ቡና በአገሪቷ ካሉ የግብርና ምርቶች መካከል ቀዳሚው የኢኮኖሚ ምንጭ ነው። ባለፉት ዓመታትም ይሁን በአሁን ወቅት ለአገሪቱ የኢኮኖሚ ዋልታና ማገር በመሆን የላቀ ድርሻ እያበረከተ ይገኛል። በተለይም አገሪቷ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በውጭ ምንዛሪ እጥረት እየተፈተነች ባለችበት በዚህ ወቅት ከቡና ምርት የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም።
‹‹የኢኮኖሚዊ ዋልታ ቡና ቡና…›› የተባለለት የኢትዮጵያ ቡና ከቀደመው ጊዜ በበለጠ በአሁን ወቅት በዓለም ገበያ ተፈላጊና ተወዳዳሪ እየሆነ በመምጣቱ አገሪቷም የዘርፉ ተጠቃሚ መሆን እንደቻለች በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ያነሳሉ። ከቡና ምርት የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅም ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ ቡና አምራች በሆነው አርሶ አደር ላይ ሰፊ ሥራ መሥራት የግድ መሆኑንም ባለሙያዎች አጽንኦት ሰጥተው ይናገራሉ።
የዕለቱ እንግዳችንም በቡና ልማት እንዲሁም በግብይት ሰፊ ልምድ ያላቸው፤ የትምህርት ዝግጅታቸውም ከግብርናው የተዋደደና በሥራ ዓለም ዘመናቸው ሙሉ በቡና ልማት፣ ዝግጅትና ግብይት ላይ በማድረግ አንቱ የተባሉ አንጋፋ ባለሙያና የዘርፉ አማካሪ ናቸው። የሥራ ዓለምን ‹‹ሀ›› ብለው ሲቀላቀሉ ጀምሮ ስለ ቡና ጠርቀም ያለ ዕውቀት ከማከማቸታቸው ባለፈ ለዘርፉ ጥልቅ ፍቅር ያላቸው ናቸው።
እንግዳችን በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ምዕራብ ኦሮሚያ በምስራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ ተወልደው አድገዋል። እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም እንደማንኛውም የአካባቢው ነዋሪ በአቅራቢያቸው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም በሻምፑ፣ በአምቦና በነቀምት ተከታትለዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቅቀው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደብረ ዘይት እርሻ ኮሌጅ በመግባት በግብርና ዘርፍ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። የእርሻ ኮሌጅ ትምህርታቸውን አጠናቀው የመጀመሪያ የሥራ ቅጥራቸውን በቀድሞው ቡናና ሻይ ልማት ሚኒስቴር ያደረጉት የዕለቱ እንግዳችን የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ደሳለኝ ጀና ናቸው።
አቶ ደሳለኝ ሰፊ አበርክቶ ያላቸውና ዛሬም ድረስ ሙሉ ጊዜያቸውን ለሙያው በመስጠት እያገለገሉ ያሉ ሲሆን በተለይም በቡና ልማትና ግብይት ያካበቱትን ዕውቀትና ልምድ ለአርሶ አደሩና በዘርፉ ለተሰማሩ አባላት በሙሉ በማካፈል ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን በሙሉ አቅማቸው እያገለገሉ ይገኛሉ።
በቀድሞ አጠራሩ በሲዳሞ ክፍለ አገር ይርጋለም ከተማ አካባቢ የቡና ልማት ሥራን የጀመሩት አቶ ደሳለኝ፤ በተሰማሩበት ሙያ ውጤታማ ሥራ መሥራት በመቻላቸው በአካባቢው በኃላፊነት ቦታ ላይ ሆነው አገልግለዋል። በወቅቱም አርሶ አደሩ ቡናን በስፋት ማምረት እንዲችልና ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆን ህብረት ሥራ ማህበራትን በማቋቋም ጭምር የጎላ ድርሻ እንደነበራቸው ይናገራሉ።
