ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ መጀመሯን ተከትሎ ህልውናዋን የሚፈታተኑ በርካታ ተግባራት ሲፈጸሙ ከርመዋል። ከውስጥ እንደ አሸባሪው ሕወሓትና ሸኔ አይነቶቹ፤ ከውጭ የእጅ አዙር ቀኝ አገዛዝ ህልማቸው የጨነገፈባቸውና የህዳሴው ግድብ ግንባታ እረፍት የነሳቸው ኃይሎች በሚፈጽሟቸው ሴራዎች ኢትዮጵያ ስትፈተን ቆይታለች።
ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ባለፉት ዓመታት የብሔር ግጭቶችን በመቀስቀስ የኢትዮጵያ ሕዝቦች እርስ በእርሳቸው እንዳይተማመኑና አንዱ ሌላውን በጠላትነት እየፈረጀ ጥቃት እንዲያደርስበት ሲሠሩ ከርመዋል። በዚህም በርካቶች ለስደትና ለመከራ ተዳርገዋል። ይሁንና ይህ ሴራቸው የሚፈልጉትን ያህል ውጤት እንዳላስገኛላቸው ሲረዱ ደግሞ የሃይማኖት ግጭቶችን በመፍጠር ኢትዮጵያን ወደለየለት ትርምስ ለማስገባት እየጣሩ ይገኛል።
ከሰሞኑ በጎንደር፣ በወራቤ፣ በአዲስ አበባና በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ያየነው ግጭት የዚህ ማሳያ ነው። ከብሔር ግጭት ወደ ሃይማኖት ግጭት መልኩን የቀየረው ስልትና የተቀነባበረው ሴራ ለአገር ህልውና አደጋ ያለው በመሆኑ ወጣቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጉዳዩን በንቃት ሊመለከተው ይገባል።
የኢትዮጵያ ጠላቶች የሃይማኖት ግጭት እንደሚያዋጣቸው አውቀው ወደ ሥራ የገቡት ሕዝቡ በተለይም ወጣቱ በሃይማኖቱ ከመጡበት ወደኋላ አይልም የሚለውን ስስ ስሜቱን ሊጠቀሙበት አስበው መሆኑ ለማናችንም ግልጽ ነው።
በዛሬው የወጣቶች አምድ ዝግጅታችን ወጣቶች በየጊዜው መልኩን እየቀያየረ ስለሚገኘውና አሁንም ሃይማኖታዊ መልክ ይዞ ስለመጣው የጠላት ደባ ምን ያህል ግንዛቤ አላቸው? በዚህ አይነቱ የጠላት ሴራ እንዳይጠለፉ ምን ማድረግ አለባቸው? አንድነታቸውንና አብሮነታቸውን እንዴት ማስቀጠል ይገባቸዋል? በሚሉትና በሌሎችም ጉዳች ዙሪያ ሁለት ወጣቶችን አነጋግረን ተከታዩን ጽሁፍ አቅርበናል።
ወጣት እስሌማን አባይ /የአባይ ልጅ/ አገራዊና ወቅታዊ ጉዳዮችን በንቃት እየተከታተለ ጠቃሚ ሀሳቦችን በማህበራዊ ሚዲያዎች በማጋራት ይታወቃል። በተለይም በህዳሴው ጉዳይ ዙሪያ የግብጾችን ሴራ እና የምዕራባዊያንን ጫና አስመልክቶ በርካታ ቁም ነገሮችን አስነብቦናል። በየጊዜው መልኩን እየቀያየረ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚፈጠረው ትርምስ ጀርባ የውጭ ኃይሎች እንደሚገኙበት እምነቱ ነው። በተለይም ግብፅ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ በየጊዜው በጥናት የተደገፉ ሴራዎችን እየፈበረከች በጥቅም ለገዛቻቸው አካላት ማስታጠቋ የአደባባይ ምስጢር እንደሆነ ይናገራል።
ጋዜጠኛ እስሌማን ሰሞኑን የሃይማኖት መልክ ይዞ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተቀሰቀሰው ግጭት “ኢምፖርት” የተደረገ ወይም የውጭ ኃይሎች ቀርጸው ወደ አገራችን ያስገቡትና በፋይናንስ የሚደግፉት የታሰበበት አጀንዳ ነው ይላል።
ኢትዮጵያ ውስጥ በሃይማኖትም ይሁን በብሔር ጉዳይ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉ የሚለው እስሌማን የውጭ ኃይሎች በተለይም ግብፅች በውይይትና በንግግር ይፈታሉ እያልን በይደር ያቆየናቸውን ጉዳዮች ወደ ግጭት እንዲያመሩ በማድረግ የኢትዮጵያን ሰላም ለማወክ እየተጠቀሙበት መሆኑን ይናገራል።
