ሰው ከሌሎች ፍጥረታት የሚለየው የአዕምሮውን ምጥቀት እየተጠቀመ ለችግሮቹ መፍትሄ የሚያበጅ መሆኑ ነው:: ይህ ደግሞ እንጨትን አሹሎ ለአደን መሳሪያ ከማዋል ጀምሮ ዛሬ እስከደረሰባቸው ቴክኖሎጂዎች ያሉትን ያካትታል::
ያም ሆኖ ሰው በተሰጠው አዕምሮ ልክ እንዳልተጠቀመ ቢታሰብም በጥቂት የፈጠራ ሥራዎቹ ችግር ፈቺ ግኝቶችን ማበርከቱ አልቀረም:: እነዚህ የሰው ልጅ የምርምር ውጤቶች አንዳንዶቹ የዓለምን ተፈጥሯዊ ገጽታ የለወጡና ታላቁ ፍጡር ዘልማዳዊ አሠራርና አስተሳሰቡን እንዲያዘምን የረዱ ናቸው::
በዛሬው የወጣቶች አምድ ዝግጅታችን «306 የፈጠራ ሥራዎችን ለማስተዋወቅ ተዘጋጅቻለሁ» ያለ ኢትዮጵያዊ አትሌትና አሰልጣኝን ይዘንላችሁ ቀርበናል:: ወጣቱ ከሩጫው ጎን ለጎን ጊዜውን በማንበብና በመመራመር የሚያሳልፍ በመሆኑ ሁል ጊዜ አዳዲስ አስተሳሰቦችንና አሠራሮችን ያፈልቃል:: እስከ አሁን ሁለት ሥራዎቹን ለሙከራ አቅርቦ በአንዱ እውቅና አግኝቶ በሁለተኛው እውቅና ለማግኘት እየተንደረደረ ይገኛል::
‹‹ለሙከራ የማቀርባቸውን ሥራዎቼን እያዩ የራሳቸው በማስመሰል የሚያቀርቡ ሰዎች ስለገጠሙኝ የፈጠራ ሥራዎቼን በአንድ ጊዜ ለማስተዋወቅ ተቸግሬያለሁ›› ይላል::
ሙልዬ እያዩ ይባላል፤ አትሌትም አሰልጣኝም ነው:: ትውልዱና እድገቱ አማራ ክልል፣ ጎንደር ዞን፤ ከጎንደር ከተማ በስተ ምዕራብ አስር ኪሎ ሜትር ወጣ ብላ በምትገኘው አምባ ጓሊት ቀበሌ ነው:: በልጅነቱ ትምህርቱን ሲማር ከቤቱ እስከ ትምህርት ቤቱ አርባ ደቂቃ ይጓዝ ነበር:: አብዛኛውን ጊዜ ወደ ትምህርት ቤት የሚያደርገው ምልልስ በሩጫ የታጀበ ነው:: ጠዋት የትምህርት ሰዓት እንዳይረፍድ ሮጦ ይደርሳል፤ ስድስት ሰዓት ከትምህርት ቤት ሲለቀቅ ደግሞ ከብቶችን ውሃ ለማጠጣት እየሮጠ ወደ መንደሩ ይደርሳል:: በዚህ ሁኔታ ነበር አትሌት ለመሆን ያስቻለውን እርሾ ያስቀመጠው::
አትሌት ሙልዬ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል እዚያው በተወለደበት ገጠራማ አካባቢ ከተማረ በኋላ የዘጠነኛ ክፍል ትምህርቱን ለመማር ወደ ጎንደር ከተማ ይሄዳል:: አንድ ዓመት እየተመላለሰ ከተማረ በኋላ ልክ እንደጓደኞቹ እርሱም ጎንደር ከተማ ውስጥ ቤት ተከራይቶ መማር ይጀምራል:: ከትምህርቱ ጎን ለጎን የሩጫ ልምምድ ያደርግ ነበር:: አልፎ አልፎም ውድድር ያደርጋል:: በተለያዩ ጊዜያት ለሚማርበት ትምህርት ቤት፣ ለጎንደር ከተማና ለጎንደር ዞን በአጭር ርቀት ተወዳድሯል::
ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላም ለአንድ ዓመት ያህል እዚያው ጎንደር፣ ደባርቅ አካባቢ በባለሀብቶች በሚደገፍ አንድ ክለብ ውስጥ ገብቶ ልምምድ ያደርጋል:: በዚህን ወቅትም አጭር ሩጫውን ትቶ የረዥም ሩጫ ልምምዶችን ይሠራ ጀመር:: አልፎ አልፎም በባህርዳርና በአንዳንድ አካባቢዎች እየሄደ ይወዳደራል::
