ሀዋሳ ከወትሮው በተለየ መንገድ ደማቅ ሆናለች። ምክንያቱ ደግሞ በየዓመቱ ተከብሮ የሚውለውን የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ ፍቼ ጫምባላላ ክብረ በዓልን አስመልክቶ ነው። ወጣቶች፣ እናቶችና ሽማግሌዎች የማኅበረሰቡን እሴቶች የሚገልፁ አልባሳት፣ የፀጉር አሠራር፣ ምግቦችና ጭፈራዎች አዘጋጅተው ከምንግዜውም በተለየ መንገድ እንድትደምቅ አድርገዋታል። የፍቼ ጫምባላላ በዓል ከክልሉ አልፎ የአገርና የዓለም የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ ሆኖ የተመዘገበ እንደመሆኑ ቀኑ ሲደርስ ሁሉም በከተማዋ ተገኝቶ ዋናው ሥነሥርዓት በሚከበርበት “ጉዱማሌ” በተባለ ሰፊ ስፍራ ላይ ያከብረዋል።
የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ ፍቼና አዲሱ ዓመት ክብረ በዓል መንፈሳዊ (ኢንታንጀብል) ባህል ከሆኑት አንዱ ሲሆን፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሻገር የመጣ የብሔሩ ማንነት መገለጫ መሆኑ ይታወቃል። በሲዳማ ሕዝብ ፍቼና ጫምባላላ የማይነጣጠሉ የበዓሉ ሁነቶች ናቸው፡፡ ፍቼ የአሮጌው ዘመን መጠናቀቅ (ዋዜማ) ጫምባላላ የአዲሱ ዘመን (መባቻ) ብስራቶች መሆኑን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አበበ ታፈሰ ለዝግጅት ክፍላችን ነግረውናል፡፡ ከዚህ እንደሚከተለው የ”ፍቼንና” የ”ጫምባላላን” ጥቂት እውነታዎች እናጋራችሁ
ፍቼ የአሮጌው ዓመት መጨረሻ የአዲሱ ዋዜማ እንደመሆኑ የብሔሩ ሊቃውንት የጨረቃና ኮከብ አቅጣጫና ቁጥር ተመልክተው የዘመን መለወጫ ትክክለኛ ወሩንና ቀኑን ከወሰኑ በኋላ ለሕዝቡ ከአንድ ሳምንት በፊት በገበያ ይታወጃል፡፡ የዘመን መለወጫ ቀኑ ከታወጀ በኋላ የብሔሩ ባህላዊ መሪዎች (ዎማች) ለፍቼ ሳምንት ሲቀረው ከአንድ ወር በፊት የጀመሩት ጾምና የሱባኤ (የንስሐ) ጸሎታቸውን ያጠናቅቃሉ፡፡ ሴቶች ለበዓሉ ማድመቂያ ቅቤ፣ ቆጮ፣ ወተትና ቅመማቅመም ያዘጋጃሉ፡ ፡ ወጣት ወንዶች እንጨት ወጣት ሴቶች ለእናታቸውና ረዳት ለሌላቸው ጎረቤቶች የሚያቀርቡበትና የሚረዱበት ጊዜ ይሆናል፡፡ ዋዜማን ከደረሱ በኋላ በእርጥብ ቅጠል የተዘጋጀ መሽሎኪያ (ሁሉቃ) ፀሐይ ስታዘቀዝቅ የቤተሰቡ አባላትና ከብቶች በዚያ ሾልከው እንዲያልፉ ይደረጋል፡ ፡ ጫምባላላ (ዞሮ መምጣት ማለት ነው) አዲሱ ዓመት የሚጀመርበት ልጆች ምንም ሥራ የማይሠሩበትና እየዞሩ የሚመገቡበት፣ ከብቶች ለዚህ ቀን ተከልሎ በቆየ ጥብቅ(በረት) ውስጥ ተለቀው የሚግጡበት ቀን ነው፡፡ ልጆቹ ‹‹አይዴ ጫምባላላ››(ዞረን መጣን) እያሉ ተስብስበው በየአካባቢው ሲዞሩ እናቶች ‹‹እሌ…እሌ..››፣ ወይም ‹‹ድረሱ….ድረሱ›› በማለት በቅቤ የተዘጋጀውን ቆጮ (ቡሪሳሜ) ያቀርቡላቸውና ይበላሉ፡፡
የዘንድሮው የፍቼ በዓል አከባበር
የሲዳማ ማኅበረሰብ የማንነት ጥያቄ ለዘመናት ሲያነሳ ቆይቶ አሁን ጥያቄዎቹ ተመልሰውለት የኢትዮጵያ አስረኛ ክልል መሆን ችሏል። ይህ አጋጣሚ ደግሞ ማኅበረሰቡ ቋንቋውን ባህሉንና ሌሎች ታሪካዊ ሃብቶቹን ጠብቆና አስተዋውቆ ማሳደግ እንዲችል ከምን ግዜውም በላይ እድል እንደፈጠረለት እየተነገረ ይገኛል።
