ለየት ባለው ውዝዋዜና በፈጠራ ሥራዎቹ መድረክን መቆጣጠር ችሏል። ታዳሚውን በማስደመም አንቱታን አትርፏል ። ዳንስ ማለት ለእሱ አንድ እና አንድ ሁለት የሚል ፎርሙላ አይደለም። መደበኛ ከሆነው አካሄድ ወጣ በማለት በማንኛውም ድምጽ የተለያዩ ውዝዋዜዎች ይጫወታል፤ ይተውናል። መድረክ ላይ በሚያሳየው ተዓምራዊ እንቅስቃሴ ታዲያ አንገቱ፣ እግሩና ወገቡ ብቻ ሳይሆኑ ከራስ ጸጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ ድረስ መላ አካላቱ ይንዘፈዘፋሉ። ቀዝቀዝ ደብዘዝ አለ ሲሉት ሞቅ ደመቅ እያለ ከሚሰማው የሙዚቃ መሳሪያ ጋር በሚያሳየው ሙዚቃዊ ዳንስ የሚስተካከለው የለም።
ኪነጥበብለአንድአገርየሚያበረክተውን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አስተዋጽኦ በእጅጉ የተረዳ በመሆኑ ለዘርፉ ሰፊ ድርሻ እያበረከተ ይገኛል። ይሁንና ‹‹በእጅ የያዙት ወርቅ ከመዳብ ይቆጠራል›› እንዲሉ በዘርፉ እያደረገ ላለው አስተዋጽኦ ከአገር ውስጥ በተሻለ የውጭው ዓለም ዕውቅና እንዲሁም ሽልማቶችን በመስጠት ያበረታታዋል።ከሃገሩ ይልቅ በውጪው ዓለም አድናቆትን ተችሯል። ሽልማትም ጎርፎለታል። በሃገር ውስጥ የሚገባውን ዕውቅና አግኝቷል ለማለት ግን አልደፍርም። በርካቶች በሥራው ቢያውቁትም ለሃገር እያበረከተ ባለው አስተዋጽኦ ልክ ግን ያልተዘመረለት ባለሙያ መሆኑ አሌ የሚባል አይደለም።
ሃገርኛ በሆኑ ማናቸውም የሙዚቃ ሥራዎች ያለውን ዕምቅ አቅምና ችሎታ ማውጣት በመቻሉ በቀላሉ በዓለም አይንና ጆሮ ውስጥ መግባት ችሏል። የውጭው ዓለም ቀልቡ ያረፈበት የዕለቱ እንግዳችን ኢትዮጵያን ወክሎ በተለያየ ጊዜ ድንቅ የውዝዋዜ ብቃቱን በዓለም መድረክ አሳይቷል። በዓለም መድረክ ድንቅ ብቃቱን ማሳየት በመቻሉ በተደጋጋሚ ተሸላሚ ሲሆን አገሩን ማስጠራት የቻለ ዕውቅ አርቲስት ነው።
ባህላዊ ጭፈራዎችን በዓለም መድረክ ይዞ መቅረብ ከጀመረ ዓመታትን አስቆጥሯል። በቅርቡም በካናዳ ቫንኮቨር ከተማ በተካሄደው #TED FELLOW 2022 ሾው ላይ 1700 ከሚደርሱ ሰዎች ጋር ተወዳድሮ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ በመሆን ምርጥ 20 ዎቹ ውስጥ መግባት ችሏል። ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ማስጠራት የቻለው የዕለቱ የስኬት እንግዳችን የፈንድቃ ባህል ማዕከል መስራችና ባለቤት አርቲስት መላኩ በላይ ነው። አርቲስቱ ባህላዊ ውዝዋዜ በዓለም አቀፍ መድረክ ይዞ መቅረብ በመቻሉና በድንቅ ብቃቱ የኢትዮጵያ ስም በዓለም መድረክ ከፍ ብሎ እንዲጠራ አድርጓል።