በክለብ ከመታቀፍ ይልቅ በግል መሮጥ የተለየ ነፃነትን ይሰጣል በሚል ክለቡን ትቶ በግል መንቀሳቀስ ይጀምራል:: በአንድ ወቅት ከአገር ውጭ ወጥቶ መወዳደር ይፈልግና ሁኔታዎችን ማጥናት ይጀምራል:: በራሱ ጥረት ውድድሮች የሚካሄዱባቸውን ቦታዎች እያጠና ኦርጋናይዘሮችን በማነጋገር የአውሮፕላንና የመኝታ እየተቻለው መወዳደር ይጀምራል:: በኤዢያ፣ በላቲን አሜሪካ፣ በአውሮፓ የተለያዩ ከተሞች ተወዳድሯል:: አንዳንዴ ደረጃ ውስጥ እየገባ አንዳንዴም ሳይገባ፤ አንዳንዴ ጥቅም እያገኘ፤ አንዳንዴም ወጪውን ብቻ እየሸፈነ ይመለስ ነበር::
ሙልዬ የሩጫ ልምምድና ውድድሮችን ካደረገ በኋላ ጊዜውን ማሳለፍ የሚያዘወትረው በምርምርና በፈጠራ ሥራዎች ላይ ነው:: በተለይም የውጭውን ዓለም የመመልከት ዕድል ማግኘቱ ሀገሩን የማዘመን ተነሳሽነት እንዲፈጠርበት አድርጎታል:: ከተለምዷዊ አሠራሮች መላቀቅ፣ ትኩረት ለሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ትኩረት መስጠት፣ አገርንና ሕዝብን ወደ ፊት ሊያራምዱ የሚችሉ የሀሳብ ልዕልናዎችን መሬት ላይ ማውረድ የሚተኩርባቸው ጉዳዮች ናቸው::
ሙልዬ ከፈጠራ ሀሳቡ አንዱ ‹‹ስፖርት ለአየር ንብረት ለውጥ›› /Sport for climate change/ የሚል ነው:: ሁኔታውን እንዲህ ያስረዳል:: ‹‹የሰው ልጅ የተስተካከለ
ሥርዓተ ትንፈሳ ለማካሄድ
ንጹህ አየር ሊያገኝ ግድ
ይለዋል:: አሁን ባለው ሁኔታ ዓለማችን በተለያዩ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ምክንያቶች ለአየር ብክለት ተጋላጭ እየሆነች መጥታለች:: የአየር ንብረት ለውጥ ደግሞ የብዙ ዓመታት ሂደት ውጤት ነው:: የምንተነፍሰው አየር በመበከሉ ምክንያት የመተንፈሻ አካላችን ይጎዳል:: ሰው አረፈ የሚባለው እስትንፋሱ ሲቆም ነው:: ስለዚህ እስትንፋስ ለሰው ልጅ ህልውና አስፈላጊውና ትልቁ ነገር ነው:: ሰው በሕይወት ሲኖር ኑሮውን ለማሸነፍ ሲል የተለያዩ ሥራዎችን ያከናውናል:: ይህን የሚያደርገው ሥርዓተ ትንፈሳ ስላለው ነው::
በዓለም ላይ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች በምሁራን ጥናት ተደርጎባቸው መመሪያና ደንብ ወጥቶላቸው ተቋማዊ ሆነዋል:: ለምሳሌ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ የቦሊቦል ፌዴሬሽን ወዘተ መጥቀስ እንችላለን:: መመሪያና ደንቦቹ ፌዴሬሽኖቹ የተቋቋሙበትን የእንቅስቃሴ ዓላማ በአግባቡ እንዲያከናውኑ የሚያግዙ ናቸው::
