ወጣት ሜሮን ተስፋዬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ህንፃ ኮሌጅ በአርክቴክት የትምህርት መስክ የመጀመሪያ ዲግሪያዋን ከያዘች በኋላ እንደማንኛውም ተመራቂ ተማሪ ስራ ፍለጋ መዞር አላሻትም ። የተማረችበት የትምህርት መስክ (አርክቴክቸር) ከዲዛይን ጋር በጣም የተገናኘ ነበር። በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ የሚማሩበትን ደብተር በራሳቸው እንዲሰሩ መምህራኖቻቸው ያበረታቷቸው ስለነበር መፍጠር የሆነ ነገር መስራት የሚል እሳቤ ልቧን ሞልቶት ምን መስራት እንደምትችል እያሰላሰለች ሳለ ነበር በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ወጣቶች አንድ ላይ በመሆን ያላቸውን ሃሳብ የሚያሳድጉበት፤ ሃሳቡንም ወደ መሬት አውርደው እንዲጠቀሙ የሚያስችል‹‹ ክሬኤቲቭ ሀብ ››የተባለ ማእከል መኖሩን የሰማችው።
በተለያየ ዘርፍ የተወሰነ ቁጥር ያላቸውን ወጣቶች መወዳደር እንደሚችሉ ስትሰማ በቆዳ ዘርፍ ተወዳድራ ወደዚህ ተቋም ገባች፤ በዚህም የቆዳ ውጤቶችን ማምረት፤ ቆዳን ከእንጨት ጋር፤ ቆዳን ከጨርቅ ጋር በማዋሃድ ለአይን የሚማርኩ ቦርሳዎችን በማምረት በዛው በክሬኤቲቭ ሀብ ውስጥ ባለ የማሳያ ቦታ በማሳየት እና በመሸጥ ኑሮዋን እየገፋች ትገኛለች። ከቦርሳዎቹ ባሻገር በቆዳ የተለበጡ የተለያዩ ማስታወሻ ደብተሮችን ፣የሰአት ማሰሪያዎችን ትሰራለች። የፈጠራ ስራዎች ሃሳብ በውስጧ ሲመጡ ዲዛይን አድርጋ ከመስራቷም በላይ ሰዎች ትእዛዝ ሲሰጧት በትእዛዙ መሰረት ሰርታ እንደምታስረክብ ትናገራለች።
አሁን በመኖሪያ ቤቷና በክሬኤቲቭ ሀብ ውስጥ ስራዎቿን እየሰራች መሆኑን የምትናገረው ይች ወጣት ዛሬ ላይ ሀሳብ ብላ የያዘቻቸውን ነገሮች ወደ ፈጠራ ስራ አሳድጋለች። በቀጣይ ደግሞ ሀገሯን በቆዳው ዘርፍ እሴት ጨመራ በመስራት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ማቀዷን ትናገራለች። በጣም ብዙ ወጣቶች ልባቸው ውስጥ ብዙ የፈጠራ ሃሳቦች አላቸው። ይሄንን አውጥተው ግባቸውን እስኪመቱ ድረስ የሚያግዝ ድጋፍ ቢደረግላቸው መልካም ነው ስትል ትመክራለች።
አሁን የምታመርታቸው አነስተኛ ቦርሳ እስከ አንድ ሺህ ብር ድረስ የሚሸጥ ሲሆን ከፍ ያለ ቦርሳ ደግሞ እስከ ሶሰት ሺህ ድረስ ዋጋ ተቆርጦላቸው ለገበያ ታቀርባለች። እሷና እሷን መሰል ሃሳብ ያላቸው ወጣቶችን ከፍ ለማድረግ ሃሳብን ወደ ገንዘብ የሚቀየርበት ጊዜና ምቹ ቦታ ያስፈልጋል ትላለች።
