አንድ ሆኖ በመኖር ውስጥ አንድ አይነት መሆን ግድ አይደለም። አንድ ሆኖ በመቆም ግን የመለያየትን እና የመጣረስን ሳንካ ማሰወገድ እጅጉን ይቀላል። ምድር በራስዋ አንድ ሆነው በትብብር ሲኖሩባት እንጂ አንድ አይነት ብቻ ሲሆኑባት ትሰለቻለች። አለያይቶ በተለያየ ቋንቋ የፈጠረን ለምክንያት አመለካከታችን የተሰበጣጠረው ለጥበቡ እርሱ ለሚፈልገው መሻቱ ይሆናል። ጣቶቻችን ተመሳስለው በእኩል ቁመትና እና ውፍረት በተመሳሳይ ቅርፅና መጠን ያልተሰሩ ለምን ይሆን? ብለን አስበን እናውቃለን?
አዎን! እያንዳንዱ ለእኛ አስፈላጊ ናቸውና አንድ አይነት ሳይሆን አንድ ሆነው መስራት እንዲያስችሉን፣ እንዲመቹን በዚያ መልኩ ተገኙ ወይም ተፈጠሩ፤ እናም አንዱ ካንዱ ጋር አብሮ በመሆን አንድ ተግባር በትክክል ይከውናል። ይህ አንድ ታላቅ ነገር ያሳየናል፤ እሱም አንድ የመሆን ልዩ ጥበብ አንድ አይነት ከመሆን ፍላጎት ጋር እጅጉን የተለያየ መሆኑን።
ወገን ትልቁ መረዳት ያለብን ቁም ነገር እዚህ ላይ ነው። አንድ ሆኖ ለመቆም አንድ አይነት ሆነን መገኘት የለብንም። አንድ አይነትነት በራሱ ስለሌለ መፍጠርም ይከብዳል። አንድ አገር በመገንባት ሂደት ውስጥ ብዝሀነት ማክበር ወሳኝ ጉዳይ ነው። የእኛን አመለካከት፣ ፍልስፍና፣ ባህል እምነትና ወግ ከሌላው ጋር ፍፁም የተለየ ሊሆን ይችላል። ያ መለየት ተፈጥሯዊ ነው። ለምን ተለያየ የሚል ምላሽ የሌለው ማብራሪያም መጠየቅም ተገቢነት የለውም።
የእኛ ያልነውን እንደወደድነው ሁሉ ሌሎች የራሳቸው መውደዳቸው ግድ ነውና የእነርሱን ማክበር ይገባል። የእኛ ያልነው እንዲጠበቅ ስንገለገልበት የሌላውን በማይነካ መልክ መጠቀም፤ የሌሎችንም እንዳንነካ መጠንቀቅ እንዲያከብሩልን ክብር መስጠት ይገባናል። ያኔ አንድነቱ ይደረጃል፤ ያን ጊዜ አብሮነቱ ይጠነክራል። አገር በዚህ ውስጥ ሀያልነትዋ እውን ይሆናል።
በተለይ እንደኛ ብዝሃነት በተለያየ መልኩ በዝቶ ባለበት አገር ውስጥ የሚኖር ማህበረሰብ አይደለም፤ተመሳሳይ የሆነ እምነት ባህልና ተቀራራቢ የሆነ ስልቦናዊ ስሪት ባለው ማህበረሰብ ውስጥ እንኳን የሀሳብ ልዩነት ገዝፎ ይታያል። ዋነኛው ጉዳይ የተለያየው ሀሳብ በምን መልክ ነው አስታርቆ በአንድነት መጓዝ የሚቻለው የሚለው ላይ ነው። የእኛ መሰረታዊ ችግርም ይሄው ነው።
አዎ! የችግራችን መነሻው ይህ ነው፤ ልዩነታችን ተቀብለን ተቻችሎ በአንድነት መቆም አለመቻል፤ የጋራ መግባባት ላይ የደረሰ ማህበረሰብ አለመገንባት።
ከማቅረብ ይልቅ የምንገፋው ይበዛል። በአንፃሩ ሲገፉን መገፋታችን ያንገፈግፈናል። አቤት የምንገፋው ነገር እኮ ነፍ ነው ጎበዝ፤ የማንገፋው ምን አለ ? የሌሎችን ሀሳብ፣ የተጠጉን መልካም እድሎች፣ የኖርንበት ባህል፣ የተሰጠን ኃላፊነት ብቻ ምኑ ቅጡን ዘርዝሬ እጨርሰዋለው ወዳጆች ገፊ ነን። መልካም ነው ብለን ያመንበት ሀሳብ በሌሎች ተቀባይነት ቢያገኝ እንወዳለን። ነገር ግን የእኛን ሀሳብ ሌሎች እንዲቀበሉን የምንወደውን ያህል የሌሎችን ሀሳብ ለማድመጥ ዝግጁ ያልሆን የሀሳብ ገፊዎች ነን።
የእኛ እምነትና እሳቤ የፈጠረውን ሀሳብ ለሌሎች ማሻገር ወይም መስጠት የመውደዳችን ያህል፤ የሰዎችን ሀሳብ ከመቀበል ይልቅ መግፋት ልምዳችን ሆኗል።
አዎ! ብዙ የገፊነታችን ማስረጃ ገፆቻችን ስንገላልጥ ጥንካሬ የሌለን ምክንያት አልባዎች መሆናችን ይለያል። በምክንያት የሚያምን ትውልድ፤ የመስጠትን ያህል መቀበል ያውቃል።
