ወፈፌው ይልቃል አዲሴ ሁለንተናዊ በሆኑ ክርክሮች መሐመድ ይመርን ከረታ ወዲህ ከጧት የጀመረ እስከ ማታ ድረስ መጮሁን አቁሞ ነበር። ከሰሞኑ ግን የእድር እና የሰፈራችን ሁኔታ አልጥምህ ቢለው በፊት ያደርግ እንደነበረው ጠዋት ሰማይ የአህያ ሆድ ሲመስል ጀምሮ ጨለማው ለአይን ያዝ እስከሚያደርግ ድረስ ይጮህ ይዟል። ለዚህ ደግሞ ሁለት ምክንያቶች እንዳሉት የቅርብ ሰዎች ይናገራሉ ። የእድር መሪዎቻችን እና እድራችንን ለመምራት የሚፎካከሩ ሃይሎች የእድራችንን ህልውና በጠጅ ፖለቲካ እየተፈታተኑት መሆኑ አንደኛው ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በየጊዜው የእድር መሪዎቻችን እና ተፎካካሪዎቹ በሚፈጥሯቸው አላስፈላጊ አጀንዳዎች እየተታለሉ የሰፈራችን እና የእድራችን ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል የሚራኮቱ ዜጎች በሚወስዱት ግብዝነት የተሞላበት እርምጃ እረፍት በማጣቱ ነው ።
ወፈፌው ይልቃል አዲሴ ዋርካው ስር በሚገኘው ድንጋይ ላይ ቆሞ መጮህ ሲጀምር ሁሉም የሰፈራችን ሰዎች ሴት ወንድ፤ ህጻን አዋቂ ሳይሉ በመሰባሰብ የወፈፌውን ሚስጥር አዘል ንግግር ማዳመጥ በሰፈራችን እየተለመደ የመጣ ባህል ነው። ይልቃል አዲሴ ዛሬም ከእድራችን መሰብሰቢያ ዋርካ ስር በሚገኘው ድንጋይ ላይ ቆሞ መጮህ ሲጀምር የሰፈራችን ሰዎች ተገልብጠው ወደ ዋርካው በመሄድ በጩኸቱ ውስጥ የሚሰሙትን ቅኔ አዘል ሚስጠሮች ሊኮሞኩሙ ተሰባስበዋል።
ይህ በእንዲህ እያለ ከተሰብሳቢዎች መካከል አንዱና በሰፈራችን አብሿም እየተባለ የሚሰደበው ዘረ- ሰናይ ጉግሳ ማንም እንዲናገር እድል ሳይሰጠው ከተቀመጠበት ተነስቶ ለመሆኑ የጠጅ ፖለቲካ ምንድን ነው ? ሲል ንግግር ሲያደርግ የነበረውን ይልቃል አዲሴን አቋረጠው።
አብሿሙ ዘረ- ሰናይ ጉግሳ ንግግሩን በማቋረጡ ምንም ሳይከፋ … ይልቃል አዲሴ የጠጅ ፖለቲካ ምን እንደሆነ ለማብራራት ጉሮሮውን ጠራርጎ ንግግሩን ጀመረ። ከዚህ በፊት በአንድ ጹህፍ ላይ ገልጨው ነበር። ዛሬም ማስታወሱ አይከፋም ። እየውላችሁ የጠጅ ፖለቲካ ማለት ግልጽ እንዲሆንላችሁ አንድ ምሳሌ ልንገራችሁ።
በአንድ ወቅት በሰፈራችን የሚኖር ከባህላዊ መሳሪያዎች እስከ ዘመናዊ ፋብሪካዎች የሚያመርቱትን የመጠጥ አይነቶችን ምንም ሳያማርጥ የሚጠጣ ሰው ነበር። ምን አለፋችሁ የአልኮል በርሜል በሉት….!