ሌላዋ ወጣት ናታኒየም ወንድወሰን ትባላለች። ፋሽን ዲዛይነር ስትሆን ‹‹ናታኒየም ኩቱር›› በሚባል መጠሪያ ለተለያየ ሰው ሊሆኑ የሚችሉ ልብሶችን በማዘጋጀት ትታወቃለች። ይች ወጣት የመጀመሪያ ዲግሪዋን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ብትጨርስም ልቧ ግን ለፋሽን ያደላ ነበርና፤ ይህን ውስጣዊ ፍላጎቷን ለማሳካት ከተማረችው ትምህርት በተጨማሪ በቢዝነሰ ማኔጅመንት ተጨማሪ ዲግሪ ይዛለች።
ወጣቷ በኮምፒውተርና በቢዝነስ ማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪዋን ካገኘች በኋላ ከመክሊቷ ጋር የሚያገናኛትን የፋሽንና ዲዛይን ክህሎት በአጭር ስልጠና አካብታ ወደ ስራ በምትገባበት ወቅት ነበር በዓለማችን ላይ የኮሮና ወረርሽኝ የተከሰተው።
ወቅቱ ማክስና ሌሎች ለበሽታው መከላከያነት የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች እጥረት የነበረበት ስለነበር ፈጠን ብላ አስከፊውን ወረርሽኝ እንደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር ማስኮችን አዘጋጅታ በኦንላይን ገበያ መሸጥ ጀመረች። ያ የኢኮኖሚ አቅሟን ለማሳደግ ያስቻላት ሲሆን ከዚህ በኋላ ለተለያዩ ዝግጅቶች የሚሆኑ ልብሶችን የማዘጋጀት ስራ ላይ ተሰማራች። ትእዛዞችን እየተቀበለች የፋሽን አልበሳትን ለወፍራሞችም ሆነ ለቀጭኖች ሁሉንም አይነት የሰውነት ቅርፅ ያላቸው ሰዎች እንዲለብሷቸው በማድረግ ማዘጋጀት ጀመረች።
ልብሶቿን የእናቷ ሱቅ ጀርባ ባለ ክፍት ቦታ ላይ ሆና በመስራት ክህሎቷን የምታሳድግበት መንገድ ስትፈልግ በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያው የሆነ ፈጣሪ ወጣቶች አንድ ላይ በመሆን ያላቸውን ሃሳብ የሚያሳድጉበት፤ ሃሳቡንም ወደ መሬት አውርደው እንዲጠቀሙ የሚያስችል ክሬኤቲቭ ሀብ የተባለ ማእከል መኖሩን ሰማች።
ክሬኤቲቭ ሀቡ በቀድሞ በፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለስልጣንና በዩናይትድ ኔሺን ኢንዱስትሪ ዴቨሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን ትብብር የተመሰረተ ሲሆን ለስራ ማስኬጃ የሚሆነውንም ገንዘብ የሚያገኘው ከጣሊያን ኤጀንሲ ፎር ዴቨሎፕመንት ኮርፖሬሽን ከተባለ ለጋሽ ድርጅት መሆኑን የማእከሉ ኃላፊ ነግረውናል።
በማአከሉ ለመገልገል የሚችሉ ወጣቶች ያላቸውን የስራ ሃሳብ እና ተጨባጭነቱን በደንብ ማሳየት ሲችሉ እንደነበር የምትናገረው ወጣት ናታኒየም፤ ከሷ የተሻሉ ሃሳቦች ሊኖሩ እንደሚችሉ ብታስበም የትኛውም የተከፈተ በር መዘጋት የለበትም የሚል እምነት ስለነበራት በእድሉ ተጠቃሚ ለመሆን ተወዳድራ ተሳክቶላታል። በማእከሉም የተለያዩ ክህሎቶችን ከማግኘቷም ባሻገር ናታኒየም ኩቱር የተባለውን የልብሶቿን ብራንድ ስም መስከረም 29 ቀን በማእከሉ በተደረገ ዝግጅት ለማስተዋወቅ ችላለች።