የዘንድሮው አከባበር ሥነ ሥርዓትም ይህን ድባብና ድርብ ድል ታሳቢ አድርጎ በድምቀት ሊከበር ችሏል። ከከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ የገዳ መሪዎች፣ ሽማግሌዎችና የአገር ውስጥና የውጪ ጎብኚዎችም በዚህ የፍቼ ጫምባላላ በዓል ላይ ተሳታፊ ነበሩ።
በዩኒስኮ በማይዳሰሱ ቅርሶች ዘርፍ የዓለም ባህላዊና መንፈሳዊ ሃብት ሆኖ የተመዘገበው ይህ ሃብት በርካታ ገፅታዎችና በውስጡ ጠብቆ ያቆያቸው እሴቶችን የያዘ ነው። በመሠረታዊነት “የፍቼና” የ”ጫምባላላ” በዓላት ዋንኞቹ ሥነሥርዓቶች ሲሆኑ፣የአሮጌውን ዓመት ሽኝት እና የአዲሱን ዓመት አቀባበል ይወክላሉ። ከዚህ በመነሳት በዘንድሮው የሲዳማ ብሔር መገለጫ ባህል ላይ የፍቼ (ዋዜማ) ሥነሥርዓት ልዩ ልዩ እንግዶች በተገኙበት ተከብሮ አልፏል።
የሲዳማ ብሔር የአዲስ ዘመን መለወጫ ዋዜማ የሆነው የ”ፍቼ” (ዋዜማ) በሲዳማ የባህል አዳራሽ ነበር ሥነሥርዓት የተከናወነው። በፍቼ የዋዜማ ክብረ በዓል ላይ የተገኙት የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ደስታ ሌዳሞ “የፍቼ ጨምባላላ በዓል ለሲዳማ ሕዝብ ታላቅ በዓል ነው” በማለት ለብሔረሰቡም ሆነ ለመላው ኢትዮጵያ ያለውን ትርጉም ተናግረው ነበር። በተለይ በውስጡ የያዛቸው እሴቶች የአገር በቀል እውቀቶችን ሲሆን የአንድነት፣የእርቅ የመተሳሰብ ተምሳሌት መሆናቸውን ጠቅሰው እነዚህን ሃብቶች ለኢትዮጵያውያን ታላቅ ስጦታ እንደሆኑ ይገልፃሉ። ከመቼውም ግዜ በተለየ የፍቼ ጨምባላላ የሚፈቅደውን ወንድማማችነት፣ አንድነትና ፍቅር መሠረት በማድረግ መላው ኢትዮጵያዊ ሕብረቱን ለማጠናከር የሚፈጥረው እሴትም ጉልህ እንደሆነ ይናገራሉ። በአዲሱ የዘመን መለወጫም አዲስ አስተሳሰብና ፍቅርን መላበስ እንደሚያስፈልግ አንስተው የፍቼ ጫምባላላ ዋነኛ መሠረትም ይህ እንደሆነ ተናግረዋል።
“የዘንድሮውን የፍቼ ጫምባላላ በዓል ስናከብር ደስታችን እጥፍ ድርብ ሆኖ ነው” ያሉት የክልሉ ፕሬዚዳንት፤ የሲዳማ ሕዝብ ጥያቄዎች የተመለሱበት በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል በማለት በፍቼ የዋዜማ ክብረ በዓል ላይ በሲዳማ የባህል አዳራሽ ለተገኙ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ ከአንድ ሺህ 100 በላይ ተሳታፊዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። ከፌደራል እና ከክልሎች የመንግሥት መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ እንግዶችና ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት በፍቼ የዋዜማ ሥነ ሥርዓት ላይ መሳተፋቸው ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየ መንገድ በዓሉ ልዩ ይዘትና ድምቀት እንዲኖረው አድርጎት አልፏል።
ባህላዊ መሪዎች
በዘንድሮው የፍቼ ጫምባላላ በዋነኝነት በብሔሩ ባህላዊ መሪዎች (ዎማች) በፍቼ ዋዜማና በጨምባላላ በአዲሱ ዓመት መጀመሪያ ላይ ተገኝተው ባህላዊ ምርቃት የሚሰጡበት ሲሆን፣በተለይ በዋዜማው ዕለት በባህሉ መሠረት የሚከናወን በእርጥብ ቅጠል የተዘጋጀ መሹለኪያ (ሁሉቅ) ውስጥ የማለፍ ሥነሥርዓት አካሂደዋል። በፍቼ በዓል ላይ ሻፌታ በጋራ ተቆርሶ የተቀመሰ ሲሆን፣ልዩ ልዩ ባህላዊ ሥነሥርዓትም ተከናውናል።
