ልክ በዛሬዋ ዕለት እሁድ እና በዛሬዋ ቀን ግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም ነበር ኢትዮጵያ ታሪካዊውን ምርጫ ያደረገችው። ምርጫ 97 እየተባለ ሁሌም ይጠቀሳል። ይህ ምርጫ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ አለው። ስለምርጫ ሲወራ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የፖለቲካ ጉዳይ ሲነሳም ምርጫ 97 ይነሳል።
ይህ ቀን ታሪካዊ የሆነበት ምክንያት፤ ከዚያ በፊትም ከዚያ በኋላም ከተደረጉ የኢሕአዴግ ምርጫዎች የተሻለ አሳታፊ ስለነበር ነው። አሳታፊ ሆኖ ጀምሮ ግን ሁዋላ ላይ ወደ ደም አፋሳሽነት በመቀየሩም ነው።
ይቺ ታሪካዊ ቀን በኋላ ደግሞ ‹‹ግንቦት ሰባት›› የሚባል የፖለቲካ ፓርቲ እንዲፈጠር አደረገች። ይሄው ፓርቲ የኢሕአዴግ የውስጥ እግር እሳት ሆኖበትም ነበር፤ በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ግንቦት ሰባት ታሪካዊ ስም ለመሆን በቅታለች። እኛም በዛሬው ሳምንቱ በታሪክ ዓምዳችን የግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም እና እሱን ተከትለው የነበሩ ሁነቶችን እናስታውሳለን።
ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን መግዛት ከጀመረ/ማስተዳደር ለእሱ አይሆነውም/ ከ14 ዓመታት በኋላ የ1997ቱ ምርጫ መሠረታዊ የአስተዳደር ለውጥ እንዲያመጣ የተገደደበት የመጀመሪያው ጊዜ ነው። በምርጫ 97 ብዙ ነገሮች ተቀይረዋል።
ይህ ምርጫ ከመካሔዱ በፊት የፖለቲካ ምሕዳሩ የሰፋበት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች በከፍተኛ ሁኔታ የተጠናከሩበት፣ ሐሳብን በነጻነት መግለጽ እምብዛም ያልተገደበበት፣ የፖለቲካ እስረኞች እስር ቤቶቹን ያላጨናነቁበት ጊዜ ነበር።
ይህ ሁሉ ግን በምርጫው ውጤት አጥቢያ ገዢው ፓርቲና ዋና ዋናዎቹ ተቃዋሚዎች፣ በተለይም ቅንጅት ሲወዛገቡ በአንድ ጊዜ ወደ ተቃራኒው ሁኔታ ተለወጧል። ከ97ቱ ምርጫ በኋላ ቢያንስ ለስምንት እና ዘጠኝ ዓመታት ያህል የአደባባይ የተቃውሞ ሰልፍ አልተካሔደም። የዋነኛዎቹ ተቀናቃኞች የቅንጅት ለአንድነት እና ለፍትሕ አመራሮች፣ የሲቪል ማኅበራት አባላት እና ጋዜጠኞች በገፍ እና በግፍ ታሰሩ። የፖለቲካ ምኅዳሩን የሚያጠቡ ሕግጋት ወጡ። የፖለቲካ ድርጅቶች ተዳከሙ፣ በርካታ ብዙኃን መገናኛዎች ተዘጉ፣
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ገጽታም በዓለም ፊት ተበላሸ። ከምርጫ 97 በኋላ የተከተለው ፖለቲካዊ አፈና ‹‹ኢሕአዴግ ዴሞክራሲን ለመገንባት የሚፈልገው ራሱ ምርጫ የሚያሸንፍ መሆኑን እስካረጋገጠ ድረስ ብቻ ነው›› በሚል እንዲተች አደረገው።
የምርጫውን ዕለት ክስተቶች በዕለቱ አዲስ አበባ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ያስታውሱታል። አንዳንዶችም ራሱን የቻለ መጽሐፍ ጽፈውበታል። ከእነዚህም አንዱ ኢሕአፓ መሥራችና ‹‹ኢትዮጵያ ሆይ›› በሚሉት መጽሐፎቹ የሚታወቀው ክፍሉ ታደሰ ነው። ክፍሉ ታደሰ ‹‹ግንቦት 7›› በሚለው መጽሐፉ በዕለቱ በአዲስ አበባ የተለያዩ ምርጫ ጣቢያዎች ያስተዋለውንና የታዘበውን ለታሪክ ጽፎ አስቀምጧል።
ክፍሉ ታደሰ ‹‹ግንቦት 7›› በተሰኘው መጽሐፉ፤ ምዕራፍ 5 ‹‹ግንቦት 7 ታሪካዊ ቀን›› በሚል ርዕስ ‹‹ግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም 524 የምክር ቤት ወንበሮች ለውድድር ቀረቡ። 23 የሚሆኑት በነሐሴ ወር በሶማሌ ክልል ለሚደረገው ምርጫ ወደ ጎን ተተው።