ወጣቷ የፋሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ ተቀላቅላ ማህበረሰቡ በሀገር ውስጥ የተሰሩ ብራንድ የሆኑ ልብሶችን መልበስ እስኪችል ድረስ ጥረቷን የማታቆም መሆኑን ትናገራለች። በቀጣይም ሰፊ ፋብሪካ ከፍታ የበርካቶችን የስራ እድል ከመፍጠር በሻገር በታዋቂ ብራንድ አለምን የመድረስ ህልም ይዛ ትንቀሳቀሳለች።
እንደ ሜሮንና ናታኒየም ያሉ የክህሎት ባለቤት የሆኑ ወጣቶች በዚህ እድል ምን ያህል ተጠቀሙ ስንል የማእከሉን ስራ አስፈፃሚ አነጋግረናል። የክሬኤቲቭ ሀብ ማናጀር የሆኑት አቶ ተመስገን ፍሰሃ የአዲስ ነገር ፈጣሪዎች መገናኛ የሚል ትርጉም ይዞ የሚንቀሳቀሰው የስራ ፈጣሪዎች መሰብሰቢያ ከሰባ በላይ ለሆኑ ወጣቶች ክህሎት የማሳደግ ስራ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል። ማእከሉ የአዲስ ነገር ፈጣሪ የሆኑ በተለይም በዲዛይን ላይ የተሳተፉ ልጆች የሚሰሩበት ማለትም በፋሽን ዲዛይን፤ በሌዘር ማኑፋክቸሪንግ፤ በአይቲ፤ በምርት ማሳደግና በቴክስታይል የፈጠራ ዘርፎች ላይ የተሻሉ ሃሳቦች ያሏቸው ወጣቶች አንድ ላይ ተሰብስበው ሃሳባቸውን የሚያሳድጉበት ብሎም ወደ ተግባር የሚቀይሩበት፤ ያሏቸውን የክህሎት ክፍተቶች የሚሞሉበት ማእከል መሆኑን ይገልጻሉ።
በማእከሉ ወጣቶች በፈለጉት ልክ ተቀምጠው ፣አሰላስለው ሃሳባቸውን ወደ ውጤት የሚቀይሩበት ተቋም ነው። መግቢያው ላይ የሻይ ቡና አገልግሎት አለ። ይህም ወጣቶቹ ከተለያዩ ሰዎች ጋር በመገናኘት ውይይት የሚያደርጉበት ቦታ ሲሆን፤ ሁለተኛው ክፍል ደግሞ ወጣቶች ቁጭ ብለው የመጣላቸውን የፈጠራ ሃሳብ በያዙት ላፕቶፕ የሚያስቀምጡበት፤ በማእከሉ የሰው ሀይል አስተዳደር እና የህግ ባለሙያ ሰዎችን የሚያማክሩበት ክፍል ሲኖር፤ በቀጣይ የተለያዩ ስልጠናዎችና ፕሮግራሞች የሚካሄዱበት ቦታ አለ።
በጣም ዘመናዊ የሆኑ ዓለምአቀፍ ትምህርቶች፤ ስልጠናዎች፤ የተለያዩ ክህሎቶች ማለት የዲዛይን አስተሳሰቦችን መያዝ የሚችሉበት ስልጠና ይሰጣል የሚሉት አቶ ተመስገን ፤ ልጆቹ ከሃሳብ ባሻገር ውጤት ላይ ሰርቶ ማሳያ( ሳንፕል) ይሰራሉ፤ ከዛም ፈጠራቸውን ይዘው አብራቸው ከሚሰራ ኢንቨስተር ጋር እንዴት በጋራ መስራት እንደሚችሉ፤ የቢዝነስ ፕላን አፃፃፎችንና ሌሎች የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ያገኛሉ ብለዋል።
በኮምፒውተር ላይ ያሰቡትን ካስቀመጡ በኋላ በሶፍትዌር ተግብረው ሳምፕላቸው በስሪ ዲ ፕርንተር ይታተምላቸዋል፤ የዲዛይኖቻቸውንም ቅርፅ የሚያስይዙ የተለያዩ መቆራረጫዎች መኖሩን ተናግረው በተጨማሪም ዲጅታል ቤተሙከራ ውስጥ የተከፈለበት ንባብ ያነባሉ። የፈጠራ ናሙናቸውን ከሰሩ በኋላ በተለያዩ ኤግዚቢሽኖች እንዲተዋወቅላቸው ይደረጋል። መጨረሻው ማህበሩሰቡን የሚጠቅም ውጤታማ ስራ ለመስራት የሚቻል መሆኑን ነው የተናገሩት።
በዩናይትድኔሺን ኢንዱስትሪ ዴቨሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን የእስቴከ ሆልደር አቶ መሳይ አማረ በበኩላቸው የፈጠራ ሀሳብ ያላቸው ወጣቶች ሲመረጡ የፈጠራ አቅም ያላቸው፣ የተለየ አበርክቶ ሊያደርጉ የሚችሉ በአምስቱም የፈጠራ ዘርፍ የመምረጫ መስፈርት ሲኖር ከሁሉም በላይ ሀሳባቸው መሬት ላይ መውረድ የሚችል ከሀሳብ የዘለለ ተጨባጭ ነገር ያለው ሊሆን የሚችል መሆኑ ታይቷል ። ይህ መስፈርት በማእከሉ ለስድስት ወር እንዲቆዩ የሚያደርጋቸው መሆኑን ተናግረው በቀጣይ ደግሞ ጠቀሜታው እየታየ ሊቀየር ይችላል ብለዋል።
በኦላይን በወጣ ማስታወቂያ 500 ወጣቶች የመዘገቡ ሲሆን የተሻለ የሆኑት 73 ወጣቶች ተመርጠው እየሰለጠኑ ይገኛሉ። አቅም ያላቸው በትንሽ ድጋፍ ተአመር ሊሰሩ የሚችሉ ወጣቶችን የሰበሰበው ይህ ማእከል ስራ ከጀመረ የወራት እድሜ ቢያስቆጥርም ስራ ፈጣሪዎቹ ግን በተገቢው መልኩ እየተገለገሉበት መሆኑን ለማየት ችለናል።
ዩናይትድ ኔሺን ኢንዱስትሪ ዴቨሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን ናሽናል ክላሰተር ዴቨሎፐመንት ኤክሰፐርት አቶ ሰለሞን አሰፋ በበኩላቸው ፤ወጣቱ የክህሎት ሀሳቡን ወደ ውጤት የሚቀይርበት እና የፈጣሪነት ስነ ልቦና የሚያዳብርበት ተቋም መኖሩ እጅግ በጣም የሚያስደስት ነው። የተለያዩ ሀገር ኢንቬስተሮች ሀሳባቸውን ይዘው ወደ ሀገራችን በመምጣት በርካሽ የሰው ጉልበት፣ በራሳችን ጥሬ እቃ አምርተው ለእኛው መልሰው በውድ ዋጋ ይሸጡልናል። የፈጠራ ሀሳቡ፤ ጥሬ እቃው፣ ጉልበቱም ከኛ ከሆነ ለምን የውጪ ሰዎች ያስፈልጉናል። በራሳችን መስራትና ማደግ አለብን ። ለዚህ ደግሞ የማዕከሉ መኖር የፈጠራ ሰዎችን በማበረታታት፣ በመደገፍ የተሻለ የእድገት መንገድ የሚጠርግ ይሆናል።
በአጠቃላይ የፈጠራ ባለቤቶችን በአንድ ቦታ አድርጎ ውስጣቸው ያለውን ሀሳብ በአግባቡ እንዲያወጡ ብሎም ለሀገር ኢኮኖሚ ፋይዳ ያለው ነገር እንዲሰሩ ማድረግ የቻለ ማእከል መፈጠሩ፤ ከዚህም በሻገር ወጣትነትን ከፈጠራ ሀሳብ ጋር አቀናጀቶ ትኩሱን አቅማቸውን በማውጣት ከታች ተነስተው ትላልