አገራት ዘመናትን እየተሻገሩ የሚቀጥሉት በተለያዩ የሙያ መስኮች ተሰማርተው ለነፃነታቸው፣ ለሉዓላዊነታቸው፣ ለልማታቸውና ለሁለንተናዊ እድገታቸው ዋጋ በከፈሉና አስተዋፅዖ ባበረከቱ ልጆቻቸውና ባለውለታዎቻቸው ነው።የእነዚህ ልጆቻቸውና ባለውለታዎቻቸው አበርክቶ አገራቱ ጠንካራና አስተማማኝ የሆነ መሠረት እንዲኖራቸው ያደርጋል።
እውነቱ ይህ በመሆኑም፣ ለአገር መልካም ተግባራትን ላከናወኑና ኃላፊነታቸውን ለተወጡ ዜጎች ተገቢውን ስፍራ በመስጠት ማክበር ተተኪው ትውልድ ለአገሩ የሚገባውን አስተዋፅዖ እንዲያበረክት ለማድረግ ጉልህ አስተዋፅዖ ይኖረዋል።ለአገራቸው በጎ ተግባራትን ያከናወኑ ዜጎችን አለማክበር፣ አለማስታወስና አለመደገፍ የአገርን አሻራዎች የማጥፋት ተግባር ከመሆኑም ባሻገር የባለውለታዎችን መዘንጋት የሚታዘበው አዲሱ ትውልድ በቀጣይ የሕይወት ጉዞው ለአገሩ የሚጠበቅበትን አስተዋፅዖ እንዳያበረክት ያደርገዋል።ይህ ደግሞ አገር ከዜጎቿ ተሰጥዖና ጥረት ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንዳታገኝና የእድገት ጉዞዋም ‹‹ባለህበት እርገጥ›› አልያም የኋልዮሽ እንዲሆን በማድረግ ዘላቂ አገራዊ ኪሳራና የትውልድ ክፍተት ይፈጥራል።
የዛሬው ባለታሪካችን በሙያቸው ለአገራቸው ቀላል የማይባል አበርክቶ የነበራቸው ቢሆኑም ውለታቸው ከተዘነጉትና ችላ ከተባሉት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ናቸው።ባለታሪካችን ካፒቴን አየነው ዘገየ በቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ውስጥ (በወታደራዊው የደርግ መንግሥት) በተለያዩ የሙያና የኃላፊነት ደረጃዎች ለ17 ዓመታት ያህል (አምስት ዓመታትን በአሰብ እንዲሁም 12 ዓመታትን ደግሞ በድሬዳዋ) አገልግለዋል።በአውሮፕላን ምህንድስናና ደህንነት ዘርፎች የአገር ደህንነት እንዲጠበቅ ያስቻሉ በርካታ አገልግሎቶችን ያከናወኑት ካፒቴኑ፣ በፖለቲካዊ ለውጥና መመሰቃቀል ምክንያት ከሥራቸው በመፈናቀላቸው አሳዛኝ የሕይወት ውጣ ውረዶችን እንዲያሳልፉ የተገደዱ ኢትዮጵያዊ ናቸው።
ካፒቴን አየነው የተወለዱት በ1946 ዓ.ም፣ በቀድሞው ወለጋ ክፍለ ሀገር፣ ሆሮ ጉድሩ አውራጃ፣ አሙሩ በተባለ ስፍራ ነው።አባታቸው የፖሊስ ሠራዊት አባል ነበሩ።አስተዳደጋቸው ‹‹እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ›› እንደነበር ይናራሉ።‹‹… አስተዳደጌ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወጣት እንደሚያድገው ኳስ እየተጫትኩ፣ ትምህርቴን እየተማርኩ … ነው ያደግኩት …›› ይላሉ።እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ በነቀምቴ ከተማ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።በመቀጠል ወደ አዲስ አበባ መጥተው ከአጎታቸው ጋር እየኖሩ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በቀድሞው አስፋወሰን (በኋላ ‹‹ምሥራቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት››) መከታተል ጀመሩ።
