የህክምና አገልግሎት ወሳኝ እና አስፈላጊ ስለመሆኑ አያጠያይቅም። በተለይም ተሽከርካሪ በማይገባበት፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት በማይገኝበት፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎትም ቅንጦት በሆነበት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ህክምናን በቅርበት ማግኘት አስቸጋሪ ነው። አስቸጋሪነቱ የሚሰማው ደግሞ በህክምና እጦት የተቸገረው ሰው ወይም ደግሞ ብዙዎች በቅርበት የሚያውቃቸው ሲቸገሩ የተመለከተ ወይም ችግሩ የጠነባቸው አካባቢዎችን ሮሮ በመገናኛ ብዙሃንና በመሳሰሉት የተከታተለ ነው።
የህክምና ተቋም ፋይዳ የሚገባው በህክምና እጦት የእኔ የሚለውን ሰው የተነጠቀ ሰው ወይም የእኔ የሚለው ሰው የተሰቃየበት ብቻም አይደለም፤ ማንኛውም ሰው በህክምና እጦት መሞቱን፣ መሰቃየቱን የሰማ ሁሉ የህክምና ተቋማትን ፋይዳ ይረዳል። በህክምና ተቋም አለመኖር ሳቢያ አንዲት ወላድ ህይወቷን ብታጣ፣ በእዚህ ስሜቱ የማይነካ የለም። በህክምና እጦት ህጻናት፣ ወጣቶች፣ አዛውንቶች ወዘተ ሲሰቃዩ የተመለከተም እንደዚያው።
የዛሬው የስኬት እንግዳችንም ወላጅ አባቱ በልብ ህመም ሲሰቃዩ የተሻለ ህክምና ሳያገኙ ከዚህ አለም በሞት ይለዩዋቸዋል። በዚህ ቁጭትም የህክምና ባለሙያ መሆንን ተመኝተዋል። ቀጥሎም በገጠሪቷ ኢትዮጵያ በቂ የህክምና ተቋማት በሌለበት የማገልገል ጥልቅ ፍላጎት ያድርባቸዋል። ይህ ምኞታቸው እንዲሰምርም ያለ አባት ያሳደጓቸው አርሶ አደር ወላጅ እናታቸው ብዙ ዋጋ ከፍለዋል።
አብዛኛው ኢትዮጵያዊ መሰረቱ የግብርና ዘርፍ ነው፤ እርሱ ከትምህርት ቤት ደጃፍ ሳይደርስ ልጆቹን አስተምሯል። አፈር ገፍቶ ፈጣሪውን ተማምኖ ለመሬት የሰጠው ዘር ፍሬያማ ሆኖ በሚያገኘው ውጤት ልጆቹን ጨምሮ አገሩን ይጠቅማል። አለፍ ሲልም ለአገር አለኝታ የሚሆኑ ልጆቹን በማስተማር የአገሪቱን ችግር ለማቅለል ይተጋል። ለዚህም ኢትዮጵያውያን ሴት አርሶ አደሮች ጉልህ ድርሻ አላቸው።
በርካታ ሴት አርሶ አደር እናቶች ሳይማሩ ልጆቻቸውን ማስተማር በመቻላቸው በማህበረሰብ ግንባታ ዘርፍ የጎላ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፤ እያበረከቱም ይገኛሉ። የዛሬው የስኬት እንግዳችንም ብዙ ሊያሳካቸው የሚችላቸው ዕቅዶች ቢኖሩትም አሁን ለደረሰበት ደረጃ ግን የወላጅ እናቱን የጎላ ድርሻ ተናግሮ አይጠግብም።
እንግዳችን ተወልዶ ባደገበት በሲዳማ ክልል ዳራ ወረዳ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአካባቢው በሚገኙ የገጠር ከተሞች ተከታትሏል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቅቆ የኮሌጅ ትምህርቱን ደግሞ በህክምናው ዘርፍ ማድረግ እንዲችል ወላጅ እናቱ ብዙ ዋጋ አስከፍሏል።
