አዲስ አበባ፦ በምሥራቁ የኢትዮጵያ ክፍል በተለይም በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የችኩንጉኒያ በሽታ ወረርሽኝ መከሰቱን እና ዜጎች ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ።
በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች የተከሰተውን የኩፍኝ ወረርሽኝ ለመከላከል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወነ መሆኑንም አመልክቷል።
የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ፤ ችኩንጉኒያ የተሰኘው በሽታ በአፋር ክልል በዞን አንድ ከየካቲት 29 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ መከሰቱ ታውቋል። የጤና ባለሙያዎች እና የአጋር ድርጅት ሠራተኞች በቦታው ተገኝተው ባደረጉት የመስክ ዳሰሳ በበሽታው የተጠቁ አስር ሰዎች መኖራቸውን አረጋግጠዋል።
እንደ ኢንስቲትዩቱ መረጃ ከሆነ፤ የችኩንጉኒያ ወረርሽኝ በቆላማና ሞቃታማ በሆኑ አካባቢዎች የሚከሰት በሽታ ነው። «ኤደስ ኤጂፕታይ» በምትባል ትንኝ ንድፊያ አማካኝነት የሚዛመተው በሽታው ከፍተኛ ትኩሳት እና የመገጣጠሚያ እንዲሁም የጀርባ አጥንት ህመም ያስከትላል። በተለይም በሽታው በድንገት የሚከሰት እና ከ38 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ የሆነ የሰውነት ትኩሳት ያደርሳል። ራስ ምታት፣ የዓይን መቅላት፣ ቁርጥማት፣ ማቅለሽለሽ እና የቆዳ ሽፍታ እንዲሁም ከባድ የእጅና የእግር መገጣጠሚያ ሕመም ያስከትላል። ይሁንና ለበሽታው ከሚጋለጡት መካከል ከ3 እስከ 38 በመቶዎቹ ምልክት አይታይባቸውም።
ትንኟ ልክ እንደ ወባ ትንኝ በምትናደፍበት ወቅት የበሽታ አምጪ ተህዋስያኑን ከበሽተኛው ሰው ወደጤነኛ ሰው በቀላሉ ማስተላለፍ ትችላለች። በትንኟ የተነደፈ ሰው ከሦስት እስከ ሰባት ቀናት ውስጥ የበሽታው ምልክቶች ስለሚታይበት ፈጥኖ ወደጤና ተቋማት መሄድ ያስፈልጋል። በሽታውን በመከላከል ረገድ የአቆረ ውሃ ያለባቸውን ቦታዎች በማፋሰስ እና ለወባ ትንኝ መራቢያ የሚሆኑ ቦታዎችን በማጽዳት አስቀድሞ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። በተጨማሪ ችግሩ ሊከሰት ይችልባቸዋል በሚባሉ ቦታዎች ላይ ማንኛውም ሰው የአልጋ አጎበር መጠቀም እንደሚገባው ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል።
በሌላ በኩል ኢንስቲትዩቱ በላከው መረጃ፣ በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች የተከሰተውን የኩፍኝ ወረርሽኝ ለመከላከል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወነ ነው። በክልሎቹ ለሚገኙ እድሜያቸው ከ15 ዓመች በታች ለሆኑ ከ912 ሺ በላይ ዜጎች የኩፍኝ መከላከያ ክትባትም እየተሰጠ እንደሚገኝ ጠቁሟል።
የኩፍኝ ወረርሽኝ በኦሮሚያ ክልል በባሌ ዞን 11 ወረዳዎች፣ በምዕራብ ሐረርጌ ዞን 4 ወረዳዎችና በምስራቅ ሐረርጌ 2 ወረዳዎች በድምሩ በ17 ወረዳዎች በሚገኙ ቀበሌዎች እንዲሁም በሶማሌ ክልል በስምንት ዞኖች በሚገኙ 41 ወረዳዎች ተከስቷል።
በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች ለ778ሺ553 እንዲሁም በሶማሌ ክልል ለ133ሺ838 እድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች ለሆኑ ዜጎች እንዲሁም በተለያዩ ክልሎች ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎችም የመከላከያ ክትባት እየተሰጠ መሆኑን ኢንስቲትዩቱ አመልክቷል።
የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር ለመደበኛ ክትባት ከያዘው የመጠባበቂያ ክምችት 961ሺ455 የክትባት መድኃኒቶች ወጪ ያደረገ ሲሆን፣ የሥራ ማስኬጃ በጀት ደግሞ ሙሉ ለሙሉ በኢንስቲትዩቱ መሸፈኑን አስታውቋል።
የኩፍኝ በሽታ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈው በማሳልና በማስነጠስ ወቅት ከአፍና አፍንጫ በሚወጣ እርጥበት አማካኝነት ሲሆን፣ በክልሎቹ በሽታው በከፍተኛ ሁኔታ እንዲሰራጭ ያደረገው ያልተከተቡ ህፃናት በመኖራቸው መሆኑ መግለጫው አመልክቷል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 14/2011
ጌትነት ተስፋማርያም