በሌላ በኩል ደግሞ ከሥርዓተ ትንፈሳ ጋር በተያያዘ የአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚሠሩ ተቋማት አሉ:: በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር በዚህ ፕሮግራም የታቀፉ 192 አገራት አሉ:: ይህ መርሃ-ግብር ዋና ትኩረቱን የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ያደረገ ነው:: አካላዊ እንቅስቃሴ ላይም አይሠራም::
የዓለም ኦሎምፒክ ኮሚቴን ስንመለከት ደግሞ የተለያዩ የስፖርት ፌዴሬሽኖችን በአንድ ላይ አካቶ ይሠራል:: የሚሠራው ግን ስለስፖርቱ እንቅስቃሴ እንጂ ስለ ሥርዓተ ትንፈሳ አይደለም::
ስለዚህ የእኔ ምልከታ ሁለቱም ያልሠሩትን ሥራ መሥራት ስለነበር /Sport for Climate change/ የሚል መርህን የሚከተል ነው:: የራሱ ጥናት፣ ሕግ፣ አስተዳደራዊ መዋቅር፣ ተዋረዳዊ ሰንሰለት እና እድገት አለው::
ይህን ሀሳብ ያፈለቅሁት እኔ ነኝ:: ይህ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ሲኤምሲ አካባቢ 15 ኪሎ ሜትር በሚሸፍን የጎዳና ላይ ሩጫ ይፋ ሲደረግ በወቅቱ የዋልታ ቴሌቪዢን የቀጥታ ስርጭት ሽፋን ሰጥቶታል:: 115 አምባሳደሮች ተጋብዘው በሥፍራው ተገኝተዋል፤ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና ክለቦችም ጭምር ተጋብዘው ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ ተደርጓል::
ይሄ ሀሳብ ከእኔ አልፎ የኢትዮጵያ ሆኖ ሌላው ዓለም ተግባራዊ የሚያደርገው ነው:: የዓለም አገራት ስፖርትን በመጠቀም ለአየር ንብረት ለውጥ ትኩረት እንዲሰጡ የሚያደርግ ነው::
ፕሮግራሙን በዓለምአቀፍ ደረጃ ለማሳካት ጠንክሬ እየሠራሁ ነው:: እኛ ኢትዮጵያውያን ከምንታወቅበት ሩጫ ባሻገር የሀሳብ ልዕልና ያለን ሕዝቦች መሆናችንን የዓለም ሕዝብ እንዲረዳ እፈልጋለሁ:: የአየር ብክለት የጉዳት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ በመሆኑና ኢትዮጵያም በዚህ ፕሮግራም አማካኝነት በአየር ንብረት ለውጥ በሚመጡ ችግሮች ላይ ትኩረት እንድታደርግ በስፖርት ንቅናቄ ለመፍጠር የሚያስችል ነው:: «እንዴት አድርገን ጉዳዩን ተቋማዊ በማድረግ መቆጣጠር እንችላለን?» ለሚለው መልስ የሰጠሁበት ሥራ ነው::
ለምሳሌ አፍሪካ ምድር ላይ አረንጓዴ ልማትን ማስፋፋት የአየር ንብረት ለውጥን ከመቆጣጠር አንጻር ጠቀሜታ አለው:: እንደ አሜሪካና ቻይናን በመሳሰሉ አገራት ችግኝ መትከልን እንደመፍትሄ ብናነሳ አያስኬድም:: እነርሱ ዛፍ ሲተክሉ የኖሩና ባላቸው የደን ሀብት ላይ በየጊዜው እድገት የሚያሳዩ ናቸው›› ይላል::