ይህ ለምን ሆነ? ይህ የሆነው ወላጅ አባቱ በህክምና እጦት ማጣቱ ነው። ‹‹አባቴ ህክምና ቢያገኝ በዚያ በሽታ አይሞትም ነበር›› የሚለው እንግዳችን፣ በዚህ ቁጭት ነው የህክምና ትምህርት የተከታተለው። ልጅን በግል ኮሌጅ ከፍሎ ማስተማር ለአርሶ አደር እናት ፈታኝ ቢሆንም፣ እናት ልጃቸውን የግል ኮሌጅ ከፍለው አስተምረዋል። ይህን ሲያደርጉ ደግሞ ከግብርና ሥራቸው በተጨማሪ ጨው፣ ዱቄትና የመሳሰሉትን መነገድ ውስጥ ጭምር ገብተው ነው። እንግዳችን በትምህርት ያገኘውን ዕውቀትም አባትም እናትም ሆነው ላሳደጉት ወላጅ እናቱና ለአካባቢው ነዋሪዎች መልሶ እየከፈለ ይገኛል።
‹‹በግል ኮሌጅ የጤና ትምህርቴን ተከታትዬ በህክምና ሙያ ማህበረሰቡን በማገልገል በአባቴ ህክምና እጦት ሳቢያ ያደረብኝን ቁጭት እንድወጣ አቅምና ብርታት የሆነችኝና ትልቅ ቦታ ያላት እናቴ ናት›› የሚለው እንግዳችን የጤና መኮንኑ አቶ ቦጋለ ጥላሁን ነው።
አቶ ቦጋለ በሲዳማ ክልል ዳራ ወረዳ የዳራ መካከለኛ ክሊኒክ ሥራ አስኪያጅና ባለቤት ነው። በተማረው የህክምና ሙያ ዘርፍ ሳይማሩ ያስተማሩትን ወላጅ እናቱን ጨምሮ እንደ ወላጅ በኃላፊነት ያሳደገውን የአካባቢውን ማህበረሰብ በሙያው የማገልገል ጥልቅ ፍላጎት ያድርበታል።
ይህን ፍላጎቱን እውን ለማድረግና ማህበረሰቡን ለማገልገልም ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ በአካባቢው በሚገኝ ቀባዶ የሚባል የገጠር ከተማ በአንድ የግል ክሊኒክ ተቀጥሮ ያገልግላል። በክሊኒኩ ሲሰራም በሙያው የበለጠ ማገልገል የሚችሉበትን መንገድ ይፈልጋል።
በ2010 ዓ.ም የክልሉ መንግሥት ለሥራ ዕድል ፈጠራ በሚል ያመቻቸውን ብድር ለመጠቀም የቀደመው አልነበረም። በወቅቱ አራት የሥራ ባልደረቦቹንና አብሮ አደጎቹን አስተባብሮ ወደ ሥራው ይገባል። ከመንግሥት ሁለት መቶ ሺ ብር ብድር በመውሰድ በትውልድ መንደሩ ዳራ ‹‹ዳራ መካከለኛ ክሊኒክ››ን ይከፍታል። በክሊኒኩም መሰረታዊ የሆኑ የጤና አገልግሎቶችን ለአካባቢው ማህበረሰብ በመስጠት ሙያዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።
አቶ ቦጋለ በወቅቱ አራት የጤና ባለሙያዎች የሆኑ አብሮ አደጎቹን ይዞ ወደ ሥራ ቢገባም፣ በአሁኑ ወቅት ክሊኒኩ ሙሉ በሙሉ የራሱ ሆኗል። ለሌሎችም ባለሙያዎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን የሚያስተዳድሩበትን ሁኔታ ፈጥሯል። አሁን የሰራተኞቹ ቁጥር 22 ደርሷል። ከዚህም በተጨማሪ ክሊኒኩ ከክሊኒኩ የሚያገኙት ደምወዝ ባይኖርም በክሊኒኩ ውስጥና በዙሪያው የሻይ ቡና እንዲሁም የሱቅ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ወጣቶችን በማደራጀት ሠርተው ማደር እንዲችሉ አድርጓል።
