ኢትዮጵያ ከምርቶቿ መካከል ጥቂት የማይባሉትን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ታገኛለች። በእዚህ የውጭ ምንዛሬም በአገር ውስጥ የማይመረቱና አስፈላጊ ምርቶችን እየገዛች ወደ አገር ውስጥ ታስገባለች።
ለእዚህ ግብይት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ከሚገኙት መካከል ቡና አንዱ ነው። ይህ አረንጓዴ ወርቅ እየተባለ የሚጠራው የውጭ ምርት ለኢትዮጵያ ዋንኛው የውጭ ምርት ሆኖ በርካታ አመታትን ዘልቋል። ይህን ተከትሎም ‹‹የኢኮኖሚ ዋልታ፣ የገቢ ምንጫችን›› እየተባለ ተዘምሮለታል።
ለበርካታ ዓመታት ቡናን ለውጭ ገበያ በመላክ የምትታወቀው ኢትዮጵያ ከዓለም የቡና ዋጋ መውደቅና ከግብይት ሰንሰለት መንዛዛትና ህገወጥ ግብይት ጋር ተያይዞ ባለፉት አመታት ከዘርፉ እምብዛም ተጠቃሚ ሳትሆን ቆይታለች።
መንግስት ከምርቱ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት እንደ አንድ ስትራቴጂ ሲጠቀም የቆየው ብዙ ቡና መላክን ነበር። በዚህም ብዙ ቢሰራም ከግብይት ጋር ተያይዞ ያሉት እንደ ሰንሰለት መብዛትና ህገወጥ ግብይት ያሉት ችግሮች ከምርቱ የሚገኘው ገቢ የሚጠበቀውን ያህል እንዳይሆን አርገውት ቆይተዋል።
መንግስት ባለፉት አመታት ባከናወናቸው ተግባሮች ይህን ሁኔታ መቀየር ችሏል። ይህን ተከትሎም ከቡና የውጭ ንግድ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ እየጨመረ መጥቷል። ዘንድሮም ኢትዮጵያ በታሪኳ አይታው የማታውቀውን ውጤት በማስመዝገብ ከዘርፉ ሁነኛ ተጠቃሚ መሆኗ እየተገለጸ ነው። በአስር ወራት ውስጥ ብቻ ከአንድ ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ከቡና የውጭ ንግድ መገኘቱም ይህንኑ ያመለክታል።
በበጀት ዓመቱ አስር ወራት ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ገበያ በከፍተኛ ዋጋ መሸጡን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ከትናንት በስቲያ መግለጫ በሰጠበት ወቅት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ አስታውቀዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ለዚህ ውጤትም ባለስልጣኑ በርካታ ተግባሮችን ማከናወኑን ይገልጻሉ። በኢትዮጵያ የቡና ኤክስፖርት ታሪክ በአስር ወራት ከአንድ ቢሊየን ዶላር በላይ መገኘቱን ጠቅሰው፣ ይህን ያህል ገቢ ሲገኝ በአገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያው መሆኑንም ነው ያስታወቁት። ዋና ዳይሬክተሩ የቡና ዋጋ በውጭ ገበያ ከፍተኛ አፈጻጸም ማሳየት እንዲችል በቡና ዘርፍ ተሰማርተው በቀጥታ እንዲሁም በተዘዋዋሪ መንገድ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በ2013/14 በጀት አመት በመጀመሪያው ወር ላይ ዘርፉን ውጤታማ ማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎችን አቅዶ ሰርቷል። በተለይም የውጭ ንግዱን ለማሳለጥ በቡና ልማቱና በግብይቱ ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮች ተለይተው እርምጃ ተወስዶባቸዋል። በቁርጠኝነት ወደ ሥራው መግባት በመቻሉም በኢትዮጵያ የቡና ገበያ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በበጀት ዓመቱ በአስር ወራት ብቻ አንድ ቢሊዮን 14 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ማግኘት ተችሏል።
