አለቃ ገብረ ሃና ቀልድ አዋቂ ስለመሆናቸው አገር ያወቀው ፀሀይ የሞቀው ስለመሆኑ ለእናንተ አላወጋም። አለቃ በጣም አጭር ሰው ናቸው ይባላል። ሚስታቸው ወይዘሮ ማዘንጊያሽ ደግሞ ሲበዛ ረጅም ናቸው። መንገድ ውለው ወደቤታቸው ሲመለሱ ወይዘሮ ማዘንጊያሽ ሰማዩን አይተው አለቃ ዝናብ ሊዘንብ ነው መሰለኝ ይሏቸዋል አጭር በመሆናቸውና በነገር ሊወርፏቸው ፈልገው። ከዚያ አለቃ ከኋላቸው ኩስ ኩስ እያሉ ሲመልሱላቸው! «እኔ ምን አውቃለሁ ለሰማዩ ቅርቡ አንቺ ነሽ» አሏቸው ይባላል። አንጀት አርስ መልስ ይልኸል ይህ ነው!
ወዳጄ ምን መሰለህ! አንዳንድ ጊዜ ለማን ምን እየተናገርን እንደሆነ ማወቅ ጥሩ ነው። አንዳንድ ጊዜ ዝም ብለህ ማየት የሌለብህን አትመልክት። እንበልና የሆነ ጉዳይ ገጥሞህ ወይንም የሆነ ነገር ለማስፈፀም የሆነ ቢሮ ሄደህ እንበል። ታዲያ ጉዳይህ ይህ ሆኖ ሳለ የፀሐፊዋን ሁኔታ በጥልቀት መመልከቱና ያን ያክል ስለ እርሷ መመራመሩ ጅልነት ሊሆን ይችላል። የቢሮው ውበት፣ ከፀሐፊዋ ጠረጴዛ ላይ የተደረደረው የባለጉዳይ ይሁን ምንነቱ የማይታወቅ የወረቀት ተራራ፣ በፀሐፊዋ ቢሮ ውስጥ የተደረደሩ ስልኮች ብዛት መቁጠር ምንም አይጠቅምህም። በእርግጥ! ይጠቅመኛል የሚል ሰው ካለ መብቱ ነው።
እሺ አሁን የፀሐፊዋን መቀመጫ ማየት ጥቅሙ ምንድን ነው። በቃ ይህ መቀመጫ ማለቴ ወንበሩ ይገባት ይሆናል ወይንም አለቃዋ ስለወደደው ሊሆን ይችላል። በቃ! አለቃ ከወደደው ወደደው ነው ሌላ ምን አለ? ይልቅስ ጉዳይህ ላይ ብቻ በማተኮር አጀንዳህን አጠናቀህ እግር ወደመራህ ሂድ!
በነገራችን ላይ ስለ ፀሐፊዎች ካነሳን አይቀር የሆነ ነገር አልታዘባችሁም። ለምሳሌ በቁመናቸው መልከ መልካም፣ ዓይነ ግቡ፣ ሞንዳላ ዓይነት ተክለ ቁመና የተላበሱ ሲሆኑ በባህሪያቸው ወጣ ያሉ ለምሳሌ ቆጣ ቆጣ የሚሉ ወይንም በጣም ተግባቢና አስተዋይ፣ ለምሳሌ በሁሉም ነገር ውሳኔ ሰጪ ነን የሚሉ ወይንም የማይመለከታቸውን ሁሉ የሚጠይቁ፣ ወንድ መሆንህ እየተመለከቱ ፆታህ ምንድን ነው ብለው የሚጠይቁህ፤ ትዕግስትህን የሚፈታተኑህ ወይንም የሚፈታተኑሽ። አሁን አንድን ባለ ጉዳይ ጾታ መጠየቅ ከኃላፊና ከፀሐፊዋ ጋር ምን ያገናኛቸዋል? ለነገሩ ሊገናኝ ይችል ይሆናል። ለምሳሌ በቃ ብዙ ብዙ ነገር ላይ ለምሳሌ የሚያስብሉ ነገሮችን የተላበሱ ሆነው አላገኛችሁም?
