6ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተቋቋመ እንሆ አንድ ዓመት ሊሆነው ጥቂት ጊዜያት ቀርተውታል። ህዝቡ አገር አቀፍ ምርጫውን ተከትሎ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የተወሰኑም ቢሆኑ ከሌሎች ፓርቲዎች ወንበር ያገኙ በመኖራቸው የሞቀ ክርክር ይሠማል። በአገሪቱም የተሻለ ሠላም እና ደህንነት፤ የአገር ዕድገት እና የተረጋጋ የኢኮኖሚ ሁኔታ እንደሚኖር ተስፋ ተጥሎ ቆይቷል። አዲሱ ምክር ቤት ከቀደሙት በተሻለ መልኩ አስፈፃሚዎችን ይቆጣጠራል፤ ሚናውንም ይወጣል የሚል እምነትም ነበር። ለመሆኑ 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚጠበቅበትን ሚና እየተወጣ ነው? በማለት ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ተወክለው የምክር ቤት ወንበር ያገኙትን እና የመንግስት ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑትን አቶ ክርስቲያን ታደለን አነጋግረን እንደሚከተለው አቅርበናል።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ቀደም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚናን በአግባቡ እየተወጣ አይደለም በሚል ሲተች እንደነበር የሚታወስ ነው። በእርሶ ግምገማ የአሁኑ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚና እንዴት አገኙት?
አቶ ክርስቲያን፡- ያላደጉ አገራት መልካም ያልሆነ አንዱ ተሞክሮ ያለፈ ነገርን መውቀስ ነው። ያለፈው ምክር ቤትን ለመተቸት ይሔን ሰርቷል አልሰራም ለማለት ምክር ቤቱ ይሠራቸው የነበሩ ሥራዎችን በጥልቀት ማየት እና መፈተሽ ያስፈልጋል። እንደአገር የነበርንበትን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አውዶችን መረዳት እና መገምገም የተገባ ነው። በዚህ ረገድ ባለፈው የምክር ቤት ዘመን የነበሩ እና አሁንም የምክር ቤት አባል የሆኑት በዚህ ላይ ሃሳብ ለመስጠት የተሻሉ ናቸው። ስለዚህ እኔ ስላለፈው ሳይሆን ስለአሁኑ መናገር ምቾት ይሰጠኛል።
የአሁኑ ምክር ቤት በአንፃራዊነት የተማሩ ሰዎች ማለትም ከምክር ቤት ውጪ ኑሯቸውን ለመምራት አቅምም ብቃትም ያላቸው ሁሉም ባይሆን እንኳ የተወሰኑት የምክር ቤት አባላት ከፖለቲካ ዝንባሌያቸው ባለፈ በምሁርነታቸው በአደባባይ የተመሰከረላቸው እና እንደግለሰብ ለኢትዮጵያ እና ለልጆቿ ባላቸው ቀናይ ሃሳብ የሚደነቁ ናቸው። ይህ ሲታይ የ6ኛው ምክር ቤት የመጀመሪያ ዓመት ስለሆነ እስከአሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ሊጠቅሙ የሚችሉ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ረገድ በአንፃራዊነት የተሻለ ተሳትፎ ያላቸው ናቸው ለማለት ያስደፍራል፡፡
የምክር ቤት አባላቱ ከሚወክሉት ፓርቲ ይልቅ ለህዝባቸው እና ለአገራቸው የሚወግኑ መሆኑን መመስከር እችላለሁ። በዚህ አጭር ጊዜ ይህ መልካም ጎን ነው። እርስ በእርስ እንደግለሰብ እንኳን በቂ ትውውቅ ለማድረግ ማን ምን ጠንካራ ጎን አለው የሚለውን ለማየት ጊዜው ገና በመሆኑ የቸኮለ ድምዳሜ ላይ መድረስ እንዳይሆን እንጂ እስከ አሁን ባየሁት የምክር ቤቱን ሥራዎች በሚያቀላጥፉ ቋሚ ኮሚቴዎች አባላት እና የቋሚ ኮሚቴ አመራሮች በህገመንግስቱ እና በምክር ቤት የህዝብ እንደራሴነት የተሰጣቸውን ሃላፊነት በወጉ ሲወጡ እና ለመወጣትም ሲንቀሳቀሱ እያስተዋልኩ ነው።
