ሕወሓት ሰሞኑን አዲስ ጦርነት ለመጀመር ለትግራይ ሕዝብ ጥሪ አቅርቧል። ጥሪው ፈጽሞ ያልተጠበቀ ነው ባይባልም፣ አንዳንዶች የሰላም ድርድር እየተካሄደ ነው የሚል ጭምጭምታ ከመሰማቱ አንጻር አንዳች በጎ ነገር ይፈጠራል በሚል በነበራቸው ተስፋ ላይ ቀዝቃዛ ውሃ የቸለሰ ጥሪ ነው። አሁን ላይ ለሦስተኛ ዙር ጦርነት መንገድ የከፈተ ይመስላል። ነገሩ አሳዛኝ እና አሳሳቢም ነው። በዚህም የተነሳ አንዳንድ ወገኖች በማህበራዊ ሚዲያ ጦርነት አንፈልግም የሚል ቅስቀሳ እያካሄዱ ነው።
በመሠረቱ ጦርነትን አለመፈለግ የጤነኛ ሰው ምልክት እንደመሆኑ ትክክል ነው። እንዲያውም የሚበረታታ ጉዳይ ነው። ነገር ግን ከዚህ ሀሳብ ጋር ተያይዘው ሊነሱ የሚገቡ አንዳንድ ጉዳዮች አሉ። ዋነኛው ጉዳይ ሰላም በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ ሊመጣ የሚችል ነው ወይ የሚል ጥያቄ ነው። መልሱ ደግሞ አይደለም የሚል ነው።
የአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ ሰላምን አያመጣም። ምክንያቱም በባህሪው ጠብ የሁለት ወገኖችን ተሳትፎ ይፈልጋልና። አንድ ነገር ከራሱ ጋር ሊጣላ አይችልም። እገሌ ከራሱ ጋር ተጣልቷል ቢባል እንኳ ሰውየው የተጣላው ከራሱ ጋር ሳይሆን በሰውየው ውስጥ ያሉ ሁለት ስሜቶች ወይም ሁለት ሀሳቦች ወይም ስሜቱ እና ሀሳቡ ተጋጭተዋል ማለት ነው። ስለዚህም ለጠብ ቢያንስ ሁለት ወገን ያስፈልጋል።
ለጠብ ሁለት ወገን ካስፈለገ ለሰላምም ሁለት ወገን እንደሚያስፈልግ እርግጥ ነው። ይህን ሀሳብ አንድ ግለሰብ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በአንድ የነጮች አባባል በጥሩ ሁኔታ ገልጾታል። ነጮች it takes two to tango (ታንጎ ለመደነስ ሁለት ሰው ያስፈልጋል) ይላሉ። ታዲያ ሰላም እንፈልጋለን፤ ጦርነት መሮናል ብለን ጩኸት ስናሰማ ጩኸቱ ለአንዱ ወገን ነው ወይስ ለሁለቱም የሚለውን መለየት ያስፈልጋል። ጩኸቱ ወደ አንድ ወገን ብቻ ከሆነ ጉዳዩ ሰላም ፈላጊነት ሳይሆን አንዱን ወገን የመጫን እና የማዘናጋት ጉዳይ ይሆናል።
ከዚህ ቀደም ስለ ሰላም ሲካሄዱ የነበሩ እንቅስቃሴዎች መሠረታዊ ችግርም ይሄው ነው። ሁሉም አንድ ወገን ላይ ብቻ ትኩረት ያደረጉ እና ሌላኛውን የዘነጉ ነበሩ። አብዛኞቹ ደግሞ ለሕወሓት ስልታዊ ድጋፍ ማድረጊያ መንገዶች ነበሩ። እንዲህ ዓይነት የሰላም ጥሪ ብዙም ፋይዳ የለውም። አደገኛም ነው። አንዱ አጥቂ አንዱ ተጠቂ በሆነበት ሁኔታ ላይ ተጠቂውን አንተ ታገስ ማለት ሰላም ፈላጊነት ሳይሆን ለአጥቂው ወገንተኛ መሆን ነው። ስለዚህም የሰላም ጥሪ ስናስተላልፍ እና ጦርነትን ስንቃወም የሚከተሉትን ነገሮች ከግንዛቤ ልንጨምር ይገባል።
አንደኛ ጉዳይ፤ ጦርነቱ መነሻው ምን ነበር የሚለውን እንገንዘብ። እንዲሁ በደፈናው ሰላምን እፈልጋለሁ ማለት ሰላም ፈላጊነት ሳይሆን አስመሳይነት ነው። የጦርነቱን መንስኤ ያላወቀ ሰው የጦርነቱን መፍትሄም ሊያውቅ አይችልም። መፍትሄውን ካላወቅን ደግሞ እየተመኘን ያለነው ጊዜያዊ ጸጥታን እንጂ ዘላቂ እፎይታን አይደለም ማለት ነው። ስለዚህም ሰላም ፈላጊ ወገን ነገርን ከስሩ ውሀን ከጥሩ የተረዳ ሆኖ የጦርነቱን ቆስቋሽ አካል መለየት እና አነሳሽ ምክንያቱንም ማወቅ አለበት። እንደዚያ ሲሆን ለአሁኑ ጦርነቱን ከማስቆም ባለፈ ለከርሞውም ደግሞ እንዳይነሳ ማድረግም ይቻላል።
ሁለተኛ፡- ጦርነቱን የሚቃወም ሰው ወይም አካል በግልጽም ይሁን በስውር ለአንድ ወገን የሚያደላ ስሜት ካለው ያን መተው አለበት። እስካሁን እንዳየነው የብዙዎች ሰላም ፈላጊነት ከነፃ አእምሮ የመነጨ አይደለም። በተቃራኒው በስውር ወደ አንድ ወገን ያደላ ነው። ይህም ሳያስቡት ለአንድ ወገን ያላቸው ወገንተኝነት በየጊዜው አምልጦ ሲወጣ ይታያል። አንዱን ወገን ፍጹም ተበዳይ ማድረግ እና ጥፋቱን ሁሉ ወደ አንድ ወገን ከመደፍደፍ አንስቶ አንዱን ወገን በአደባባይ ወቅሶ ሌላኛውን በምስጢር እስከማበረታታት የሚዘልቅ ኢ ፍትሀዊነት በብዙ ሰላም ፈላጊ ነን የሚሉ ኃይሎች ዘንድ ታይቷል። እንዲህ ዓይነት ሰላም ፈላጊነት ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል።
ሦስተኛ፡- ጦርነቱን ከሞራል አንጻር ብቻ ሳይሆን ከፖለቲካ ከኢኮኖሚ ከማህበራዊ ከሃይማኖታዊ ጎኖቹ አንጻር ለያይተን እንረዳ። ጦርነቱ አስፈላጊ አይደለም የሚል ሰው ብዙውን ጊዜ ጉዳዩን የሚያየው ከሞራል አንጻር ነው። ነገሩን ከሞራል አንጻር ካየነው የትኛውም ዓይነት ጦርነት ትክክል አይደለም።
ጦርነት ብዙ አነሳሽ ምክንያት እና ብዙ ገጽ አለው። ስለዚህም ሁሉንም ለመረዳት መሞከር ያስፈልጋል። ብዙ ጊዜ ሰላም ፈላጊ ነን የሚሉ ሰዎች ጦርነቱን በደፈናው መቃወማቸው ብቻ የሞራል ልዕልና እንደሚሰጣቸው ያምናሉ። ይህ ስህተት ነው። እንዲያውም ያልገባውን ነገር የሚቃወም ሰው የሞራል ልዕልና የሌለው ነው። ስለዚህም ጦርነቱን ስንቃወም በየትኛው ምክንያት እንደሆነ መለየትና በጥልቀት ማወቅ ያስፈልጋል።