‹‹ሥራዬ ጨፋሪነት ነው›› የሚለው የፈንድቃ ባህል ማዕከል መስራችና ባለቤት አርቲስት መላኩ፤ ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ከተማ ሲሆን ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፏል። በተለይም በጭፈራና ውዝዋዜ ፍቅር ወድቆ ብዙ ዋጋ በመክፈል ዛሬ ላይ ደርሷል። በተለያዩ ጭፈራዎቹ በተለይም በውጭው ዓለም በስፋት የሚታወቅ ቢሆንም በሃገር ውስጥ ግን ተገቢውን ቦታ ያላገኘ ስለመሆኑ መረዳት ይቻላል። በጭፈራውና በልዩ ልዩ ውዝዋዜዎቹ ሃገርን ማስጠራት የቻለ አርቲስት ቢሆንም ቅሉ ለመኖር መሥራት ግዴታው እንደሆነም ይናገራል። ሥራውም ጭፈራ ሲሆን ከሃገር ውስጥ በበለጠ በውጭው ዓለም ዕውቅናን አትርፎበታል። የበርካታ ሽልማቶች ባለቤት መሆን ችሏል። ስሙ በዘርፉ በዓለም ናኝቷል።
ቀድመው ስራውን ከተመለከቱት ከፈረንሳይ፣ ከሞሮኮ፣ ከኳታር መንግሥትና ከሌሎችም የዋንጫና የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝቷል። በሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የውዝዋዜ ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ከሆላንድ መንግሥትም የዓለም ሎሬት ማዕረግን አግኝቷል። በዚህ ጊዜ ታድያ 84 አገራት ለውድድር ቀርበው አፍሪካን በመወከል ተሸላሚ ሆኗል። በውድድሩ ተሳታፊ መሆን የቻለውም የሚሠራቸውን ሥራዎች ከጀርባው ሆነው ሲከታተሉ በነበሩ አካላት እንደሆነ የሚናገረው አርቲስት መላኩ፤ ፈጠራ የታከለበት ሥራውን ከልቡ በመነጨ ፍቅርና ፍላጎት የሚሠራው መሆኑን ይናገራል።
በውዝዋዜው አብረውት የሚሠሩ ቡድኖችን ይዞ ከሃገር ውጭ በመውጣት የሃገሩን ባህል በተለያየ ጊዜም ማሳየት ችሏል። ምንም እንኳን በሃገሪቱ የጭፈራና የውዝዋዜ ሥራ ትኩረት የተሰጠው ባይሆንም አርቲስቱ ግን ትልቅ የሙያ ዘርፍ መሆኑን ተረድቷል። ሙያውን አክብሮም በዓለም ደረጃ ለውድድር በመቅረብ አሸናፊነትን ተጎናጽፏል። የተሠማራበት የጭፈራና የውዝዋዜ ሙያ ወደፊት የት መድረስ እንደሚችል ብዙ አመላካቾችን እያሳየ ነው።
ማኅበረሰባችን ለተለያዩ ሙያዎች ያለው አመለካከት የተንሸዋረረ ቢሆንም አርቲስቱ ከውስጡ በሚመነጭ ፍላጎትና ዕውቀት የውዝዋዜ ሙያውን ተጠቅሞ ሌሎችንም መጥቀም ችሏል። ከዚህም ባለፈ ሃገርን በዓለም አደባባይ እያስጠራ ገጽታዋንም እየገነባ ይገኛል። በመሐል አዲስ አበባ ካዛንቺስ ያቋቋመው ፈንድቃ የባህል ማዕከል ከውዝዋዜውና ጭፈራው ባሻገር የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲሰጥ ማድረግ በመቻሉ በጥቅሉ ፈንድቃ የባህል ማዕከል የአርት ማኅበረሰብ የሚገኝበት ነው ማለት ይቻላል።