1985 ዓ.ም በአዲስ አወቃቀር ክልል በተመሰረተበት ወቅትም በየክልሉ የቡናና ሻይ ቢሮዎች የተከፈቱ ሲሆን በጊዜው ለኦሮሚያ ክልል ቡናና ሻይ ቢሮ ግንባር ቀደም ሠራተኛ ሆነው ተመድበዋል። በወቅቱም ቢሮዎችን በማደራጀት እንዲሁም ባለሙያዎችን ከየአቅጣጫው በመመልመል ቢሮው የተፈለገውን ሥራ መሥራት እንዲችል አድርገዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም የቡናና ሻይ እንዲሁም የግብርና ቢሮ በሚዋሀዱበት ጊዜም በህብረት ሥራ ኦዲተሮች አስተባባሪ በመሆን አገልግለዋል።
የህብረት ሥራ አገልግሎት ዘርፍ ከአንድ ክፍል በመውጣት ወደ ቢሮ ሲያድግም የኦሮሚያ የህብረት ሥራ ቢሮ የኦዲትና ኢንስፔክሽን አገልግሎት ኃላፊ ሆነው የተመደቡት አቶ ደሳለኝ፤ በወቅቱ በኦሮሚያ ክልል ዞኖች ውስጥ የሚገኙ የህብረት ሥራ አይነት አደረጃጀት ያላቸውንና በማናቸውም ዘርፎች የተሰማሩ አርሶ አደሮችን በህብረት ሥራ ማህበራት የማደራጀት ሃላፊነታቸውን ተወጥተዋል። በኦሮሚያ ክልል በሚመረቱ ቡናን ጨምሮ በሌሎች ምርቶች ዙሪያ እንደየአይነታቸው ማህበራትን በማደራጀት አርሶ አደሩ ምርታማ መሆን እንዲችልና ከዘርፉም ተጠቃሚ እንዲሆን አድርገዋል።
በተለይም በቡና ምርት ላይ የተሰማሩ አምራቾች የህብረት ሥራ ማህበራትን ውጤታማ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን ያነሱት አቶ ደሳለኝ፤ ወቅቱ የዓለም የቡና ገበያ እያሽቆለቆለ የመጣበት ወቅት በመሆኑ የህብረት ሥራ ማህበራት አባላቱን ለመታደግ በሚል ቡናን በአገር ውስጥ ከመሸጥ ባለፈ ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመሩን አስታውሰዋል። ለዚህም ማህበራቱን በአንድ በማዋሃድ የኦሮሚያ ቡና ገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒዬንን በመመስረት በዩኒዬን የተዋሃዱት ማህበራትም ቡናን በስፋት ማምረት እንዲችሉና በስፋት ያመረቱትን ቡናም ከአገር ውስጥ ባለፈ ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንዲችሉ የማድረግ ትልቅ ኃላፊነትን ተወጥተዋል።
በዚህ ወቅትም ህብረት ሥራ ማህበራትን በማደራጀትና በማጠናከር ከፍተኛ ድርሻ የነበራቸው አቶ ደሳለኝ፤ በ34 ህብረት ሥራ ማህበራት የተጀመረው የኦሮሚያ ቡና ገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒዬን ምክትል ሥራ አስኪያጅ በመሆን አገልግለዋል። ዩኒዬኑም በአንድ ዓመት ውስጥ እንደታሰበው ቡናን ወደ ውጭ ገበያ መላክ በመቻሉ የመጀመሪያው ዩኒዬን በመሆን የተፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል። ውጤቱን በማየትም ዩኒዬኑን የሚቀላቀሉ ማህበራት በየዓመቱ ቁጥራቸው እየጨመረ ሄዶ ዛሬ ላይ ከአምስት ሚሊዮን የሚልቁ አርሶ አደሮችን ማቀፍ ችሏል።
በወቅቱ የዓለም ገበያን በማጥናት የተፈጥሮ የሆነና የተመዘገበ ቡና የተሻለ ዋጋ የሚያወጣ መሆኑን መረዳት በመቻላቸው አስፈላጊውን ሂደት ሁሉ በማለፍ ዩኒዬኑ ቡናን ወደ ውጭ ገበያ በመላክ ቀዳሚ ከመሆኑም ባለፈ የተፈጥሮ ቡና ሰርተፊኬት በማግኘትም የኦሮሚያ ቡና ገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒዬን በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዩኒዬን እንዲሆን አስችለዋል።
በመሆኑም ቡናው የተሻለ ዋጋ እንዲያወጣና ገበሬውም ይበልጥ ተጠቃሚ መሆን እንዲችልና አገሪቷም ከዘርፉ በምታገኘው የውጭ ምንዛሪ ተጠቃሚ እንድትሆን አስችለዋል። ከዚህ በተጨማሪም ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻር ዩኒዬኑ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች በርካታ የልማት ሥራዎችን መሥራት የቻለ መሆኑንና በዚህም ከፍተኛ ድርሻ የነበራቸው መሆኑን ያስታወሱት አቶ ደሳለኝ፤ ዩኒዬኑ ከሠራቸው የልማት ሥራዎች መካከል መንገድ፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ፣ 100 የሚደርሱ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ 30 የሚደርሱ የጤና ተቋማት፣ የቡና ማጠቢያና መቀሸሪያ እጥረት ባለባቸው ክልሎችም እንዲሁ 50 የሚደርሱ የቡና ማጠቢያና መቀሸሪያ ጣቢያዎችን ማቋቋም እንደቻሉ ለአብነት አንስተዋል።