በጋራ የሥራ አፈፃፀም የምንገመግምበት ሁኔታ ስላለ ሁሉም የተሰጠውን ሃላፊነት ለመወጣት ሲታትር እየታየ ነው። ነገር ግን አገርም ህዝብም ከዚህ ምክር ቤት የተለየ ነገር ይጠብቃል። አንደኛ ላለፉት 30 ዓመታት ሥርዓት እና መዋቅር ሰራሽ በሆነ መንገድ የተለየ ጭቆና እና ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ እንዲሁም ማህበራዊ በአጠቃላይ ሁለንተናዊ በደል ውስጥ እንደነበርን አይዘነጋም። ዜጎች በማንነታቸው ሲጠቁ እና በሚከተሉት ሃይማኖት ተለይተው ሲገፉ እና ሲጨቆኑ ነበር። ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ሲዘራ የነበረው የጥላቻ እና የመከፋፈል ዘር ፍሬ አፍርቶ ዛሬ ኢትዮጵያውያንን ክፉኛ እያቃወሰ እንደሆን እያየን ነው። ከዚህ አንፃር ሕዝብም ይህ ምክር ቤት ከተለመደ የምክር ቤት አሠራር ወጣ ብሎ ለአገሩ አርበኛ እንዲሆን ለህዝቡ ፍትህ እና እኩልነት እንዲሁም ሰላም መረጋገጥ ሁነኛ እርምጃ ወስዶ አገርን ከዚህ ከመርገምቱ ጊዜ ወደ ፊት ወደ ብሩህ ተስፋ የማሸጋገር ሃላፊነት እንዳለበት እኔም ይሰማኛል። ህዝብም ይህን ይጠብቃል።
ከህዝብ ተስፋ አንፃር ምን ሥራዎች ተሠሩ ከተባለ መልሴ ገና የመጀመሪያ ዓመት ሥለሆነ ብዙ የሚጠበቅብን ሥራ አለ የሚል ብቻ ነው። ከዚህ በኋላ ሕዝብ እንደራሴ ብሎ አንዴ ልኮናል። ይህንን ተስፋውን ለማረጋገጥ በየጊዜው እንደግለሰብም ሆነ እንደምክር ቤት በሚኖሩ የህዝብ ግንኙነቶች ምን ሠራችሁ ብሎ መጎትጎት እና መደገፍ እንዲሁም ማበረታታት አለበት። ምክር ቤቱ በበኩሉ የአንበሳውን ድርሻ መጫወት አለበት። ምክንያቱም ይህ የእንደራሴዎች ምክር ቤት መላው ኢትዮጵያውያንን የሚወክል ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ አስፈፃሚው አካል ሰላምን ደህንነትን ፍትህን እና እኩልነትን ማዕከል አድርጎ እንዲሠራ መከታተል ብቻ ሳይሆን የማዘዝ ስልጣንም ጭምር ያለው ነው። አንዳንድ አካባቢዎች የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የሚፈፀሙ ከሆነ እንዲመረመር እና የፌደራል መንግስት ያንን እንዲያስቆም የማዘዝም ስልጣን ያለው ትልቅ የመንግስት አካል ነው። ከዚህ አንፃር እስከ አሁን በአንድ አመት ውስጥ ጉልህ ሥራዎችን ሠርቷል ማለት ባይቻልም ለቀጣይ ሥራ መደላድል ለመፍጠር የዝግጅት ምዕራፍ ላይ እንደነበር መውሰድ ይቻላል። በዚህ ጊዜ ውስጥ እያንዳንዱ የምክር ቤት አባል ያለው ተሰጥኦ እና አቅም ምን ያህል ነው? ምንስ ውስንነት አለበት? በሚለው ላይ በደንብ ተጠንቶ እንደየመክሊቱ እንደየችሎታው ሁሉም ለአገር ሰላም እና አንድነት ያለውን እንዲያበረክት አሠራርን የመዘርጋት እና ነገሮችን የማመቻቸት ሥራ የሚሠራበት ነበር ብሎ መውሰድ ይቻላል።
በተጨማሪ ምክር ቤቱ ካሉት አራት ተልዕኮዎች ውስጥ አንዱ ህግ የማውጣት ሥራ ነው። አሁንም ህግ በማውጣት ላይ ይገኛል። እንዲሁም አስፈፃሚ አካልን የመቆጣጠር ሃላፊነት አለበት። አሁንም በየጊዜው ህዝብን በፍትሃዊነትና በእኩልነት እያገለገሉ ስለመሆናቸው በመቆጣጠር ላይ ይገኛል። እዚህ ላይ ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ የታለመለትን ዓላማ ሊያሳካ በሚችል መንገድ እየሠሩ መሆኑን ያጣራል። እዚህ ላይ ምክር ቤቱ በፌዴራል ሥልጣን እርከን ውስጥ ለሚወድቁት አስፈፃሚዎች ዕቅዳቸውን እንዲከልሱ እስከማዘዝ የደረሰ ስልጣን አለው።