ሕወሓት ከስልጣን መልቀቁን ተከትሎ በመንግሥት እና በቡድኑ መካከል የተፈጠረውን ጦርነት የውጭ ኃይሎች እንደጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም ሕወሓትን በፕሮፓጋንዳ፣ በፋይናንስ እርዳታ እና በመሳሰሉት በመደገፍ ኢትዮጵያ ውስጥ ማሳካት የሚፈልጉትን ጥቅም ለማስከበር ሲጥሩ እንደነበር እስሌማን ያስታውሳል።
በወቅቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ ምዕራባዊያን፣ ግብፅና ሱዳን ሲፈጽሙ የነበረው ሴራ የሚታወስ ነው። ሕወሓት በጦርነት በትረ ስልጣኑን መልሶ እንዲቆጣጠርና ጥቅማቸውን እንዲያስከብርላቸው የነበራቸው ፍላጎት ከፍተኛ ስለነበር በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችን የማሳደርና ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን እየተጠቀሙ ሥም የማጠልሸቱን ሥራ ሲሠሩ ነበር። ሕወሓት በጦርነት አሸንፎ ስልጣን እንደማይዝ ሲያረጋግጡ ደግሞ ሌሎች አገር ያፈርሳሉ ብለው ያመኑባቸውን አጀንዳዎች እየቀረጹ በተላላኪዎቻቸው በኩል ለማስፈጸም እየሞከሩ ናቸው ይላል። ከነዚህም አንዱ ሰሞኑን ያየነው የሃይማኖት ግጭት ነው።
ጋዜጠኛ እስሌማን እንደሚናገረው፤ በግብጽ አገር የትኛውም ፕሬዚዳንት መጥቶ ቢሄድ ኢትዮጵያ ከአባይ ወንዝ ጋር በተያያዘ የግብፅ የምንግዜም ተቀናቃኝ ተደርጋ መታየቷ አይቀርም። ማንም ይምጣ ማንም ይሂድ ግብፅ በአባይ ላይ ያላት ጥቅም አይቀየርም። ስለዚህ ጥቅማቸውን ለማስከበር የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም።
ፕሬዚዳንት አብዱልፈታ አልሲሲ ከአመት በፊት የኢትዮጵያ መንግሥት ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር ጦርነት ውስጥ ሲገባ ቀጣናው ወደ ትርምስ ይቀየራል እያሉ ሲያስጠነቅቁ እንደነበር የሚታወስ ነው ይላል። የጦርነቱ ሁኔታ ብዙም እንደማያስኬዳቸው ሲረዱ ደግሞ የእርስ በእርስ ግጭት የሚቀሰቀስባቸውን ስስ ብልቶች እያጠኑ ተግባራዊ ለማድረግ ይሞክራሉ።
Egyptian Center for Strategic Study የሚባል አንድ የግብፅ የጥናት ተቋም ከወር በፊት በኢትዮጵያ ጉዳይ ያወጣውን ጥናት ይፋ ማድረጉን እስሌማን ይናገራል። ተቋሙ በግብፅ መንግሥት ፈንድ የሚደረግ ነው። በዚህ ተቋም የሚደረጉ የጥናት ውጤቶች ለግብፅ የደህንነት መሥሪያ ቤት እንዲሁም ለግብፅ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ይቀርባሉ። ለሕዝብ መገለጽ ያለባቸውም በተለያየ መንገድ እንዲደርሱ ይደረጋል።
ጥናቱ እንደ ሌሎች ጥናቶች መደርደሪያ ላይ የሚቀመጥ ሳይሆን ወደ ተግባር የሚለወጥ ነው። በዚሁ መሰረት ይህ ተቋም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የተለያዩ ጥናቶችን አድርጓል። ከነዚህ ውስጥ የሶስቱን ጥናቶች ይዘት እንዲህ ያስረዳል። ለምሳሌ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ የኦሮሞ ሕዝብ የፖለቲካ ውክልና እና የዲሞክራሲ ጥያቄዎች፣ ለዘመናት ያልተሰማው ጩኸት›› በሚል አንድ ጥናት አውጥተዋል፤ ሌላው ጥናታቸው ደግሞ ‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ የተካሄደውን ግጭት ሙስሊሞች እንዴት ይመለከቱታል›› የሚል ሲሆን፤ ሶስተኛው ‹‹እስልምናንና ክርስትናን በመጠቀም በናይል ዲፕሎማሲ ላይ ጫና ለማሳደር ትልቁ የኃይል አማራጫችን ይሆናል›› የሚል ነው።