ይህ ሰው በስራ ምክንያት መጠጥ በሌለበት አካባቢ ይመደባል። በዚህም መጠጥ ባለፈበት ሳይሄድ ለሳምንታት ይሰነብታል። በመጨረሻም ስራውን ጨርሶ ወደ ሰፈሩ ተመለሰ። ወደ ሰፈሩ እንደተመለሰም ወደ ቤቴ ገብቼ ቤሰቦቼን እንኳን እንዴት እንደሰነበቱ ልጠይቅ ሳይል የመስክ ቦርሳውን ከሰፈራቸው መንገድ ዳር በምትገኝ ሁለገብ የሸቀጥ መሸጫ ሱቅ ላይ ወርውሮ እየተቻኮለ ወደ ጠላ ቤት አመራ ። አንድ ሁለትም አለ። ይሁን እንጂ በስራ ምክንያት ለሳምንታት ተለይቶት የነበረውን የመጠጥ ሱሱን ማርካት ባለመቻሉ ወደ ጠጅ ቤት መሄድ ፈለገ። ከጠላ ቤቱም ወጣና ወዲያውኑ ጠጅ ቤት ገባ። ይህንን ጠጅ ይኮመኩም ያዘ። ይሁን እንጂ አሁንም የመጠጥ ሱሱን ማርካት አልቻለም። የመጠጥ አምሮቱ ባለመውጣቱ አረቄ መጠጣት አስቦ ከጠጅ ቤት ወጥቶ ወደ አረቄ ቤት ጎራ አለ። ኮማሪዋን አረቄ አዘዘ። ኮማሪዋም የታዘዘችውን አረቄ ቀድታ ጠረጴዛ ላይ አኖረች። አቶ የመጠጥ በርሜልም ከመቅጽበት አረቄውን ከጠረጴዛው አንስቶ ፉት አለ። የመጠጥ ልክፍቱን ያልተወጣው ሰው ከአረቄው በፊት ጠጅ ጠጥቶ ስለነበር ገና ከአረቄው አንድ ጊዜ እ..ፉት… እንዳለ ሊያስመልሰው አነቀው።
ለዚህም ዋናው ምክንያት ጠጅ በባህሪው መጀመሪያ ወደ ሰዎች ሆድ ከገባ በኋላ ሌላ መጠጥ እንጨርብህ ቢባል ቆይቶ የመጣውን መጠጥ ለማስገባት አለመፈለጉ ነው። ምን አልባት መጠጥ የሚጠጣው ሰው ሌላ መጠጥ መጠጣት ፈልጎ ቢቀመስ ወዲያውኑ ሊያስመልሰው ይችላል። እኔ ባለሁበት ሆድ ውስጥ ከእኔ ውጭ ሌላ ምንም አይነት መጠጥ አላስገባም ማለቱ የጠጅ ሁነኛ የስግብግነት መለያው ነው።
ለማንኛውም ወደ ተነሳሁበት ወግ ልመለስና ከመጠጥ እርቆ የሰነበተው ሰው በጠጅ ላይ አረቄ ሊጨምር ቢል ስግብግቡ ጠጅ አረቄን አላስገባም አለ። በዚህ ጊዜ የሰውየውን መጠጥ አለመጥገብ ያየችው አረቄ ጠጅን ምን ብትል ጥሩ ነው……. ካስገባህ አስገባኝ ሰውየው እንደሆነ ገና አልጠገበም አረቄም መጨመር ይፈልጋል። ሰውየው እኔን ሲጠጣ አላስገባም ካልከኝ ግን ሰውየው ያስታውክና ሁለታችንም ከውጭ ወድቀን እናድራለን ። የማንም ሰካራም ሲረግጠን ነው የምናድረው። ስለዚህ በሰላም አስገባኝ አለችው አሉ።
ይሄን ወደ እኛ ሰፈር የእድር አስተዳደር ዘይቤ ስናመጣው ከእራሳችን ጎሳ ውጭ በሰፋራችን እና በእድራችን ማንንም ሰው እንዲኖር አንፈቅድም የሚል አንድምታ አለው። በጎሳ ፖለቲካ ሲታወክ የሰነበተው እድራችን ከሰሞኑ ደግሞ በሃይማኖት ምች ሲታመስ የእየተስተዋለ ነው። እውነት ለማናገር የማንከባበር እና አንዱ አንዱን በፈለገው ቦታ እንዲቀመጥ የምንከለክል ከሆነ አረቄ እንዳለችው ሁላችንም ውጭ ወድቀን እናድራለን። የማንም ሰካራም መጫዎቻ መሆናችን የማይቀር ነው።
