“ኢትዮጵያ ታምርት” በሚል መሪ ቃል የአዲስ አበባ የስራ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት አምራቾችን አቅም የማሳደገያ የምክክርና ንቅናቄ መድረክ በቅርቡ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። መድረኩ የከተማዋን አምራች ኢንዱስትሪዎች አቅም ለማጎልበት ያቀደ እንዲሁም ችግሮቻቸውን አዳምጦ መፍታትን ያለመ ነው።
መድረኩ በተካሄደበት እለት ማልዶ በቦታው የተገኘው የመድረኩ ታዳሚ ውጤታማ የተባሉትን መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን እንዲጎበኝ ተደርጓል። በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ ሳንፎርድ ትምህርት ቤት አካባቢ የሚገኝ ደረጃውን የጠበቀ፤ ከውጭ የሚገባውን ሶፋ መተካት በሚችል ደረጃ ሶፋ የሚያመረት ኢንዱስትሪን፣ በመቀጠልም በርካታ የሰው ሀይል በውስጡ ይዞ የሚያሰራ አንድ ጋርመንት ተጎብኝተዋል።
ከጉብኝቱ በኋላም ከታዳሚው ጋር ለመወያየት በተዘጋጀው መድረክ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የስራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ዣንጥራር አባይ ባስተላለፉት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት በከተማዋ ከተያዘው እቅድ አንዱ ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› የሚለው ንቅናቄ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ከፍ ለማድረግ እንደሚረዳ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ንቅናቄው አሁን ላይ በከተማዋ ያሉትን 10 ሺህ 504 አምራች ኢንዱስትሪዎች በጥራትና ቁጥር ወደ 26 ሺህ 260 ለማሳደግ እንደሚረዳ አስገንዝበው፣ እነዚህ ኢንዱስትሪዎች አማካይ የማምረት አቅማቸውን ከ42 ነጥብ 6 በመቶ ወደ 85 በመቶ እንዲደርስ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱንም አመላክተዋል።
እንደ ምክትል ከንቲባው ገለጻ፤ ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሪ ገቢን ማሳደግ የከተማ አስተዳደሩ አንድ ስትራቴጂክ እቅድ ነው፡፡ ተኪ ምርት አምራች ኢንዱስትሪዎቸ እንዲሰፉ በማድረግ ከነበሩበት 418 ወደ 1 ሺህ 226 ለማሳደግ ታቅዷል። ወደ ውጭ የሚላከው የኢንዱስትሪ ምርት ከነበረበት 133 ወደ 381 በማድረስ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን ከነበረበት 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ወደ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የማሳደግ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው።
