1983 ዓ.ም በመላው ኢትዮጵያ የመንግስት ለውጥ ታውጇል። ዛሬ እንደትናንትናው አይደለም። ነገሮች ተቀይረዋል። ሁኔታዎች ተለውጠዋል። በደብረዘይት (ቢሾፍቱ) ከተማ በአንዱ ጣራ ስር የቤቱ አባወራ በሞት መነጠል ደግሞ መላውን ቤተሰብ ለድንገቴ ፈተና እያጋፈጠ ነው። ወይዘሮዋ የትዳር አጋራቸውን በሞት እንዳጡ የልጆቻቸው ዕጣ ፈንታ፣ የራሳቸውም ቀጣይ ሕይወት ያሳስባቸው ይዟል።
ወታደሩ አባወራ ለእሳቸው መልካም ባል፣ ለልጆቻቸው ታላቅ አባት ነበሩ። አሁን በዚህ ክፉ ቀን የማለፋቸው እውነት ግራ አጋብቷቸዋል። ለጊዜው ለኑሮ መደጎሚያ፣ ለልጆች ማሳደጊያ አይጠፋም። የቤትን ራስ፣ የጎጆን ዋልታ፣ ከናካቴው ማጣት ግን በእጅጉ ይሰብራል።
ውሎ አድሮ የቤተሰቡ ሀላፊነት በወይዘሮዋ ትከሻ ወደቀ። በወቅቱ አምስቱን ወንዶች ልጆች ያለአባት ማሳደጉ፣ ቤትን፣ጎጆን ያለአጋር ማቅናቱ ቀላል አልነበረም። ይህ ብቻ አይደለም። በወቅቱ ከባንክ ዕዳና ከቤት ሽያጭ ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ችግሮችን አሸንፎ በጽናት መቆም፣ እማወራዋን በእጅጉ ፈተናቸው፣ አንገዳገዳቸው።
አምስተኛው ልጅ…
የአባወራን ሞት ተከትሎ በቤተሰቡ ላይ የተጋረጠው ችግር መላውን ቤተሰብ በፈተነ ጊዜ የትንሹ ልጅ ብርታት ከሌሎች ልቆ መታየት ያዘ። ሌኒን ደምሴ ለቤቱ አምስተኛና የመጨረሻ ልጅ ነው። እሱ ጥቃት ይሉትን አይወድም፤ ለሽንፈት፣ለውድቀት ፈጽሞ እጅ አይሰጥም። ሁሌም ለችግሮች መፍትሄ መጣር፣ መፍጠን መለያው ሆኗል።
ሌኒን ወታደር አባቱን በሞት ካጣ በኋላ ወላጅ እናቱን ለመርዳት ያልሆነው የለም። ቆሎ ይዞ በባቡር መስኮት አዙሯል። ጀብሎ ተሸክሞ ሲጋራ፣ ሶፍትና ማስቲካ ሸጧል። የዛኔ በቤቱ ያገጠመን ፈተና ተጋፍጦ ከእናቱ ጎን ለመቆም የቀደመው አልተገኘም። መኖሪያ ቤታቸውን ጠበቃ አቁሞ፣ በፍርድ ቤት ተከራክሮ አስመልሷል። ቤተሰቡን ለማስተዳደር የልጅነት ጉልበቱን ገብሮ የእናቱ ቀኝ እጅ ሆኗል።
ትናንት ብዙ የለመደ ጎጆ ዛሬ ጎዶሎው ቢበዛ ትንሹ ሌኒን አብሮ እየተከዙ ማዘን ምርጫው አልሆነም። ጊዜ ወስዶ ጥቂት ቆም ብሎ አሰበ። ያለበት ዕድሜ ትምህርት ቤት የሚሄድበት፣ ዕውቀትን በወጉ የሚሸምትበት ነው። ያም ቢሆን እናቱን ማገዝና መደገፍ ግዴታው ሆኗል። በአቅሙ የቤተሰቡን ችግር ለመቅረፍ ደግሞ ካሰበው ቦታ መገኘት ይኖርበታል።
የሌኒን ቤተሰቦች መኖሪያ ደብረዘይት (ቢሾፍቱ) ከተማ ነው። እሱም በዚህ ስፍራ ተወልዶ ከእኩዮቹ ቦርቆ አድጓል። በየቀኑ ከተማውን አልፎ የሚሄደው የመንገደኞች ባቡር ለብዙዎች መተዳደሪያቸው መሆኑን አሳምሮ ያውቃል። ትንሹ ሌኒን እናቱን በተሻለ ለመርዳት የመጀመሪያ ምርጫው የባቡር ላይ ሕይወት ሆነ።
ሌኒንና ባልንጀሮቹ ከአዲስ አበባ ድሬዳዋ የሚያልፈውን ባቡር በመንደራቸው ሲያገኙት በዓይናቸው አይሸኙትም። አሁን ባቡሩ ለእነሱ የዕለት እንጀራቸው ሆኗል። መምጣታቸውን የሚሹ በርካቶች በፍቅር ተሻምተው ይቀበሏቸዋል። ጓደኛሞቹ በየጉዞው ከሚያገኟቸው መንገደኞች ተዛምደውና በጥቅም ተዋውለው የላባቸውን ይቀበላሉ።
የዛኔ የባቡር ላይ ጉዞ በኮንትሮባንድ ንግድ የጦፈ ነበር። አብዛኛው ነጋዴ ለትርፍ፣ ጥቂቱ ደግሞ ለድንገቴ ኪሳራ መጋለጡ ተለምዷል። ይህን የሚያውቁ ተመላላሽ ነጋዴዎች የያዙትን ዕቃ በዘዴ ለሚያሳልፉላቸው ሁሉ መልካም ክፍያን ይሰጣሉ። ሌኒንና ባልንጀሮቹም ይህ አይነቱን ስራ ቋሚ መተዳደሪያ አድርገዋል። በየኬላው በሚደራርቡት የልብስ ቁጥር አንድ ብር እየታሰበ ይከፈላቸዋል።
እነ ሌኒን ከመንገደኞች ተቀላቅለው ድሬዳዋ ደርሶ ለመመለስ ለወንበር መክፈል አይጠበቅባቸውም።፡ ለእነሱ የባቡሩ ፉርጎና ጣራዎቸ ከመቀመጫ በላይ ናቸው። እንዳሻቸው እየወጡ እየወረዱ ይጓዙባቸዋል። ሌኒን በዚህ መልኩ የሚያገኘውን ገንዘብ ፈጽሞ አያባክንም። ለቁም ነገር አውሎ፣ ለእናቱ ቆጥሮ፣ ቋጥሮ ያስረክባል። እናት በገንዘቡ ጎዶሎውን ሞልተው ከልብ ያመሰግኑታል፣ ይመርቁታል።
ግራጋዶስ ሌላው መንገድ …
ሌኒን በየባቡሩ ጉዞ የሚያገኘውን ገቢ በሌላ አማራጭ መተካት ፈለገ። በወቅቱ ለዚህ ፍላጎቱ የተገኘለት ምላሽ ከአዲስ አበባ ሀዋሳ የሚሰራው የመንገድ ግንባታ ሆነ። በ1991 ዓ.ም ግራጋዶስና ጠንካራው ሌኒን ደብረዘይት ላይ ሲገናኙ አብረው ለመዝለቅ ጊዜ አልፈጁም። አብረው በስራ ተጣመሩ።
አንድ ቀን አንድ ጓደኛው ከስራ ቦታው ዘልቆ ውሎውን አስተዋለ። አማራጭ እያለው ሲሚንቶ ሲያቦን መዋሉ አልተመቸውም። ሀሳቡን የተቀበለው ሌኒን ዕለቱን ሥራ ለማቋም አላቅማማም። ግራጋዶስን ተሰናብቶ የባቡር ላይ ስራውን ሊቀጥል ወሰነ።