እኛ የምናምንበትና የምናከብረው በሌሎች ላይ እንዲጋባ የምንፈልገው ሀሳብ ሌሎች ጋር ምንም ቦታ የሌለው ብዙም የማይገዝፍ ምንአልባትም ጉዳዩ በሌላ አይን ከቁብ የማይቆጠር ሊሆን እንደሚችል አይገባንም። ልክ እኛ የሌሎች ሀሳብ ብዙ ጊዜ ቁብ እደማንሰጠው ሁሉ ማለት ነው። ይህን እውነታ መቀበል ይኖርብናል። ሁሉም የእኛ ያቀረብነው ሀሳብ ደጋፊ ላይሆን እኛ ደግሞ የሌሎችን ሀሳብ ተቀባይ ላንሆን እንችላለን። በመሰረቱ እኛም እነሱም ልክ ነን። እኛ የሌሎች ሀሳብ መቀበል የማንችልበትን ትልቅ ምክንያት ይኖረን ይሆናል። በአንፃሩ ደግሞ ሌሎች የእኛን ሀሳብ መቀበል የማይችሉበት ብዙ ምክንያት ሊኖራቸው እንደሚችል መረዳት ይገባል።
መግባባት ይቻል ዘንድ ጥበብ በተሞላበት መንገድ ሀሳብን ወደሌሎች ለማስረፅ መሞከር ከሰለጠነ ዜጋ የሚጠበቅ ነው። የያዝነው ሀሳብ ልክ ነው ብለን ካመንን የሀሳቡ ግዝፈትና የጉዳዩ እውነተኝነት ደግሞ ለማሳየት መሞከር ይገባል። ይሄኔ ግን ሌሎች የራሳቸው የሆነ ከኛ ሀሳብ ጋር የማይሄድና ተቃራኒ ሊሆን እንደሚችል ሀሳብ ሊኖራቸውና የእኛን ሊቀበሉ መረዳት ይኖርብናል።
በእርግጥ የያዝነው ሀሳብ ግዝፈት ብዙዎችን ወደኛ ሊጠራና የሀሳባችን ደጋፊ ብሎም ተሟጋች ሊያደርግ ይችላል። ነገር ግን ምንም ያህል ታላቅ እና አሸናፊ እንዲሁም ሀቀኛ እምነት የሚወልድ ሀሳብ ከእኛ ወደሌሎች እንካችሁ ስንል ከሌሎች የምናገኘው ምላሽ የተሟላ ላይሆን ይችላል። ምን አልባትም ጭራሽ ተቀባይነት ላናገኝም እንችል ይሆናል። ምን አልባትም አንዳንዴ ሀሳባችን የተሳሳተ መሆኑን በሌሎቹ ሀሳብ ውስጥ ሊገለጥልንም ይችላል።
ከሌሎች ጋር እየተናጋገርን አልያም እያወራን ሳለ፤ የተላመድነው የሀሳብ ገፊነት ልማዳችን ይቆጣጠረንና እንዴት እንዲህ ሊሆን ይችላል በፍፁም ብለን እንደመድማለን። ነገር ግን ሀሳባችን በሌሎች ሀሳብ ውስጥ ጠልቆ ሊመረመር የሚችል እና በዚያኛው ወገን የጠነከረ ምክንያት ሊገጥመን እንደሚችል መረዳ ይገባል። ሀሳባችን አሳማኝ በሆነ መልኩ በሌላ ሀሳብ ሊረታ የሚችል መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል።
አንቀበልም ብለን የምንገፋው የሌሎች ሀሳብ የእኛ ሀሳብ ተቃራኒ በመሆኑ ምክንያት አልታይ ያለን ግን ደግሞ የገዘፈ ሊሆን ይችላል። ለእኛ የተሰወረው ነገር ግን ግዙፍ የሆነው ሀሳብ እኛ ከቆምንበት ሀሳብና እውነት ነው ብለን ካመንበት ጋር የሚጣረስ ቢሆን እንኳ መሆኑን መቀበል ይኖርብናል። በሌላ በኩል ደግሞ እኛ ያቀረብነው ሀሳብ ምንም ያህል ሚዛን የሚደፋ እንኳን ቢሆን ወደሌሎች ስናሻግር ጥበብ በተሞላበት መንገድ ቢሆን ስኬታማ እንሆናለን።
አንድ ወደፊት አራምዶ ሁለት ወደ ኋላ የሚመልሰን ጉዳይ ምንነት ለማወቅ ያስችለን ዘንድ መነሻችን ላይ ቆም ብለን እንዴት መጓዝ እንዳለብን ማሰብ ይገባናል። የጉዟችን ገቺ ምክንያቶች ምንነት ስንመረምር ደግሞ አብሮ ለመጓዝ የሚያስችሉ ስንቆች ሁላችን አለመታጠቃችን እንገነዘባለን። የአብሮነት ጉዞ ስንቅ ከሆኑት መካከል ደግሞ ተደጋግፎ መሻገር፣ተነጋግሮ መግባባትና ለሌላው ክብር መስጠት ዋንኞቹ ናቸው። ላዛሬ አበቃሁ ቸር ይግጠመን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2014