ክፉና ደጉን መለየት በማንችልበት የሕጻንነት እድሜ ላይ እያለን ለወላጆቻችን እንደ ጌጥ የምንታይ ነን። መሮጥ፣ መቦረቅ፣ መጫወት … የዘወትር ተግባራችን ናቸው። ትንሽ ከፍ ስንል ደግሞ ወላጆቻችን ፊደል እንድንቆጥር ትምህርት ቤት ያስገቡናል። በዚህ ወቅትም ከልጅነት ጓደኞቻችን ጋር በሳቅ በጫወታ እየደመቅን ትምህርታችንን እንማራለን፤ አንዳንዴም እዚያው ተቧቅሰን እዚያው እንታረቃለን። እርስ በርሳችን ጉንተላና ጥል እናብዛ እንጂ ቂምና በቀልን አናውቅም። እንባችን ከአይናችን ላይ ሳይደርቅ መልሰን እንተቃቀፋለን።
ያኔ እኛ ለዚህች ዓለም እንግዶች ስለነበርን ከጫወታ ውጭ ሌላ ነገር ያለ አይመስለንም። ስለምግባችን፣ ስለልብሳችን፣ ስለትምህርት ቁሳቁስ እና ስለሚያስፈልጉን ነገሮች አናስብም፤ የሚያስቡት /የሚጨነቁት/ ወላጆቻችን ናቸው።
ስለዚህ ልጅነታችንን እንወደዋለን፤ እንናፍቀዋለን፤ ግን ሁላችንም አይደለንም። አብዛኛዎቻችን ልጅነቴ … ልጅነቴ … ማርና ወተቴ ብለን ልናጣጥመው እንሞክር ይሆናል። በችግርና በስቃይ የተፈተነ የልጅነትን ዘመን ላሳለፉ ልጆች ግን ልጅነታቸው እንደ ሬት ቢመራቸው እንጂ እንደማርና ወተት ሊጣፍጣቸው ከቶ አይችልም። ትዝ የሚላቸው በልጅነታቸው ኃላፊነት ተሸክመው ሕይወታቸውን ለመምራት ያሳለፉት ውጣ ውረድ ነው።
የዛሬው የ”እንዲህም ይኖራል” አምድ እንግዳችን ከልጅነት እስከ ወጣትነት እድሜው /ከ1ኛ እስከ 12ኛ ክፍል/ እራሱን በራሱ እየረዳ፣ ራሱን ያስተማረ ነው። እንደ ልጅ እየቦረቀ፣ እየሳቀና እየተደሰተ ያደገበት ጊዜ እምብዛም ትዝ አይለውም። ከሰባት ዓመቱ ጀምሮ እራሱን በራሱ ማስተዳደር ስለጀመረ ልጅነቱ በፈተና የተሞላ ነው። ያንን በፈተና የታጀበ ሕይወት በራሱ ጥረት ለማሸነፍ ከገጠር እስከ ከተማ ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፏል። የቆሎ ተማሪ ሆኖ በእንተ ስለማርያም ብሏል፤ ኋላም በዘጠኝ ዓመቱ ከተማ ገብቶ የጉልበት ሥራዎችን እየሠራ ቤተክርስቲያን አጥር ጥግ እያደረ ዘመናዊ ትምህርቱን ለመማር ሞክሯል። ለትምህርት ቤት የሚከፍለው ገንዘብ ቢያጣ በክፍያው ፈንታ የጽዳትና የአትክልት እንክብካቤ አገልግሎት እየሰጠ ተምሯል። በትምህርቱም የተመሰከረለት ተማሪ ለመሆን በቅቷል። ከመንግሥት ትምህርት ቤት፣ የግል ትምህርት ቤት፤ ከግል ትምህርት ቤት አዳሪ ትምህርት ቤት እያለ ዳገቱን ዘልቋል።
ያ ትንሽ ልጅ አሁን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ወስዶ ውጤት በማምጣት በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ተመድቧል። ከብላቴናነቱ እስከ ወጣትነቱ ያለፈባቸው የሕይወት መስመሮች አስቸጋሪ ቢሆኑም በጽናት ተወጥቷቸዋል። ለዛሬው የአምዳችን እንግድነቱም አቢይ ምክንያቱ ይኸው ነው።