ሳይማር ያስተማረን ማህበረሰብ በቅርበት ሆኖ ማገልገል ከፍተኛ እርካታ እንዳለው የጠቀሰው አቶ ቦጋለ፤ በተለይም ወላጅ እናቱ ሲያሳድጉዋቸው የከፈሉትን ዋጋ በማሰብ ለአካባቢው እናቶች ልዩ እንክብካቤ እንደሚያደርግም ነው ያጫወተን። አቅም የሌላቸውም እንዲሁ የነጻ ህክምና በመስጠት ጭምር ዳራ መካከለኛ ክሊኒክ በአሁኑ ወቅት በቀን ከ300 ለሚልቁ ተገልጋዮች የ24 ሰዓት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት መካከለኛ ክሊኒኩ አገልግሎት እየሰጠ ያለው በተከራየው ቤት ሲሆን፣ በቀጣይ ደረጃውን የጠበቀ መካከለኛ ክሊኒክ ለመገንባት በሲዳማ ክልል ቀባዶ ወረዳ ላይ በአንድ ሚሊዮን ብር ቦታ ገዝቷል። በዚህ ቦታ ታዲያ በቀጣይ ሁለት ዓመታት ውስጥ ደረጃውን የጠበቀ መካከለኛ ክሊኒክ በመገንባት አገልግሎቱን በስፋት ለመስጠት አቅደው እየሰሩ መሆናቸውንና አሁን ካለው የሥራ ዕድል በተጨማሪ ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚቻል አቶ ቦጋለ ያብራራል።
እንደ አቶ ቦጋለ ገለጻ፤ ክሊኒኩ መካከለኛ ክሊኒክ እንደመሆኑ ሙሉ ለሙሉ የላብራቶሪ አገልግሎትን ጨምሮ ማንኛውንም የህክምና አገልግሎ ይሰጣል፤ ተኝተው ለሚታከሙ ታካሚዎችም በቂ አልጋዎች አሉት። በህክምና ጉዞውም ስኬታማ መሆን ችሏል። ለዚህም የህክምና ባለሙያዎቻቸው በሙሉ ልምድ ያላቸውና ሥራቸውን ወደውና ፈልገውት የሚሠሩ መሆናቸው አስተዋጽኦ አድርጓል።
በመንግሥት ሆስፒታል የማዋለድ አገልግሎት በነጻ እንደሚሰጥ አቶ ቦጋለ ጠቅሶ፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች በድንገተኛ ለሚመጡ እናቶች ግን ክሊኒኩ አዋላጅ ነርስ ቀጥሮ አስፈላጊውን ግብዓት በማሟላት የማዋለድ አገልግሎት ይሰጣል ይላል። ለአገልግሎቱም ክፍያ እንደማይጠይቅ ተናግሮ፣ መጠቀሚያ ለሆኑ ቁሳቁስ ብቻ በጣም ትንሽ ክፍያ ማለት ከ100 እስከ 150 ብር ብቻ ክፍያ እንደሚጠየቅ ነው ያብራራው። ህክምናው ከክሊነኩ አቅም በላይ ሲሆን ደግሞ ወደ ሆስፒታል እንደሚልክ ተናግሯል።
ክሊኒኩ በአካባቢው ከሚገኝ የመንግሥት ሆስፒታል ጋርም መልካም የሥራ ግንኙነት አለው፤ ሙያዊ መደጋገፍ አላቸው የሚለው አቶ ቦጋለ፣ ሆስፒታሉ የተለያየ እገዛ ሲፈልግ ከባለሙያ ጀምሮ ማንኛውንም አይነት እገዛ ክሊኒኩ በተቻለ መጠን ያደርጋል። ሆስፒታሉም እንዲሁ ክሊኒኩ በሚፈልገው ሁሉ እገዛ የሚያደርግ ሲሆን፣ ተቋማቱ በመካከላቸው ጤናማ ግንኙነት መመስረት ችለዋል ሲል ያብራራል።
ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻርም ክሊኒኩ ለአቅመ ደካሞች ከመንግሥት ጋር በመተባበር የነጻ ህክምና አገልግሎት ይሰጣል። ለአገልግሎቱም በቀበሌና በወረዳ በኩል አቅመ ደካማ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ደብዳቤ ይዘው ከመጡ በቀጥታ ክሊኒኩ የሚሰጠውን ማንኛውንም አገልግሎት እንዲያገኙ ያደርጋል። ችግረኞች የነጻ ፈቃድ ወረቀት ባይኖራቸው እንኳ አቶ ቦጋለ ከማህበረሰቡ የወጣ እንደመሆኑ የማህበረሰቡን ማንነት በሚገባ ያውቃልና ከወረቀት ውጭም ክሊኒኩ አገልግሎት እንዲሰጥ አርጓል።
ሁለት የጤና መኮንኖችን ሰባት የጤና ባለሙያዎችን፣ ሁለት ላብራቶሪስቶችን፣ አንድ ሚድዋይፍ ወይም ደግሞ አዋላጅ ነርስን እና ሌሎች ባለሙያዎችን ይዞ በገጠራማዋ ቀበሌ ዳራ ወረዳ ላይ የተከፈተው ዳራ መካከለኛ ክሊኒክ፣ ለአካባቢው ማህበረሰብ ተደራሽ መሆን መቻሉንም አቶ ቦጋለ ይናገራል፤ በተለይም ባለሙያዎቹ በፈረቃ ሌትና ቀን ለ24 ሰዓት ሳይተኙ አገልግሎቱን የሚሰጡ እንደሆኑ ይገልጻል። ይህም በማህበረሰቡ ዘንድ ተወዳጅነትና ተቀባይነትን አትርፎለታል።
‹‹ጥሩ አገልግሎት መስጠት ሲቻል ውጤታማ መሆን ይቻላል›› የሚለው አቶ ቦጋለ፤ ሥራ ብለው የያዙትን ትኩረት ሰጥቶ ለለውጥና ለተሻለ አገልግሎት መሥራት ጠቃሚና አስፈላጊ እንደሆነም ነው የሚናገረው። አገልግሎት ሰጪ እንደመሆናቸውም አገልግሎቱን ፈልገው የሚመጡ ሰዎች ወደው ሳይሆን ተቸግረው ነውና ችግሩ ደግሞ መችና እንዴት እንደሚፈጠር አይታወቅም። ለዚህም ነው ክሊኒካችን በዓልን ጨምሮ ቀንና ለሊት በሩን ክፍት አድርጎ የሚጠብቀው ይላሉ።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ባለሙያዎችን በአግባቡ በመያዝ ተነሳሽነት ኖሯቸው እንዲሠሩ የተለያዩ ማበረታቻዎች አስፈላጊ እንደሆነ የሚያምነው አቶ ቦጋለ፤ በመጀመሪያ ቅጥር ሲፈጽሙም መንግሥት ከሚከፍለው ክፍያ በበለጠ ዋጋ ቅጥሩ እንደሚፈጸም ይናገራል። ለአንድ ባለሙያ ከ7500 እስከ 9000 ብር ክሊኒኩ ይከፍላል ይላል። በተመሳሳይ ደግሞ በመንግሥት ሆስፒታሎች የሚገኙ የተለያዩ ስልጠናዎች በግል ክሊኒክ ውስጥ የማይገኙ መሆናቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ምሳና ቁርስን ጨምሮ የሻይ ቡና አገልግሎት በክሊኒክ ውስጥ እንደሚሰጥ ነው የሚገልጸው። የሞባይል ካርድ በመሙላትም እንዲሁ የሥራ ተነሳሽነትን የሚጨምሩ ተግባራትን እያከናወኑ እንደሆነም አጫውቶናል።
እንደ እሱ ገለጻ፤ ሰዎች ከህመማቸው እንዲፈወሱና ጤናማ እንዲሆኑ 24 ሰዓት በሩን ክፍት አድርጎ የሚሠራው ዳራ መካከለኛ ክሊኒክ፣ ከሁሉ አስቀድሞ አገልግሎት የሚሰጠው ለማን እንደሆነ ማህበረሰቡን ጠንቅቆ የሚያውቅ በመሆኑ በርካታ ሙያዊ ድጋፎችን ያደርጋል። ለአብነትም አንድ እናት ራሴን ያዞረኛል ብላ ከመጣች ገንዘብ ከፍላ ግሉኮስ እንድትወስድ ከማድረግ ባሻገር በቀላሉ ሸንኮራ በልታ ጤናዋን ማስተካከል የምትችል መሆኑን በማስረዳት ክሊኒኩ ከሚያገኘው ገቢ ባለፈ ሙያዊ ምክሮችን በመለገስ የማህበረሰቡን አቅም ባገናዘበ መልኩ እየሠራ ይገኛል።