ወቅቱ ወታደራዊው የደርግ መንግሥት ‹‹የብሔራዊ የዕድገት በኅብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ›› (ዕድገት በኅብረት) የተሰኘውን መርሃ ግብር ያወጀበት ጊዜ ስለነበር አየነውም የ11ኛ ክፍል ተማሪ እንደነበሩ በእድገት በኅብረት ዘመቻ ምክንያት ወደ ደብረ ብርሃን ዘምተው ማስተማርን ጨምሮ በሌሎች የልማት ተግባራት ላይ ተሳትፈዋል።ከዘመቻው መጠናቀቅ በኋላም ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ተምረው አጠናቀቁ። አየነው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው
እንዳጠናቀቁ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለካዴት ኮርስ የስልጠና ማስታወቂያ አወጣ።አየነውም ተመዘገቡ፤ ፈተናውን ተፈትነውም አለፉ።የአየር ኃይል ስልጠናቸውን አጠናቀው በምክትል መቶ አለቃነት ማዕረግ ከተመረቁ በኋላ በ1970 ዓ.ም ለተጨማሪ ትምህርት ወደ ውጭ አገር ተላኩ።የተጓዙትም ወደ ቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት ነበር።በሶቭየት ቆይታቸው የአየር ኃይል ምህንድስና ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላም አሰብ ተመደቡ።በአሰብ ለአምስት ዓመታት ያህል አገልግለው ወደ ድሬዳዋ ተዛወሩ።በድሬዳዋ ደግሞ ለ12 ዓመታት ያህል አገለገሉ።በእነዚህ የሥራ ጊዜያት ካፒቴን አየነው በአውሮፕላን ምህንድስናና ደህንነት ዘርፎች አገርን የጠቀሙ በርካታ ተግባራትን አከናውነዋል።
ካፒቴን አየነው ድሬዳዋ በነበሩበት ወቅት ወታደራዊው መንግሥት ተወግዶ ኢሕአዴግ ስልጣን ያዘ።በዚህ ጊዜ የካፒቴን አየነው የሙያና የግል ሕይወት ጉዞ አደገኛ እክል ሊገጥመው ግድ ሆነ።‹‹… ኢሕአዴግ ሲገባ ድሬዳዋ ነበርኩ።ያለምንም ጥያቄና ማብራሪያ ሥራዬን እንድለቅ ተደረግኩ።‹አታስፈልግም› ተባልኩ።ለምን? ብዬ ስጠይቃቸው ‹እናንተን አንፈልግም፤ እኛ የራሳችንን ሰዎች እናሰለጥናለን› አሉኝ።ጡረታዬስ? ብዬ ስጠይቃቸውም ‹ጡረታም አይከፈልህም› ተባልኩ።እስካሁንም ድረስ ጡረታ የለኝም …›› ይላሉ፡፡
አዲስ አበባ ቀጣይ መዳረሻቸው ሆነች።የፖሊስ ባልደረባ የነበሩት አጎታቸው ጋር ጥቂት ከቆዩ በኋላ ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር የሚያስችላቸውን ሥራ መፈለግ ጀመሩ።እንዳሰቡት ባይሳካላቸውም አንዳንድ መጠነኛ ሥራዎችን እየሠሩ ቀጠሉ።ለአብነት ያህል በአሜሪካ ኤምባሲ (የአዲስ አበባው) በጥበቃ ሥራ ላይ ተሰማርተው ነበር።ከኤምባሲው የጥበቃ ሥራቸው እንዲለቁ ከተደረጉም በኋላ በሌሎች ተቋማት ውስጥ በጥበቃ ሠራተኛነት ተቀጥረው እየሠሩ ለምግብና ለቤት ኪራይ የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ ለማግኘት ይጥሩ ነበር።ጊዜው እየገፋ ሲሄድ ግን ኑሮም እየከበዳቸው ሄደ።
‹‹… በወቅቱ ለቤት ኪራይ ይከፈል የነበረው ገንዘብ እንዳሁኑ የተጋነነ ስላልነበር ዛሬ ላይ ሆኜ ሳስበው ይገርመኛል።‹ያን ጊዜ የነበረው የቤት ኪራይ ዋጋ እንዳሁኑ ውድ አልነበረም።እንዳሁኑ ቢሆን እንዴት እሆን ነበር? እንዴትስ ሆኜ እኖር ነበር?› ብዬ አስባለሁ …›› በማለት የቀድሞውን ከአሁኑ ጋር እያነፃፀሩ በአግራሞት ያስታውሳሉ፡፡