በአስር ወራት ውስጥ 220 ሺ ቶን ለመላክ አቅደው 232 ሺ ቶን ቡና ወደ ውጭ ገበያ በመላክ በመጠን ከ105 በመቶ በላይ አፈጻጸም ማስመዝገብ ተችሏል። በገቢ ዕቅዱም እንዲሁ 810 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማስገባት ታቅዶም አንድ ቢሊዮን 14 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ተገኝቷል፤ አፈጻጸሙም የእቅዱ 112 በመቶ ነው። ይህም ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር፣ በመጠን 40 በመቶ በገቢ ደግሞ 62 በመቶ ብልጫ የተመዘገበበት ነው።
በሚቀጥሉት ሁለት ወራትም ከሶስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን ዶክተር አዱኛ ጠቅሰው፣ በአጠቃላይ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በድምሩ ከአንድ ነጥብ ሁለት እስከ አንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከቡና ብቻ ማግኘት እንደሚቻል አብራርተዋል።
ይህ ገቢም ኢትዮጵያ በአስር ወራት ውስጥ አጠቃላይ በውጭ ገበያ ካገኘችው ገቢ ጋር ሲነጻጸር 30 በመቶ የሚሆነውን ይሸፍናል ሲሉ ገልጸው፣ ከግብርናው ዘርፍ ጋር ሲነጻጸር ደግሞ 50 በመቶ ያህሉን ይሸፍናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በቡናው ዘርፍ ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገቧ የተለያዩ ምክንያቶች መኖራቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፣ ውጤት ለማስመዝገብ ባለስልጣኑ ካከናወናቸው ተግባሮች መካከል በግብይት ሰንሰለት ውስጥ ያሉትን ችግሮች ነቅሶ ማውጣት አንዱ መሆኑን አስታውቀዋል። በተለይም በቀጥታ ትስስር አርሶ አደሮችንና አቅራቢዎች ምርታቸውን በቀላሉ መቀባባል እንዲችሉ መደረጉን ተናግረዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ ጥራቱን የጠበቀ ቡና በመጠንም እንዳይባክን አርሶ አደሮች ለአቅራቢዎች፤ አቅራቢዎች ደግሞ በቀጥታ ለላኪዎች ማስረከብ እንዲችሉና ላኪዎችም ዱካውን ተከትለው መለየትና ማወቅ የሚቻል ምርት ለዓለም ገበያ ማቅረብ የሚያስችላቸውን ስርዓት በመዘርጋት የኢትዮጵያ ቡና በተሻለ ዋጋ በዓለም ገበያ ላይ እንዲሸጥ ተደርጓል።
እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል በቁርጠኝነት መሥራት በመቻሉ የተገኘ ውጤት ስለመሆኑ ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በተለይም በግብይት ሥርዓት ውስጥ የነበሩ ለኤክስፖርቱ ማነቆ ሆነው የቆዩ አሰራሮችን በመፈተሽ በማስተካከልና በተለይም የኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድን በሶፍትዌር በመከታተል ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል። ቡና ጭነው ከመንገድና ከመሥመር የሚወጡ ባለሃብቶች እንዲሁም ተሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ የኮንትሮባንድ መጠኑ እንዲቀንስና ቡና ወደ ዓለም ገበያ በቀጥታ እንዲገባ ተሠርቷል ሲሉም ያብራራሉ። በተጨማሪም እምነት በመፍጠር ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የተሰራው ሥራ ለተመዘገበው ውጤት የጎላ ድርሻ እንዳለውም ነው ዋና ዳይሬክተሩ ያመለከቱት።
ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት ያለው የዓለም የቡና ገበያ ለገቢው መጨመር ሌላው ምክንያት ነው። ይህም ለተገኘው ገቢ 20 በመቶ ድርሻ አለው ይላሉ። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የቡና አቅርቦት መጠን መጨመሩ ሲሆን ይህም ከ70 በመቶ ድርሻ በላይ ነው። ሌሎች የጊዜና የጥራት ሁኔታዎችም የራሳቸው ድርሻ አላቸው። አሁን ላይ ለተገኘው ውጤት የአንበሳውን ድርሻ የሚይዙት የአቅርቦት መጠን መጨመርና የዓለም ቡና ገበያ ዋጋ መጨመር ናቸው።
የስፔሻሊቲ ቡና በድርድርና በስምምነት፤ የኮሜርሻል ቡና ደግሞ በጨረታ የሚሸጥ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የዓለም የቡና ዋጋ መጨመር ጠቀሜታው ለኮሜርሻል ቡና እንደሆነ አስረድተዋል። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ቡና ወደ ስፔሻሊቲ ቡና ገበያ በመሸሽ በየጊዜው የሚቀያየረውን የዓለም የቡና ዋጋ ለመቋቋምና የተሻለ ምርት በተሻለ ዋጋ ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል።
ለዚህም የዛሬ ሁለት ዓመት ይህን ስትራቴጂ በመያዝ ወደ ሥራው መገባት መቻሉን ጠቅሰው፣ በተለይም በአሁኑ ወቅት 60 በመቶ የሚደርሰው የኢትዮጵያ ቡና በስፔሻሊቲ ገበያ የሚሸጥ መሆኑን ገልጸዋል። 40 በመቶ የሚያህለው ቡና ደግሞ በኮሜርሻል ገበያ ይሸጣል ይላሉ። ይህ አይነቱ ግብይት በየጊዜው የሚቀያየረውን የዓለም የቡና ገበያ ዋጋን ለመቋቋም እንደሚያስችል ተናግረው፣ ወደ ስፔሻሊቲ ቡና ገበያ በስፋት መግባት እንደሚያስፈልግ ዋና ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ በአሁኑ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በተጠና መልኩ ከኮሜርሻል ይልቅ ወደ ስፔሻሊቲ ቡና ኤክስፖርት ሽግግር እየተደረገ ነው። ይህም አሰራር በየጊዜው እየተቀያየረ የሚገኘውን የዓለም የቡና ዋጋ ለመቋቋም እንዲሁም ጥራት ያለው ቡና በማቅረብ የተሻለ ገቢ ማግኘት እንዲቻል አድርጓል። በግብይት ውስጥ ያሉ ማነቆዎችን መፍታት እና የቀጥታ ትስስር ተግባራዊ መደረጉም ለተገኘው ገቢ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የገበያ ልማትና ቁጥጥር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ኡመር በተለይ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ግብይቱን የማዘመንና ፍትሃዊ የማድረግ እንዲሁም እሴት የመጨመር ተግባርን በማከናወን አገሪቷ ከዘርፉ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ ግብ ይዞ እየሠራ መሆኑን ይገልጻሉ። አጠቃላይ ግቡን ሊያሳኩ የሚችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
የኢትዮጵያ ቡና በአሁኑ ወቅት ላስመዘገበው ውጤት ምርቱ ሳይባክን ከምርት እስከ ኤክስፖርት መዳረሻ ድረስ በትክክል መውጣት የሚያስችለውን ሥራ መሥራት መቻሉ እንደሆነ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ይገልጻሉ፤ በአሁኑ ወቅት ከዘርፉ ከፍተኛ ውጤት መመዝገብ እንዲችል በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውንም አስታውሰዋል።
ባለስልጣኑ ከሠራቸው ሥራዎች መካከልም አንደኛው አገራዊ ግብረ ሃይልን የማጠናከር ሥራ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደራሽ ቁጥጥር በማድረግ ቡና እንዳይባክን ማድረግ ተችሏል። ሶስተኛው በሶፍትዌር ሲስተም በመገንባት ሁለቱን በመደገፍ ቡናው ሳይባክንና ከመጣበት ቦታ በቀጥታ ወደ መዳረሻው እንዲደርስ የማድረግ ሥራ ነው።