አንዴ ንግግር ከጀመረ መናገር የማያቆመው ይልቃል አዲሴ ንግሩን ቀጥሎ…ከሰሞኑ በሰፈራችን እና በእድራችን የተመለከትነው የጠጅ ፖለቲካ ከወለዳቸው መፈክሮች ደግሞ የሚያስገርሙ መሆናቸው ያስረዳል። ሁሉንም መጥቀስ ባይቻልም አለ ይልቃል አዲሴ፤ አንድ ሁለቱን ላስታውሳችሁ ብሎ ያልበላውን ጢሙን በማከክ ንግግሩን ገታ አደረጋና ከአፍታ ቆይታ በኋላ ንግግሩን እንዲህ ሲል ቀጠለ ….. ከሰሞኑ ከተመለከትኳቸው መፈክሮች ውስጥ የፈጣሪአቸውን ስም እየጠሩ ከእነሱ ሃይማኖት ውጪ ያሉ ሰዎችን እናጠፋልን የሚለው አንዱ ነው። የትኛው እምነት ነው የፈጣሪን ስም እየጠራችሁ ሰዎችን ግደሉ ፤ ቤተ እምነቶችን አቃጥሉ የሚለው? ጉድ እኮነው ! አይ የጠጅ ፖለቲካ … ሲያሳብድ እኮ ቅጥ የለውም።
ሌላው ከሰሞኑ ሃይማኖትን ሽፋን ተደርጎ ከታዩ አስገራሚ መፈክሮች መካከል የአጼዎችን አገዛዝ ለማምጣት የምትናፍቁ ሃይሎች የአጤዎች ስርዓት ላይመለስ ተቀብሯል። የተቀበረን ስርዓት ለማምጣት የምትደክሙ ሰዎች በከንቱ አትልፉ የሚል ነው። የአጤው ስርዓት እንዲመለስ ከማይፈልጉ ሰዎች መካከል አንዱ እኔ ብሆንም የአጤዎቹ ስርዓት በእስልምና እና በክርስትና ሃይማኖቶች ላይ የሰሩት በደል ግን ፈጽሞ አይታየኝም።
ስለ እውነት ከሰሞኑ በሰፈራችን ለተፈጠረው ስርዓት አልበኝነት ዋና መነሻ ሃይማኖት ከሆነ ስለምን የአጤዎችን ስም በክፉ ለመጥራት ፈለግን ? ክርስትና እና እስልምና ሁለቱም የመጡት በአጤዎቹ ዘመን በአጤዎቹ ይሁንታ አይደለም እንዴ?
የክርስትና እምነት በውጪ አለም መሰበክ በተጀመረ ጊዜ በርካታ የውጪ አለም ሰዎች ክርስትና ሃይማኖትን ተቀበሉ። በዚህም በንጉሳቸው ቀጭን ትዕዛዝ ክርስትናን የተቀበሉ ሰዎች እንደወንጀለኛ ተቆጥረው ለአስፈሪ አውሬዎች ተሰጡ። በሚነድ እሳት ውስጥም ተጨመሩ። በሰው ልጆች ይፈፀማል ተብሎ የማይታሰብ በደልም ተፈጸመባቸው። የእኛ ሰፈር ንጉስ ግን የክርስትና እምነት ሰባኪዎች ወደ እኛ ሰፈር በመጡ በቤተ መንግስቱ በማስቀመጥ ከመንከባከቡም ባለፈ ራሱ ንጉሱ የክርስትናን ሃይማኖትን ተቀብሎ እንዲስፋፋ በከፍተኛ ደረጃ ሰራ።
የእስልምና እምነት ተከታዮችም በተመሳሳይ በሳውዲ አረቢያ የእስልምና እምነት በተሰበከ ጊዜ የእስልምና እምነትን በመቀበላቸው እንደ ወንጀለኛ ተቆጥረው በቋራይሾች ተሳደዱ። የእስልምና አማኞችም ከቋራይሾ ግድያ በመሸሽ ወደ እኛ ሰፈር ንጉስ መጥተው ተደበቁ። በዚያን ጊዜስ የራሳቸው ሰዎች ቋራይሾች ያላዘኑላቸውን የእስልምና እምነት ተከታዮች ከሞት የታደጋቸው የእኛው ሰፈር ገዥ አጼው አይደለም እንዴ? የእኛን ሰፈር የተለያዩ እምነቶች መሰባሳቢያ ሙዚየም እንድትሆን የአደረጉ አጼዎች አይደሉም እንዴ?