የኢንተርፕርይዝ ኃላፊዎች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትም በመድረኩ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ የከተማው አስተዳደርም ለቀረቡ ጥያቄዎች በወቅቱ መልስ ሰጥቷል፤ አስተዳደሩ እንደ መስሪያ ቦታ ያሉ የአንዳንድ ኢንተርፕራይዞችን ጥያቄዎች በአፋጣኝ የመለሰበት ሁኔታም ታይቷል፡፡ በእዚህ ጥያቄያቸው ከተመለሰላቸው መካከል በንቃናቄው ተሳታፊዎች ጉብኝት የተደረገበት ዘናጭ ጋርመነት አንዱ ነው።
በአዲስ አበባ ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ የሚገኘው ይህ ጋርመንት፣ በምርቶቹ ከውጭ የሚገቡ አልባሳትን ለመተካት እየሰራ ይገኛል። ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር የእለት ጉርስ ሆኖላቸዋል።
ወጣት አብረሃም ተስፋዬም በጋርመንቱ የስራ እድል ካገኙ ወጣቶቸ አንዱ ነው። በጋርመንቱ መስራት ከጀመረ ሁለት አመታተን አስቆጥሯል፡፡ ወጣቱ የሙያ ስልጠና አግኝቶ ወደ ስራ መሰማራቱ ሌላ የስራ አማራጭ እንደሆነለት ነው የሚናገረው። አብረሃም ዘናጭ ጋርመንት ከመቀጠሩ በፊት እየተማረ በትርፍ ጊዜው ደግሞ ጂብሰም እየሰራ ያገኘውን በመቆጠብ ለመለወጥ ጥረት ያደርግ ነበር፤ የኮንሰትራክሽን ስራዎች መቀዛቀዝ ግን በእዚህ ስራው እንደ ፊቱ መቀጠል አላስቻለውም፤ ስራ አጣ፤ ይሄኔ ታዲያ አስቀድሞ ወደ ጋርመንቱ የመጡ ጓደኞቹ ስለ ድርጅቱ መረጃ ሰጥተው ድርጅቱን እንዲቀላቀል አድርገውታል።
ከዚያም የልብስ ስፌት ስልጠና ይወስዳል፤ በየደረጃው እየሰለጠነ ውጤታማ ስራ መስራት የጀመረው ወጣት አብረሃም፣ ለነገ የተሻለ ሙያ ኖሮት የራሱን ስራ ለመፍጠር እያቀደ ስራውን በትጋት እያከናወነ መሆኑን ይገልጻል። በጋርመንቱ ደመወዝ እንደየደረጃው እንደሚከፈል ጠቅሶ፣ ሰራተኞቹ የሙያ ብቃታቸው እየጨመረ ሲሄድ ክፍያውም እየተጨመረለት እንደሚሰራ ተናግሯል።
ሌላዋ ወጣት ብርቱኳን ጌታቸው ከሶስት አመት በፊት ጀምራ በጋርመንቱ መስራት መጀመሯን ትናገራለች። በማታው የትምህርት መርሀ ግብር እየተማረች ቀን ቀን ለመስራት እያሰበች ባለችበት ወቅት ነው የቀን ስራ ስትፈለግ ጋርመንቱ ምንም ሙያ የሌላቸውን ወጣቶች አስልጥኖ ወደ ስራ የሚያስገባ መሆኑን ትሰማለች። የ23 አመቷ ወጣት ብርቱኳን በማታው የትምህርት መርሃ ግብር የቀለም ትምህርቷን፣ በቀን ደግሞ የሙያ ክህሎቷን አዳብራ ልብስ ሰፊ ለመሆን መቻሏን ታስረዳለች። አሁን ሁለት ሺ አምስት መቶ ብር እየተከፋላት ትምህርቷንና ስራዋን ጎን ለጎን ታስኬዳለች።
እንደ ወጣት አብረሃምና እንደ ወጣት ብርቱኳን አይነት በርካታ ስራ አጥ ወጣቶችን በአንድ አሰባስቦ የስራ እድል የፈጠረላቸው ጋርመንት ዘናጭ ጋርመንት ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ አባቴነህ ይባላሉ። በመካከለኛ እድሜ ክልል የሚገኙት እኚህ ሰው ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ቅጥርን ከመጠበቅ የራስን ስራ ፈጥሮ መንቀሳቀስ በሚል ሀሳብ ከጓደኛቸው ጋር መከረው አንድ የስራ ዘርፍ ላይ ለመሰማራት ተስማሙ።