በነገራችን ላይ መልከ መልካም፣ ተግባቢ ብቻ መሰል ባህሪ የሚስተዋልባቸው ፀሐፊዎች ጥቅማ ጥቅማቸው ምንድን ነው ብዬ አስባለሁ። ለረጅም ጊዜ ቢሮ ውስጥ ናቸው። ወጭ ወራጁ ሁሉ በእነርሱ ዘንዳ ካላለፈ የተሰራም አይመስላቸውም። ይህን ሁሉ የሚከታተሉት ጥቅማጥቅማቸው ምንድን ነው ብዬ ሳስብ ግን ግራ ይገባኛል። ለነገሩ እንደዚህ እኮ አይጠየቅም። ዝም ብሎ ማለፍ አይበጅም። ለዚያም በትይዩ ሳይሆን በስር ማለፍ፤ ዝቅ ብሎ።
ከማህበራዊ ሚዲዎች ያገኙሁት አንድ የእብዶች ቀልድ ትዝ አለኝ። ‹‹አማኑኤል ሆስፒታል አንድ የአዕምሮ ዶክተር እብዶች ወደ ውጭ እየወጡ ያስቸግሩትና በመውጫው በር ወለሉ ላይ መስመር ያሰምርና «ከዚህ በኋላ ማንም ከዚህ መስመር እንዳያልፍ» ይላቸዋል። ትንሽ ቆይቶ ሲመጣ ወለሉ ላይ እነዚህ አዕምሮ ህመም ያለባቸው ታካሚዎች ሲንፏቀቁ ያያቸውና «ምን እየሠራችሁ ነው?» ሲላቸው አንዱ ተነሳና «በሥር ልናልፍ ነው» ብሎ ይመልሳል። መሬት ላይ በቀለም ከተሰመረው መስመር ሥር መሆኑ ነው። አያችሁ አንዳንዴ ማለፍ ጥሩ ነው። መጠየቅ የማይገባንን መጠየቅ፣ ማወቅ የሌለብን ለማወቅ መጨነቅ፣ የማይፈቀደውን ለማስፈቀድ መራኮት ምን ሊበጅ! በቃ ማለፍ ነው። ሌላው ቀርቶ በማይቻል ሁኔታም ቢሆን እንደ ዕብዶቹ ከመስመሩ ስር ለማለፍ መመኮር።
ማለፍ የሚለውን ካነሳን አይቀር ትዕግስተኛ መሆን፤ ማለፍ መልካም ነው። ወደ ኃላፊ ለማለፍ ወይንም ለመሄድ ፀሐፊዋ ማለፍ አለብህ። እንዴት ብሎ መጠየቅ ምት ቢሆንም ለዚህ ብዙ መልስ መስጠት አልችልም። ብዙ የማለፍና የመተላለፍ ህጎች በመኖራቸው እንዲያው ማለፍ መልካም ነው በሚለው ብንረዳዳ ሸጋ ነው።
እንዲያውም ይህን ሃሳብ አላልፈውም። ማለፍ ማለት መተው ነውን፤ አይደለም። ማለፍ ማለት በተበላሹ ዛሬዎች ውስጥ የተበላሸ ነገን ላለመፍጠር መታገስ ማለት ነው። ማለፍ ማለት አለመቻል ሲሆን እየቻሉም ቢሆን አለመቻል ነው። መሰንዘር ስንችል መሰብሰብን፤ መናገር ስንችል አለመናገርን፣ መቆጣት ስንችል መታገስ እና ብቻ በብዙ መቻሎች ውስጥ ምንም አለመቻል ነው።
ይህ ማለት ግን እልም ያለ ጅልነት አለመሆኑን ልብ ይሏል!፡ አንዳንድ ጊዜ እኛ ብቻ ብልጥ የሆንን የሚመስለን፣ እኛ ብቻ የመራን፣ እኛ ብቻ የገነባን፣ እኛ ብቻ የተማርን፣ እኛ ብቻ የተሰማን፣ እኛ ብቻ ያገኘን፣ የእኛ ብቻ የጻፍን የሚመስለን አያሌዎች ነን፤ ያው ስለፀሐፊ አንስቼ የለ!