ከግብረሃይል አንጻር በተለይም ከፌዴራል ፖሊስ፤ ከጉምሩክ ኮሚሽን፤ ከአዲስ አበባ ከንግድ ቢሮ፤ ከኦሮሚያ፣ ከደቡብ ምዕራብና ከሲዳማ ብሔራዊ ክልል መንግሥት ጋር በጋራ በመሆን የተጠናከረ የቅንጅት ኮሚቴ በማዋቀር ኮሚቴዎቹም ከታች ያሉትን ግብረሃይሎች በማጠናከር ትርጉም ያለው ሥራ ተሰርቷል። በቁጥጥርና ክትትል ሥራውም ህገወጥ ነጋዴዎችን በመቅጣት አጠቃላይ ከ83 ሚሊየን ብር በላይ በቅጣት ገቢ ማግኘት ተችሏል።
እስካሁን በነበረው አሠራር የኢትዮጵያ ቡና ግብይት የላላ ቁጥጥር የነበረውና በትክክልም ቡናው የት እንደደረሰ የማይታወቅበት ሁኔታ እንደነበር ያስታወሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ በተለይም በምርት ገበያ ላይ ኮንትሮባንዱ በዝቶ ቡናው ወደ አገር ውስጥ ይመለስ እንደነበርም አስታውሰዋል። በአሁኑ ወቅት ባለስልጣኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ማከናወኑን ተከትሎ ችግሮችን ማቃለል ችሏል ይላሉ። የጥራትና ቁጥጥር ሶፍትዌሮችን በመገንባት የአገሪቷ ቡና የት እንደሚገኝ፤ ከየት እንደተሰበሰበና የት እንደደረሰ በመከታተል እርምጃ እየወሰደ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም መሰረት 18 የሚደርሱ ቡና የጫኑ መኪኖች ቡናውን የት እንዳደረሱ ያልታወቁ ከተመረተበት ቦታ አንስተው ወደ ኤክስፖርት ማዘጋጃና ማከማቻ ያላደረሱ መሆኑ ተጠርጥሮ ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመሆን በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን ይገልጻሉ። ከእነዚህም መካከል ስድስት የሚደርሱ ተሽከርካሪዎች 77 ቶን የሚደርስ ቡና በመሰወራቸው ማስረጃ ተገኝቶባቸው በቁጥጥር ሥር እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንደገለጹት፤ የቡና ህገወጥ አሰራርን ለመከላከል በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በገበያ ልማትና ቁጥጥር ዘርፍ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ ሲሆን፣ በተለይም ህገወጦችን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የተለያዩ ስልቶች ተቀይሰው ተግባራዊ እየተደረጉ ናቸው። በተለይም ህገወጦችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ሶፍትዌር እንዲበለጽጉ ተደርጎ ወደ ሥራ ከተገባ በኋላ ህገወጥ አሰራሮች ቀንሰዋል፤ ህገወጦችንም በቀላሉ ለይቶ ለመያዝ ተችሏል።
የኢትዮጵያ ቡናን በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ መዝለቅ እንዲችል በጥራት ከማምረት ባለፈ ገበያ ውስጥ ሰብሮ ለመግባት ሁለት ስትራቴጂዎችን ተቀርጸው እየተሰራ መሆኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፤ አንደኛ ነባር የገበያ መዳረሻዎች የሆኑትን አውሮፓ አገራትን ጨምሮ በዋናነት በሰሜን አሜሪካ፣ በደቡብ ኮርያ፣ በጃፓን፣ ጀርመንና በጣሊያን ገበያ ውስጥ መቆየት መሆኑን አስታውቀዋል። በሁለተኛው ስትራቴጂ መሰረት ደግሞ የኢትዮጵያ ቡናን በማስተዋወቅ የተሻለ ገበያ ለማግኘት አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎች የማፈላላግ ሥራ በስፋት እንደሚሠራም ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅትም ቻይና እና ታይዋን አዳዲስ የገበያ መዳረሻ እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቅሰው፣ በቀጣይም በዚህ ላይ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2014