ሙልዬ «የግል ፈጠራዬ ነው» በሚለው አዲስ ሀሳብ ፓተንት ራይት የማግኘት ጥረት አድርጓል:: ነገር ግን ፓተንት ራይት ለማግኘት አንዱ መስፈርት የሥራው አዲስ መሆን ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈጠረ የተባለው ሥራ አለመሠራቱም መረጋገጥ ሲቻል ነው:: ኢትዮጵያ ውስጥ ይህን የሚያረጋግጥ ጠለቅ ያለ አሠራር ባለመኖሩ ማረጋገጫውን አለማግኘቱን ተናግሯል::
ሙልዬ ያፈለቀው ሃሳብ ለውጡ የሚታየው በሂደት ነው:: ፓተንት ራይት ለማግኘት ደግሞ ተጨባጭ ለውጥ መታየት አለበት፤ ስለዚህ ውጤቱ ሂደትን ተከትሎ የሚመጣ መሆኑም ዓለም አቀፍ ፓተንት እንዳያገኝ ሌላው ምክንያት ሆኗል::
በዚህ የተነሳ የኮፒ ራይት /ቅጂና ተዛማጅ መብቶች/ ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ከአእምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ለመውሰድ ተገዷል:: የወሰደው ማረጋገጫ ‹‹የዓለም ሕዝብን በአየር ንብረት ብክለት ለውጥ ማነሳሳትና ግንዛቤ መፍጠር›› የሚል ነው:: ይህንን የምስክር ወረቀት ለማግኘት ብዙ ውጣ ውረድ ማሳለፉን ይናገራል::
ሀሳቡን ተቋማዊ ለማድረግ ግን ፈተና ሆኖበታል:: የአየር ንብረት ብክለትን ለመቆጣጠር ያስችላሉ ተብለው በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት እንዴት መተግበር እንዳለበት የሚገልጹ ዝርዝር ጉዳዮችን የያዙ ሰነዶችን ሰጥቷል፤ ነገር ግን አንዳቸውም በሥራ ላይ አላዋሉትም:: ነገሮችን በቅንነት አለመመልከትና ነገ የአየር ንብረት ብክለት በአገር ብሎም በዓለም ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት አሻግሮ ካለመመልከት የመጣ ነው ይላል::
ይህ ፕሮግራም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና አግኝቶ ተግባራዊ ቢሆን በዓመት 4መቶ ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማስገኘት ይችላል የሚለው ሙልዬ ለምሳሌ /ስፖርት ፎር ክላይሜት ፕሮግራም/ ላይ ሁለት መቶ አገራት እያንዳንዳቸው 50 ሰዎችን ይዘው ቢመጡ በ20 ሁነቶች ላይ እንዲሳተፉ ቢደረግ፣ አንድ ሰው 500 ዶላር ቢከፍል ሁነቱ ለሰላሳ ቀን የሚቆይ ቢሆን፤ በእነዚህ ቀናት ውስጥ ለምግብ፣ ለአልጋ፣ ለመዝናኛ፣ ለትራንስፖርት፣ ለሚዲያ ስርጭት፣ ለየቱሪዝም ዘርፍ ወዘተ በርካታ ገቢ ማስገኘት ይቻላል ብሏል:: ከዚህ ውጪ ከስፖንሰር ብቻ ዳጎስ ያለ ጥቅም ማግኘትም ይቻላል::