እነ ሌኒን በባቡር ጉዞ የጀመሩትን የንግድ ስራ ማሳደግ ፈልገው አዲስ ዕቅድ ነደፉ። ለውጥ ፈላጊ ባልንጀሮቹ ‹‹ለሌሎች መስራቱ ይብቃን›› አሉና ነጋዴ መሆን ተመኙ። ሀሳባቸው በምኞት አልቀረም። በቂ ገንዘብ ይዘው ንግዱን ጀመሩት። ሌኒን በልጅነቱ የወጠነውን ጉዞ ዳር ለማድረሰ ለተከታዩ እርምጃ ተዘጋጀ። ከዚህ በኋላ ከመንገዱ፣ የሚመልሰው፣ ከሀሳቡ የሚያደናቅፈው አይኖርም። ራሱን ለውጦ የእናቱን ሕይወት ይቀይራል። ዛሬን አሸንፎ ለነገው ታሪክ ይተጋል።
ሌኒን ለራሱ የንግድ ስራ በመጀመሪያው ቀን ከባቡሩ በተገኘ ጊዜ ስለወደፊቱ አሻግሮ አሰበ። አሁን ጥሩ ዕቃዎች ይዞ በደህና ትርፍ ይመለሳል። ትርፉን አስቀምጦም ለተሻለ ነገ ይዘጋጃል። እሱና ባልንጀሮቹ መንገዳቸውን ቀጠሉ። ለስራው እንጂ ለእንዲህ አይነቱ መንገድ አዲስ አይደሉም።
በመጀመሪያው ቀን የመጀመሪያው ስራ
‹‹ቢኬ›› ከተባለ የኮንትሮባንድ ቦታ ቦንዳ ጨርቅ የገዙት እነሌኒን የያዙትን ዕቃ ያለስጋት ማሻገር አለባቸው። አዋሽ ወርደው ሜኤሶን እንዳለፉ ግን የሚጠብቁት ባቡር እንዳመለጣቸው አወቁ። ዕቃውን ወደ መተሀራ በመኪና አሳልፈው ቀጣዩን ባቡር መጠበቅ ያዙ። ሳይዘገይ በሰዓቱ ደረሰ።
በነጻነት ከባቡሩ አናት መቀመጥ የለመዱት ባልንጀሮች እንደልማደቸው ሆነው ጉዞ ጀመሩ። ባቡሩ ረጅሙን መንገድ በሀዲዱ እያዘገመ፣ ከሩቁ ድምጹን እያሰማ ወደ ወለንጪቲ ጣቢያ ተጠጋ። ሌኒን ስፍራው ላይ ሲደርሰ ከባቡሩ ዘሎ ለመውረድ ተዘጋጀ። ይህ አይነቱ ልምድ ለእሱ አዲስ አይደለም። የዛሬው ጉዞ ግን ራሱን ችሎ ንግዱን የጀመረበት የመጀመሪያ ቀኑ ነው። ንብረቱን እያሰበ፣ ነገውን እያለመ፣ ከባቡሩ እመር ብሎ ዘለለ። ሌኒን እንዳሰበው አልሆነም። እግሮቹ መንገዳቸውን ስተው ወደፊት ተሸንራተቱ። ድንገቴው ማዳለጥ ከመሬቱ አስቀድሞ ከሀዲዱ መሀል አሳረፈው። በመጣበት መስመር የሚሽከረከረው ባቡር አልማረውም ። በፍጥነት ቀኝ እግሩን ረግጦ፣ ገጭቶት አለፈ።
