የ አንዲትን ሀገር ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ መስተጋብር ወደ ተሻለ ደረጃ ከሚያሸጋግሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ወጣቶች ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳሉ። ወጣቶች በሀገራችን የፖለቲካ ታሪክ በተለይም ከ1966 ዓ.ም ወዲህ ጨቋኝ ስርዓቶችን በማስወገድ በየወቅቱ ለተከፈቱት አዳዲስ ምዕራፎች ግንባር ቀደም ሚና ተጫውተዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት የነበረውን የመልካም አስተዳደር ብልሹነት፣ ሙስናን፣ ግለኝነትን፣ ቡድናዊነትንና ምዝበራን በመቃወም በየአካባቢው የሚገኙ ወጣቶች አደባባይ በመውጣት የተቃውሞ ድምጻቸውን አሰምተዋል፤ መስዋዕትነትም ከፍለዋል። እንደ ቄሮ፣ ፋኖ፣ ዘርማ፣ ኤጄቶና የመሳሰሉት አዳዲስ የወጣት አደረጃጀቶችም ተፈጥረዋል። ይህ የወጣቶች የተደራጀ እንቅስቃሴ ኢህአዴግ እራሱን እንዲያስተካክልና የህብረተሰቡን ጥያቄዎች እንዲመልስ ጫና አሳድሯል።
ወጣቶች አሁን ለታየው ለውጥ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን የሚጠራጠር አካል ባይኖርም ዛሬ ላይ የሚታይባቸው የአድራጊ ፈጣሪነት ባህሪ በብዙዎች ዘንድ አደረጃጀታቸው የሀገር ስጋት ነው ወይስ ብርታት የሚል ጥርጣሬ አሳድሯል። ይህን በተመለከተም አዲስ ዘመን የተለያዩ ምሁራንን በማነጋገር ተከታዩን አስተያየት ሊያስነብባችሁ ወዷል። አቶ ደርሶልኝ የእኔአባት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል ዲን ናቸው።
እንደ እርሳቸው ገለፃ ወጣት በየትኛውም ሀገር ፖለቲካዊ ሁኔታ ውስጥ የለውጥ ማዕከል ነው። በሀገራችን በተደረጉት ለውጦችም ወጣቱ የለውጡ እንብርት ነበር ይላሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን ለውጥ ለማምጣት በተደረገው እንቅስቃሴም በተለያዩ አካባቢዎች የተደራጁ ወጣቶች በሂደቱ ንቁ ተሳታፊ በመሆን የጎላ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ይላሉ። የመንግስት አሠራርን በመቃወም ዛሬ አዲሱ አመራር ላሳያቸው የዴሞክራሲ ጭላንጭሎች የድርሻቸውን ተወጥተዋል።
አሁን አሁን ከመስመር የወጡና ሀገሪቱን አደጋ ላይ የጣሉ ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎች በወጣቱ እየተፈጸሙ እንዳሉም ይናገራሉ። እንደውም በአንዳንድ አካባቢዎች የመንግስትን ሚና በመንጠቅ ‹‹በእኛ ተመሩ›› የሚል አመለካከትን ሲያራምዱ ይታያል ብለዋል። ወጣቶች የክልል አስተዳደሮችንና ከንቲባዎችን ሳይቀር እስከ ማዘዝ ደርሰዋል የሚሉት ምሁሩ ይህ ሥርዓት አልበኝነት በብሄሮች መካከል ያለውን መገፋፋት በጣም እንዲጦዝ አድርጓል ሲሉ ይወቅሳሉ።
ወጣቶች ‹‹ጨቋኝ መንግሥትን አስወገድን›› ብለው በተናገሩ ማግስት መልሰው እራሳቸውም የጨቋኝነት ባህሪን እየተላበሱ መጥተዋል። ሻሸመኔ፣ ጅግጅጋ፣ ቡራዩ፣ ጉጂ፣ ሀዋሳ፣ ጎባ፣ ቴፒ፣ ቤኒሻንጉል፣ ጉራጌ፣ ጎንደር ወዘተ የተከሰቱት አሰቃቂ ግድያዎችና መፈናቀሎች አብዛኛዎቹ ይመሩ የነበረው በወጣቱ ነበር። ለዚያውም ለራሳቸው ሥም ሰጥተው በይፋ በሚንቀሳቀሱ ቡድኖች። በአማራ ክልል መንገድ በመዝጋት የትራንስፖርት አገልግሎትን በማስቆም የንግድ ግንኙነትና ማህበራዊ መስተጋብር እንዳይኖር ተደርጎ የነበረውም በወጣቶች /በፋኖዎች/ ነው።
ከዚህም አልፈው መኪኖች የጫኑትን የምግብ እህልና ሸቀጣሸቀጥ እያወረዱ እስከ መከፋፈል ደርሰዋል። በቅርቡም የሀዋሳ ኤጄቶዎች ጥያቄያችን መልስ አላገኘም በሚል የሥራ ማቆም አድማ በመጥራት የመንግሥት ሠራተኞች የዘወትር ሥራቸውን እንዳያከናውኑ አድርገዋል። እንደ አቶ ደርሶልኝ አስተያየት ከምስራቅና ከምዕራብ ጉጂ ዞን ቤት ንብረቱን ትቶ የተሰደደው የጌዲዎ ህዝብ ለሰው ሰራሽ ረሀብ እንዲጋለጥ ያደረጉት ወጣቶች ናቸው።
ቄሮ ነን የሚሉ ወጣቶች የኮዬ ፈጬ የጋራ መኖሪያ ቤት የሚገባው ለአካባቢው ተፈናቃዮች ነው ሲሉ ያሳዩት ያልተገባ ሁኔታ እና አዲስ አበቤዎችም ‹‹የመዲናዋን ህልውና ማስጠበቅ የሚገባን እኛ ነን›› በማለት እንደራጃለን እያሉ ነው። ወጣቶች ይሁን ያሉትን እንደሚያደርጉና ‹‹መንግስትን መጠምዘዝ እንችላለን›› በሚል እሳቤ ፈላጭ ቆራጭነታቸው እየጨመረ መጥቷል። ይህ ድርጊት ወደ የት እያመራ ነው ስንል ‹‹አንቺው ታመጪው …›› አንዲሉ ለለውጡ አስተዋጽኦ አድርገዋል የተባሉት ወጣቶች ራሳቸው የመንግስትን መልካም ጅምር ወደ ኋላ እየጎተቱት ነው።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ ዕጣ ፈንታው በወጣቱ እጅ እንዳለና መንግስት ዋስትና ሊሰጠው እንዳልቻለ እያሰበ ነው የሚሉት አቶ ደርሶልኝ ሌላው ቀርቶ የጸጥታ አስከባሪው ኃይል ስራውን በአግባቡ እየተወጣ አይደለም፤ለጉዳዩ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ አይቶ እንዳላየ መሆንን ይመርጣልም ብለዋል። በወጣቶች የሥነምግባር ችግር ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥሩትም ማህበራዊ ሚዲያዎችና የአክቲቪስቶች ንግግር እንደሆኑ ያስረዳሉ። በአሁኑ ወቅት በማህበራዊ ሚዲያ በሚተላለፉ ሀሰተኛና ጥላቻ አዘል መልዕክቶች ወጣቶች ምክንያታዊ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል ይላሉ አቶ ደርሶልኝ።
ማህበራዊ ሚዲያ አላስፈላጊ የተቃውሞ ሰልፎችንና አድማዎችን ለማነሳሳት አጋዥ መሳሪያ ሆኗል። ከዚህም በተጨማሪ አክቲቪስቶችና አንዳንድ ኃላፊነት የሚጎድላቸው ሚዲያዎች በወጣቶች ግብታዊ ድርጊት አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ይጠቁማሉ። የመንግስት ሚና የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ማክበርና ህግን ማስከበር እንደሆነ የገለጹት አቶ ደርሶልኝ መንግስት የሚከተለው ከልክ ያለፈ ትዕግስት ወጣቶች ላልተፈለገ ጥፋት የሚዳረጉበት እንጂ የሚማሩበት እንዳልሆነ አስረድተዋል።
‹‹መንግሥት ለጥቂት ህገ ወጦች ያለው ሆደ ሰፊነት ለብዙ ሰላማዊ ሰዎች ሞት፣ መፈናቀልና ረሀብ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ዛሬ ላይ ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያሉት የኢትዮጵያ ህዝቦች በሥጋት ውስጥ ናቸው፤ እናም የሀገሪቱን ሰላም በማስጠበቅ መንግስት ሰላማዊ ህዝቦችን በመያዝ አካሄዱን ማስተካከል ይጠበቅበታል፤›› ብለዋል አቶ ደርሶልኝ።