አንዳንዴ ብልጠታችንና ማወቃችን በወጉ መያዝ ጥሩ ነው። ብልጥ እኛ ብቻ የሚመስለን ግን ደግሞ ምንም የሆንን ብዙዎች ነን። እኔ ብቻ ብልጥ ለሚሉ ሰዎች አንድ ተረት ትዝ አለኝ።
ከዕለታት አንድ ቀን እንዲህም ሆነ፤ የደብሩ አለቃ ዛፍ ቆራጮችን ይኮናተሩና ሥራው እየተካሄደ ሳለ የገብርኤል ዕለት ከቆራጮቹ አንዱ በጣም ረጅም ዛፍ ላይ ወጥቶ ቅርንጫፍ ሲመለምል፤ ክፉ ነፋስ ይነሳና ያን ረጅም ዛፍ እንደጭራሮ ያወናጭፈው ጀመር። የዚህ ሁኔታ መፈጠር እጅግ በጣም ያስደነገጠውና ያስፈራው ቆራጭ፤ «ወይኔ ሲያቀብጠኝ በገብርኤል ዕለት! ለዚያውም በደብር ውስጥ። ገብርኤል ተቆጥቶ ሊገለኝ ነው» እያለ ካለቃቀሰ በኋላ «እንዲያው ቅዱስ ገብርኤል! የዛሬን ያወጣኸኝ እንደሁ አሥር ብር አገባልሃለሁ» ብሎ ይሳላል። ወዲያው ስለቱን ሲጨርስ ነፋሱ ጸጥ ረጭ ይልለትና ከዚያ ዛፍ ላይ እየተሽቀዳደመ ይወርዳል። ሁለት እግሮቹ መሬት ላይ ሲቆሙ የአሥር ብሩ ነገር ይከነክነውና «ኤጭ! እኔ ሠርቼ በላቤ ወዝ ነው የማድረው፤ ገብርኤልም ሠርቶ ይብላ» ብሎ ስለቱን ላለማግባት ወሰነ። ትዝ ቢለው ለካ መፋሱን እዚያ ረጅም ዛፍ ላይ ትቶት ወርዶ ኖሯል። ፊቱን ወደሰማይ ዞር አድርጎ፤ የርብድብድ ፈገግታ እያሳየ «ምነው ገብርኤል ቀልድ አታውቅም እንዴ!» አለ ይላሉ።
ወዳጄ! ቀልድህን በልኩ አድርገው፤ የምታሞኘው ሰው ሁሉ ሞኝ ስለሆነ ሳይሆን ማለፍን ለነገሮች እንደመተላለፊያ አድርጎ ስለሚያስብ፤ እርሱ ከአንተ የተሻለ መሆኑን ስለሚያውቅ ነው። ማንን እየሸወድክ እንደሆነ እወቅ። ፀሐፊዋን ገላምጠህ ከኃላፊው ዘንድ ስትደርስ ምንም እንዳልተፈጠረ አድርግህ ጉዳይህን ልታወራ ትችላለህ። ወዳጄ አትሞኝ አንተ ከኃላፊው ዘንድ ከመድረስ በፊት እንኳስ የተናገርከው ያሰብከው ሁሉ ቀድሞ ከእርሱ ዘንድ ይደርሳል። ያወቅህ ይመስለህል፤ ግን ተሸውደሃል። በምትናገራቸው ነገሮች ሁሉ ምንነትህ ይገለፃል። ተረጋጋ! በማለፍ ውስጥ መተላለፍ መኖሩን አትርሳ። ዓለም ዝብርቅርቅ ናት። ከፀሐፊ እስከ አለቃዋ ድረስ ረጅም ጉዞ ሰፊ ልዩነት አለ፤ ዓለም አሽቃባጭ ናት የምንላት ነገር አለች ብሽቅ ሲለን።