በባህል ማዕከሉ ከሚስተናገደው የሙዚቃ ሥራ በተጨማሪ የስዕል፣ የግጥምና ሌሎች የጥበብ ሥራዎችም የሚቀርቡበትን ዕድል ያመቻቸው አርቲስት መላኩ፤ የውዝዋዜም ሆነ የስዕል ሥራ በሃገሪቱ እንደ ሙያ መታየት ካለመቻሉ የተነሳ ዘርፉ ቦታ መድረስ አልቻለም ከሚል ቁጭት በመነሳት መሆኑን ያስረዳል። ቁጭቱን ለመወጣትም በፈንድቃ ባህል ማዕከል የሥዕል ጋለሪ፣ ቤተመጽሐፍት፣ አዝማሪ ቤት፣ ጃዝ የግጥም ምሽትና ሌሎች የጥበብ ሥራዎች መንሸራሸር እንዲችሉ ሜዳውን አመቻችቷል።
በተመቻቸው ሜዳ ላይ ታድያ በርካቶች ችሎታቸውን እያጎለበቱ አቅምና ብቃታቸውን እያወጡ ሲሆን በተለይም ለሰዓሊያን ብሎ ባዘጋጀው የሥዕል ጋለሪ በየሶስት ሳምንቱ ሥዕላቸውን ለዕይታ ለሚያቀርቡና ለሚሸጡ በርካታ ሰዓሊያን ሰፊውን በር መክፈት ችሏል። አንድ ሰዓሊ የሥዕል ሥራዎቹን ለተከታታይ ሶስት ሳምንት ለዕይታ የሚያበቃና መሸጥ የሚችል ሲሆን ሌሎችም እንዲሁ እንደየቅደምተከተላቸው ሥዕላቸውን ለዕይታና ለገበያ ያቀርባሉ። ወደ ፈንድቃ የባህል ማዕከል የሚመጡ ደንበኞችም የጥበብ ሥራዎቹን የመመልከትና የመግዛት ዕድል ያገኛሉ።
‹‹ጭፈራን በእናቴ ሆድ ውስጥ እያለሁ ነው የጀመርኩት›› የሚለው አርቲስት መላኩ ከልጅነቱ ጀምሮ ሙዚቃ የሚመስል ድምጽ ካለ የእሱ ሰውነት በእንቅስቃሴ ያደምቀዋል። ሙዚቃ ባለበት ቦታና ሰዎች ሰብሰብ ብለው ከደረሰ መሐል ገብቶ መወዛወዝ ውስጡ እንደነበር ያስታውሳል። በተለይም ሠርግ ቤትና ጥምቀት የመጀመሪያዎቹ የውዝዋዜ ትምህርት ቤቶቹ እንደነበሩ ይናገራል። በዚህ ሁኔታ የጀመረው ውዝዋዜ ዛሬ ከሃገር አልፎ በዓለም አቀፍ መድረክ ታዋቂ አድርጎታል። አርቲስቱ ጭፈራዎቹ ዝም ብሎ ጭፈራ አልያም እስክስታ ብቻ ሳይሆኑ፤ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ በርካታ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ያነሳል፤ ይጠይቃል፤ ይሞግታልም። ይህም ለየት ከሚያደርጉት ችሎታዎቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
በማንኛውም መድረክ ላይ ከተገኘ ቀዳሚ ሥራው መረበሽ እንደሆነ የሚናገረው አርቲስቱ፤ ውዝዋዜን በመደበኛው ስልጠና ሳይሆን ከስድስተኛው የስሜት ህዋሱ በላይ ባለው ስሜት ውስጥ ሆኖ እንደሚሠራና ከፍ ብሎ ብዙ ርቀት እንደሚጓዝም ይናገራል። ይህ ደግሞ ከሌሎች ተወዛዋዦች ለየት እንዲል አድርጎታል። ለአብነትም መርካቶ በተለምዶ ምን አለሽ ተራ ተብሎ ከሚጠራበት አካባቢ በሚወጡ የተለያዩ ቂው ቋ ኪል ቋቋ… አይነት ድምጾች ብቃቱን ማሳየት የቻለ ሲሆን ይህም በማንኛውም ድምጽ መጨፈር መቻሉን ያረጋገጠ ነው።
