ነጠላ በየፈርጁ ይለበሳል፤ ሕይወትም ያው ነው። እዚህ ሞቀ ሲሉት እዚያ ይቀዘቅዛቀል፤ እዚያ ቀዘቀዘ ሲሉት እዚህ እንፋሎቱ ይፋጃል። በመሆኑም “ፈርጁ ብዙ ነው” ብቻ ሳይሆን ቁጥሩ እራሱ የዓለምን ህዝብ ቁጥር ነው ማለት ይቻላል። ለምን? የእያንዳንዱ ሰው የሕይወት ፈርጅ የራሱና የራሱ ብቻ ስለሆነ። ይህ የትኛውም ዓለም ቢኬድ፤ ቢወጣም ሆነ ቢወረድ – የአይነት፣ ደረጃና ጥራት ልዩነት ካልሆነ በስተቀር፣ ያው ነው። ምናልባት ልዩነት አለ ከተባለ ሕይወት እንደ ሀብታምና ደሀ (“ም” ከንፈር (አፍ) ይገጠማል፤ “ሀ” ከንፈር (አፍ) ይከፈታል)፤ የጎዳና ሕይወት እንደ ግለሰብ፤ የጎዳና ሕይወት እንደ ቤተሰብ ሲታሰብ ነው።
ኑሮም ቢሆን ያው የሕይወት አካል ነውና አሁንም ያው ነው። መቃብር ይሙቅ አይሙቅ ባይታወቅም “…. መቃብር ይሞቃል” ስለ ተባለ ይሞቃል ማለት አይደለምና ኑሮ ሁሉ የሞላ፣ የደላና የተደላደለ አይደለም። ሁሉ በእጅ፤ ሁሉ በደጅ … ሲሉት በእጅም በደጅም የሌለ ይኖራልና አለም ሙሉ ሆኖ አያውቅም ባዮች ትክክል ናቸው ማለት ይሆናል። ለምን ? ያው ከላይ እንዳልነው ነውና ባለቤትና ቤት አልባው፤ ጎዳና ተዳዳሪውና ባለ እልፍኝ ካዳራሹ በምንም መለኪያ አንድ ስለማይሆኑ። በተለይ ሕፃናት ሲጨመሩበት ጉዳዩ ይብሳል፤ ሲበዛም ሆድ ያስብሳል፤ አንጀትም ያላውሳል።
ምን አልባት ይህንን ታሪክ ስናነብና ባለታሪኮችን ስንመለከት ያ አንድ ሰሞን በየ ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው ሲዘወተር፤ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የጎዳና ተዳዳሪዎች ብሶታቸውን ሲቆዝሙበት የነበረውና ሕፃናት ጥሩ አድርገው ያዜሙት “ጎዳና ነው ቤቴ … / … ችጋር ጎረቤቴ …” ዜማ ጉዳዩን የበለጠ ያብራራዋልና እኛም እሱን ታስታውሱ ዘንድ እያስታወስን ወደ ታሪካችንና ባለታሪኮቻችን እንሂድ።
የዛሬው እንግዳችን አብዱልከሪም መሀመድ ይባላል። የ”ከ30 በላይ …” እድሜ ያለው እና የወይዘሮ ኪላ ሽኩሪ ባለቤት ሲሆን፤ የ10ኛ ክፍል ትምህርቱን ያጠናቀቀቀ፤ የአራት (በተቀራረበ እድሜ የተወለዱ ህፃናት) አባት ነው። እህቱ (ዘምዘም መሀመድ)ን ከሁለት ልጆቿ ጋር ከመኖሪያ አካባቢያቸው አምጥቶ አብረው እየኖሩ ይገኛሉ። ባጠቃላይ፣ ከራሱ ጋር ዘጠኝ ቤተሰብ በአንድ ላስቲክ ቤት (ጎዳና) ይኖራሉ፤ አብዱልከሪም መሀመድም ዘጠኝ ቤተሰብ ያስተዳድራል። ይህንን አጠቃላይ መረጃ ይዘን ወደ ዝርዝሩ እንሂድ።
አዲስ ዘመን፡– መች ነው ወደ እዚህ የመጣኸው?