መልካሙ ሲሳይ ይባላል። የተወለደው ሰሜን ጎንደር ዞን፣ ጠራ ወረዳ፣ ጮውጮው በሚባል ለሱዳን ተዋሳኝ በሆነ የገጠር ቀበሌ ነው። ቤተሰቦቹ አርሶና አርብቶ አደር ናቸው። ሶስት ወንድምና ሁለት እህቶች አሉት። አባታቸው በአካባቢው ስለማይኖሩ ቤተሰብ የማስተዳደሩ ጉዳይ በእናታቸው ጫንቃ ላይ የወደቀ መሆኑን ይናገራል።
‹‹የሚናፈቅ የልጅነት ጊዜ የለኝም›› ይላል። በአምስትና በስድስት ዓመቱ ጋራና ሸለቆውን እየወጣና እየወረደ፤ ዝናብና ፀሐይ እየተፈራረቀበት ፍየል መጠበቁን ያስታውሳል። ያኔ እግሩ ጫማ አያውቅም፤ እንቅፋት ይመታዋል፤ እሾህም ይወጋዋል። በአካባቢው ከዘመናዊ ትምህርት በበለጠ ለኃይማኖታዊ ትምህርት ትልቅ ቦታ ይሰጣል። ልጆች በቤተክህነት ትምህርት ውስጥ እንዲያልፉ ይበረታታሉ። በዚሁ መሰረት መልካሙ የሰባት ዓመት ልጅ እያለ ከሰፈሩ ልጆች ጋር ከትውልድ አካባቢው ርቆ ሊማር ይሄዳል። በእንተ ስለማርያም እያለና መቃብር ቤት እያደረ መማር ይጀምራል። ለሁለት ዓመት ያህል የአብነት ትምህርቱን ሲከታተል ቆይቶ በዘጠኝ ዓመቱ የዲቁና ክህነት ይቀበላል።
በዲቁና ተቀጥሮ በማገልገል በሚያገኘው ገቢ መተዳደር ቢያስብም በአካባቢው በርካታ የተማሩ ልጆች በመኖራቸው እድሉን ሳያገኝ ይቀራል። እንደገና ትምህርቱን ለማሻሻል ወደ ሌላ ቦታ ይሄዳል። ትንሽ ከተማረ በኋላ መምህሩ ማስተማር ያቆማሉ። አብረውት የሚማሩት ልጆች ወደየቤተሰቦቻቸው ሲመለሱ መልካሙ እናቱ ላይ ጫና ላለመፍጠር ሲል ወደ አዲስ አበባ ሄዶ በዲቁና በመቀጠር እራሱን አሸንፎ ለመኖር ያስባል።
መልካሙ በዘጠኝ ዓመቱ ወደ አዲስ አበባ መጣ። ከዚያም ሃና ማርያም አካባቢ የቤተክህነት ትምህርት የሚያስተምሩ ሰው አሉ መባልን ሰምቶ ወደዚያው ያቀናል። በዲቁና እንዲቀጥሩትም ደጅ ይጠናል።
ነገር ግን ሁሉም ሳይሳካለት ይቀርና ጂማ አባቱ ያለበትን ቦታ አጠያይቆ ይሄዳል። አባቱ አዲስ ሕይወት በመጀመሩ ሁኔታው ለመልካሙ ምቾት አልሰጠው ይልና ተመልሶ ወደ አዲስ አበባ ይመጣል። በአባቱም በእናቱም በኩል ያለው ሁኔታ ተስፋው እንዲሟጥጥ ስላደረገው እራሱን በራሱ ማውጣት እንዳለበት ቁርጥ ውሳኔ ላይ ይደርሳል።
ወትሮም ከቤተክርስቲያን መራቅ የማይፈልገው ብላቴና አዲስ አበባ በአንድ ቤተክርስቲያን አጥር ጥግ እየተኛ ቀን ቀን ያገኘውን ሥራ ይሠራ ጀመር። በመቀጠልም ለገጣፎ አካባቢ የግለሰቦችን ግቢ ማስዋብና አትክልት የመንከባከብ ሥራ ያገኛል። በዚህ አጋጣሚ የተዋወቃቸው መልካም ሰዎች “ለምን እየሠራህ አትማርም?” የሚል ምክር ይለግሱታል።