ግንቦት 7 በተካሄደው ምርጫ ተሳትፌያለሁ። ማን ይናገር ነበረ፤ ማን ያርዳ የቀበረ እንደሚባለው፤ ያየሁትን፣ የሰማሁትን፣ የተሳተፍኩበትን ነው የማቀርበው። እኔ የዚህ መጽሐፍ ደራሲ ታሪኩን በሦስተኛ ሰው አድርጌ ላቀርበው አስቤ ራቀብኝ። የእኔ መስሎ አልሰማህ አለኝ፤ እናም በቀጥታ ላቀርበው ወሰንኩኝ›› በማለት ደራሲው ግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም በአዲስ አበባ ውስጥ የነበረውን ሁነት በቀጥታ በመሳተፍ ያየነውን ነግሮናል።
ማለዳ 12፡00 ተነስቶ መገናኛ ሲደርስ ረጅም ሰልፍ አጋጠመው። ሰልፉ እየተጠማዘዘ ቢያንስ ከ300 ሜትር በላይ እንደሚሆን ይገምታል። ደራሲው የዕለቱን እንቅስቃሴ ማየት ፈልጎ ስለነበር ብዙ የምርጫ ጣቢያዎችን እየተዘዋወረ ተመለከተ። ሁሉም ረጃጅም ሰልፎች ያሉባቸው ናቸው።
ደራሲው ከዚያ በፊት የነበሩ ምርጫዎችንም ያስተዋለ መሆኑን አስታውሶ፣ የዚያን ዕለት የነበረው ተሳትፎ ግን የተለየ እንደነበር ይገልጻል። በነገራችን ላይ መጽሐፉ የተጻፈው ከባለፈው ዓመት (2013) ምርጫ በፊት ስለሆነ ባለፈው ዓመት የተካሄደውን 6ኛውን አገር አቀፍ ምርጫ አይመለከትም።
የግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም ምርጫ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍተኛ ተስፋ ጥሎበት የነበረ ለመሆኑ፤ የምርጫው እንቅስቃሴ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ያለውን ተሳትፎ አስተውሏል። በምርጫው ዕለትም እንደሌላ ጊዜ ‹‹ውጣ›› እየተባለ ሳይሆን፤ ሕዝቡ በራሱ ተነሳሽነት በነቂስ ወጣ።
በዚህ ዕለት ሕዝቡ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች የሄደው በመንግሥት ካድሬዎች ቅስቀሳ ብቻ ሳይሆን በተፎካካሪ ፓርቲዎችም ቅስቀሳ ነው። በዚያ ምርጫ የምርጫ ካርድ ያላወጡ ዜጎች ተፀፀተዋል።
ምርጫው በዕለቱ ፍጹም ሰላማዊ እንደነበር ደራሲው ይገልጻል። ምንም አይነት አጠራጣሪ እንቅስቃሴ ስላልነበረ ፖሊሶች ደክሟቸው ቁጭ ይላሉ። ሕዝቡም አዛውንትና አካል ጉዳተኞችን እያስቀደመ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሲመርጥ ዋለ። በዕለቱ ከወለደች ገና 15 ቀን የሆናት አራስ፣ ታመው ከአልጋ ላይ የመጡ፣ በሰው ድጋፍ የመጡ… መራጮች እንደነበሩ ደራሲው አስተውሏል።
ምርጫ 97 ብዙ ነገሮችን ያሳየ ምርጫ ነው። በዕለቱ አዲስ አበባ የነበረውን ሁነት ያስተዋሉ ሁሉ የተለያየ ገጠመኝ አላቸው። የምርጫ 97 ታላቅ የሕዝብ እንቅስቃሴና የታየው ተስፋ ግን ምርጫው በተካሄደበት ቀን ሌሊት በአጭር መቀጨት ጀመረ። የምርጫውን አጠቃላይ ውጤት ይፋ ማድረግ ያለበት ምርጫ ቦርድ ተብዬው መሆን ሲገባው የምርጫው እለት ሌሊቱን ኢሕአዴግ ማሸነፉን ገለጸ። የቅንጅት መሪዎች በበኩላቸው በምርጫው ማሸነፋቸውን ገለጹ።
ከዚህ በኋላ ጸረ ዲሞክራሲ ተግባሩ ተጠናክሮ ቀጠለ። የምርጫው ውጤት ተጭበርብሯል፤ ኮሮጆ ተገልብጧል በሚል ቅንጅትና ደጋፊዎቹ ይጠይቁ ጀመር። ለወራት ሕዝባዊ ቁጣዎች ተቀሰቀሱ። ይህ የሆነው ደግሞ ቅንጅት በተወዳደረባቸው ክልሎችና ከተሞች ሁሉ ነበር።
ኢሕአዴግ ይህን ቁጣ ለማስቆም ያልወሰደው እርምጃ የለም። የምርጫው ውጤት ተጭበርብሯል፤ ኮሮጆ ተገልብጧል በሚል ተቃውሞ የሚወጡትን ሁሉ መደብደብ፣ ማፈስ፣ማሰቃየት አልፎም ተርፎ መግደል ውስጥ ገባ፤ ያፈሳቸውን ሁሉ ወለጋ ውስጥ ወደ ሚገኘውና በደርግ ወቅት ወታደራዊ ማስልጠኛ ወደ ነበረው ደዴሳ አጎረ።
በዚህ እስር በፖለቲካው ንቁ ተሳትፎ ያልነበራቸው ምንም የማያውቁ፣የአዕምሮ ሕሙማን ሳይቀሩ ታስረው እንደነበር በእስሩ ላይ የነበሩ ይናገራሉ። በዚያም የተገደሉና የሞቱ በርካታ መሆናቸው ይገለጻል። የፓርቲው መሪዎች ወህኒ እንዲወርዱ ተደርገ። ይህ ታሪካዊ ቀን እነሆ በበጎም በመጥፎም እየታወሰ ይኖራል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ግንቦት 7 ቀን 2014 ዓ.ም