል። በዚህ በኩል የመገናኛ ብዙሃንና የፕሮሞሽን ተቋማት ለዚህ ትልቁን ድርሻ ይጫወታሉ። ይህን መስመር ተከትለው በእያንዳንዳችን ደጃፍ የሚደርሱት የማስተዋወቅና የመስህብ ስፍራነታቸውን ተደራሽ የማድረግ ስራዎች አብዛኛውን ጊዜ ስኬታማ ይሆናሉ። ከሁሉም አቅጣጫ ጎብኚዎች ወደ እነዚህ የስልጣኔ ምልክቶችና የዓለም ቅርሶች በመትመም የታሪኩ አካል ይሆናሉ። አገራቱም ይህን መሰረት አድርገው ጠንካራ የኢኮኖሚ አቅም ይፈጥራሉ።
ቀኑን ለማክበር በባለስልጣኑ በኩል በዩኔስኮ የተመዘገቡ ቅርሶች የተመዘገቡበትን ቀን በመለየት የግንዛቤ ፈጠራ ለመስራት የኮሙዩኒኬሽን ስትራቴጂ ተነድፎ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ይፋ አድርጓል። ባለስልጣኑ እስካሁን ደካማ የሆነ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ እንደነበረው የሚናገሩት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፤ ጠንካራ ኮሙዩኒኬሽን እንዲኖር ለማድረግ በአዲስ መልክ ለማደራጀት ስትራቴጂ ተነድፎ ምክክር እየተደረገበት እንደሆነም ያስረዳሉ።
የቅርስ ቀንን እንደማንኛውም አገር ማክበር ሳይሆን ግንዛቤ ለመፍጠር ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ በመሆኑ ግንዛቤ የሚፈጥሩ መልዕክቶች ተዘጋጅተው እንዲተላለፉ በማድረግ ቀኑ ይከበራል። አሁን ባለው ሁኔታም በርካታ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ከቦታቸው የተወሰዱና የጠፉ በመሆናቸው የሚመለከታቸው አካላት ክትትል እንዲያደርጉ የሚያስችል ሥራ እንደሚሰራ ምክትል ዳይሬክተሩ ለዝግጅት ክፍላችን አሳውቀዋል።
“በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ዙሪያ ወቅቱን የመጠነ የኮሙዩኒኬሽን ስትራቴጂ መኖር መቻል አለበት” የሚሉት ምክትል ዋና ዳሬክተሩ፤ በቅርስ ውድመትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ አልፎ አልፎ የተሳሳቱና የተዛቡ ግንዛቤዎች በማህበራዊ ሚዲያ እንደሚሰራጩ ነው የሚናገሩት። እነዚህን ማስተካከልና ትክክለኛ መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግ ባለስልጣኑ ጠንካራ ኮሙዩኒኬሽን ስትራቴጂ እንዲኖር እየሰራ መሆኑንም ያመለክታሉ።
ዩኔስኮ ቅርሶችን ከመጠበቅ አንጻር አንድ ባለድርሻ አካል ቢሆንም ዋናው ባለቤት የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ የተመዘገበውን ቅርስ የመጠበቅና የመንከባከብ ግዴታ እንዳለም ያስገነዝባሉ። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን ያስመዘገበች አገር እንደመሆኗ ለቅርሶቿ ደህንነት ቅድሚያ እንዲሰጥ እየተሰራ እንደሚገኝም ይናገራሉ።
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ነች። ከ3 ሚሊዮን ዓመታት በላይ እድሜ ያስቆጠረው፤ “የሉሲ” ወይም ድንቅነሽ ቅሪተ አካል እንዲሁም የአረቢካ ቡና ዝርያ መገኛም ነች። የዓለማችን ረጅሙ ወንዝ ጥቁር አባይም መነሻም ኢትዮጵያ ነው። የኤርታአሌ የእሳተ ገሞራ ሀይቅና የዓለማችን እጅግ ረባዳና ሞቃት ስፍራ ዳሎልም የሚገኙት በኢትዮጵያ ነው።
እነዚህ ብቻ አይደሉም። ኢትዮጵያ የንግስት ሳባ አገር ነች፣ የሙሴ ፅላትም/ ጽላተ ሙሴ/ የሚገኘውም በኢትዮጵያ ነው፤ በአክሱም ፅዮን ቤተክርስቲያን። ከእነዚህ ሌላ ለመዝናናት አመቺ የሆኑ በርካታ የስምጥ ሸለቆ ሃይቆችና ፍል ውኃዎች፣ እንዲሁም የዱር እንስሳት ፓርኮችና መጠበቂያዎች ይገኛሉ።