አብዱልከሪም መሀመድ፡– ከስምንት አመት በፊት።
አዲስ ዘመን፡- እንዴት ልትመጣ ቻልክ?
አብዱልከሪም መሀመድ፡– አንድ መንገድ ተቋራጭ ነበር፤ እሱ ጋ ተቀጥሬ።
አዲስ ዘመን፡– ወደ’ዚህ ከመምጣትህ በፊት የት ነበርክ?
አብዱልከሪም መሀመድ፡– ሻሸመኔ። ከሻሸመኔ ነው የመጣሁት። የትውልድ አካባቢዬ እዛ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከዛስ?
አብዱልከሪም መሀመድ፡– እየሰራን እያለ እሱ ስራውን አቋርጦ ጥሎ ጠፋ። በቃ፣ ከዛ ስራ አጥ ሆንኩ።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ምን እየሰራህ ነው?
አብዱልከሪም መሀመድ፡- ይህ ነው የምለው ቋሚ ስራ የለኝም። ተባራሪ ስራ ነው የምሰራው። አንዳንዴ እዚህ አካባቢ ለሊት ለሊት ጥበቃ። በወር እስከ 600 ብር አገኛለሁ። በቃ ይሄው ነው። አልፎ አልፎ እኔ ጀምሬ የነበረውን ስራ አሁን ባለቤቴ እየሰራች ነው።
አዲስ ዘመን፡- ምንድን ነው ስራው?
አብዱልከሪም መሀመድ፡- ልብስ ማጠብ።
አዲስ ዘመን፡- ከባለቤትህ ጋር ነው ወደ አዲስ አበባ የመጣኸው?
አብዱልከሪም መሀመድ፡– አይ፣ አይደለም። እሷ በኋላ ነው የመጣችው። የተጋባነው ግን እዛ ነው። ስልክ ደውላ ችግር ሎይ ነኝ ና ውሰደኝ አለችኝ፤ ሄጄ አመጣኋት።
አዲስ ዘመን፡- ልጆቹ ይማራሉ?
አብዱልከሪም መሀመድ፡- አዎ የደረሱት ሁለቱ ይማራሉ። አንድ የእኔና አንድ የእህቴ ልሎች ይማራሉ።
አዲስ ዘመን፡- ማስተማሩ አልቸገረህም? ማለትም ወጪው?
አብዱልከሪም መሀመድ፡- አይ መንግስት ነው የሚያስተምርልኝ። በዚህ በኩል መንግሥት በጣም ነው የረዳኝ። እኔ ምንም አላወጣም። ከጫማና ዩኒፎርም ጀምሮ ቁርስና ምሳ ጭምር መንግስት ነው የሚችላቸው። እኔ እራት ብቻ ነው የማስበው።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ያለኸው አደባባይ ላይ ነው። ተነስ ብትባልስ ምንድን ነው የምታደርገው፣ ወዴ’ትስ ትሄዳለህ?
አብዱልከሪም መሀመድ፡- የት እሄዳለሁ። ምንም መሄጃ የለኝም። እነዚህን ልጆች ይዤ ወዴት ነው የምሄደው፤ ምንም መሄጃ የለኝም።
አዲስ ዘመን፡- ተነስ ተብለህ አታውቅም?
አብዱልከሪም መሀመድ፡- አውቃለሁ። እናፀዳለን ብለው ሁሉ መጥተው ነበር። ነገር ግን እኔን ወደ የትም መውሰድ አልቻሉም። እነዚህን ሁሉ ልጆች ምንም ሊያደርጓቸው ስላልቻሉ ተመልሰዋል።
አዲስ ዘመን፡- የመንግሥት አካላትን ጠይቀህ ታውቃለህ?