ከሀረማያ ዩኒቨርሲቲ በኮኦፖሬቲቭ አካውንቲንግ የትምህርት ዘርፍ የተመረቁት እኚህ ሰው በወቅቱ ዲግሪ ኖሯቸው ስራ ያጡ ወጣቶችን በማደራጀት ወደ ስራ እንዲገቡ የማድረግ አሰራር ስለነበር በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት ተደራጅተው ለመስራት ተዘጋጁ። በስራ ጉጉት ላይ ጥቂት የቤተሰብ ድጋፍ ተዳመረ፡፡ የየካ ወረዳ አንድ ደግሞ የመስሪያ ቦታ ፈቀደላቸው፡፡ እነዚህ ወጣቶች በወጣትነት ሀይል ስራ ለመጀመር መንገዱ እየቀናላቸው መጣ፡፡ ከያዙት በተጨማሪ ከአዲስ ብደርና ቁጠባ በተገኘ ብድር 20 የስፌት ማሽኖች በመግዛት ቦታውን ለስራ ምቹ አደረጉት።
በ2010 ዓ.ም 12 ሰራተኞችን ይዞ ስራ የጀመረው ዘናጭ ጋርመንት፣ ሰራተኞቹ ከቴክኒክና ሙያ ተቋም በልብስ ስፌት የተመረቁ ናቸው፡፡ ስራው ሲጀመር እነሱ ያገኙትን የስራ እድል ለሌሎች ለማካፈል በማሰብ ከአዲስ ምሩቆች ጋር ስራ ይጀመራሉ።
መነሻ ካፒታሉ ሰማኒያ ሺ ብር ከቤተሰብ የተገኘ ብድር ሲሆን፣ ከአዲስ ብድርና ቁጠባ ለማሽን መግዣ 430 ሺ ብር ብድር ወስደው ማሽኖቹን ይገዛሉ። በቅድሚያ መርካቶ ውስጥ ያሉ ሱቆች የተቀበሉትን የስፌት ትእዛዘ በመቀበል ጨርቅ ከነጋዴዎቹ ጉልበት ደግሞ ከጋርመንቱ በማድረግ እየሰሩ የእጅ ዋጋ እየተከፈላቸው መሰራት ይጀምራሉ።
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ስራ አብረው ከጀመሩት ጓደኛቸው ጋር ቢለያዩም አቶ ተስፋዬ ስራውን አጠናክሮ በመቀጠል ማሳደግ ጀመሩ። ለአንድ አመት ያህል በእጅ ዋጋ ሲሰራ የቆየው ጋርመንቱ ከአመት በኋላ ሰራተኞቹን ወደ አርባ አሳድጎ የራሱን ምርት ማምረት ውስጥ ገባ። የሰራተኞች ብዛት በየጊዜው ቢቀያየርም፣ አሁን በወቅታዊነት በጋርመንቱ ከአንድ መቶ አስራ አራት በላይ ሰራተኞች በጋርመንቱ ይሰራሉ።
በኢንዱሰትሪ ፓርኮች የተመረቱ ጣቃ ጨርቆችን በመጠቀም ማሊያዎችን፤ ቲሸርቶችን፤ ፓካውቶች፤ የወንዶች የውስጥ ሱሪዎችን በምርጥ አጨራረስ በመስፋት ከውጭ ከሚገቡት ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን የሚችል ምርት እያመረተ መሆኑን አቶ ተስፋዬ ያብራራሉ። ብትን ጨርቁም በአገር ውስጥ የሚመረት በመሆኑ ምንም አይነት የውጭ ምንዛሪ ሳይፈልገ ስራውን ማካሄድ የሚችል ጋርመንት በመሆን ለአገር ኢኮኖሚ የበኩሉን አስተዋፅኦ እያደረገ የሚገኝ መሆኑን አስረድተዋል።
ጋርመንቱ አሁን እያመረተ ካለው በእጥፍ የማምረት አቅም እንዳለው የሚናገሩት አቶ ተስፋዬ የመስሪያ ቦታ ጥበት፤ ስራ ለማስፋፋት የገንዘብ አቅም ማነስ፤ ለብድር የሚጠየቅው የዋስትና ንብረት ከአቅም ጋር ያልተመጣጠነ መሆኑን እንደ ችግር ይጠቅሳሉ። በቅርቡ በተካሄደው ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› በሚል የንቀናቄ መድረክ ላይ እነዚህን ችግሮች ማንሳታቸውንና ፈጣን ምላሽ እንዳገኙም አስረድተዋል።
አሁን ከሚሰሩበት ሺድ ተጨማሪ ስለተሰጣቸው የማምረቻ ቦታ ጥበቱ ተፈትቶላቸዋል፡፡ የቦታ እጥረቱ መፈታቱ ብዙ ችግሮችን እንደፈታላቸው አቶ ተስፋዬ ይናገራሉ፡፡ ማሽኖችንም በማስመጣትና አሁን ካለው የሰው ሀይል እጥፍ ለመቅጠር እንዲሁም በምርት በኩል እጥፍ ለማምረት የሚያስችል ቁመና ላይ መድረሱን ይገልጻሉ።