ሀዲዱ ላይ የወደቀው ሌኒን ጥርሱን ነክሶ ስቃዩን ችሎ እየተሳበ ወጣ። በርካቶች ሊረዱት፣ ሊያነሱት ተረባረቡ። ክፉኛ የተጎዳው ቀኝ እግሩ ሊያዩት ያሰፈራል። ከሰዓታት በኋላ ሌኒን ራሱን ናዝሬት ሀይለማርያም ማሞ ሆስፒታል አገኘው። ትናንት ሲሮጥበት የነበረው እግሩ ዛሬ ታሪኩ ተቀይሯል። አብሮት የቆየው አዲስ ተስፋ ከጎኑ ርቋል። ደጋግሞ እናቱን አሰበ፣ ራሱን ተመለከተ። ድብልቅልቅ ያለ ስሜት ከበበው።
ከዓመታት በኋላ…
ሌኒን ደምሴን ሳገኘው በአጋጣሚ ነበር። ቁመተ ረጅም፣ መለሎ ይሉት ሎጋ ነው። በአንድ እጁ የያዘው ክራንች ከጉልበቱ ከፍ ብሎ ለተቆረጠው ቀኝ እግሩ አጋዥ ሆኖታል። ከሚያሽከረክራት ዘመናዊ መኪና ወርዶ ሰላምታ አቀረበልኝ። ለጨዋታ አይከብድም። ጥቂት አውርተን በቀላሉ ተግባባን። ቅልጥፍናው፣ በራስ መተማመኑ እያስገረመኝ ነው።
አካል ጉዳተኝነቱን ያዩ አንዳንዶቸ መኪናውን አቁሞ ሲወርድ በአድናቆት ሲቃኙት አስተዋልኩ። በውስጣቸው ‹‹እንዲህም አለ ለካ›› የሚሉ ይመስላል። ቦታ ይዘን አሁን ስላለበት ሕይወትና ኑሮ፣ እንዲያጫውተኝ ጋበዝኩት። አልደበቀኝም።
ሌኒን ደምሴ ዛሬ ትልቅ ሰው ሆኗል። ከዓመታት በፊት ቀኝ እግሩን በአደጋው እንዳጣ በአስቸጋሪ መንገዶችን ተሻግሯል። የዛኔ አብዛኞች ሱቅ ተቀምጦ እንዲውል ይመኙለት ነበር። ከእኩለ ሌሊት በኋላ ዓይኖቹ የማይከደኑት ብርቱ ግን ሰፊ ዕቅድ እየነደፈ ከራሱ ሲመክር ያድራል። ሌኒን አሁንም ብርታቱ አልተለየውም። ዛሬም ስለነገው ያስባል። እግሩን እንጂ ወኔውን እንዳላጣ ደጋግሞ ለራሱ ይነግረዋል።
የመጀመሪያ ስራውን በኤልፎራ ቄራ ላይ ወጠነ። ፈጥኖ ለመድረሰ በአንድ እግሩ ብስክሌት እየነዳ ይጓዛል። ለድመቶች ሳንባ እየወሰደ ይሸጣል። አጋጣሚው ጨጓራ እየገዙ ከሚሸጡ ሰዎች አገናኘው። ከእነሱ ተግባብቶ ሊሰራላቸው ተስማማ። ሙያውን ሲለምደው ገበያው ደራለት። ደንበኞቹ ሲበራከቱ ጨጓራ ማከፋፈሉን ገፋበት። የድመቶቹን ሳንባ ጨምሮ ለውሾች የተፈጨ ቀንድና አጥንት መሸጡ አዋጣው። በየቤቱ ያሉ ውሻና ድመቶች ፉጨቱን ለምደው እጁን ናፈቁ።
ሌኒን ገቢው ሲጨምር ስለነገ ማንነቱ ማሰቡን ቀጠለ። በቂ ገንዘብ ይዞ የዕቃ ባጃጅ በዘጠኝ ሺህ ብር ገዛ፣ ከቀኝ መሪ ወደ ግራ አቅጣጫ አዙሮ ከሁለት አመት በላይ ሰራበትና በሀያ ስድስት ሺህ ብር ሸጠው። በገንዘቡ ሌላ ባጃጅ ገዝቶም መንገደኞችን ያመላልስ ያዘ። በዓመቱ ባጃጁን በትርፍ ሸጦ ሌላ እየተካና እየሸጠ በቂ ገንዘብ ያዘ። ይህ አይነቱ መንገድ የታክሲ መሪን ሲያስጨብጠው አልዘገየም። ታክሲውን እያሸከረከረ ሌሎች ስራዎችን ዳሰሰ። ጣራ ላይ ዲሽ በመግጠም ሙያ ዝና ማትረፉን ተከትሎ እጁን የሚሹ ደንበኞቹ በረከቱ። የዲሽ ገጠማው በተሻለ ገቢ ወደ ለውጥ ጎዳና አንደረደረው። ታክሲውን ለሾፌር ሰጥቶ በሙያው ገፋበት። ጥረቱ በዚህ አልተቋጨም። በየጊዜው የታክሲዎቹን ሞዴል ቀያየረ። ስኬት ከጉኑ ቆማ አብራው ተጓዘች።
ከጥቂት ጊዚያት በኋላ ሌኒን በአይሱዙ ጋቢና ተቀምጦ ያዩ እጃቸውን በአፋቸው ጫኑ። ‹‹ለካ !እንዲህም ይኖራል›› ያሉ በርካቶች ስለማንነቱ እያወጉ በበጎ ተምሳሌት ሰየሙት። ጠንካራው ሾፌር በአይሱዙው ከፍ ያለ ጭነት አስሮ መቀሌ፣ ጅግጅጋ፣ ሀረር ተጓዘ። ጥቂት ቆይቶ በተሻሉ ሞዴሎች መኪኖቹን ቀያየረ። እንዲህ በሆነ ቁጥር የገቢ መጠኑ ጨመረ፣ የኑሮ መልኩ ተለወጠ።
አሁንም ቆም ብሎ ያስባል። በእጁ ያለውን መኪና ሸጦ የተሻለ ከባድ መኪና መግዛት ፈልጓል። ያሰበው አልቀረም። የዕቅዱን አሳክቶ ባለ አስር ጎማ ‹‹ካሶኒ›› የጭነት መኪናን ከእጁ አስገባ። ጠንካራው ሰው እንደሱ ብርቱ ለሆኑት ሁሉ ልቡ ቅርብ ነው። እጅ ያጠራቸውን እያገዘ ከፍላጎታቸው ያገናኛል። መማር ያለባቸውን ቀርቦ ያበረታል። ከእሱ ሆነው በሙያቸው ያደጉ ታታሪዎች ዛሬ ስለነጋቸው መሰረት ጥለዋል። እሱም ይህን በማድረጉ ደስተኛ ነው።
ሌኒን በውጣ ውረድ ዋጋ ለከፈለበት ንብረቱ የሚሰጠው ግምት የተለየ ነው። መኪኖቹን ለሌሎች አሳልፎ ከመስጠት በጥንቃቄ መያዝን ይመርጣል። ንብረቶቹ ትናንት ላለፈበት ፈታኝ መንገድ ማሳያዎች ናቸው። እሱን ከልመና በዘለለ ለማያስቡት አንዳንዶችም ምስክር ሆነውታል። ንብረቱ አካሉ ከተጎዳ፣ በኋላ የተገኘ ነው። ይህ እውነታ እሱን ለመሰሉ ወገኖች ብርታትና ጥንካሬ ሆኗል።
አንዳንዴ አንዳንዶች የሌኒንን ችሎታና ለውጥ አምነው መቀበል ይሳናቸዋል። ቀረብ ብለው ካዩት በኋላ ባለው አቋም መኪና ማሽከርከሩን አይቀበሉትም። እንዲህ አይነቶቹ ከአድናቆት ይልቅ ወቀሳ ይቀናቸዋል። ሌኒን በአንድ ወቅት ለህግ አካላት ጠቁመው የከሰሱትን ሰዎች ድርጊት አይረሳም። በአጋጣሚው ግን አልተከፋም። ከሳሾቹን በበጎነት አስተምሮ መልሷል። ጠንካራው ሾፌር በመንገዱ ላይ ብዙዎችን ለመርዳት የፈጠነ ነው። ችሎታና ልምድ አንሷቸው ግራ ለሚጋቡና መንገድ ለሚስቱ የከባድ መኪና ሾፌሮች መፍትሄያቸው ነው። ከመኪናው ወርዶ መሪያቸውን ይገራል። የጉዞ አቅጣጫን አመላክቶ አረጋግቶ ይሸኛል።