ማኅበረሰቡን የሚያነቁ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ ሕይወት ያለው ሥራ በመሥራት የሚታወቀው አርቲስት መላኩ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራዎቹን ለማሳየት ወደ ውጭ አገር መሄድ የቻለው ፈንድቃ ባህል ማዕከልን በሚጎበኝ አንድ የውጭ ዜጋ አማካኝነት እንደሆነ አጫውቶናል። በወቅቱ ብዙዎች ተመልሶ እንደማይመጣ ግምት ቢኖራቸውም እርሱ ግን በሃገሩ ተስፋ አለውና ህልሙን ሊኖረው ወደ ሃገሩ ተመልሷል። ይሁን እንጂ በተለያዩ ውድድሮችና ሌሎች ፕሮግራሞችም በተደጋጋሚ ወደ ውጭው ዓለም ቢሄድም ከሥራው በኋላ የውዝዋዜ አባላቱን ይዞ ወደ ሃገሩ ይመለሳል።
ጭፈራን ከመጨፈር ባለፈ በማስተማርም ሰፊ ጊዜ ሰጥቶ ላለፉት ሰባት ዓመታት በየቤቱ ተዘዋውሮ ሲያስተምር እንደነበርም አጫውቶናል። በዚያን ወቅት ታድያ አዝማሪ ደመወዝ ያልነበረውና በሽልማት በሚያገኘው ገንዘብ ብቻ የሚተዳደር በመሆኑ ኢኮኖሚያዊ ጉዳቱን ያውቀዋል።እናም አዲስ አበባ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአዝማሪ ደመወዝ መክፍል ከዛሬ 14 ዓመት በፊት ጀምሯል። በመሆኑም በአሁን ወቅት በፈንድቃ የባህል ማዕከል የሚጫወቱ አዝማሪዎች በሽልማት ከሚያገኙት ገቢ ባለፈ ወርሐዊ ደመወዝ አላቸው ማለት ነው።
በአብዛኛው ወደ ውጭ አገር ውዝዋዜን ሊያሳይ የሚሄደው ብቻውን ቢሆንም በአሁን ወቅት ግን አብዛኞቹን ይዞ መሄድ ጀምሯል። አዝማሪዎቹን ጨምሮ የተለያዩ በውዝዋዜ ቡድን ውስጥ ሆነው አብረውት የሚሠሩ ባለሙያዎችን ወደ ውጭው ዓለም ይዞ በሚሄድበት ወቅትም እንዳይጠፉና በዛው እንዳይቀሩ አስፈላጊውን ምክር በመለገስ ደግመው ደጋግመው መሄድ እንደሚችሉና ተከብረው መሥራትና መመለስ ያለባቸው መሆኑን ግንዛቤ ይፈጥርላቸዋል።
በፈንድቃ የባህል ማዕከል የሚገኙ ባልደረቦች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሠማርተው የሚሠሩ ሲሆን ከጽዳትና ከመልዕክት ሠራተኛነት ተነስተው በልምድ ብቻ ተወዛዋዥ የሆኑ የጭፈራ ባለሙያዎችን ጨምሮ በጠቅላላው ለ43 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ተከራይቶ ይሠራበት የነበረውን የፈንድቃ ባህል ማዕከልንም በግዢ በማስቀረት በማዕከሉ የተለያዩ አገርን ገጽታ የሚገነቡ የቱሪስት መስህብ የሆኑ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል።