ጦርነት የሚያፈርሳቸው አገራት እንዳሉ ሁሉ በጦርነት ቅርጽ የያዙ አገራትም አሉ። ጦርነት ሰብአዊ ኪሳራ ቢያስከትልም ፖለቲካዊ ትርፍ ሊያመጣ ይችላል። ጦርነት ኢኮኖሚያዊ ድቀት ቢያስከትልም ዘላቂ አገራዊ መሠረትንም ሊፈጥር ይችላል። ለዚህም ነው ትልልቆቹ ኢምፓየሮች አሜሪካንን ጨምሮ በማያቋርጥ ጦርነት ውስጥ የሚኖሩት።
ስለዚህም ይህን ጦርነት ስንቃወምም ከየትኛው መነሻ ላይ ቆመን በምን ምክንያት እንደምንቃወም መለየት አለብን። ከዚያም በኋላ ጦርነቱን የምቃወመው በዚህ በዚህ ምክንያት ነው ብሎ ማስረዳት እና ያን ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ እንዴት መፍታት እንደሚቻል የመፍትሄ ሀሳብ ማዋጣት ይቻላል። አልያም እንዲሁ ሰላም ወዳድ ነኝ ወይም የሞራል ልዕልና አለኝ ለማለት ብቻ የሚደረግ ጦርነትን የመቃወም እንቅስቃሴ የአፍ ጂምናስቲክ ወይም ልዩ ሆኖ የመታየት አባዜ ብቻ ይሆናል።
በመጨረሻም ጦርነትን ስንቃወም በአፍ ወይም በማህበራዊ ሚዲያ ብቻ ሳይሆን በተግባርም የሰላም ዘብ መሆናችንን በማሳየት ነው። ሰላም መልኩ ብዙ ነው። አሁን እንደሚካሄደው ዓይነት የለየለት ጦርነት እንዳለ ሆኖ ሌሎች ብዙ ዓይነት ጦርነቶች ይካሄዳሉ። በሌሎች ክልሎች መንግሥት ከሌሎች አነስተኛ አሸባሪዎች ጋር የሚያደርገው ጦርነት፤ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል እና በውስጣቸው የሚካሄድ የአንጃ ጦርነት፤ በንጹሃን እና በሙሰኞች መካከል የሚደረግ ጦርነት፤ በማህበራዊ ሚዲያ የሚካሄድ የሀሳብ ሳይሆን የቃላት ጦርነት፤ ወዘተ…።
የሰላም ዘብ ነኝ የሚል አካል በነዚህ ሁሉ ጦርነቶች ላይ ወጥ የሆነ አቋም መያዝ ይጠበቅበታል። በፌዴራል መንግሥቱ እና በሕወሓት መካከል የሚደረግ ጦርነት እንዲቆም የሚፈልግ ነገር ግን በፌዴራል መንግሥቱ እና በሸኔ መካከል ያለው ጦርነት እንዲፋፋም የሚገፋፋ ግለሰብ በተግባር ጦርነትን የሚቃወም ሳይሆን ጦርነትን የሚያማርጥ አስመሳይ ነው።
የመሣሪያውን ጦርነትን እየተቃወመ በሙስና ጦርነት ላይ ፊታውራሪ የሆነ ሰውም እንደዚያው ነው። መንግሥት እና ሕወሓት እንዳይዋጉ እየወተወተ ዘወር ብሎ በቃላት ጦርነት ብሔር ከብሔር፣ ሃይማኖት ከሃይማኖት እንዲዋጉ የሚያደርግ ሰውም በተመሳሳይ። ስለዚህም ለሰላም ዘብ የሆነ ሰው ሰላምን በተመለከተ ወጥ አቋም ሊኖረው እንዲሁም በቃል ያለውን በተግባርም ሊደግም የሚገባ መሆን አለበት።
ስናጠቃልለው፤ ሁላችንም ጦርነትን እንጸየፍ። ነገር ግን ስንጸየፍ ከልባችን ሆኖ በተግባር ተደግፎ እና ሁሉንም ወገን በፍትሀዊነት ተመልክቶ መሆን አለበት።
(አቤል ገ/ኪዳን)
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 8 ቀን 2014 ዓ.ም