በ2010 ዓ.ም ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ የተለያዩ ባለሙያዎችን እያወያዩ ነበር። ከእነዚህ ባለሙያዎች መካከልም የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ይገኙበታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ማወያየታቸው የዚያ ሰሞን አጀንዳ ሆኖ ነበር። ያንኑ ውይይት ምክንያት በማድረግ ኤፍ ኤም አዲስ 97.1 የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ስቲዲዮ ጋብዞ አንድ ውይይት ማካሄዱን አስታውሳለሁ። በውይይቱም አድማጮች የራሳቸውን አስተያየት ሲሰጡ ነበር። ከውይይቱ አንድ የኪነ ጥበብ ባለሙያ የተናገሩት ዛሬም ድረስ ውስጤ አለ። የገረመኝ ምክንያት ደግሞ የኪነ ጥበብ ሰው ሆነው ራሳቸው የኪነ ጥበብ ባለሙያውን መተቸታቸው ነበር።
ባለሙያው እንዳሉት፤ የኢህአዴግ አፋኝነት ለብዙ የጥበብ ሰዎች የስንፍና መደበቂያ ሆኖ ነበር። የሚገርም ድርሰት ጽፌ መንግሥት አገደብኝ ይባል ነበር። የኢትዮጵያን የፊልም ኢንዱስትሪ የሚያስመነድግ ፊልም ሰርተን መንግሥት እንዳይወጣ ከለከለን ይባል ነበር። እነዚያ ሰዎች ‹‹እስኪ ድርሰቱን አምጡት!›› ቢባሉ ላይኖራቸውም ይችላል ነበር ያሉት። ‹‹አሁን ነፃነቱ ተሰጥቷልና እስኪ ታግዶብኝ ነው ሲል የነበረ ሁሉ ያምጣው!›› ማለታቸውን አስታውሳለሁ። እኚህ ሰው ያንን አስተያየት የሰጡት በቅርበት የሚያውቁት ቢኖር ነው። ስንፍናን በመንግሥት ማሳበብና ይህንንም መደበቂያ ማድረግን ከተወቃሽነት ለመዳን ይጠቀሙበታል።
እዚህ ጋ ደግሞ ሌላ ወቀሳ አለ። ይህኛው እኔ ራሴ የታደምኩበት መድረክ ነው። የያኔው የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል የተገኙበት አንድ መድረክ ስድስት ኪሎ በሚገኘው ባህል ማዕከል (በተለምዶ ስብሰባ አዳራሽ) ‹‹ኪነ ጥበብ ለሰላም›› በሚል ከኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ጋር የተደረገ አንድ ውይይት ነበር።
በውይይቱ ላይ ከተለያዩ የጥበብ ባለሙያዎች የተነሱ ቅሬታዎች ሲጨመቁ፤ መንግሥት የኪነ ጥበብ ባለሙያውን የሚፈልገው ሲጨንቀው ነው። ኪነ ጥበብ በሕዝብ ውስጥ ያለውን ሚና፣ ተቀባይነት፣ ፣ ሃይል ፣ወዘተ ስለሚያውቅ፤ ከሕዝብ ቁጣ ባጋጠመው ወቅት ወደ ኪነ ጥበብ ባለሙያው ያተኩራል። በአዘቦት አብረን እንሥራ ያላለውን በችግር ወቅት የአብረን እንሥራ የጥሪ ደብዳቤ ጋጋታ ያበዛል። የኪነ ጥበብ ዘርፉን ለማሳደግ ራሱን የቻለ ተቋማዊ አደረጃጀት ፈጥሮ ከባለሙያው ጋር አልሰራም የሚሉ ቅሬታዎች ተነስተዋል።
በነገራችን ላይ እስከአሁን በኪነ ጥበብ ዘርፉ ላይ እዚህ ግባ የሚባል የተመሰገነ ለውጥ ባይመጣም፣ በቅርቡ አዲሱ መንግስት ያወቀረውን ካቢኔ ተከትሎ በአደረጃጀት ደረጃ ራሱን የቻለ ዘርፍ ተቋቁሟል። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ወደ ባህልና ስፖርት ሚኒስትርነት ሲቀየር ኪነ ጥበብ ራሱን የቻለና በሚኒስትር ዴኤታ የሚመራ ዘርፍ ሆኗል። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደረጃ ደግሞ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የነበረው፤ ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ተብሏል። እነዚህ ነገሮች ኪነ ጥበብ ቢያንስ በስም ደረጃ እንኳን ትኩረት እየተሰጠው መሆኑን ይጠቁማሉ።
ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ በዚህ ዓመትም መድረኮች ተካሂደዋል። በቅርቡ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደውን የምስራቅ አፍሪካና የታላላቅ ሀይቆች ሀገሮች የባህልና ኪነጥበብ ሳምንት አስመልክቶ ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጋር ውይይት አድርጎ ነበር።
በውይይቱ ላይ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኪነጥበብ፣ ስነጥበብና ፈጠራ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ነፊሳ አልማሀዲ፣ ከኪነጥበብ ዘርፉ መጠቀም ያለብንን ያህል አልተጠቀምንም። የኪነ ጥበብ ባለሙያውም
ህዝቡም መጠቀም ባለባቸው ልክ አልተጠቀሙም። ሌሎች አገሮች ግን በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ፋይዳው በሚገባ እየተጠቀሙበት ሲሉ አስታውቀዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በኪነ ጥበብ ባለሙያው ይነሳ የነበረውን ቅሬታም አንስተዋል። ተጠቃሚ አልሆነም፤ ችግር ሲደርስበት እርዳታ ሲጠይቅ ነው የሚታየው ብለዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለጻ፤ ከኪነጥበቡ አንደኛ የጥበብ ሰዎች መጠቀም አለባቸው፤ ጥበቡን ከምናባቸው አውጥተው ነው የሚፈጥሩት፤ ማግኘት የሚገባቸውን ማግኘት አለባቸው፤ ማግኘት ያለባቸውን ማግኘት እንዳይችሉ ያረገው ምንድን ነው የሚለው መታወቅ አለበት።
‹‹ሰዎች ሙዚቃ እያዝናና ያስተምራል ብቻ ብለው ነው የሚያስቡት፤ እያዝናና ያስተምራል ብቻ ሳይሆን ሰዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ወደሚለው ወስደን በዚህ ላይ በደንብ መስራት አለብን። ወደ እዚህ መስሪያ ቤት ከመጣሁ በኋላ እንደምመለከተው የሚታየው ብዙም የሚያስደስት አይደለም፤ ያመኛል›› ሲሉ ያለውን ችግር ገልጸውታል። መሰራት ያለበት እንዳለም ተረድተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ እንደተናገሩት፤ መንግስትም ይህንን ተመልክቶ ነው የኪነጥበብና ስነጥበብ ክፍሉ ራሱን ችሎ በሚኒስትር ዴኤታ እንዲደራጅ ያደረገው። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሰዎች የሚያነሷቸውን እና ሌሎች የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ነው በሚኒስትር ዴኤታ ደረጃ በአዋጅ የተቀመጠው።
ከዚህ አንጻር ምቹ ሁኔታ አለ ብለን መጠቀም አለብን፤ አደረጃጀቱ በባህል ስር ነበር፤ አሁን ራሱን ችሏል። አደረጃጃቱ አለ፤ በሙያው የሰለጠኑ ሰዎች አሉ፤ ጥበቡን የሚፈልጉ ማህበረሰብ ክፍሎች አሉ። ስራው ከኛ ነው የሚጠበቀው፤ ሁሉም ነገሮች አሉ ሲሉም አስገንዝበዋል።
የኪነ ጥበብ ባለሙያውም ሆነ መንግሥት እርስበርስ መወቃቀስ ሳይሆን አብረው መስራት ነው ያለባቸው።
ራሱን የቻለ ዘፍር መደራጀቱ በመንግሥት በኩል ትኩረት እንዲሰጠው ያግዛል። የኪነ ጥበብ ባለሙያውም በራሱ በኩል መወጣት ያለበትን በመወጣት አብረው ከሰሩ ተገቢውን ጥቅም ያገኛሉ።
የኪነ ጥበብ ባለሙያው ተገቢውን ጥቅም ላለማግኘቱ በተደጋጋሚ የሚነሳው አንዱ ምክንያት ደግሞ የባለቤትነት መብት ጉዳይ ነው። በተለይም በሙዚቃው ዘርፍ ይሄ ችግር ሲደጋገም ይሰማል።
የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ዳዊት ይፍሩን በዚሁ ጉዳይ ላይ አነናግረን ነበር። ፕሬዚዳንቱ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ አርቲስቱ የፈጠራ ሥራው ተጠቃሚ ለመሆን እየጣረ ነው። ለዚህም የቅጅና ተዛማጅ መብት ማህበር ተቋቁሟል። ማህበሩ ከአዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ጋር በጋራ እየሰራ ነው። ከሚዲያ ተቋማትም ጋር ይሰራል።
የፈጠራ ባለቤቱን ተጠቃሚ ለማድረግ ከአዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤትና ከሚዲያ ተቋማት ጋር በጋራ የሚደረገው ሥራ ከመጪው ሐምሌ እስከ መስከረም ባለው ጊዜ እንደሚጀመርና በትኩረት እንደሚሰራበትም ነው ፕሬዚዳንቱ የተናገሩት።
እንደ አርቲስት ዳዊት ገለጻ፤ ባለሙያዎቹ በፈጠራ ሥራዎቻቸው እስከ አሁን ተጠቃሚ ባይሆኑም ከዚህ በኋላ በትኩረት ከተሰራበት ግን ተጠቃሚ ይሆናሉ። ሥርዓቱ ከተዘረጋ ብዙ ሰው ተጠቃሚ ይሆናል። ዜማና ግጥም የደረሰው ብቻ ሳይሆን ያንን መድረክ ላይ የተጫወቱትም ሰዎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት መንገድ እንዲኖር እየተሰራበት ነው። ምክክሩ ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድ ቢችልም ከተጠናቀቀ ግን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።
‹‹በመንግሥት በኩል ሕግ ወጥቷል›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ መንግሥት ያወጣውን ሕግ እና ለኪነ ጥበብ ዘርፉ የሚቀርብ አደረጃጀት መፍጠሩን እንደ ጥሩ ዕድል በመጠቀም በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። የመብት ባለቤቶች መብታቸውን ለማሳከበር ከሁሉም ባለድርሻ አካላትና እና ከባለሙያው ጋር መሥራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
‹‹በግለሰብ ደረጃ መሯሯጥ መፍትሔ አያመጣም›› ያሉት ባለሙያው፤ ባለሙያውንም፣ ሕዝብንም ተጠቃሚ የሚያደርገው በጋራና በትብብር መሥራት ሲቻል እንደሆነም ተናግረዋል። የፈጠራ ባለሙያውም ከቸልተኝነት መውጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በሌላ በኩል ባለሙያዎቹ ራሳቸው የአንዱን ፈጠራ አንዱ መውሰድ እንደሌለባቸውም የማህበሩ ፕሬዚዳንት አሳስበዋል። በተለይም ጀማሪ ባለሙያዎች የራሳቸውን የፈጠራ ሥራ ማቅረብ አለባቸው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ያለባለቤቱ ፈቃድ የቀደሞ ሥራዎችን ያቀርባሉ። መሥራት ካስፈለገ ባለቤቱን በማስፈቀድና ለባለቤቱም ተገቢውን ጥቅም በመስጠት ነው ሲሉ ያብራራሉ። እነዚያ የቀደሞ ሥራዎች ተወዳጅ የሆኑት የራሳቸው ወጥ ፈጠራ ስለሆኑ ነው፤ ስለዚህ የጥበብ ባለሙያውም እንዲህ አይነት ችግሮችን ለመቅረፍ በጋራ መሥራት አለበት ሲሉ ያስገነዝባሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፊልም ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት አቶ ዳንኤል ወርቁ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ኪነ ጥበብ አገርን ለማስተዋወቅ ከየትኛውም ነገር በላይ አቅም አለው። መንግሥትም ሆነ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ይህን መረዳት አለባቸው። መንግሥት ኪነ ጥበብን የተመለከተ መዋቅር ሲዘረጋ ባለሙያው ደግሞ ዕድሉን መጠቀም አለበት።