በባህል ማዕከሉ ከሚስተናገዱት የሙዚቃና የውዝዋዜ ሥራ በተጨማሪ ለሕጻናት የሚመጥኑ መጽሐፍቶችን ጨምሮ ለሙዚቃ፣ ለፊልምና ለፎቶግራፈር ቲያትር ግብዓት መሆን የሚችሉ የተለያዩ መጽሐፍቶችን በአግባቡ ሰድሮ በማዘጋጀት ለተጠቃሚው ክፍት አድርጓል። ለሥራ ወደ ውጭ በሄደባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ መጽሐፍቶችን ማሰባሰብ እንደቻለ የሚናገረው አርቲስት መላኩ፤ ከመጽሐፍቶቹ ባሻገር በማዕከሉ ውስጥ በወር አንድ ጊዜ የአካባቢውን ሕጻናት አሰባስቦ በሙዚቃ፣ በስዕልና ቅርጻቅርጽ ሥራዎች በመሳተፍ ችሎታቸውን ማውጣት የሚችሉበትን ዕድል በማመቻቸት ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።
ሕጻናቱ በማዕከሉ ውስጥ የተለያዩ ፍላጎቶቻቸውን እየከወኑ እንዲውሉ ሲያደርግ ወላጆችም አብረው መገኘት የሚችሉ ይሆናል። ሕጻናቱ ችሎታቸውን ማውጣት እንዲችሉ ለልጁ በገዛው ድራም ሙዚቃ ይጫወታሉ። ሰዓሊ ከሆኑ ከጓደኞቹ ደግሞ ቀለምና ብሩሽ በማዘጋጀት የስዕል ችሎታ ያላቸው ሕጻናት የፈለጉትን ነገር በመሳል ችሎታቸውን እንዲያወጡ ያደርጋል። በተጨማሪም የተለያዩ ቅርጻቅርጾችን የመሥራት ዝንባሌ ላላቸው በአንድ ልጅ 50 ብር በመክፈል የሸክላ መሥሪያ ጭቃ በመግዛት ሕጻናቱ እንዲጠቀሙበትና ችሎታና ፍላጎታቸውን እንዲያሳዩ በማድረግ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት በዙሪያው የሚገኙ ሕጻናትን እያበቃ ይገኛል።
ፍጹም ኢትዮጵያዊ በሆኑ ባህላዊና ታሪካዊ ቁሳቁሶች የተሞላውና በርካታ የኢትዮጵያን ታሪክ በሚያሳዩ ስብስቦች የተንቆጠቆጠው ፈንድቃ የባህል ማዕከል የብዙዎችን ቀልብ የሚስብ ኢትዮጵያዊ ቀለም አለው። በዚህ ስፍራ ታድያ በየዕለቱ በሚኖረው የተለያየ መስተንግዶ ታዳሚ የሆኑ ጥበብ አፍቃሪ የሆኑ የሃገር ውስጥና የውጭ አገር ሰዎች ይስተናገዳሉ። በእያንዳንዱ መስተንግዷቸውም ኢትዮጵያዊ የሆኑ ባህሎችን ማወቅና መረዳት ይችላሉ። ይህም ለሃገራዊ የገጽታ ግንባታ የሚኖረው ድርሻ የጎላ እንደሆነ ይታመናል።
በቀጣይም በዘርፉ ብዙ ሥራዎችን የመሥራትና ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ ዕቅድ ያለው አርቲስት መላኩ ለዘርፉ አስፈላጊና ተገቢ የሆነ ትኩረት ቢሰጠው ከዘርፉ ብዙ ማትረፍ ይቻላል በማለት መልዕክቱን አስተላልፏል። እኛም የአርቲስቱ መልዕክት ከሚመለከተው አካል ጋር ደርሶ ኪነ ጥበብ በአገሪቱ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት፤ አድጎና ተመንድጎ ብዙ ፍሬ ማፍራት እንዲችል እንዲሁም ሃገርም በሀብቱ እንድትጠቀም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ስልን አበቃን።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22 /2014