አቶ ደሳለኝ፤ በዩኒዬኑ ብቻ ለ18 ተከታታይ ዓመታት በምክትል ሥራ አስኪያጅነት ያገለገሉ ሲሆን በዘርፉ ሰፊ ዕወቀትና ልምድ ማካበት ችለዋል። ያካበቱትን ዕውቀትም ወደ ሥራ በመለወጥ በዘርፉ ሰፋፊ ኢንቨስትመንቶች እንዲቋቋሙ በማድረግ የቡና ምርት በአገሪቱ ውጤታማ እንዲሆንና አምራቹም ተጠቃሚ መሆን እንዲችል ትልቅ አበርክቶን አድርገዋል። አሁንም እያደረጉ ይገኛሉ። ለበረከተው አገልግሎታቸውም በዘርፉ መቆየት መቻላቸው ቀዳሚው ምክንያት ቢሆንም የትምህርት ዝግጅታቸውም እንዲሁ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም።
ከግብርና ኮሌጅ ትምህርታቸው ባለፈም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግና በፋይናንስ የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝተዋል። ለትምህርት ካላቸው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳም ከአገር ውስጥ ባለፈ በህንድ አገር በሩራል ዴቭሎፕመንት፣ በእስራኤል አገርም እንዲሁ የሩራል ኢንዱስትሪያላይዜሽን ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን ኮፕሬቲቭ ኮሌጅ በአገሪቱ ያልነበረ በመሆኑ በኬኒያ የኮፕሬቲቭ ቢዝነስ አድሚንስትሬሽን ትምህርታቸውን ተከታትለው አድቫንስ ዲፕሎማ አግኝተዋል።
‹‹የተከታተልኳቸው የትምህርት ዝግጅቶች በአብዛኛው ከግብርና እንዲሁም ከዴቭሎፕመንት ጋር የተቆራኘ ነው›› የሚሉት አቶ ደሳለኝ፤ ሌላ መስሪያ ቤት የማያውቁና በጠቅላላው ከአራት አስርት ዓመታታ በላይ በቡናና ሻይ መስሪያ ቤት አገልግለዋል። ልምድና ዕውቀታቸውን በቡና ልማትና ግብይት ዘርፍ በማተኮር በተለይም በቡና ምርትና ንግድ ላይ ለተሰማሩ አርሶ አደሮችና ነጋዴዎች ያላቸውን ከፍተኛ ልምድ በማካፈል ዘርፉን እየደገፉ ይገኛሉ።
ምንም እንኳን ተወልደው ባደጉበት አካባቢ ቡና ከቤት ፍጆታ አልፎ ለገበያ የሚወጣ ባይሆንም ቡናን በአካባቢያቸው እየተመለከቱ ያደጉት አቶ ደሳለኝ፤ ነብስ ካወቁበት ጊዜ ጀምረው በዘርፉ መሰማራት በመቻላቸው ለቡና ልማት ጥልቅ ፍቅር አላቸው። ታዲያ በከፍተኛ ልምዳቸውና በትምህርት ዝግጅታቸው ዘርፉን ጠንቅቀው ቢያውቁትም ከግል ጥቅማቸው በበለጠ በስፋት ለሚያመርተው አርሶ አደር ሙሉ ጊዜያቸውን ተጠቅመው ዕውቀታቸውን በማካፈል አገር ከዘርፉ ማትረፍ እንድትችል ያቅማቸውን አድርገዋል።
ከራስ ጥቅም ይልቅ አርሶ አደሩ የሚጠቀምበትና ሥራ በመሥራት ሙሉ ጊዜያቸውን ያሳለፉት አቶ ደሳለኝ፤ በተለይም በውጭው ዓለም ኢትዮጵያ ያላትን ገጽታ መቀየር የሚቻለው ሰፊው ህዝብ መለወጥ ሲችል እንደሆነ ያምናሉ። ለዚህም ዋናውና ሰፊ ድርሻ ያለው ገበሬው በመሆኑ በተለይም ቡና አምራች ገበሬው ምርቱን በስፋትና በጥራት አምርቶ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆንና አገርም ከዘርፉ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንድትሆን ቁጭት ያላቸው መሆኑን ያነሳሉ። በዚሁ ቁጭታቸው ልክም አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ እያደረጉ ይገኛሉ።