ሌላው የመንግስት በጀት እና ንብረት ለታለመለት ህዝባዊ ዓላማ እየዋለ ስለመሆኑ ይከታተላል። በዚህ ሒደት ክፍተት አለ ብሎ ካመነም እርምጃዎች እንዲወሰዱ ትእዛዝ መስጠት ይችላል። ሌላው የመራጭ ተመራጭ የውክልና ሥራ ነው። በዓመት ሁለት ጊዜ ሁሌም እንደሚደረገው የካቲት እና ሃምሌ ላይ የውክልና ሥራዎች ተሠርተዋል። በተለይም ገዢው ፓርቲ በምርጫ ቅስቀሳው ቃል የገባቸው የልማት ዕቆዶች በአስር ዓመቱ የልማት ዕቅድ የተካተቱትን ማለት ነው በተጨባጭ ሕዝብ ጋር ደርሰዋል ወይ? በማለት ሥራዎች የሚሠሩባቸው ከህዝብ ጋር ግንኙነት የሚደረጉባቸው ጊዜያቶች ናቸው።
ከዚህ ባሻገር መራጭ ሕዝቡ የሚያነሳቸው ተጨማሪ የፍትህ፣ የልማት፣ የእኩልነት፣ የመልካም አስተዳደር እና የሠላም ጥያቄዎች ካሉ ከቀበሌ ጀምሮ ወረዳ፣ ዞን፣ ክልል እየተባለ በየደረጃው ወደ ፌዴራል የሚመጡትንም በማቅረብ በተቀናጀ መንገድ የፌዴራል ተቋማት እንዲፈቷቸው አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል። ያም ክትትል የሚደረግበት ነው። ሌላው እስካሁን ተሠርቶ የማያውቅ እና ይሔኛው ምክርቤት በትኩረት እየሠራበት ያለው የህዝብ ዲፕሎማሲ ነው። በእርግጥ ኢትዮጵያ በመደበኛነት የዲፕሎማሲ ሥራ በውጪ ጉዳይ በኩል ትሠራለች። ነገር ግን ይሔ ምክር ቤት በተለያዩ የዓለም ዐቀፍ ምክር ቤቶች ህብረት አባል ነው። ስለዚህ በዛም ሆነ እንደፓርላማ ቡድን ኢትዮጵያ በተለይም አዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ከተማ በመሆኗ እዚህ ላሉ አምባሳደሮች እና ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በማሰማት፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ዘላቂ መብቶች፣ ጥቅሞች እና ዘላቂ ፍላጎት ላይ የተመሠረቱ ውሳኔዎች እንዲተላለፉ፤ የኢትዮጵያ ወዳጆች እና አጋሮች እንዲያደርጉ የተለያዩ የማህበረሰብ አባላት የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ወኪሎችን መደበኛ በሆነ መልኩ በሰላም እና ውጪ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ በኩል እየተሠራ ነው። ነገር ግን እንደየአገሩ ሁኔታ የወዳጅነት ቡድን ተቋቁሞ መሠራት ይኖርበታል። በዚህ በኩል መዘግየት መኖሩ እኔም ይሠማኛል። ወደ ፊት ለኢትዮጵያውያን ጥቅም የሚያስገኙ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ሊሠሩ እንደሚችሉ ተስፋ እናደርጋለን። በቋሚ ኮሚቴዎች እና በልዩ ልዩ ኮሚቴዎች በኩል በመደበኛነት እየተሠሩ ቢሆንም በተጠናከረ መልኩ መቀጠል አለበት። ነገር ግን ሕዝብ ከሚጠብቀውና ምክር ቤቱ ካለው አቅም አንፃር ግን ገና ብዙ መሥራት የሚገባን ሥራዎች መኖራቸው ይሠማኛል።
አዲስ ዘመን፡- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ከማካሔድ ባለፈ አስፈፃሚ ተቋማትን በመገምገም ተጠያቂነትን እስከማስፈን የሚደርስ ስልጣን አለው። በእርግጥ ይህንን ሚናውን እየተወጣ ነው?