ለህክምና አገልግሎት አስፈላጊ የተባሉ ቁሳቁስን በተለይም መድሃኒቶችን ክሊነኩ ከሶስተኛ ወገን የሚያገኝ መሆኑ ለሥራው ፈታኝ እንደሆነ ነው አቶ ቦጋለ የሚያመለክተው፤ የመንግሥት ሆስፒታሎችም ሆኑ የግል ክሊኒኮች ዓላማቸው አንድ በመሆኑና ሁሉም ህብረተሰቡን የሚያገለግል እንደመሆኑ መድሃኒት በቀጥታ ከመንግሥት ማግኘት ቢቻል መልካም እንደሆነም ያስገነዝባል። ይህ ሲሆን የተቀላጠፈ እና የማህበረሰቡን አቅም ያገናዘበ አገልግሎት መስጠት እንደሚቻል ነው የሚገልጸው። ይሁንና በአሁኑ ወቅት ማንኛውንም መድሃኒት ከመንግሥት ተቋማት ውጭ ነጋዴዎች ተጨማሪ ዋጋ ከፍለው ለራሳቸው ደግሞ ከሁለት እስከ ሶስት ብር ትርፍ ይዘው እየሠሩ መሆኑን ይናገራል። ይህ ስራውን ፈታኝ እንዳደረገው ይጠቁማል።
ወደፊት አቅመ ደካሞችን በተለይም በገጠር ውስጥ የሚኖሩትን የመጎብኘትና በተለያዩ ዘርፎች የማገዝ ዕቅድ እንዳለው የጠቀሰው አቶ ቦጋለ፤ ከዕቅዱ አንዱም በከተሞች የሚገኙ ሰዎች የማይጠቀሟቸውን አልባሳትና መጫሚያዎች እንዲሁም ሌሎች ቁሳቁስ በማሰባሰብ ለተቸገሩ ወገኖች ማድረስ መሆኑን ይናገራል። መኖሪያ ቤታቸው ለመኖሪያ ምቹ ያልሆኑትን የህብረተሰብ ክፍሎች ለይቶ ቤት የመሥራት ዕቅድ ይዘው እየሰሩ መሆናቸውን ያብራራል።
ሰዎች በሚያውቁትና በሚያውቃቸው የማህበረሰብ ክፍል ውስጥ ሆነው የሚሰጡት አገልግሎት ትልቅ እርካታን እንደሚሰጥ የሚያስገነዝበው አቶ ቦጋለ፤ እርሱ በሙያቸው ማህበረሰቡን ማገልገል በመቻሉ ትልቅ ደስታና እርካታ ማግኘቱን ገልጾ፤ በተለይም ወደ ክሊኒኩ ሄደው መታከም ላልቻሉ ሰዎች ቤት ለቤት በመሄድ የሚሰጠው ህክምና ትልቅ እርካታ እንደሚሰጠው ይጠቁማል።
አቶ ቦጋለ እንዳለው የተለያዩ የህክምና ቁሳቁስን ይዞ እየሰራ ያለው ዳራ መካከለኛ ክሊኒክ በተለይም ራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስ ለማይቹሉ ታካሚዎች ባሉት ሁለት ሞተር ሳይክሎች ታማሚው ቤት ድረስ በመሄድ ህክምና ይሰጣል። የህክምና አገልግሎት አግኝተው ወደ ቤታቸው መመለስ ካልቻሉም እንዲሁ ወደ ቤታቸው የመመለስ ሥራ ይሠራል።
አጠቃላይ በወላጅ አባቱ ህክምና አጥቶ መሞት በመቆጨት ለተገኘበት የማህበረሰብ ክፍል የህክምና አገልግሎት በመስጠት ለብዙዎች የተረፈው አቶ ቦጋለ፤ በአሁኑ ወቅት መካከለኛ ክሊኒኩ ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ ከሁለት ሚሊዮን አምስት መቶ ሺ ብር በላይ ካፒታል ማፍራት መቻሉን ተናግረዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2014