አብዱልከሪም መሀመድ፡- አዎ። ያልገባሁበት ቀበሌና ወረዳ የለም። ሁሉም ጋ ሄጃለሁ፤ የቀረኝ ክፍለ ከተማ የለም። እባካችሁ የቀበሌ ቤት ስጡኝ ብዬ ስጠይቅ ነው የኖርኩት። እስከ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ቢሮ ድረስ ሄጃለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ምን አሉህ ታዲያ?
አብዱልከሪም መሀመድ፡– አይ፤ ጥበቃ ላይ ያሉት አላስገቡኝም። አትገባም ተብዬ ተከለከልኩ።
አዲስ ዘመን፡- የቀበሌ/ወረዳ አመራሮችን ስታናግር የሚሰጡህ ምላሽ ምንድን ነው?
አብዱልከሪም መሀመድ፡– ምንም ምላሽ የለም። አንዳንዶቹ “ቆይ እስቲ” ነው የሚሉት፤ አንዳንዶቹ ምንም አይነት ምላሽ አይሰጡም። እነዚህን ሁሉ ቤተሰቦች ይዤ እየተሰቃየሁ መሆኔን ግን ሁሉም ያውቃሉ። የአካባቢው ሰው ሁሉ ያውቃል።
አዲስ ዘመን፡- ደግመህ ስትሄድ የሚሰጡህ ምላሽ ወይም ምክንያት አለ፣ ካለ ምንድን ነው?
አብዱልከሪም መሀመድ፡- የሚሰጡኝ መልስ “የነዋሪነት መታወቂያ የለህም፤ በመሆኑም ልናስተናግድህ አንችልም” የሚል ነው። “እሺ መታወቂያ ስጡኝ” ብዬም ያልጠየኩበት ጊዜ የለም። ለምን እንደ ሆነ እንጃ ሁሉም ሊሰጡኝ አልቻሉም። እኔ ላለፉት ስምንት አመታት እዚህ መኖሬን ማንም ያውቃል፤ ይህ እየታወቀ እንደ ነዋሪ ሳልቆጠር መታወቂያ ሊሰጠኝ አለመቻሉ ለምን እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም። እኔ ከሌላ ቦታ (ሻሸመኔ) መምጣቴ ከሆነ ችግሩ ከየትም ልምጣ ከየት ያው ዜጋ ነኝ፤ ኢትዮጵያዊ ነኝ። “እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ለምን አልስተናገድም?” የሚል ነው የእኔ ጥያቄ።
አዲስ ዘመን፡- ለምን መልቀቂያ አምጥተህ እዚህ አታስገባም?
አብዱልከሪም መሀመድ፡- ወደ እዛ አልሄድኩም። እኔ እዚሁ ነው ያለሁት።
አዲስ ዘመን፡- እዛ መልቀቂያ እንዲሰጡህ ጠይቀሀል?
አብዱልከሪም መሀመድ፡- አይ፤ አልጠየኩም።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አሁን እየነገርከን ካለው ችግርህ አኳያ፣ በተለይም ከመኖሪያ ቤት አኳያ እስከ ዛሬ ያናገረህ አካል፣ ተቋምም ይሁን ድርጅት ወይም ሌላ የለም?
አብዱልከሪም መሀመድ፡- ያልመጣ የለም። ብዙ ናቸው። ከኮተቤ ነው፣ ከዚህ ድርጅት ነው፤ ከዛ ድርጅት ነው ….. በማለት ብዙዎቹ መጥተው አናግረውኛል። እስካሁን ግን ምንም ያደረጉልኝ ነገር የለም። አንዱ ብቻ መጥቶ ለስድት ወር የቤት ኪራይ እንከፍልልሀለን፤ ከዚህ ተነስ አለኝ። አይሆንም አልኩ።
አዲስ ዘመን፡- ለምን?