አቶ ክርስቲያን፡- አዎ! እንደአብነት ልጥቀሰው የምችለው እኔ የምመራው ቋሚ ኮሚቴን ነው። የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዋናነት የመንግስት በጀት እና ንብረት ህግ እና ሥርዓት በሚፈቅደው መንገድ ለታለመለት ዓላማ መዋል አለመዋሉን የማረጋገጥ ሥራን ይሠራል። የፋይናንስ እና የክዋኔ ኦዲት ላይ በስፋት ይሠራል። ከዚህ አንፃር እንደሚታወቀው ኦዲት ወደ ኋላ የሚሠራ ነው። የዘንድሮ የሚሠራው ከርሞ ነው። ከዚህ በፊት በነበረው የፓርላማ ዘመን የነበረው አስፈፃሚ ያከናወነው የ2012 እና የ2013 ዓ.ም የኦዲት ዓመት የተገኙ የኦዲት ግኝቶች ላይ ይፋ መድረክ እናዘጋጃለን።
የኦዲት ባለድርሻ አካላት የሚባሉ የተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች አሉ። ፍትህ ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ሥነምግባር እና ፀረሙስና ኮሚሽን፣ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ገቢዎች ሚኒስቴር፣ ገንዘብ እና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር፣ ፕላንና ልማት ሚኒስቴርን የመሳሰሉት በተገኙበት ኦዲት ተደራጊዎች ይመጣሉ። ኦዲተር ጀነራሉ ቀርቦ ጥያቄዎችን አዘጋጅተን እንጠይቃለን። በትክክል መረጋገጥ የሚችሉ ማስረጃ ያላቸው ጉዳዮች ቀርበው ምላሽ ይሠጥባቸዋል። ነገር ግን የሚያስጠይቅ ነገር ሲያጋጥም ደግሞ ተጠያቂ ይደረጋሉ። ለአብነት ያህል ባለፈው ሳምንት ገንዘብ ሚኒስቴር 39 የሚደርሱ አስፈፃሚ አካላት ላይ አስተዳደራዊ እርምጃዎችን ወስዷል። ይህን ትዕዛዝ የሠጠው ቋሚ ኮሚቴው ነው። ቋሚ ኮሚቴው ሁልጊዜም ይፋዊ መድረኮችን ሲያዘጋጅ መጨረሻ ላይ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል። የኦዲት ማሻሻያዎች እንዲቀርቡለት ቀነ ገደብ ያስቀምጣል። የገንዘብ ሚኒስቴር አስተዳደራዊ እርምጃዎችን መውሰድ እንዲችል በአዋጅ የተፈቀደለት መብት ያለው በመሆኑ ማስጠንቀቂያን መፃፍ እና የገንዘብ ቅጣት ማስቀመጥ ይችላል። ስለዚህ 39 አካላት ላይ እንዲህ አይነት ውሳኔን አስተላልፏል።
የፍትህ ሚኒስቴር ደግሞ እነዚህ አስተዳደራዊ ውሳኔ የተላለፈባቸው የወንጀል ጥያቄን የሚያስከትሉ ወይም የማያስከትሉ ሊሆኑ ይችላሉ። የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ ከሆኑ በቂ ምርመራ አድርጎ እነርሱን እንዲወስድ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል። አሁን የምርመራ መዝገቦችን እያደራጀባቸው ያሉ ባለሞያዎች እና የሥራ ሃላፊዎች ስለመኖራቸው መረጃዎች አሉን። ሲደርስ ለመገናኛ ብዙሃን በፍትህ ሚኒስቴር በኩልም ሆነ በእኛ በኩል ይፋ የሚደረጉ ይሆናሉ። ነገር ግን አሁንም በተጨባጭ ክስ የተመሠረተባቸው ባለሞያዎች አሉ። እንደምክር ቤት ግን የእኛ ዋነኛ ተልዕኮ አመራር እና ባለሞያዎችን መክሰስ ተቋማትን ማንኳሰስ አይደለም።