እንደ አቶ ዳንኤል ገለጻ፤ የጥበብ ባለሙያዎች ከመንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማግኘት ጥረት የሚያደርጉት በተናጠል ነው፤ ያ ደግሞ ውጤታማ አያደርግላቸውም፤ መንግሥትም ነገሩን እያድበሰበሰ ሊያልፈው ይችላል፤ ባለሙያዎች በሕብረት ሆነው ከጠየቁ ግን አስፈላጊውን እገዛ የማግኘት ዕድላቸው ይሰፋል።
መንግሥት ለጥበብ ሥራዎች ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት የገለጹት መምህር ዳንኤል፤ ሀገሮች የፊልም ኢንዱስትሪያቸው ያደገው ፈንድ ስለሚመደብላቸው መሆኑን ጠቅሰዋል። ከአፍሪካ አገራት እነ ናይጀሪያ ፈንድ ስለሚደረግላቸው ነው ፊልማቸው አድጎ አገራቸውን ያስተዋወቀው፤ በኢትዮጵያ ግን ይህ አልተለመደም። ባለሙያውም ሆነ መንግሥት በመተጋገዝ መሥራት አለባቸው። መንግሥት በሚያቋቁመው ዘርፍ ውስጥ ለሙያው ቅርበት ያላቸው ሰዎች መግባት አለባቸው ሲሉም አሳስበዋል።
የጥበብ ባለሙያዎች አቅም ፈጥረው ተወዳጅ ፊልም ቢያቀርቡ የመንግሥት ተቋማትም ተባባሪ እንደሚሆኑ መምህር ዳንኤል ይገልጻሉ። ለምሳሌ የፊልም ኢንዱስትሪው በተደጋጋሚ ሲወቀስ ይሰማል፤ ይህን የሚሰማ የመንግሥት ተቋምም ለፊልም ሥራ ተባባሪ ለመሆንና ለሚቀርብለት ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ወኔ አይኖረውም። ስለዚህ የፊልም ባለሙያው በሕብረት ሆኖ በመሥራት የፊልሙን አቅም ማሳየት እንዳለበት ያሳስባሉ። በግለሰብ ደረጃ ዓለም አቀፍ ሽልማት የሚያስገኝ ሥራ ሊሰራ ይችላል፤ ዳሩ ግን በጋራ የሚታይ ሥራ ካልተሰራ ውጤታማ አይሆንም ይላሉ።
እንደ አቶ ዳንኤል ገለጻ፤ ሥራዎች በባለሙያው መተጋገዝ በጋራ ካልተሰሩ ግለሰብ ላይ ሲንጠለጠሉ ትኩረታቸው ገንዘብ ለማስገኘት ብቻ ይሆናል። ስለዚህ ባለሙያው ከመንግሥት ለሚያገኘው ድጋፍም ሆነ የሚሰራውን የጥበብ ሥራ ደረጃ ለማስጠበቅ በጋራ ሊሰራ ይገባል።
ልክ እንደ ሕንጻና ሌሎች የሙያ ሥራዎች ሁሉ የጥበብ ሥራም ‹‹ስታንዳርድ›› ሊኖረው ይገባል ይላሉ መምህሩ። ለዚህ ደግሞ መፍትሔው የባለሙያው መተጋገዝና አብሮ መሥራት ነው። አለበለዚያ የተበላሸ ሥራ ለሕዝብ ሲቀርብ ተወቃሽ የሚሆነው አጠቃላይ ዘርፉ ነው ሲሉ ያስገነዝባሉ።
የጥበብ ባለሙያውም ተገቢውን ጥቅም የሚያገኘው በባለሙያ እይታ ደረጃውን የጠበቀ ሥራ ሲቀርብ ነው። አንድ ሕንጻ ከንድፉ ውጭ ዝንፍ ቢል እንደገና ይፈርሳል እንጂ ከንድፍ ውጭ አይሰራም፤ የፊልም ሥራ ግን ለ100 ብር ብሎ እንኳን ቢሰራው ዝም ሊባል ይችላል፤ ስለዚህ ዘርፉን ያስወቅሰዋል፤ እንዲህ አይነቱን አሰራር ለማስቀረት ባለሙያው በጋራ መሥራት አለበት ብለዋል።
በመንግሥት በኩልም፤ ልክ ለዘጋቢ ፊልሞችና ለሌሎች ሥራዎች ፈንድ እንደሚደረገው ሁሉ ለኪነ ጥበብ ዘርፉም ማድረግ እንዳለበት ያሳስባሉ። ለአገር የሚጠቅም ከሆነ የመንግሥት ድርጅቶች አዋጥተውም ቢሆን ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው ነው ያስገነዘቡት፤ የአገር ጉዳይ የማይመለከተው የመንግሥት ተቋም የለም። ስለዚህ ዘርፉን ማሳደግ በዋናነት የመንግሥትና የባለሙያው ጥረት መሆኑን ተናግረዋል።
ለኢንዱስትሪው ማደግ ባለሙያውም ጥረት ማድረግ፤ መንግሥትም ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ አለባቸው እንላለን! ባለሙያው ምንም ሳይንቀሳቀስ መንግሥትን ብቻ ቢወቅስ ለውጥ አይመጣም፤ መንግሥትም የሚመጣለትን ጥያቄ ሁሉ ትኩረት ሳይሰጥ ቆይቶ ሲያስፈልጉት ብቻ ‹‹ኑ አግዙኝ›› ቢል ከተወቃሽነት አይድንም፤ ስለዚህ ተጋግዞ በመሥራት አገርንም ባለሙያውንም የሚጠቅም ሥራ ይሰራ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20 /2014