መልካሙ በለገጣፎ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በማታው የትምህርት መርሐ-ግብር አንደኛ ክፍል ተመዝግቦ መማር ይጀምራል። ያኔ አስር ዓመቱ ነበር። የቤተክህነት ትምህርቱን ሲማር ፊደል መቁጠርና ማንበብ አጠናቆ ስለነበር ትምህርት ለመቀበል አልተቸገረም። እንደውም የተሻለ ውጤት በማስመዝገቡ ከአንደኛ ክፍል ወደ ሁለተኛ ከዚያም ወደ ሶስተኛ ክፍል ተዛውሮ በዓመቱ መጨረሻ ወደ አራተኛ ክፍል ይዛወራል። በየዓመቱ ከክፍሉ ደረጃ እየያዘ ይሸለማል። ካሉት የማታ ተማሪዎች ትንሹ እርሱ ነበር። መምህራኑ የመልካሙን ብቸኝነትና የትምህርት ብቃት ስለሚያደንቁ አንዳንድ ጊዜ ቀን ቀን የሚሠራቸውን ሥራዎች ሳይቀር ያመቻቹለት ነበር። በዚህም የበለጠ መነቃቃትን እየፈጠረና በትምህርቱም የበለጠ እየጎበዘ ይመጣል።
መልካሙ በሶስት ዓመት ውስጥ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ይሆናል። ልክ ግማሽ ዓመት ላይ እያለ የቀን ተማሪ መሆን ይፈልጋል። ይሁንና በመንግሥት ትምህርት ቤት ከማታ ወደ ቀን ለመምጣት አስቸጋሪ መመሪያዎች በመኖራቸው ኤልሮኢ ለሚባል የግል ትምህርት ቤት ያመለክታል።
የማታ ተማሪ ሰነፍ ነው የሚል የተሳሳተ ግምት ስላለ ጥቂት ወራት አይተውት በትምህርቱ ውጤታማ ካልሆነ ላይቀበሉት ተስማምተው ለጊዜው በኤልሮኢ ትምህርት ቤት ተመዝግቦ መማር ይጀምራል። ብላቴናው ግማሽ ቀን እየሠራ ግማሽ ቀን አትክልት እየተንከባከበ ከሚያገኘው ገንዘብ የትምህርት ቤት ክፍያውን እየሸፈነ ትምህርቱን ቀጠለ።
ትምህርት ቤቱን የተቀላቀለው ከግምሽ ሴሚስተር በኋላ ስለነበር ለነገሮችም አዲስ እንደመሆኑ የሶስተኛው ኳርተር (ሶስተኛው ሩብ አመት) ውጤት ሲገለፅ ከአስራ አራት ተማሪዎች አስራ ሁለተኛ ደረጃ ይወጣል። ትምህርት ቤቱ በአራተኛው ኳርተር ካላሻሻለ እንደሚያባርረው ነግሮት አንድ እድል ይሰጠዋል። መልካሙ ሰነፍ ሆኖ አልነበረም፤ ለጥናት የሚሰጠው ጊዜ ስላልነበረው ነው። ኋላ ግን ከሥራው ውጭ ያለውን ጊዜ በሙሉ ለትምህርቱ በመስጠት ጠንክሮ በማጥናት በአራተኛው ሩብ ዓመት ከክፍሉ ሶስተኛ ይወጣል።
በቀጣይ ዓመትም ሰባተኛ ክፍልን እዚያው ተምሮ በመጀመሪያው ኳርተር አንደኛ ደረጃ ይወጣል። አብዛኛውን ጊዜውን ለትምህርቱ መስጠቱን ተከትሎ እንደቀድሞው ተሯሩጦ በመሥራት ገቢውን ማሳደግ ስላልቻለ ኑሮ ይከብደው ጀመር። በሚያገኘው ገንዘብ የአልባሳት፣ የትምህርት ክፍያ፣ የቤት ኪራይና የምግብ ወጪውን መሸፈን አቃተው። መልካሙ ያኔ የአስራ አራትና አስራ አምስት ዓመት ታዳጊ ነበር።