ዋነኛ ተልዕኳችን እና ፍላጎታችን እነዚህ አስፈፃሚ ተቋማት የኦዲት ግኝት ማሻሻያ አድርገው ቋሚ ኮሚቴው በሚያደርገው ድጋፍ ከነበሩበት የተበላሸ አሠራር እንዲላቀቁ ማስቻል ነው። በተሻለ ቅልጥፍና እና ፍጥነት ማገልገል የሚችል ተቋም እንዲገነባ ነው። ምክንያቱም አገር የምትመሰለው በተቋማት ነው። ጠንካራ ተቋም ያላት አገር ጠንካራ ትሆናለች። ዜጎች የተቀላጠፈ አገልግሎት ያገኛሉ። የእኛ ዋነኛ ፍላጎት ያ ነው። ግን ደግሞ ማንኛውም አመራርም ሆነ ባለሞያ የተጣለበትን የሕዝብ አደራ በአግባቡ የማይወጣ ከሆነ ሌብነትን ማስቆም እና መቅጣት ያስፈልጋል። ይህንን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በባዕለ ሲመታቸው በይፋ ለህዝብ የገቡት ቃል ኪዳን አለ። መንግስታቸው ሌብነትን በፅኑ እንደሚዋጋ ቃል ገብተዋል። እኛም ከዚህ ጋር ተያይዞ በምንሠራው የቁጥጥር ሥራ እንቅፋት አልገጠመንም። የምንሰጣቸው ትዕዛዞችም እስከ አሁን ተፈፃሚ እየሆኑ ነው። ይህ ግን በቂ አይደለም። የምር ቁርጠኝነት ያስፈልጋል።
አንዳንድ የኦዲት ግኝቶች በተለይ የክዋኔ ኦዲት ላይ ያሉት የንብረት ብልሽቶች አስደንጋጭ ናቸው። ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ የወጣባቸው ንብረቶች አፈር በልቷቸው ሣር በቅሎባቸው እንዴትም የትም ተጥለው ይታያሉ። ይሔ እንደ ኢትዮጵያ ባለች ድሃ አገር ተቀባይነት የለውም። በእርግጥ የኦዲት ግኝት ማለት ሁሉም የተበላ የተመዘበረ ነው ማለት አይቻልም። ምናልባት ያልተመዘገበ ሊሆን ይችላል። ይህ ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል። ዋናው ነገር ግን ተጠያቂነትን ለማስፈን ቁርጠኛ የሆነ ምክር ቤት አለ። ነገር ግን ምክር ቤቱ ተጠያቂነትን ለማስፈን ቁርጠኛ ቢሆንም የኢትዮጵያ ተቋማት በሙሉ ከብልሹ አሠራር የፀዱ ይሆናሉ ማለት አይደለም። የፍትህ ተቋማት የፀጥታ አካላት ብርቱ ጥረት ማድረግ አለባቸው። መገናኛ ብዙሃን ተኪ የለሽ ሚናን መጫወት አለባቸው። መሠል ጉዳዮችን የምርመራ ጋዜጠኝነትን መሠረት አድርጎ ብልሹ አሠራርን በማጋለጥ ማህበረሰቡ ምክር ቤቱንም የሚደግፍ ሞጋች እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል።
በተባበረ ክንድ የኢትዮጵያ ተቋማት የሚታሰበውን በጎ ተስፋን የሚመጥኑ፤ ያለፈውን ብሶት ማካካስ የሚችሉ ተቋማዊ ቁመና ላይ እንዲገኙ የሚያስችል መደላድል ከተፈጠረ ቀጣዩ ምክር ቤት ደግሞ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በመጨመር የተሻለ የህዝብ ተቀባይነት ያለው ይሆናል። ይህ እንዲሆን የተቻለንን ሁሉ እየሠራን ነው። ተጠያቂነትን ለማስፈን ዝግጁነት አለ ወደ ትግበራውም እየገባን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከላይ ብልሹ አሠራርን በሚመለከት የተወሰነ ነገር ብለዋል። አሁን በሚካሔዱ የህዝብ መድረኮች ተደጋግሞ የሚነሳው ይኸው የብልሹ አሠራር እና የሌብነት ጉዳይ ነው። በእርግጥ 6ኛው ምክር ቤት አንድ አመት ብቻ አሳለፈ ብንልም አንድ አመትም ከዚህ ጋር ተያይዞ ቀላል አይደለም። በእርግጥ ምክር ቤቱ ሌብነትን ለመከላከልም ሆነ ብልሹ አሠራርን ለመቀነስ ሚናውን እየተወጣ ነው?