ካፒቴን አየነው በሚወዱት የሙያ መስክ ተሰማርተው አገራቸውን ያገለግሉ በነበረበት ወቅት በግል ኑሯቸውም ደስተኛ ነበሩ።የአየር ኃይል ባልደረባ በነበሩበት ወቅት የ500 ብር ደመወዝተኛ እንደነበሩ የሚያስታውሱት ካፒቴን አየነው፣ የወቅቱ ደመወዛቸውን ‹‹በሚገባ ምቹ ኑሮ ያኖረኝ ነበር›› በማለት ያስታውሳሉ።የአየር ኃይል ባልደረባ በነበሩበት ወቅት ከመሠረቱት ትዳር ሁለት ልጆችን አፍርተዋል።ከሌላ እናት የተወለደ አንድ ሌላ ልጅም አላቸው።ይሁን እንጂ ከሥራቸው መፈናቀላቸው ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር የሚያስችላቸውን ገቢ ስላሳጣቸው ትዳራቸውንም አፈረሰው።እርሳቸው ሥራቸውን ሲያጡ ባለቤታቸውም ወደ ትውልድ መንደራቸው ነቀምቴ ተመለሱ።
ካፒቴን አየነው ከሥራቸው መፈናቀላቸው ኑሯቸውን በእጅጉ አከበደው።የመኖሪያ ቤት ኪራይ፣ የምግብ፣ የልብስ … ወጪዎችን ለመሸፈን ተቸገሩ።ለእነዚህ ወጪዎች የሚከፈል ገንዘብ ለማግኘት የሠሯቸው ሥራዎችም በቂ ገቢ ሊያስገኙላቸው አልቻሉም።ያ ጥሩ ኑሮ ይኖሩ የነበሩት የአየር ኃይል ባልደረባ፣ ያ በአውሮፕላን ምህንድስናና ደህንነት ዘርፎች አገርን የጠቀሙ በርካታ አገልግሎቶችን ያከናወኑ ባለሙያ ለችግር ተዳረጉ።መቸገራቸውን የተመለከቱ ሰዎች ‹‹መቄዶንያ የሚባል የበጎ አድራጎት ድርጅት አለ፤ ድርጅቱ አረጋውያንን እንዲሁም የቀድሞ ሠራዊት አባላትን ይረዳል።ወደዚያ ብትሄድ ጥሩ ነው …›› ብለው መከሯቸው።
ካፒቴን አየነውም የሰዎቹን ምክር ሰምተው የ‹‹መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል››ን አድራሻ ፈልገው ወደ ማዕከሉ ሄዱ።ወደ ማዕከሉ ስለገቡበት አጋጣሚና ማዕከሉ እንደደረሱ ስለነበረው ሁኔታ ሲገልፁ ‹‹… የምግብና የቤት ኪራይ ወጪ እየከበደኝ ሲመጣ የሚያውቁኝ ሰዎች መቄዶንያ ወደሚባለው ማዕከል እንድሄድ በነገሩኝ መሠረት ወደ ማዕከሉ ሄድኩ።መቄዶንያ ማዕከል በር ላይ ስደርስ መስራቹ አቶ ቢኒያም አየኝ።ስለጉዳዩ ነገርኩት፤ እርሱም ‹አስገቧቸው› ብሎ ወደ ማዕከሉ ገባሁ፤ ቦታም ተሰጠኝ …›› በማለት ያስረዳሉ።
‹‹ላይክስ አይበድልም›› እንዲሉ ካፒቴን አየነው ቀድሞም ሆነ ዛሬ የጤና ችግር እንደሌለባቸው ይናገራሉ።የምግብ፣ የልብስና የቤት ኪራይ ወጪዎችን ለመሸፈን የሚውል የገንዘብ ችግር ኖሮባቸው ሳለ በጤና እክል ምክንያት ተጨማሪ ችግር ቢገጥማቸው ኖሮ ፈተናቸው በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ይሆንባቸው እንደነበር መገመት አይከብድም።
ካፒቴን አየነው ‹‹መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል›› ውስጥ መኖር ከጀመሩ ስድስተኛ ዓመታቸውን አስቆጥረዋል።በማዕከሉ ስላላቸው ቆይታ ሲናገሩ ‹‹… ምግብ እመገባለሁ።ብታመም እታከማለሁ።በማዕከሉ ውስጥ የሚደረገው እንክብካቤ ሰፊ/ብዙ ነው።ሕዝቡ ያለውን ነገር ሁሉ ይዞ ይመጣል።የኢትዮጵያን ሕዝብ ደግነት ለመግለፅ ይከብደኛል።እንዲያውም የሕዝቡን ማንነት ያየሁት መቄዶንያ ከገባሁ ወዲህ ነው።የዋህ፣ አዛኝ ሕዝብ ነው።ያለውን አምጥቶ ‹ብሉ፣ ጠጡ› የሚል ደግ ሕዝብ ነው።ብዙ ሰው ድርጀቱን እንደ እናቱ ነው የሚያየው።አቶ ቢኒያምና ባለቤቱም ጭምር ይንከባከቡናል።ይህ ሁሉ እንክብካቤ ባይኖር ኖር ይህ ሁሉ ሰው እዚህ አይኖርም ነበር …›› ይላሉ።
ካፒቴን አየነው ‹‹መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል›› ምን/ማን እንደሆነ በመግለፅ ሁሉም ነገር ጨለማ ሆኖ ሰማዩ በተደፋባቸው ጊዜ የደረሰላቸውን ይህን ምግባረ ሰናይ ተቋም ለኅብረተሰቡ ለማስተዋወቅ እቅድ ይዘዋል።እርሳቸው እንደሚሉት ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ ወደሚገኙ ትልልቅ ከተሞች በመጓዝ በችግራቸው ጊዜ ከለላና አለኝታ ስለሆነላቸው ስለዚሁ ማዕከል የሥራ እንቅስቃሴ ለሕዝቡ ለማሳወቅ ምኞት አላቸው።ይህን ምኞታቸውን ወደ ተግባር ለመለወጥም በቅርቡ እንቅስቃሴ እንደሚጀምሩ ይናገራሉ።ድርጅቱም ይህንኑ ተግባር እንዲያከናውኑ ጥያቄ አቅርቦላቸዋል።ይህን አስታዋሽና ደጋፊ ያጡ ወገኖችን የሚንከባከበውን ግብረ ሰናይ ተቋም ማስተዋወቅ ፋይዳው ብዙ እንደሆነ ያምናሉ።
ካፒቴን አየነው ስለልጆቻቸውና የቀድሞ ባለቤታቸው ሲያስረዱ ‹‹… የመጨረሻው ልጄ ከዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ተመርቋል።እንደ ምንም ብዬ አቅሜ የፈቀደውን ያህል ልረዳው ሞክሬያለሁ፤ የምችለውን አድርጌያለሁ።ከተመረቀ በኋላም አይቼዋለሁ።ትልቁ ልጄ ደግሞ ባጃጅ አሽከርካሪ ሆኖ እዚያው ነቀምቴ ከተማ ይሠራ እንደነበርና ሚስት አግብቶ ልጅ እንደወለደም ሰምቻለሁ። … የዕድል ጉዳይ ሆነና ሁኔታው ሊያገናኘን አልቻለም›› በማለት ይገልፃሉ።የቀድሞ ባለቤታቸውን በተመለከተ ደግሞ ሌላ ባል አግብታ እየኖረች እንደሆነ መስማታቸውን ይናገራሉ፡፡
ካፒቴን አየነው እንደሚሉት እርሳቸው ‹‹መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል›› ውስጥ እንደሚኖሩ ዘመዶቻቸው አያውቁም ነበር።በቅርቡ ግን እርሳቸው በማዕከሉ ውስጥ እንደሚኖሩ ባወቀችው እህታቸው በኩል ቤተሰቦቻቸውንና ወዳጅ ዘመዶቻቸውን እንደሚያገኙ ተስፋ ሰንቀዋል።‹‹… ሳዑዲ አረቢያ ትኖር የነበረችው እህቴ እዚህ እንደምኖር አውቃለች።በቅርቡ ዘመዶቼን አገኛለሁ ብዬ አስባለሁ›› በማለት የሚመኙትን ይናገራሉ።
እኛም ዘመድ ፈላጊው ካፒቴን ከቤተሰቦቻቸውና ዘመዶቻቸው ጋር እንዲገናኙ እንመኝላቸዋለን።በሥራ ዘመናቸው ያገለገሉት አገርና ወገንን ነውና ያለ አግባብ የተነጠቁት የጡረታ መብታቸውም እንዲመለስላቸው እንመኛለም።
ባለውለታዎቿን ያላከበረችና በችግራቸው ጊዜም ድጋፍ ያላደረገች አገር ዘላቂ መሠረት የመገንባቷ ጉዳይ ዋስትና አይኖረውም።ቀጣዩ ትውልድም በአገሩ ተስፋ እንዳይኖረው በማድረግ ለአገሩ የሚገባውን እንዳይሠራ ታላቅ መሰናክል ስለሚሆን የካፒቴን አየነው ዘገየን ታሪክ በማሳያነት በመጠቀም ባለውለታዎቻችንን ማስታወስና ማክበር ለነገ የማይባል ጉዳይ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል!
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 6/2014