የአላባማ ግዛት ፖሊስ በግድያ ወንጀል የተከሰሰ እስረኛ እና ከእርሱ ጋር አብራው የጠፋች የማረሚያ ቤት መኮንንን እያሰሰ ነው።
እስረኛ ኬሲ ዋይት የማረሚያ ቤቱ መኮንን ከሆነችው ቪኪ ዋይት ጋር ለመጨረሻ ጊዜ አብረው ቢታዩም በኋላ ግን ሁለቱ ግለሰቦች የት እንደገቡ አልታወቀም።
የማረሚያ ቤቱ መኮንን ቪኪ ዋይት እስረኛውን ኬሲ ዋይትን ለአዕምሮ ጤና ግምገማ እየወሰደችው እንደነበር ተናግራ የነበረ ሲሆን፣ በኋላ ላይ ግን ባለሥልጣናት የአዕምሮ ጤና ግምገማው ቀድሞ ፕሮግራም የተያዘለት እንዳልነበር ደርሰውበታል።
ባለሥልጣናት መኮንኗ፣ እስረኛው እንዲያመልጥ ረድታው አልያም ደግሞ በግለሰቡ ታግታ እንደሆነ ለማጣራት ምርመራ እያካሄዱ ነው።
እስረኛውና ጠባቂዋ በስም ቢመሳሰሉም ዝምድና ግን የላቸውም። ባለሥልጣናት እንደሚሉት እስረኛው ኬሲይ ዋይት የፖሊስ አባሏን መሳሪያ ይዞ ሊሆን ስለሚችል የታጠቀና አደገኛ ነው ተብሎ ይታሰባል።
የላውደርዴል ካውንቲ ፖሊስ አዛዥ ሪክ ሲንግልተን በሰጡት መግለጫ መርማሪ መኮንኗ ለባልደረቦቿ እስረኛውን ለአዕምሮ ጤና ግምገማ ፍርድ ቤት ልታደርሰው እንደሆነ በመንገር ከእስረኛው ጋር እስር ቤቱን ለቀው ወጥተዋል።
ከዚያም ጤንነት እየተሰማት ስላልሆነ ህክምና ለማግኘት እንደምትጥር መናገሯን የፖሊስ አዛዡ ተናግረዋል። ሁለት ሰዓታት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ግን መኪናዋን በአንድ የንግድ ማዕከል የመኪና ማቆሚያ ስፍራ ውስጥ ተገኝቷል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
ከዚያ በኋላም ባለሥልጣናት እስረኛው ወደ እስር ቤቱ አለመመለሱንና ማንም መኮንኗን ሊያገኛት እንዳልቻለ ተረዱ። ይህንንም ተከትሎ የአሜሪካ የማርሻል አገልግሎት ኬሲ ዋይትና ቪክ ዋይት ያሉበትን ለሚጠቁም እስከ 10 ሺህ ዶላር ድረስ እንደሚሸልም አስታውቋል።
የአሜሪካ ማርሻል ኬሲ ዋይት ለመኮንኗ እና ለሕዝቡ ደህንነት ስጋት እንደሆነ እንደሚታመን በመግለጫው አመልክቷል።
ሼሪፍ ሲንግልተን እንዳሉት የእስር ቤቱ ተቆጣጣሪ መኮንኗ በሥራ ክፍሏ ለ25 ዓመታት አገልግላለች።
የእርምት ረዳት ዳይሬክተር ስትሆን እስረኞችን ወደ ፍርድ ቤት መውሰድ ከኃላፊነቶቿ መካከል አንዱ ነው።
እስረኛውን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ በራሷ የወሰነችው ውሳኔ ፖሊሲን የሚጥስ መሆኑን የተናገሩት የፖሊስ አዛዡ፤ “እንደዚህ በከባድ ወንጀል የተከሰሰ ሲንቀሳቀስ በሁለት ፖሊሶች መታጀብ አለበት” ብለዋል።
በመርማሪዋ መጥፋት እና በክስተቱ ሁሉም ሠራተኛ ተደናግጧል ብለዋል።
ሼሪፍ እንደሚሉት እርሷን ከመውቀሳቸው በፊት ጥፋተኛ መሆኗን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ማየት እንደሚፈልጉም አክለዋል። “እንዲያመልጥ አግዛው ነው? ወይስ ይዛው ስትሄድ አግቷት ነው? የሚለውን እየመረመርን ነው” ብለዋል።
እስረኛው ዋይት የ38 ዓመት ጎልማሳ ነው። እአአ በ2020 በ58 ዓመቷ ኮኒ ሪጂዌይ በስለት በመግደል በሁለት ከባድ የግድያ ወንጀሎች እንደተከሰሰ የአሜሪካ ማርሻል አገልግሎት አስታውሷል።
የአሜሪካ የፌዴራል ሕግ አስከባሪ ኤጀንሲ በበኩሉ ግለሰቡ እአአ በ2015 ማጭበርበርን እና የተሽከርካሪ ስርቆት ጨምሮ በተከታታይ የወንጀል ድርጊቶች በቀረበበት ክስ በእስር ላይ እንደነበር አስታውቋል።
ግለሰቡ ግድያውን መፈፀሙን በማመኑም በሎዴርዴል ካውንቲ እስር ቤት ውስጥ የፍርድ ሒደቱን እየተጠባበቀ ሳለ መጥፋቱንም ባለሥልጣናት ገልጸዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25 ቀን 2014 ዓ.ም