እሱ ለዓመታት የተጓዘባቸውን መስመሮች አሳምሮ ያውቃቸዋል። ኩርባ ቁልቁለቱ፣ ዳገትና ሜዳው ከእሱ እይታ የተሰወረ አይደለም። ሁሌም ከረጅሙ መንገድ ተግባብቶ፣ ከጥንቃቄ ተዛምዶ ፈተናውን ሲሻገር ከታላቅ ስኬት ጋር ነው።
እንዲህም ይኖራል!
የዓመታት ውጣውረድ የፈተነው ሌኒን ደምሴ የዛሬ ኑሮው ተወልዶ ባደገበት የቢሾፍቱ ከተማ ነው። ትናንት ቦርቆ ባደገበት ቀዬ፣ ሰርቶ በኖረበት አገር ሙሉ አካሉን ቢያጣም ከበርካታ ፈተናዎች ብዙ ተምሯል። አካል ጉዳቱ ሳይበግረውና እጁን ሳይሰጥም ለዚህ አይነቱ መልካም ሕይወት ደርሷል።
ዛሬ ትዳር ይዞ ሁለት ሴቶች ልጆችን በሚያሳድግበት ጎጆው ለችግር እጅ አይሰጥም። ልክ እንደሱ ልጆቹን ጠንካራ ለማድረግ ይተጋል።
ሌኒን ከአካል ጉዳቱ በኋላ ራሱን በተስፋ መቁረጥ አልደፋም። በርካታ ስራዎችን ሞክሮ ስኬትን ተጎናጽፏል። በእሱ ዘንድ ‹‹አልችልም›› ይሉት ቃል ቦታ የለውም። ይህ ጥንካሬ ለበርካቶች ማሳያ ሆኖም አድናቆት ተችሮታል። እሱ በተለይ አካል ጉዳተኞች በፈተናዎች ባህር ተሻግረው ለስኬት እንደሚደርሱ ታላቅ ምስክር መሆን ይሻል።
እነዚህ ወገኖች ልመና ብቻ መገለጫቸው አይደለም። እንደማንኛውም ሰው በርካታ ምርጫዎች አላቸው። ሌኒን በአካል ጉዳት ምክንያት ተስፋ በመቁረጥ፣ ባልተገባ አመለካከት መቃኘት ጠንቅ ስለመሆኑ ያምናል። መስራት እየቻሉ ልመናን የመጀመሪያ ምርጫ ያደረጉ ጉዳተኞች ልማድ ያናድደዋል።
እሱ ሰርቶ መቀየር እንደሚቻል፣ በጥረትና ልፋት ከስኬት ጫፍ መድረስ እንደሚኖር አስመስክሯል። በተስፋ መቁረጥ ብቻ ሳይሆን በስኬትም ‹‹እንዲህ ይኖራል›› የሚለው ሌኒን ልክ እንደትናቱ ዛሬን ተሻግሮ ነገን ብሩህ ለማድረግ መታተሩን ቀጥሏል። ከአካል ጉዳት ተያይዞ በአጉል አመለካከት ለተቃኙ ወገኖችም የራሱ ድንቅ ታሪክ ምሳሌ ይሆን ዘንድ ‹‹እነሆኝ›› ብሏል።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2014