ለነዚህ ጥናቶች መደረግ መነሻቸው አገር ውስጥ ያሉት መልስ የሚሹ ጥያቄዎች ናቸው። ጥናቶቹ በሰላማዊ መንገድ ሊፈቱ የሚችሉትን የሃይማትና የብሔር ጥያቄዎችን ቤንዚል ጠብ እያደረጉበት የእርስ በእርስ ቀውስ ውስጥ እንድንገባ የሚያደርጉ ናቸው።
“ጥያቄ አለኝ” የሚለው አካል ደግሞ አንዳንዱ በማወቅ፤ አንዳንዱም ባለማወቅ በሰላማዊ ውይይት የሚፈቱ ጉዳዮችን የግጭት መንስኤ እያደረገ አጀንዳቸውን ያስፈጽምላቸዋል።
ግብፅ በአባይ ወንዝ ጉዳይ ከየትኛውም የተፋሰሱ አባል አገራት ግንባር ቀደም ተሰሚነት እንደነበራትና ፈላጭ ቆራጭ እንደነበረች፣ ከደርግ መንግሥት መምጣት በፊት ኢትዮጵያ የግብፅ ተባባሪ እንደነበረች፤ በተለይም በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የራሷን ጳጳስ ከመሾሟ በፊት ጳጳሳት በግብፅ ይሾሙላት እንደነበር በጥናቱ ተጠቅሷል። ያ ዘመን ግብፅን ተጽዕኖ ፈጣሪ እንድትሆን አስችሏታል ይላል። በኢህአዴግ ዘመነ መንግሥትም ኢትዮጵያና ግብፅ እንደቀድሞው ባይሆንም ሰላማዊ የትብብር መንፈስ እንዳላቸው ይገልጻል። አሁንም ሃይማኖታዊ ቅርርቦችን በማጠናከር ለናይል ድርድር መጠቀም በሚያስችል ወሳኝ ሰዓት ላይ እንዳሉ ጥናቱ ያመላክታል።
እስሌማን እንደሚለው በትግራይና በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች ሁሉ ከዚህ በፊት ትምህርት ቤቶችንና የጤና ተቋማትን እያሠሩ እንደነበር በመጥቀስ አሁንም ይህንኑ አጠናክሮ መቀጠል አንዱ አማራጭ እንደሆነ ጥናቱ ይጠቅሳል።
ጥናታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ለምሳሌ ኦሮሚያ ክልል ከሰማኒያ በመቶ በላይ ሙስሊም ማህበረሰብ አለ ይላል። ቤኒሻንጉልን፣ አፋርን፣ ሶማሌንም እያነሳ ሙስሊሙ ማህበረሰብ አብላጫ አሃዝ እንዳለው ይጠቅሳል። ያም ሆኖ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ፖለቲካዊ ተሳትፎው አናሳ ነው ይላል።
ጽሑፉ አሁንም እንዲህ አይነት ጥያቄዎችን የሚያነሱ አካላት መኖራቸውን አትቶ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከለሩ እስላማዊ እስካልሆነ ድረስ የግብፅ ፍላጎት ሊሳካ አይችልም ይላል። የተለያዩ ቅንጥብጣቢዎችን ገጣጥመን ስንመለከት ግብፅ ሃይማኖትን መሰረት አድርጋ ኢትዮጵያን የማተራመስ እቅድ እንዳላት እንረዳለን። በጣም የተቀናጀና የተናበበ ነገር እንዳለም የሚያሳዩ ነገሮች አሉ።
ሌላው የውጭ ተራድኦ ድርጅቶች ይዘው የሚመጡት ተልዕኮ ነው። ከሌሎች አገራት ተሞክሮ ስናይ በእነዚህ ድርጅቶች የሚደረገው ድጋፍ ሰዎችን በተለይም ወጣቶችን በገንዘብ እያማለሉ የራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት ሲጠቀሙበት ነው። መንግሥት ይህን የሚገታ የህግ አሠራር ቢኖረው ችግሩን ማቅለል ይቻላል ብሏል።
ጋዜጠኛ እስሌማን ወጣቱ ምንም አይነት ጥያቄ ቢኖርበት መፍታት ያለበት እንደአገራችን ወግና ባህል በምክክሮችና በውይይቶች እንጂ የውጭ ኃይሎች በቀየሱለት መንገድ ሊሆን እንደማይገባ ይገልጻል። መንግሥትም የውይይትና የምክክር መድረኮችን እያዘጋጀ አስቀድሞ ችግሮችን መፍታት እንዳለበት ይጠቁሟል።