ከሰሞኑ በሃይማኖት ስም የተደረገው እያንዳንዱ ድርጊት ሰፈራችንን እና እድራችንን ለማተራመስ የተደረገ የፖለቲካ ግብግብ እንጂ ሃይማኖት እንዳልነበር አንድ ማሳያ ልጥቀስ… በመካከለኛው ዘመን በኢትዮጵያ በዘይላ ወደብ የሚደረገውን እጅግ አትራፊ የሆነውን የንግድ ልውውጥ በበላይነት ለማስተዳደር በማሰብ በወቅቱ በሰፋራችን የነበሩ የክርስቲያን እና የእስልምና መሪዎች ወደ ከፋ ጦርነት ውስጥ ገቡ። የጸባቸው መነሻ ኢኮኖሚያዊ ሆኖ ሳለ የሁለቱም ሃይማኖት መሪዎች ጦርነቱንም ለማሸነፍ ሲሉ ሃይማኖታዊ ሽፋን ሰጡት። በዚህም የሰፈራችንን ሰዎች ለበርካታ ዓመታት በችግር እና በጦርነት አመሱት።
ከሰሞኑም የሰፈራችን ፖለቲከኞች እና የሰፈራችን ታሪካዊ ጠላቶች የፖለቲካ ጥማቸውን ለመወጣት ሲሉ ለእኩይ ፍላጎታቸው የግል ጥቅማቸውን የሃይማኖታዊ እሳቤዎችን በማላበስ ሰፈራችን ሲበጠብጡ ይስተዋላል። በዚህም በርካታ ሰዎችን ከግራ እና ከቀኝ ማሰልፍ ችለዋል። ይህ ደግሞ ለሰፈራችን ህልውና አደገኛ ነው።
ስለሆነም ከቀደመው በሃይማኖት ሽፋን የሰፈራችን ሰዎች የደረሰባቸውን መከራ ከራሳችን በደንብ አድርጎ በመገንዘብ የእድር መሪዎቻችን እና የሰፈራችን ታሪካዊ ጠላቶቻችን የፈጸሙብንን በደል ተገንዝባችሁ ከተጠመደላችሁ የመጥፋት ወጥመድ መውጣት ያስፈልጋል።
እነ ምስር እና ወዳጆቿ ሰፋራችንን እና እድራችንን ለማፍረስ መጀመሪያ በጦርነት ሞከሩ። በጦርነቱም መነሳት እንዳይችሉ አድርገን ክፉኛ አደባየናቸው። በጦርነት አልችለን ሲሉ በብሄር ፖለከቲካ ሞከሩን። በዚህም ጉንፋን ሰፈራችንን ክፉኛ መረዙት። ግን እንዳሰቡት ሰፋራችንን ሊያጠፉት አልቻሉም ። የብሄር ጉንፋንን መቋቋም ስንጀምር ደግሞ በሰፋራችን የሚገኙ የነዋይ ሴሰኞችን ተጠቅመው በሃይማኖት ስም መጡብን ። ግማሾቻችን ሳናውቅ፤ ግማሾቻችን ደግሞ በግብዝነት ባጠመዱልን ወጥመድ ገባን።
ብሔርንም ሆነ እምነትን አስታከው ሰፈራችንን ለማወክ እና ለማበጣበጥ የሚመጡ ሃይሎችን እኩይ ሴራ የሚያከሽፍ ሃይል ከሰፈራችን ብቅ ማለት ሲጀምር የዝንጀሮ ፖለቲካ ተግባራዊ ያደርጉበታል። ብሎ ንግግሩን ሳይጨረስ አብሿሙ ዘረ- ሰናይ ጉግሳ የዝንጀሮ ፖለቲካ ደግሞ ምንድን ነው ? ሲል በድጋሚ ይልቃል አዲሴን ንግግር አቋረጠው።
ይልቃል አዲሴ አሁንም በአብሿሙ ዘረ- ሰናይ ጉግሳ ሳይናደድ የዝንጀሮ ፖለቲካን ትርጉም ያብራራ ያዘ። በአለም የፖለቲካ ፍልስፍና ታሪክ ውስጥ የዝንጀሮ ፖለቲካ የሚል የፖለቲካ ፍልስፍና እንደሌለ አውቃለሁ። ይሁን እንጂ በእኛ ሰፈር የነበረውንና ያለውን ፖለቲካ አካሄድ የዝንጀሮ ፖለቲካ ብየዋለሁ።
ለምን የዝንጀሮ ፖለቲካ ተባለ ? የሚል ካለ ምክንያቱን እነሆ፦በአንድ የዝንጀሮ መንጋ ውስጥ አንዲት እናት ዝንጀሮ ወንድ ልጅ ከወለደች በልጇ እና በእሷ የሚደርስባቸው ግፍ ከኮሶ እጅጉን የመረረ ነው። ምክንያቱም የተወለደው ዝንጀሮ ወንድ ከሆነ የወደፊት መንጋው መሪ ሊሆን ይችላል በሚል ፍራቻ እና ስጋት በመንጋው የሚገኙ ትላልቅ ወንድ ዝንጀሮዎች በአዕምሯቸው ክፋትን ስለሚያረግዙ ነው። በዚህም ምንም የማያቀውን ህጻን ዝንጀሮ ለመግደል ይነሳሳሉ።
ይህን ተከትሎ እናት ዝንጀሮ ልጇን ለማትረፍ ከመንጋዋ ለመነጠል ትገደዳለች። ከመንጋቸው በተነጠሉበት ወቅት ምናልባትም ልጅና እናትን እስከ ሞት ሊዲያደርስ ለሚችል ለአስከፊ ችግር ሊጋለጡ ይችላሉ። ገና ለገና የወደፊት የመንጋው መሪ ይሆናል በማለት የራሱን የመንጋ አባል ማሰቃየት እና መግደል የዝንጀሮ ሁነኛ መታወቂያ ባህሪው ነው።
አሁንም በእኛ ሰፈር ያለው ገና ለገና የጠጅ ፖለቲካችንን ሊያከሽፍ ይችላል ተብሎ የሚገመት ሰው ከሰፈራችን ብቅ ማለት ከጀመረ የሰፈራችን የእድር መሪዎች እና የእኛ ሰፈር ታሪካዊ ጠላቶች ያንን ሰው ያለምንም ሃጢያቱ በመወንጀል ሊያጠፉት ይነሳሳሉ። ይህ ባህል አሁን ላይ በእኛ ሰፈር እንደ ትልቅ የፖለቲካ ብልሃት ተደርጎ እየተወሰደም ነው ብሎ ንግግሩን ሳይጨርስ በዋርካው ስር የተሰበሰቡ ሰዎች ንግግሩን በድጋፍ በጭብጨባ አቋረጡት። ከጭብጨባው በኋላ ያለውን የይልቃል አዲሴ ንግግር ለሚቀጥለው ሳምንት እናቀርባለን። እስከዚያው ከጠጅ ፖለቲካ እንዲጠብቃችሁ ምኞቴ ነው!!! ሰላም።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 27 /2014