በሀዋሳ ጉዱማሌ የጫምባላላ የአዲስ ዘመን መለወጫ በተከበረበት ወቅት በስፍራው የተገኙት የባህል ሚኒስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳ ይህን ታላቅ የሲዳማ ሕዝብ መገለጫ አስመልክተው ሲናገሩ የፍቼ ጫምባላላ በዓል ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ በሲዳማ ብሔር አባላት ዘንድ በየዓመቱ በድምቀት የሚከበር የዘመን መለወጫ በዓል መሆኑን አንስተዋል፡፡ በዓሉ በቤተሰብና በጎረቤት ደረጃ ተሰባስቦ በማክበር የሚጀምርና ከዚያም እየሰፋ በመሄድ በባህላዊ አደባባይ (ጉዱማሌ) በጋራ የማክበር ሒደትን የሚያጠቃልል ነው በማለትም ከወንድም ሕዝቡ የኦሮሞ የኢሬቻ ሥነሥርዓት ጋርም ብዙ የሚያመሳስለው ሥነሥርዓቶች እንዳሉት አስረድተዋል፡፡
ፍቼ ከዘመን መለወጫ በዓልነት ፋይዳው ባሻገር በርካታ ባህላዊና ማኅበራዊ ፋይዳዎች ያሉት መሆኑን በመግለፅም ፣ ሃገር በቀል የሆነ የዘመን አቆጣጠር ዕውቀትን አካቶ ከመያዙ ባሻገር የሲዳማ ብሔር አንኳር የሆኑ ባህላዊ ገጽታዎች የሚንፀባረቁበት ኢንታንጀብል (ግዙፍነት የሌለው ወይም የማይዳሰስ) ቅርስ መሆኑን
መስክረዋል፡፡ የፍቼ በዓል ሰላም፣ መከባበር፣ መቻቻል እንዲሰፍን፣ ዕርቅ እንዲወርድ እንዲሁም ልማት እንዲፋጠንና ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ የጎሳ መሪዎችና የበቁ አረጋውያን ለኅብረተሰቡ በሰፊው ትምህርት የሚሰጡበት ወቅት ከመሆኑ አንፃር ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ይህን ታላቅ ባህላዊ ሥርዓት ለመጠበቅ፣ ለማልማትና ለማስተዋወቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ እንደሚሠራ ቃል ገብተዋል፡፡
የፍቼ በዓል አፈ ታሪክ
የፍቼ በዓል በአፈ ታሪክ እንደሚወሳው መጠሪያውን ያገኘው ፊቾ ከምትባል የሲዳማ ሴት ነው፡፡ ፊቾ ዕድሜዋ ለአቅመ ሔዋን ሲደርስ በሲዳማ ብሔር ባህልና ሥርዓት መሠረት ተዳረች፡፡ ይህች ሴት በየዓመቱ ለወላጆቿ፣ ወንድሞቿ፣ ለዘመድ አዝማድና ጎረቤት ቡርሳሜ (ከእንሰት ላይ የሚፋቅ ቆጮ በእሳት ላይ ተነኩሮ እና ቅቤ በብዛት ተጨምሮበት የሚዘጋጅ ባሕላዊ ምግብ) እና እርጎ በመያዝ በየዓመቱ በሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል በሚውልበት ዕለት በቋሚነት ትጠይቃቸው
ነበር፡፡ በዓሉ የሚውለው በተመሳሳይ ቃዋዶ (በሲዳማ ብሔር የቀን አቆጣጠር የሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን) ሲሆን፣በአፈ ታሪኩ መሠረት ፊቾ ያመጣችውንም ምግብ በዚሁ ዕለት ምሽት ላይ ዘመድ አዝማድ፣ የአካባቢ ጎረቤትና ቤተሰብ ተሰባስበው ይመገቡት ነበር፡፡ አባቷና ታዳሚዎች ዘወትር የፊቾን ደግነትና ያመጣችውን ምግብ በማድነቅ ይመርቋታል፡፡ ፊቾ ይህንን በተደጋጋሚ ስትፈጽም ቆይታ ከዚህ ዓለም በሞት ስትለይ የአካባቢው ነዋሪዎች ፊቾ በመሞቷ ጥልቅ ሐዘን የተሰማቸው ከመሆኑም በላይ የሷ ድግስ ታዳሚ የነበሩ ሰዎች ይህችን ሩህሩህ ደስታ ፈጣሪ ሴት በዘላቂነት ለማስታወስ ይቻል ዘንድ ቀደም ሲል እርሷ ምግብ ይዛ የምትመጣበትንና ግብዣው የሚካሄድበትን የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ ቀን በስሟ ፍቼ ብለው ሰየሙት፡፡ የፍቼ በዓል ሁሌም በቃዋዶ ቀን የሚውልበት ምክንያት ቀኑ በብሔሩ የሳምንቱ የመጀመሪያውና ታላቅ ቀን ተደርጎ የሚቆጠር በመሆኑ ነው፡፡