እንግዲህ፤ ኢትዮጵያ በርካታ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ፤ ሰው ሰራሽና ባህላዊ ቅርሶችን በዩኔስኮ በማስመዝገብ በአፍሪካ ቀዳሚዋ አገር ለመሆን በቅታለች። በተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች የበለፀገች፤ አያሌ የቱሪስት መስህብ ያላት ናት። እነዚህንም ቅርሶችን በዩኔስኮ መዝገብ በብዛት በማስመዝገብ ከአፍሪካ አገራት ቀዳሚዋ ብትሆንም የአገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ ግን የሚፈለገውን ያህል ወይም የሚገባውን ያህል አላደገም።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መንግስት የቱሪዝም ዘርፉ የኢትዮጵያ የጀርባ አጥንት እንደሆነ በማመን ልዩ ትኩረት መስጠቱን አስታውቋል። በተግባር ሰፋፊ ልማቶችን፣ ፕሮጀክቶችን እያከናወነ መሆኑን የሚያመላክቱ መረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል። ታዲያ ይሄን መልካም አጋጣሚ መጠቀም ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። በተለይ በግሉ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች በቱሪዝም ሆስፒታሊቲ ዘርፍ፣ በፕሮሞሽንና የገበያ ልማት ብሎም በአስጎብኚ ድርጅቶች ውስጥ በቀጥታ ሊሳተፉ ይገባል። የዚህ ድምር ውጤት ደግሞ “ምድረ ቀደምት” አገራችንን ለመላው ዓለም ከፍ አድርጎ ማስተዋወቅ እንዲቻል ከማድረጉም ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ትርፉ ለአገር እድገት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ጥርጥር አይኖረውም።
ባለስልጣኑ በቅርብ ጊዜ ውስጥ “የኢትዮጵያ የቅርስ ቀን” በሚል በተለያዩ መርሃ ግብሮች ለማክበር ማሰቡ ደግሞ ተጨማሪ መነቃቃትን እንደሚሆን ይጠበቃል። በተለይ የቱሪዝም መስህብ የሆኑ ስፍራዎችን በልዩ ሁኔታ ለማስተዋወቅና ህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲይዝባቸው ለማድረግ ይረዳል።
በዋናነት ግን ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ሃብቶች ከሚገኝ ምጣኔ ሃብት ተጠቃሚ የምትሆንበት እድል እንዲጨምር በልዩ ሁኔታ የሚከበሩ ቀኖች ፋይዳቸው ከፍተኛ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ከኢትዮጵያ ያነሰ የመስህብና የቅርስ ስፍራ ያላቸው አገራት በስፋት ሃብቶቻቸውን ለማስተዋወቅ የተለያዩ ስልቶችን መንደፍ በመቻላቸውና ለተግባራዊነቱም በመስራታቸው የዚህ እድል ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። ይሁን እንጂ “የቅርስ ቀን” ተብሎ ሲከበር ከዚህ ቀደም እንደሚደረገውና የስብሰባና ቲሸርት ህትመት አሊያም ግቡን ከመነሻው ያላወቀ የሁነት ዝግጅት ከሆነ አሁንም የሚፈለገውን ውጤት ሊያመጣ አይችልም። ከላይ የባለስልጣን መስሪያቤቱ “የኮምኒኬሽንና የግንኙነት አወቃቀራችን ደካማ ነበር” በማለት ዳግም ለማዋቀር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ነግሮናል። የማስተካከያ ስራው ሲተገበር የግንኙነት መስመሩን ዓለማቀፋዊ እንዲሆንና በብቁ ባለሙያዎች ሊመራ ይገባል የሚል እምነት አለን።
እንደ መውጫ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም ቅርስነት በተመዘገቡ የኢትዮጵያ መስህቦች ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደቀኑ ችግሮች እንዳሉ ይታመናል። በተለይ በሰሜኑ ክፍል በነበረው ጦርነት፣ አሁንም በተደቀነው ዓለመረጋጋትና ስጋት ምክንያት የላሊበላ፣ አክሱምና መሰል ቅርሶች ለጉዳት ተጋላጭ እየሆኑ ነው። ከዚህ መነሻ መሰል የቱሪዝም ዘርፉንና በውስጡ ያሉትን ሃብቶች የሚዘክሩና ሰፊ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ “የቅርስ ቀንን” የመሰሉ በዓላት ሲከበሩ ጉዳት የተጋረጠባቸው የመስህብ ስፍራዎች በሚመለከተው አካል ትኩረት እንዲያገኙ ለማድረግ አስተዋጽኦ ያበረክታል። ይህንን አጋጣሚ መጠቀምና ሊደርስባቸው የሚችለውን ጉዳት አስቀድሞ መከላከል የሚቻልበትን አጋጣሚም መፍጠር ይቻላል ብለን እናምናለን።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ግንቦት 15 ቀን 2014 ዓ.ም