አብዱልከሪም መሀመድ፡- ስድስት ወር ስድስት ቀን ነው። “ከዛስ ወዴት እሄዳለሁ፤ ምን ውስጥ እገባለሁ? እነዚህን ሁሉ ልጆች ይዤ የት እወድቃለሁ?” በሚል ስጋት ነው ፈቃደኛ መሆን ያልቻልኩት። ድጋፉ ዘለቄታ ከሌለው አስቸጋሪ ነው። ልጆቼ ሕፃናት ናቸው። ዘጠኝ ነን። ዘጠኝ የቤተሰብ አባላት ….
አዲስ ዘመን፡- ኑሮ እንዴት ነው፤ አይከብድም?
አብዱልከሪም መሀመድ፡– በጣም ይከብዳል፤ ከባድ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የቀለብ ሁኔታስ፣ ከየት ነው?
አብዱልከሪም መሀመድ፡– በፊት የሸገር ዳቦ በደንብ ይዞን ነበር። ማታ ማታ አስርም አስራ ሁለትም ብር ይገኝ በእሱ ወደ 10 ዳቦ አካባቢ ገዝተን እንመገብ ነበር። አሁን እሱም ቆመ። ኑሮ በጣም ችግር ነው።
አዲስ ዘመን፡- እንደው ለመሆኑ፣ መጀመሪያውኑ ይህ አደባባይ መሆኑን እያወቅህ እንዴት አስበህ እዚህ ላይ ኑሮህን መሰረትክ?
አብዱልከሪም መሀመድ፡– ይህ ቅድም እንዳልኩህ ከቦታው ጋር የተዋወኩት በስራ ምክንያት ነው። በመንገድ ስራ። ቀደም ሲል የመንገድ ተቋራጩ ስራውን አቋርጦ ሲጠፋ ሰራተኞች ተበተንን። እኔ እዚሁ ቀረሁ። መነሻው ይህ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በክረምት እንዴት ነው፣ ዝናብ አያስቸግርም?
አብዱልከሪም መሀመድ፡- አንዳንዴ ያስቸግራል። (እኛ እንደ ተመለከትነው በተቻለ መጠን በተገኘው ነገር ሁሉ “ቤቱ” ተጠቅጥቋል። ክፍሎችም አሉት። “ግቢ” ውስጥም ነው።)
አዲስ ዘመን፡- አሁን “ጥያቄህን ባጭሩ አቅርብ” ብትባል ጥያቄህ ምንድን ነው?
አብዱልከሪም መሀመድ፡- የመኖሪያ ቤት፤ የቀበሌ ቤት ብቻ ስጡኝ ነው የእኔ ጥያቄ። እነዚህን ህፃናት ይዤ የምጠለልበት ቤት ብቻ ነው ችግሬና ቤት ስጡኝ የሚል ነው የኔ ጥያቄ። ምግብ የትም ተውሎ፣ የትም ተበልቶ ይገባል። ቤት ከሌለ የት ይገባል? ምን ውስጥ ይገባል? ምንም ሆነ ምን፣ እኔም ሆንኩ የማስተዳድራቸው ቤተሰቦቼ ኢትዮጵያዊ ነን። እኔ ዜጋ ነኝ፤ ከየትም አልመጣሁም፤ ከዚሁ ከኢትዮጵያ ነው የመጣሁት። ስለዚህ ይህ ሁሉ ግንዛቤ ተይዞበት ቤት ብቻ እንዲሰጠኝ ነው የምጠይቀው። የልጆች ትምህርት ቤትን ነገር ያው መንግስት እያገዘኝ ስለ ሆነ ብዙም አልተቸገርኩም። የእኔም ሆነ የቤተሰቤ ዋና ችግር ቤት ነው። እንዲሰጠን የምንጠይቀውም እሱኑ ነው።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 29 /2014