
አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መጪውን 1443ኛውን የኢድ አልፈጥር በዓል ምክንያት በማድረግ በአንድ ቀን ብቻ ከ101 ሺ በላይ ለሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ማዕድ ማጋራቱን አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የኢድ አልፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ ትናንት የማዕድ የማጋራት መርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት፤ መስጠት አያጎድልም ይልቁንም ካለን ላይ ይጨምራል።
ከዚህ ቀደም የፋሲካ በዓልን ምክንያት በማድረግ የኑሮ ውድነቱ ጫና የፈጠረባቸውን ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውንና ምንም ገቢ የሌላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ታሳቢ በማድረግ ማዕድ የማጋራት ሥራ ሲሠራ ቆይቷል።
በዓላት የሚፈጥሩትን ጫና ምክንያት በማድረግም ሰፋ ያለ ማዕድ የማጋራት መርሃ ግብር እየተከናወነ ነው።የፋሲካ በዓልን ምክንያት በማድረግ በሁሉም ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች 240 ሺ ለሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ማዕድ እንደተጋራ አስታውሰዋል።
የኢድ አልፈጥርን በዓል ምክንያት በማድረግም ከአንድ መቶ አንድ ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች በአጠቃላይ በከተማዋ ማዕድ መጋራቱን ገልጸዋል።
መስጠት አያጎድልም ያሉት ከንቲባዋ፤ ‹‹ እኛ ኢትዮጵያውያን በመስጠት በመተሳሰብ፣ እርስ በርሳችን ተረዳድተን፣ አንተ ትብስ፣ አንቺ ትብሽ ተባብለን የኖርን ሕዝቦች ነን››።እርስ በእርሳችን መደጋገፋችን አላጎደለብንም ይልቁንም ጠንካራ ማኅበረሰብ ለመገንባት አጋዥ ሆኗል ብለዋል።
እንደ ወይዘሮ አዳነች ገለጻ፤ በአሁኑ ጊዜ የኑሮ ውድነቱ ጫና የሚፈጥርባቸው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የከተማችን ነዋሪዎችና ምንም ገቢ የሌላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ማድረግ ተመልካች ያላቸው የመንግሥት አካል፣ የተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶችና የማኅበረሰብ ክፍሎች እንዳሉ ማሳያ ነው።የኑሮ ውድነቱ ያስከተለውን ይህን አስቸጋሪ ጊዜ በመደጋገፍ ማለፍ አለብንም ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረተሰብ ተሳትፎና የበጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አስፋው ተክሌ እንደተናገሩት፤ እኔነትን በመተው እኛነትን በማስቀደም ካለን ላይ ስናካፍል ለአንድነታችን ሁሉንም ዋጋ የምንከፍል መሆናችን ማሳያ ነው።በመረዳዳትና በመደጋገፍ ይህን አስቸጋሪ ጊዜ ማሳለፍ ይገባል።የኑሮ ውድነት የተጫነው ወገናችን ማድረግ የሚቻለውን ሁሉ በትብብር መርዳት ያስፈልጋልም ብለዋል።
መደጋገፋችን ለአንድነታችንና ለአብሮነታችን ሁሉንም ዋጋ የምንከፍል ሕዝቦች መሆናችን ማሳያ ነው ያሉት አቶ አስፋው፤ መቻቻልና መደጋገፍ የሚባለውን የቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን ለዓለም ማኅበረሰብ የሰጠነው የችግሮች መፍቻ ሀብትና የማይዳሰስ ቅርሳችን ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በትናንትናው ዕለት አንድ ሺ አንድ መቶ 84 ለሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች 20 ሺ 396 ኩንታል ዱቄት፣ ሰባት ሺ 134 ኩንታል ሩዝ፣ ስድስት ሺ 632 ኩንታል ማካሮኒ፣ ስድስት መቶ 63 ሺ 200 ፓስታ (በፍሬ)፣ ሦስት መቶ አራት ሺ 920 ሊትር ዘይትና ሰባት ሺ ሁለት መቶ ስድስት ካርቶን ቴምር ድጋፍ ተደርጎላቸዋል። በተጨማሪም አንድ መቶ 82 በሬ፣ አንድ ሺ አንድ መቶ 76 በግ፣ 16 ሺ ሁለት መቶ አንድ ዶሮ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን፤ በገንዘብ ሲተመን ከሁለት መቶ 12 ሚሊዮን ብር በላይ ነው ብለዋል።
በአጠቃላይ ከሚያዝያ አንድ ጀምሮ ባለፉት አራት ሳምንታት ለሦስት መቶ 41 ሺ 480 የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ የተደረገ ሲሆን፤ ማዕድ የማጋራት ሥራው ለሚቀጥሉት ሦስት ወራት እንደሚቀጥልም ተገልጿል።
ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 23 ቀን 2014 ዓ.ም