የኢኮኖሚ ችግሩን መቋቋም ሲያቅተው እንደገና ወደ መንግሥት ትምህርት ቤት ለመግባት ይወስንና መልቀቂያ እንዲሰጠው ያመለክታል። ነገር ግን ትምህርት ቤቱ የታዳጊውን ጥረትና የትምህርት ትጋት ተመልክቶ ያለ ክፍያ እንዲማር ያደርገዋል። ብላቴናው ትምህርት ቤት ለመቀየር የፈለገው የኢኮኖሚ ችግር ስላለበት ብቻ አልነበረም፤ የተሻለ ተፎካካሪ ተማሪዎች ወዳሉበት ትምህርት ቤት ሄዶ እራሱን መመልከት ስለፈገም ጭምር ነበር።
በዚሁ መሰረት የሰባተኛ ክፍል ትምህርቱን እዚያው ኤልሮኢ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሮ ከጨረሰ በኋላ ቅዱስ ሚካኤል የሚባል የግል ትምህርት ቤት ሄዶ ይመዘገባል። ትምህርት ቤቱ ተፎካካሪ ተማሪዎች ያሉበትና በወቅቱ ጥሩ ሥም ከነበራቸው አንዱ ነው።
መልካሙ ያለበትን የኢኮኖሚ ችግር አስረድቶ ልክ አንደ ኤልሮኤ በነጻ እንዲያስተምሩት ይጠይቃቸዋል። እንደማይችሉ ይነግሩታል። ኋላ ሌላ አማራጭ ያቀርብላቸዋል። ችግኞችን እየተንከባከበና የጽዳት አገልግሎት እየሰጠ እንዲማር ይጠይቃቸዋል። የትምህርት ፍላጎት ያለው ጎበዝ ተማሪ መሆኑን ተረድተው ግማሹን ክፍያ እንዲከፍል፤ ግማሹን ደግሞ እንዳለው በጉልበት ሥራ እንዲያካክስ ይፈቅዱለታል።
መልካሙ ጠዋት ጠዋት ከተማሪዎች ቀድሞ በመግባትና ማታም አርፍዶ በመውጣት እንዲሁም እሁድና ቅዳሜ ሳይቀር ግቢውን እያጸዳና ችግኞችን እየተንከባከበ መማር ይጀምራል። በትምህርቱም ከደረጃ ተማሪዎች አንዱ ይሆናል፤ እንደውም በወረዳ ደረጃ በትምህርት ቤቶች መካከል በተደረገ የሲቪክ ትምህርት ውድድር እርሱና አንድ ጓደኛው ትምህርት ቤታቸውን ወክለው በመወዳደር ዋንጫ ያስገኛሉ።
መልካሙ በትምህርት ቤቱ አይን ከሚጣልባቸው ጎበዝ ተማሪዎች አንዱ ለመሆን ይበቃል። የስምንተኛ ክፍል ትምህርቱን በጥሩ ውጤት አጠናቆ ወደ ዘጠነኛ ክፍል ይዛወራል። የዘጠነኛ ክፍል ትምህርቱንም እዚያው ይማራል። አስረኛ ክፍል ሲደርስ ግን ለትምህርት ቤቱ የሚሰጠውን የጉልበት አገልግሎት እንዲያስቀሩለት ይጠይቃቸዋል። ትምህርት ቤቱ ፈቃደኛ ሳይሆን ይቀራል። መልካሙ በወቅቱ ትምህርት ቤቱ ከሥራ ውጭ እንዲያደርገው የፈለገው የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ የምግብ፣ የአልባሳትና የቤት ኪራይ ወጪውን ይሸፍን ስለነበርና የጊዜ ጥበት ስለገጠመው ነበር። ልጆችን በማስጠናት፣ የግለሰቦችን ግቢ በመንከባከብ፣ ዲሽ በመግጠም፣ የብየዳ ሥራ በመሥራት፣ በመደለል፣ ሰዎች አንብበው የሚጥሉትን ጋዜጣ እየሰበሰበ በኪሎ በመሸጥም ገቢ ያገኝ ነበር። የእጅ ስልኮችንም እየገዛ በትንሽ ትርፍ ይሸጥ ነበር። እንዲህ እንዲህ እያደረገ የሚያገኘውን ገንዘብ ከራሱ አልፎ ሃገር ቤት ላለችው ታናሽ እህቱም በመላክ ያስተምራት ነበር።