ማኅበራዊ ክንዋኔዎች
የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አበበ ታፈሰ የጫምባላላን ማኅበራዊና ባህላዊ ክንዋኔ ከዚህ እንደሚከተለው አብራርተውልናል።
የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል የሆነው ፍቼ ለሁለት ሳምንታት ያህል በድምቀት የሚከበር ሲሆን አከባበሩም ቅደም ተከተላዊ ሥርዓትና ሂደት ያለው
ነው፡፡ ከነዚህ ማኅበራዊ ክንዋኔዎች መካከል የመጀመሪያው ላኦ (ምልከታ) ነው፡፡ የፍቼ በዓል ሁሌም በብሔሩ የሳምንቱ የመጀመሪያው ቀን ማለትም በቃዋዶ ቢውልም ቀኑ በየዓመቱ በተመሳሳይ ቀን ስለማይውል መቼ እንደሚውል ተለይቶ የሚታወቀው በባህላዊ ቀን ቆጠራ ስሌትና የሥነ ክዋክብት ምልከታ ነው፡፡ የሥነ ክዋክብት ምልከታውን የሚያከናውኑት አያንቶ የተሰኙ የሥነ ክዋክብት ጠበብቶች ናቸው፡፡ አያንቶዎች ቡሳ የተሰኙ ኅብረ ክዋክብት ከጨረቃ አቀማመጥ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማገናዘብ ማለትም የክዋክብቱ ከጨረቃ የመቅደምና ወደ ኋላ የመቅረት ሁኔታ በትኩረት በመከታተል በተለይ ከክዋክብቱ መካከል አውራ የሆነችው ኮከብ ከጨረቃ መቅደሟን ሲያረጋግጡ ፍቼ በቀጣይ ቀናት ውስጥ ባለው የቃዋዶ ዕለት እንደሚውል ይወስናሉ፡፡
ከዚያም የሥነ ክዋክብት ምልከታውን የሚያከናውኑት አያንቶዎች የፍቼ በዓል የሚውልበትን ቀን ለጎሳ መሪዎች (ገሮ) ያሳውቃሉ፡፡ አያንቶዎች ባቀረቡት ሐሳብ ላይ ተመሥርተው የጎሳ መሪዎች ከጪሜሳዎች (የበቁ አረጋውያን) ጋር ሶንጎ (የአዛውንቶች ስብሰባ) በማድረግ በጉዳዩ ላይ ከተወያዩ በኋላ ቀኑ በአዋጅ ለኅብረተሰቡ እንዲገለጽ ከስምምነት ይደርሳሉ፡፡ የጎሳ መሪዎችም በየአካባቢያቸው በሚገኙ የገበያ ሥፍራዎች የበግ ቆዳ ረዥም ዘንግ ላይ ሰቅለው በመያዝ ለኅብረተሰቡ የፍቼ በዓል የሚውልበትን ቀን ያውጃሉ (ላላዋ ያደርጋሉ)፡፡ ከላላዋ በኋላ ሳፎቴ ቄጣላ (የመጀመሪያው ባህላዊ ጭፈራ) ይቀጥላል፡፡
ፍቼ ጫምባላላ ከሲዳማ ብሔር ባህላዊ ሃብትነት ባሻገር በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣የሳይንስና የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) የማይዳሰስ መንፈሳዊ ሃብትነት ከተመዘገቡ የኢትዮጵያ ሃብቶች መካከል የሚመደብ ነው። እንደሌሎቹ መሰል የአደባባይ በዓላት ሁሉ ይህ ታላቅ ባህልም ለሕዝቦች አንድነት፣ መተሳሰብና ፍቅር ምሰሶ በመሆኑ ልናለማው፣ ልንጠብቀውና በተገቢው መንገድ ለትውልድ እንዲሻገር ልናስተዋውቀው እንደሚገባ ጠቁመን ሃሳባችንን እዚህ ላይ እንቋጫለን።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23 ቀን 2014 ዓ.ም