
ሶስቱም ሀገራት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በመፈንቅለ መንግሥት ሲታመሱ የቆዩ ሀገራት ናቸው የጊኒው ጁንታ ባወጣው መግለጫ ‹‹ስልጣን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለማሸጋገር ቢያነስ 39 ወራት ያስፈልገኛል›› ብሏል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ኃላፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ቡርኪናፋሶ፣ ጊኒና ማሊ በፍጥነት ወደ ሲቪል አገዛዝ እንዲመለሱ አሳስበዋል። አገራቱ በሳህል ቀጠና ካለው የጂሃዲስት ዓመጽ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ትግል ሲያደርጉ የነበሩ ሀገራት ቢሆኑም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ፤ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ሲታመሱ የቆዩ ናቸው።
በአፍሪካ ‹‹የረመዳን የአጋርነት ጉብኝት›› ላይ የሚገኙት ጉቴሬዝ፤ ሴኔጋል ዳካር ከፕሬዚዳንት ማኪ ሳል ጋር በነበራቸው ቆይታ ሶስቱም ሀገራት በፍጥነት ወደ “ህገ-መንግሥታዊ ሥርዓት” ሊመለሱ ይገባል ማለታቸውን ኤ.ኤፍ.ፒ ዘግቧል።
በማሊ በነሐሴ 2020 እና በግንቦት 2021፤ በጊኒ መስከረም 2021 እንዲሁም በቡርኪናፋሶ በጥር 2022 መፈንቅለ መንግሥት እንደተካሄደ ይታወሳል። የሴኔጋሉ ፐሬዚዳንት ማኪ ሳል፤ ሶስቱንም ሀገራት ከአባልነት ያገደው የምዕራብ አፍሪካ ህብረት ኢኮዋስ ሊቀመንበር ናቸው።
የምእራብ አፍሪካው ተቋም ኢኮዋስ በማሊ በጥር ወር ከፍተኛ ማዕቀብ ቢጥልም፤ የማሊው ወታደራዊ ኃይሎች ስብስብ እስካሁን ስልጣን ወደ ሲቪል መመለስ ሳይችል ቀርቷል።
ኢኮዋስ ጊኒ እና ቡርኪናፋሶ ስልጣንን በፍጥነት ወደ ሲቪል አገዛዝ ማሸጋገር ካልቻሉ “በምክንያታዊ” የጊዜ ገደብ ውስጥ ተመሳሳይ ማዕቀብ ሊጣልባቸው እንደሚችል ማስጠንቀቁ አይዘነጋም።
ነገር ግን የሁለቱም ሀገራት ወታደራዊ መንግሥታት፤ ኢኮዋስ ያወጣውን የጊዜ ሰሌዳ አልተቀበሉትም። የቡርኪናፋሶው ወታደራዊ ኃይል ቀደም ብሎ ይፋ ያደረጉትን የሶስት ዓመት የሽግግር ጊዜ ለማሳጠር እቅድ እንደሌለው መግለጹ ይታወሳል፡፡
በተመሳሳይ ኢኮዋስ፤ የጊኒው ወታደራዊ ኃይል ቢያንስ በ16 ወራት ውስጥ ስልጣኑን ለሲቪል አስተዳደር ማስረከብ አለበት የሚል የጊዜ ገደብ አስቀምጦ የነበረ ቢሆንም፤ የጊኒው ጁንታ የኢኮዋስን ምክረ-ሃሳብ እንደማይተገብር በትናንትናው እለት ባወጣው መግለጫ አረጋግጧል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25 ቀን 2014 ዓ.ም