በኮትዲቯር አዘጋጅነት የሚካሄደው የ2023 አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ሊካሄዱ ከአንድ ወር ያልበለጠ እድሜ ብቻ ይቀራቸዋል። የተለያዩ አገራትም ለማጣሪያ ጨዋታዎች ውድድር የሚያስተናግዱባቸውን ስቴድየሞች ለካፍ እያሳወቁ ይገኛሉ። የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በጥቅምት ወር ባሳለፈው ውሳኔ ያስቀመጣቸው መስፈርቶች እስኪሟሉ ድረስ ኢትዮጵያ በሜዳዋ የምታደርጋቸው ጨዋታዎችን በገለልተኛ አገር እንድታከናውን መወሰኑ ይታወቃል።
ከእገዳው በኋላ የባህር ዳር ስቴዲየም ሁኔታን በማሻሻል ውድድር የማስተናገድ ፈቃዱን መልሶ እንዲያገኝ የተለያዩ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፤ በመጫወቻ ሜዳ፣ በሚዲያ ክፍል፣ በቪአይፒ፣ በተመልካች ፋሲሊቲ፣ በህክምና ክፍልና ተያያዥ አገልግሎት መስጫዎች ላይ የተደረገውን የማሻሻያ ሥራ ከካፍ ተወክለው የመጡት ሚስተር ኢቫን ኪንቱ ከትናንት በስቲያ በስቴድየሙ ተገኝተው ምልከታ አድርገዋል።
ሚስተር ኢቫን የምልከታቸውን ሪፖርት ለካፍ ካቀረቡ በኋላ ኢትዮጵያ ከግብፅ ጋር የምታደርገውን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ሁለተኛ ጨዋታ ጨምሮ በቀጣይ በሜዳዋ የምታደርጋቸው ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን እንድታከናውን የሚያስችላት ፈቃድ ማግኘት ያለማግኘቷ ጉዳይ በቅርብ ቀናት ምላሽ እንደሚያገኝ ይጠበቃል።
ካፍ ባለፈው አመት ከሃያ በላይ የአፍሪካ ስቴድየሞች አለም አቀፍ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ ዝቅተኛ መስፈርቶችን አያሟሉም በማለት ማገዱን ተከትሎ በርካታ አገራት በቅርቡ የሚያደርጓቸውን የማጣሪያ ጨዋታዎች በገለልተኛ ሜዳ ለማድረግ እንደሚገደዱ ስጋት ሆኖ ነበር። ይሁን እንጂ ካፍ ባለፉት የተወሰኑ ቀናት በርካታ ስቴድየሞችን ገምግሞ መጪዎቹን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች እንዲያስተናግዱ ይሁንታ እንደሰጠ አሳውቋል።
በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ አርባ ስምንት አገራት የሚሳተፉ ሲሆን፣ ካፍ ይህ ዘገባ እስከ ተጠናከረበት ሰአት ድረስ ለሰላሳ ስቴድየሞች ብቻ ጨዋታዎችን እንዲያስተናግዱ ይሁንታ መስጠቱ ተረጋግጧል። የቀሪ አስራ ስምንት አገራት ስቴድየሞችም በቀጣይ ጥቂት ቀናት ካፍ የግምገማ ቡድኑን ልኮ በሚያገኘው ግብረመልስ መሰረት ይሁንታውን ይሰጣል ወይም እገዳውን ያጸናል ተብሎ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ ከአንድ አመት በላይ አለም አቀፍ ጨዋታዎችን በሜዳቸው እንዳያስተናግዱ እገዳ ከተጣለባቸው አገራት መካከል አንዷ መሆኗ ይታወቃል፤ ካፍ በቀጣይ ቀናት ስቴድየሞችን ገምግሞ መጪዎቹን የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች ማስተናገድ አለማስተናገዳቸውን ከሚወሰንላቸው አገራት መካከልም ኢትዮጵያ አንዷ እንደምትሆን ታውቋል።
በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያው በምድብ አራት ከግብጽ፣ ማላዊና ጊኒ ጋር የተደለደለችው ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የማጣሪያ ጨዋታ ከማላዊ አቻዋ ጋር ከሜዳዋ ውጪ ታደርጋለች። በመጪው ሰኔም ከግብጽ ጋር በሜዳዋ ትጫወታለች። ዋልያዎቹ ከፈርኦኖቹ ጋር ለሚያደርጉት ፍልሚያ ኢትዮጵያ አሁን ስቴድየሞቿ ከሚገኙበት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ከባህርዳር ስቴድየም በስተቀር ሌሎቹን ለካፍ ግምገማ ማቅረብ አልቻለችም።
የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን ከዛሬ ጀምሮ የሚያስተናግደው የባህርዳር ስቴድየም ባለፉት በርካታ ወራት በካፍ ግብረመልስ መሰረት እድሳት ሲደረግለት መቆየቱ ይታወቃል። የተደረገለት እድሳት ተጠናቆ ካፍ ብቁ መሆኑን ይሁንታ ካልሰጠው ግን ኢትዮጵያ በገለልተኛ አገር ለመጫወት እንደምትገደድ ተረጋግጧል።
ኢትዮጵያ አለም አቀፍ ጨዋታዎችን እንዳታስተናግድ ከአመት በፊት በካፍ ከመታገዷ አስቀድሞ የባህርዳር ስቴድየም በብቸኝነት አለም አቀፍ ጨዋታዎች ሲካሄዱበት መቆየቱ ይታወቃል። የባህርዳር ስቴድየም ጨዋታዎችን ሲያስተናግድ የነበረውም በካፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ከስር ከስር የማሻሻያ ስራዎችን እንዲያከናውን ነበር። የማሻሻያ ስራዎቹ እየተከናወኑ በነበረበት ሁኔታም ካፍ በቂ ማሻሻያ አልተደረገም ብሎ በማመን እገዳውን መጣሉ ይታወሳል። በዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለኳታሩ የአለም ዋንጫ ማጣሪያ የመጨረሻ ጨዋታዎች ጋናንና ዚምቡዋቤን በገለልተኛ ሜዳ ለመግጠም ተገዷል።
ለመጪው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከሚሳተፉ አርባ ስምንት አገራት ሃያ አራቱ ብቻ ወደ አፍሪካ ዋንጫ በሚያልፉበት ፉክክር ዋልያዎቹ ከጠንካራው ምድባቸው ቢያንስ ሁለተኛ ሆነው ለማለፍ በሜዳቸውና በደጋፊያቸው ፊት ወሳኝ ነጥቦችን መሰብሰብ እንደሚኖርባቸው ይታመናል። በስቴድየሞች መስፈርት አለማሟላት ይህ እድል ከእጃቸው እንዳይወጣ በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ያለው ስጋት በቅርብ ቀናት ይለይለታል።
ካፍ ከትናንት በስቲያ ለአፍሪካ ዋንጫው ማጣሪያ ጨዋታዎች ይሁንታ ከሰጣቸው ሰላሳ ስቴድየሞች መካከል ከዋልያዎቹ ጋር በምድብ ማጣሪያው የተደለደለችው ግብጽ አንዷ ስትሆን ጊኒና ማላዊ የካፍን ይሁንታ ለማግኘት እንደ ኢትዮጵያ በቀጣይ ቀናት ይጠባበቃሉ።
የአልጄሪያው ኮምፕሌክስ ደ ኦራን፣ የአንጎላው ስታዲዮ ናሺዮናል፣ የቤኒኑ ስታድ ዲ አሚቴ፣ የቦትስዋናው ኦቤድ ኢታኒ ስታዲየሞች ይገኙበታል፡፡ ሞሮኮ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ካሜሩን፣ ሴኔጋል፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ጋቦን፣ ኮሞሮስ፣ ጋና፣ ማሊ፣ ማዳጋስካር ስቴድየሞቻቸው ጨዋታዎችን እንዲያከናውኑ ፍቃድ ከተሰጣቸው አገራት መካከል ይገኙበታል።
የአፍሪካ ዋንጫውን የምታስተናግደው ኮትዲቯር በቀጥታ የምታልፍ አገር ብትሆንም የማጣሪያ ጨዋታዎችን እንዲያስተናግዱ ከተመረጡ ሰላሳዎቹ ስቴድየሞች መካከል አለመካተቷ አስገራሚ ነው። ሌሴቶ፣ ናሚቢያና ደቡብ ሱዳን ደግሞ በገለልተኛ ሜዳ ጨዋታዎችን እንደሚያደርጉ ያረጋገጡ አገራት ናቸው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 29 /2014