ሌላው የግል አስተያየቱን የሰጠን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራተኛ ዓመት የሕግ ተማሪው ወጣት ዮሐንስ አበባው ነው። ዮሐንስ እንደሚለው ምዕራባዊያን የምስራቅ አፍሪካን ቀጣና ለመቆጣጠር ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ኢትዮጵያን እንደፈለጉ የሚያዟት አገር እንድትሆን ይፈልጋሉ ይላል። ከለውጡ በፊት ይህ ፍላጎታቸው ተሟልቶላቸው ነበር። የብልጽግና መንግሥት ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ግን እንዲህ አይነቱን እድል አጥተዋል። የሚታዘዛቸውን መንግሥት ለማስቀመጥ ሲሉ ኢትዮጵያ ሰላም እንዳይኖራት ይጥራሉ። ኢትዮጵያ ለቀይ ባህር ቀረቤታ ያላት አገር መሆኗና የአባይ ወንዝ ምንጭ በመሆኗ አገሪቱን በመቆጣጠር በርከት ያሉ ፍላጎቶቻቸውን ማሳካት ይፈልጋሉ ይላል።
የሚታዘዛቸው መንግሥት ከሌለ ደግሞ በሚቻላቸው መንገድ ሁሉ አገሪቱን ያተራምሳሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ የለውጥ ንፋስ መንፈስ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ አንዴ የብሔር ሌላ ጊዜ የሃይማኖት ግጭቶች የሚቀሰቀሱት በውጭ ኃይሎች ነው የሚለው ዮሐንስ የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያ ላይ ከሚፈጥሩት ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ተጽእኖ ባሻገር ለዘመናት በሰላምና በፍቅር የኖረው ሕዝብ እርስ በእርሱ እንዲጋጭ የተለያዩ ሴራዎችን ይዶልታሉ ይላል ዮሐንስ። በብዙ መንገድ ሞክረው እንዳሰቡት ኢትዮጵያ አልፈርስ ስትላቸው አሁን የሃይማኖት ግጭት ፈጥረዋልም ባይ ነው።
አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዘጠና በመቶ በላይ አማኝ እንደሆነ ይነገራል የሚለው ዮሐንስ በእነርሱ አስተሳሰብ አማኝ ሕዝብ በሃይማኖቱ ከመጡበት አይደራደርም በሚል ወደ ትርምስ ሊከቱት አስበዋል ሊሆን ይችላል።
እንደ ዮሐንስ አስተያየት ሃይማኖት የጥፋትና የክፋት እጆቻችንን እንድነሰበስብ የሚያደርግ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን ያቆዩዋቸውን የመቻቻልና የመተዛዘን እሴቶቻችንን አጠንክረን አብሮነታችንን በማስቀጠል የጠላቶቻችንን እቅድ ማክሸፍ ይኖርብናል።
በተለይም ወጣቶች ግጭቶች በአገርና በሕዝብ ላይ የሚያስከትሉትን አደጋ አሻግረው በመመልከት በስሜት ከመጓዝ ይልቅ ቆም ብለው ሊያስቡ ይገባቸዋል። ከግጭቱ ጀርባ የማን እጅ ሊኖር ይችላል? ግጭቱ ምን አይነት አገራዊ ቀውስ ሊስከትል ይችላል? ምን ኪሳራ፣ ምንስ ጥቅም ይኖረዋል? የሚለውን መመርመር እንደሚኖርባቸው መክሩን ለግሷል።
ወጣቱ ችግሮችን በመነጋገር መፍታት እንደሚቻልና መጨረሻ ላይም ቢሆን ሁኔታዎች ቦታ የሚይዙት በሀሳብ የበላይነት እንደሆነ አውቀው እጆቻቸውን ከጥፋት መሰብሰብ ይኖርባቸዋል ብሏል። ነገ አብሯቸው የሚኖረውን መከራና ችግር የሚጋራቸውን ወገናቸው ላይ ክፉ ነገር ማሰብ መልሶ የሚያሳፍር ተግባር እንደሆነ ይገልጻል።
‹‹ሃይማኖት የግል አገር የጋራ›› እንደ መሆኑ ለራሳችን ሃይማኖትና ቤተ-አምልኮ የምንሰጠውን ክብር ለሌሎች መስጠት ይጠበቅብናል ሲል ዮሐንስ የግል አስተያየቱን ሰጥቷል።
የሃይማኖት አባቶችን ተግሳጽና ምክር እንዲሁም የየሃይማኖታችንን መልካም አስተምሮ በልባችን አኑረን መልካም ሥራዎችን ብቻ በመሥራት የኢትዮጵያንና የሕዝቦቿን ሰላም የማስጠበቅ አደራ ወጣቱ ላይ ተጥሏል ብሏል። በመሆኑም በዚሁ ልክ መስራትና ትውልዳዊ ኃላፊነትን መወጣት ከወጣቱ ይጠበቃል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28 /2014