የክልል መስተዳድሮች ራሳቸው መጠየቅ የሚፈልጉትን ጥያቄ በእነዚህ በተደራጁ ወጣቶች እያመካኙ የሚጠይቁ ይመስለኛል የሚሉት አቶ ደርሶልኝ ይላሉ። አንዳንድ ግዜ የክልል መንግስታት ፍላጎትና የወጣቶቹ ጥያቄዎች ሲመሳሰሉ ይታያል፤ ስለዚህ አክቲቪስቶቹ ብቻ ሳይሆኑ የመንግሥት አካላትም የጉዳዩ ተዋናይ ናቸው የሚል አቋም አለኝ ብለዋል። ሌላው አስተያት ሰጪ አቶ ኪያ ጸጋዬ ናቸው፤ የህግ ባለሙያና በህግ ጉዳዮች ዙሪያ ጥናታዊ ፅሁፎችን የሚያቀርቡ ወጣት ምሁር ናቸው።
እንደ እርሳቸው ገለፃ ወጣቶች አሁን ከተጀመረው ለውጥ ጀርባ የነበራቸው ሚና ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነው።
ወጣቶች ከታችኛው እስከ ላይኛው መዋቅር ድረስ ተንሰራፍቶ ያለውን ብልሹ አሰራርና ሙስናን መቃወማቸው መንግስት እራሱን ቆም ብሎ እንዲያይና አካሄዱን እንዲያስተካክል ትልቅ አስተዋጽኦ እንደነበረውም አስታውሰዋል። ይህ ሁሉ ሆኖ ኢህአዴግም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን የድርጅቱ ሊቀመንበር አድርጎ ከመረጠ ወዲህ የወጣቱም ሆነ የህዝቡ ጥያቄዎች መልስ እየተሰጣቸው፣ ሀገሪቱ በዲሞክራሲም ይሁን በመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ በዚህ አጭር ግዜ ውስጥ ይፈጸማሉ ተብለው የማይገመቱ መልካም ስኬቶችን ማስመዝገቧን አስታውሰዋል።
ለአብነትም የሚዲያውን ነጻነት፣ የፖለቲካ እስረኞች መፈታት፣ የዲፕሎማሲ ስኬቶችን፣ ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎችንና የመሳሰሉትን ለአብነት ጠቅሰዋል። ‹‹‹ዛሬ ግን እኛ ለውጡን ስንመራ ነበር፤ ውጤትም የመጣው በእኛ ትግል ነው››› የሚል አስተሳሰብ በመያዝ ሀገሪቱን በሚፈልጉት መንገድ ለመዘወር የሚሹ አካላትን እያስተዋልን ነው። ይህ አካሄድ ደግሞ አደገኛ ነው፤ ስለዚህ ሀይ ሊባል ይገባል›› ሲሉ ተናግረዋል።
የዓለም ሀገሮች እንደ ሀገር መቆም ከጀመሩበት ከ13 እና ከ14ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በተለይ በአውሮፓ ህግን የሚያስከብረው ዋና አካል መንግሥት ነው። በኢትዮጵያም ሲሰራበት የኖረ ነው። ህግ አውጭ ህግ ተርጓሚና ህግ አስከባሪ ተቋማት ባሉበት ሀገር ወጣቶች እየተደራጁ የእነዚህን ተቋማት ሚና በመውሰድ ሀገሪቱን ለመምራት መሞከራቸው ዝም ሊባል አይገባም ሲሉ አቶ ኪያ ያስገነዝባሉ።
የሰላም ባለቤት ህዝብ ነው፤ ያም ሆኖ ጥቂት ግለሰቦችና ቡድኖች በቡዙኃኑ ውስጥ ተሸጉጠው የሚፈጽሙት ሴራ ጉዳት እያስከተለ ስለሚገኝ መንግስት ከሰላማዊው ህዝብ ጋር ተባብሮ ህግን ማስከበር ይኖርበታል ሲሉም ይመክራሉ። በሚታየው ችግር ልክ መንግስት የኃይል እርምጃ ቢወስድ ሀገርን ከማዳን አንጻር እንደሆነ ሊታሰብ ይገባል የሚሉት አቶ ኪያ መንግስት አንባገነን ሆነ ብሎ የሚፈርድ ሰው ይኖራል ብዬ አልገምትም። እንደውም የሚያሥተቸው የመንግስት ትዕግስት ከልክ ያለፈ መሆኑና የብዙ ዜጎችን ዋጋ ያስከፈለ ነው ብለዋል።
‹‹ሰው ከገባው በትምህርት ይማራል። ካልገባው በቅጣት እንዲማር ተደርጎ ሀገር ይከበራል እንጂ ለነውጠኞች እንደፈለጋችሁ ሁኑ ተብሎ ሊተው አይገባም። የሩዋንዳን ያለፈ ታሪክ ዞርብሎ መመልከት ያስፈልጋል። ብልህ ከሆንን ከዚህ መማር አለብን እንጂ ችግር ወልደን ከችግራችን ልንማር አይገባም። በእርስ በእርስ ጦርነት እልቂት እንጂ አሸናፊ አይኖርም ሲሉ መክረዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2011
ኢያሱ መሰለ