ይልቅስ እጅና እግር በሌለው ነገር ሰው ለማሳመን አትሄድ ከንቱ ድካም ይሆንብሃልና። በነገራችን ላይ እጅና እግር ስል ትዝ ያለኝ ነገር ቢኖር ዘንድሮ በእግር ብቻ ሳይሆን በእጅህም መሄድ አለብህ የሚሉት ጣጣ እየመጣ ነው። ባለጉዳይ ሆነህ ፀሐፊዋም ከጥሩ መቀመጫዋ ብድግ ብላ ፈገግታ የተሞላበት የሞቀ ሰላምታ ሰጥታህ አለቃው ዘንድ ደረስክ አንበል። ደስ ይላል! ጉዳዬ በቅፅበት ሊሳካ ነው ብለህ አሰፍስሃል።
ኃላፊው ከተመቻቸው ወንበር ላይ ሆኖ እያዳመጠህ ነው፤ ድንቄም ማዳመጥ!፡ ጉዳይህን ዘርዝረህ አስረድተሃል፤ የሚጠበቅብህን መስፈርት በሙሉ አሟልተሃል። አሁን ግን ትንሽ መጠበቅ አለብህ ትባላለህ። ዛሬ የምትጨረሰውን ጉዳይ ነገ በጠዋት ብቅ ብለህ እንዲፈፀምልህ ይነገርህና እጅ ነስተህ፤ ከወገብህ ጎብጠህ ትወጣለህ። በነጋታው ማለዳ እንደተለመደው ከባለጉዳይ ሁሉ ቀድመህ ተገኝተሃል።
ወዳጄ አሁን ግን ትንሽ ጠብቅ ትባላለህ። መጀመሪያ መጥተህ መጨረሻ ትገባለህ። የሌሎች ጉዳይ ፈር ሲበጅለት አንተ በአንድ አዳር ጉዳይህ እንደ አዲስ ውስብስብ ሆኖ ታገኛለህ። ይፈፀምልሃል የተባለው ጉዳይ ሊሳካልህ ቀርቶ፤ የሕይወት ፍፃሜ ላይ የደረስክ እስኪመስልህ ድረስ እንደ አዲስ ግራ ትጋባለህ።
ቅድም እንደነገርኩህ ዘንድሮ በእግር ብቻ መሄድ አያወጣም። በእጅ መሄድ የሚባል ነገር አለ። እንዴት በእጅ እሄዳለሁ አይባልም። ይኬዳል እንጂ ለዚያውም መላ ሰውነትህን እስከሚያሳክክህ፤ እንደ ኪስ ሰውነትህ ጉርጉድ እስኪል ድረስ። ደግሞ ኪስ እና ባለጉዳይ ምን አገናኛቸው አትበል። የማይገናኙ ብዙ የተገናኙ ነገሮች አሉ። እሺ ኃላፊ እና ፀሐፊዋን ምን አገናኛቸው፤ አንተ እና ፀሐፊዋ ምን አገናችሁ፤ አንተና ኃላፊውን ምን አገናኛችሁ፤ አንተ እና ጉዳይህን ማን አስተሳሰራችሁ፤ ጭራሽ የማይታሰበውን አታስብ ወዳጄ።
አየህ ትኩረትህ በሚጠቅምህ ነገር ላይ አድርግ የምልህ ለዚህ ነው። የፀሐፊዋን መቀመጫ (ተሽከርካሪ ወንበር!) ማማር ሳይሆን፤ አካሄድህን አሳምር ብሎ የመከረህን ጓደኛ ምክር አትርሳው። እንደጊዜው በእግርህ ብቻ ሳይሆን በእጅህም ሂድ የሚለው ምክሩ በጣም ላትስማማበት ትችላለህ። ግን እኮ እየሆነ ያለው ይህ ነው። እንደ ዛፍ ቆራጩ የማይታለለውን ለማታለል ከምትሞክር ዝም በል። አለቃ ገብረሃናን የመሰሉ ሰዎች ሲገጥሙህና ምላሽ መስጠት በማትችልበት ሁኔታ ውስጥ ስትሆን ዝም በል፤ ነገም ሌላ ነው። በቃ ታገስ ዝም በል! ዝም አይነቅዝም ይባል የለ
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2014