አሁን ባለው አቅም በቀን እስከ ሶስት ሺ ልብስ የሚሰራ መሆኑን ገልፀው፣ በቀን ከሚመረተው ልብስ እስከ አስራ አምስት ሺ ብር ገቢ እንደሚገኝ አስረድተዋል። የማስፋፊያ ቦታ ሳይጨመር በቤቱ ውስጥ በአጠቃለይ 100 ማሽኖች ይዘው የሚሰሩ እንደነበር ጠቅሰው፣ ከገበያ ፍላጎቱ አንፃር ምንም እየተሰራ አለመሆኑን ነው ያስታወቁት።
እንደ ስራ አስኪያጁ ገለጻ፤ በጥቂት ጥሪት የተነሳው ይህ ጋርመንት አሁን 25 ሚሊየን አካባቢ የተመዘገበ ካፒታል ይዞ ይንቀሳቀሳል። ማስፋፊያው ተጠናቆ አቅሙ በእጥፍ ሲያደግ ደግሞ ለበርካቶች የስራ እድል ከመፍጠሩ ባሻገር ተኪ ምርቶችን በማምረት እነዚህን ልብሶች ለማምጣት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረት መቻሉን ያስረዳሉ።
በጥቂቱ ተነሰተው ለበርካቶች የስራ እድል መፍጠር የቻሉ፤ ለራሳቸው ሀብት አፈርተው አገርን ከድህነት ለመላቀቅ የሚያስችል ስራ የሚሰሩ፤ የአገርን የውጭ ምንዛሪ አገር ውስጥ ለማስቀረት የሚታተሩ በርካታ አነስተኛ መካከለኛና፤ ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎችን አገሪቱ አፍርታለች፡፡ እነዚህ ኢንዱስትሪዎች አሉብን የሚሏቸውን ችግሮች በመንቀስ ድጋፍ ከተደረገላቸው የበለጠ ለውጥ የማይመጣበት ምክንያት አለመኖሩንም አቶ ተስፋዬ ያብራራሉ።
በንቀናቄ መድረኩ ላይ የተለያዩ ሀሳቦች መነሳታቸውንና በዋንኛነት የፋይናንስ እጥረት ስራቸውን አስፋፍተው እንዳይሰሩ እንዳደረጋቸው አቶ ተስፋዬ አስታውሰው፣ ለብድሮች መያዣ ተብለው የሚጠየቁት ንብረት ከአቅም በላይ የሆነ የተለያዩ የቢሮክራሲ መስመሮች ስራውን በተቃና መልክ እንዳይሄድ እንዳደረገው ተናግረዋል።
የሀይል አቅርቦት ችግር፤ ሰፊ የማምረቻ ቦታ ማጣት፤ ስልጠናዎችን የሚፈለጉ አምራቾች የክህሎት ስልጠና አለማግኘታቸው፤ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና ሌሎችም በመድረኩ የተነሱ ሲሆን፣ ለዚህም ከመድረኩና የውይይቱ ታዳሚ የነበሩ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ በዚህ ብቻ ሳይወሰኑ ለተግባራዊነቱ መትጋት ግድ ይላል።
ከዘናጭ ጋርመንት ተሞክሮ እንደተረዳነውም እንዲህ አይነት ኢትዮጵያ ታምርት አይነት ንቅናቄዎች የአምራቾች ችግሮች አዳምጦ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ወሳኝ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ አስፈፃሚውም ሆነ አምራቹ የሚያከናውኑት ተግባር ለአገር ኢኮኖሚ ጠቀሜታው የላቀ ነው። አገር በሌሎች አገራት ምርቶችና ኢኮኖሚ ላይ ከመንጠልጠል የሚያወጣትን ተግባር ለማከናወን አምራቾችን መደገፍ የግድ መሆኑን በመረዳት መሰል እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው ይቀጥሉ በሚል መልእክታችን የዛሬውን አበቃን።
አሥመረት ብሥራት
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2014