አቶ ክርስቲያን፡– አስቀድሜም ገልጬዋለሁ። በተሟላ መልኩ ሚናውን እየተወጣ ነው ለማለት ያዳግታል። አሁን እንደአገር ዋነኛ ትኩረታችን የአገርን ቀጣይነት ማረጋገጥ ላይ ነው። ምክር ቤትም፣ አስፈፃሚውም ሁሉም ኢትዮጵያን ለማፍረስ ፍላጎት ያላቸው ስብስቦች መኖራቸውን አውቆ እዛ ላይ እየሠራ ነው። ይሔ ለፕሮፓጋንዳ ሳይሆን በተግባር ያንን የጥፋት ዕቅዳቸውን ለመተግበር በመንቀሳቀስ በህዝባችንም ላይ ከፍተኛ በደልን ያደረሱ ማህበራዊ ቀውስ እየፈጠሩ ስለነበር ያንን ቀውስ መቀልበስ ላይ እንደነበርን አይካድም። ምክር ቤቱ ሙሉ ትኩረቱን በምክር ቤታዊ ሥራ ላይ ባላደረገበት ሁኔታ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት በሙሉ ተወጥቷል ማለት አይቻልም።
ይህም ቢሆን ግን ትርጉም ያላቸው ሥራዎች ተሠርተዋል የሚል እምነት አለኝ። ምክንያቱም በተጨባጭ የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎች ወደ ተለያዩ የአገራችን ክፍሎች በመንቀሳቀስ መሬት ላይ ያለውን ኢኮኖሚያዊ፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታም ሆነ የፍትህ እና የፀጥታ ሁኔታዎችን በሚመለከት ህብረተሰቡን በማነጋገር ጭምር ክትትል በማድረግ የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወስዱ የምክር ቤት አባላቱ ሚናቸውን እየተወጡ ነው። ቋሚ ኮሚቴዎች እንዲያስተባብሩላቸው በተመደቡላቸው አስፈፃሚ ተቋማት በመከታተል ማስተካከያ እንዲያደርጉ ሲሠራ ቆይቷል። የሚታቀደው ዕቅድ የህዝብን ፍላጎት ማዕከል ያደረገ መሆኑን ክትትል በማድረግ ሲገመገም ነበር። መገምገም ብቻ አይደለም፤ በቀጣይ የመቶ ቀናት ዕቅዳቸው ውስጥ እንዲያካትቱ አቅጣጫ ሲያስቀምጥ ነበር። ይሔ በጎ ጅምር ነው። ነገር ግን ለዘመናት የተከማቸውን የሕዝብ ችግር ሊቀርፍ የሚችል አይደለም። እንኳን መቅረፍ ሊያስታግስ የሚችል አይደለም። እንቅልፍ አጥተን ሌት ተቀን መሥራት ይኖርብናል። ይሔ ከተለመደው ምክር ቤት ከፍ ያለ ምናልባትም የህዝብን ፍላጎት ከማሳካት፣ የአገር አንድነትን ከማስቀጠል የህዝብን ደህንነት ከማረጋገጥ አንጻር በአርበኝነት መንፈስ መሥራት ያለበት፤ ሁለንተናውን ለአገር አንድነት እና ለህዝብ ደህንነት መስጠት ያለበት ነው። ይህ የምክር ቤቱ እና የትውልዱ ሃላፊነት ነው የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ
አቶ ክርስቲያን፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 27 /2014