ትምህርት ቤቱ ጥያቄውን ሊመልስለት ባለመቻሉ የአስረኛ ክፍል ተማሪ እያለ እንደገና ወደ መንግሥት ትምህርት ቤት፤ ወደ /የካ አባዶ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት/ ይመለሳል። እዚያም ሄዶ የደረጃ ተማሪ ይሆናል። የአስረኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ወስዶ በጥሩ ውጤት ወደ አስራ አንደኛ ክፍል ያልፋል።
ከአስረኛ ወደ አስራ አንደኛ ክፍል ተዛውሮ እያለ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለአዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ሲያወዳድር መልካሙ ተመዝግቦ ይወዳደርና ያልፋል። የአዳሪ ትምህርቱን ገላን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብቶ በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ መማር ይጀምራል።
በኮረና እና በወቅታዊ የሃገሪቱ ሁኔታ ምክንያት የሁለት ዓመት ትምህርቱ ወደ ሶስት ዓመት ይሸጋገርና በ2014 ዓ.ም የ2013 ዓ.ም የአስራ ሁለተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን ይቀበላል። መልካሙ 543 በማምጣት ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሚያስገባውን ውጤት አግኝቶ ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ይመደባል። ተጠቃልሎ ወደ ካምፓስ እስኪገባም ድረስ ለአንዳንድ ወጪ ያግዘው ዘንድ የኔትዎርክ ማርኬቲንግ ሥራ እየሠራ ይገኛል።
መልካሙ ታናናሽ ወንድሞቹን የማስተማር ጉጉት ስላለው በአጭር ዓመት ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ ሥራ መያዝ ይፈልጋል። በዚህ የተነሳ ሕክምና የመማር ፍላጎቱን ገድቦታል። ሌላም ምክንያት አለው፤ መልካሙ ከራሱ አልፎ የቀን ሥራ እየሠራ ሲያስተምራት የነበረችው እህቱ በማታውቀው ሰው ተጠልፋ ከትምህርቷ መስተጓጎሏ ይቆጨዋል። ጠለፋ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የነበረና አሁን የቀረ ጎጂ ልማድ ቢሆንም በእርሱ የትውልድ አካባቢ ግን ዛሬም ድረስ አለ። ይህን ሲያስብ የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቱን ትቶ ሕግ በማጥናት ለብዙዎች ድምጽ መሆን ፈልጓል።
እኛም ለመልካሙ መልካም የዩኒቨርሲቲ ሕይወትና ቆይታ እንዲሆን እየተመኘን፤ ሌሎች ወጣቶችም ከመልካሙ እልህ አስጨራሽ ጥረትና ስኬታማ የሕይወት ጉዞ ብዙ ይማራሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22 /2014