በአሁን ወቅትም ለአራት አስርት ዓመታት ከሰሩበትና ከፍተኛ ልምድ ካካበቱበት ቡናና ሻይ ባለስልጣን ከጡረታ አስቀድመው በመውጣት የቡና ላኪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት በመሆን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሰማርተው እያገለገሉ ይገኛሉ። በዘርፉ የተሰማሩ የተለያዩ አካላትንም እንዲሁ ካላቸው ልምድና እውቀት በመነሳት ያማክራሉ። በተጨማሪም የተቆላ ቡና በማዘጋጀት ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እያቀረቡ የሚገኙ ሲሆን በዘርፉም አስር ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል።
የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ደረጃ ታዋቂና ተወዳዳሪ ሆኖ እስካሁን ባለው ሂደትም በከፍተኛ ዋጋ መሸጥ እንዲችል ካደረጉት ምክንያቶች መካካል የኦሮሚያ ቡና ገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒዬን መመስረቱ አንዱ መሆኑን ያነሱት አቶ ደሳለኝ፤ ለዚህም ትልቅ ድርሻ ያላቸው መሆኑንና የዩኒዬኑ መስራች በመሆን ለ18 ዓመታት ማገልገል በመቻላቸውና ባስመመዘገቡት ውጤትም እጅጉን ደስተኛ እንደሆኑ ይናገራሉ።
ከግል ስኬታቸው በበለጠ ያላቸውን ልምድና ዕውቀት ለብዙሃኑ በማካፈል ቡና አምራች አርሶ አደሮች ምርታማ ሆነው ከአገር ውስጥ ባለፈ ለውጭ ገበያ ቡናን በብዛትና በጥራት ማቅረብ እንዲችሉ ማድረጋቸው ትልቁ ስኬታቸው እንደሆነም አጫውተውናል። አያይዘውም በሥራ ዓለም ምንም የሚቆረቁራቸውን ሥራ ያልሰሩና ያላቸውን ዕውቀትና ልምድ በሙሉ ተጠቅመው ብዙሃኑንና አገርን ለመጥቀም ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ መሆናቸውን ሲናገሩ የነበራቸውን በራስ መተማመን የፊት ገጽታቸውም በግልጽ ይናገር ነበር።
ከቡና ልማት እስከ ዓለም ገበያ ድረስ በዘርፉ ሰፊ ልምድና ዕውቀት ያካበቱት አቶ ደሳለኝ፤ ቡና በሚያመርቱና በሚሸምቱ አገራት ተዘዋውረው የተለያዩ ጥናት ማድረግ በመቻላቸው አገሪቷ ከዘርፉ ይበልጥ ተጠቃሚ መሆን እንድትችል እየሰሩ ይገኛሉ። በተለይም በአሁን ወቅት በአገሪቱ ያለው ፖሊሲ ማሠራት የሚችል በመሆኑ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ በመጠቆም ቡና በዓለም ገበያ የሚሸጥ ምርት እንደመሆኑ ምርቱ ለኢትዮጵያ እጅጉን አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ አሁንም ይሁን በቀጣይ አጭር ጊዜ ቡናን የሚተካ ምርት የሌለ እንደሆነ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። ረጅም መንገድ ከቡና ጋር በመጓዝ ከቡና የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ለመጠቀም የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ከልባቸው ሆነው በእውነት መሥራት እንዳለባቸውም አመላክተዋል።
በቅርቡም በአሜሪካን አገር በየዓመቱ በሚካሄድ የቡና ኤግዚብሽን ላይ ከተለያዩ ዓለም አገራት የቡና ተመራማሪዎችን ጨምሮ ቡና አምራቾችና እሴት ጨምረው ለገበያ የሚያቀርቡ አገራት በተገኙበት 100 የሚደርሱ ቡና ላኪዎች ተሳታፊ መሆን ችለዋል። በኤግዚብሽኑ ላይ ተሳታፊ ከሆኑት መካከልም አብዛኞቹ ወደ ውጭ ተጉዘው የማያውቁ ቡና ላኪዎች በመሆናቸው አጋጣሚው መልካም ነው። ላኪዎቹ ቡና ገዢ ከሆኑ አገራት ጋር ተገናኝተው የገበያ ትስስር መፍጠር የቻሉ ሲሆን ውጤቱም በቀጣይ የሚታይ እንደሆነ አመላክተዋል።
የቡና ዘርፍ ቸል የሚባልና የሚተው አለመሆኑን የገለጹት አቶ ደሳለኝ በቀጣይም ሌሎች በርካታ የሚሰሯቸው ሥራዎች ቢኖሩም ከዘርፉ ሳይለዩ ከኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ፕሬዘዳንትነት ባለፈ የዘርፉ አምባሳደር መሆንና የጀመሩትን የተቆላ ቡና በአገር ውስጥና በውጭ ገበያ የማቅረብ ሥራ አጠናክረው የመቀጠል ዕቅድ አላቸው። እኛም ዕቅዳቸው እንዲሰምር በመመኘት አበቃን።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 29 /2014