ሙልዬ በተመሳሳይ ሁኔታ አፍልቄዋለሁ የሚለው ሀሳብ ‹‹ዓለማ’ቀፍ የዓድዋ ሽልማት ፕሮግራም›› /International Adwa Award/ ነው:: ለፍቅር፣ ለሰላም፣ ለአንድነት ሲሉ ሀብታቸውን፣ እውቀታቸውንና ስልጣናቸውን በአግባቡ የተጠቀሙና ለሕዝባቸው ጥቅም ያዋሉ ሰዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሸለሙበት መርሃ-ግብር ነው::
በዓመት አንድ ወንድና አንድ ሴት ተሸላሚ ሲሆኑ ተምሳሌትነታቸው በእቴጌ ጣይቱና በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ነው:: ይህ አዋርድ የራሱ ታሪክ ያለው ነው የሚለው ሙልዬ ጥቁሮች ለነጮች አንገዛም ብለው መስዋዕትነት የከፈሉበትና ለመላው ጥቁር ሕዝብ ነፃ መውጣት ፋና ወጊ የሆነ ነው:: ዓለም አሁን ያላትን መልክ /ይዘት/ ይዛ እንድትቀጥል ያደረገው የዓድዋ ድል ነው:: ለዘመናት በባርነት ስር የነበሩ ጥቁሮች ነፃነታቸውን እንዲያረጋግጡ ያደረጋቸው እና ራሳቸው ነጮችም አስተሳሰባቸውን እንዲያስተካክሉ፤ «ለካስ ጥቁርም እንደኛ ድል ማድረግ ይችላል» ብለው እንዲያስቡ ያደረጋቸው የዓድዋ ድል ነው:: ዓድዋ የእኩልነት፣ የዴሞክራሲ ምልክት ነው፤ ነጮች ከበላይነት አስተሳሰብ፤ ጥቁሮች ከባርነት ነፃ የወጡበት የጋራ ሀብታቸው ነው ይላል::
በዚህ እሳቤ መነሻነት የዓድዋ ድል 125ኛ ዓመት ሲከበር የመጀመሪያው የዓድዋ ሽልማት መርሃ-ግብር ተከናውኗል:: ይህ የሽልማት ፕሮግራም ወደ ፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲከናወን እየሠራ መሆኑን ሙልዬ ተናግሯል::
በመረጃ አያያዝ፣ በትምህርት፣ በኢንዱስትሪ፣ በሶላር ኢነርጂ ወዘተ በርካታ አዳዲስ ሀሳቦችን አፍልቆ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን በመግለጽ የሰውን የፈጠራ ሥራ ቀምተው የራሳቸው በማድረግ የሚያስተዋውቁ ሰዎች በመኖራቸው ሥራዎቹን ለሕዝብ ይፋ ከማድረጉ በፊት መናገሩ ጥሩ አለመሆኑን ጠቅሶ በሂደት አንድ በአንድ ለሕዝብ እንደሚያስተዋውቃቸው ገልጿል::
ሙልዬ በትልልቅ ዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ላይ በግሉ በሚሳተፍባቸው ውድድሮች ሁሉ ዓለም አቀፍ ይዘት ያላቸው የፈጠራ ሥራዎቹን የማስተዋወቅ እቅድ እንዳለው ይናገራል:: ለዚህም በሩጫው ውድድር አሸናፊ ሆኖ መውጣት ዓላማውን ለማሳካት እንደሚረዳው አውቆ ጠንክሮ በመለማማድ ላይ ይገኛል::
ዓለም በትንሽ ሃሳቦች መነሻነት ትቀይራለች የሚለው ወጣቱ መንግሥት አዳዲስ ሃሳብ ይዘው የሚመጡ ወጣቶችን የማበረታታት ልምድ ቢያዳብር አገራቸውን ከመለወጥ አልፈው ዓለምን መለወጥ የሚችሉ ዜጎችን ማፍራት ይቻለዋል ይላል:: ለወጣቱ መልካሙን ተመኘን::
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22 ቀን 2014 ዓ.ም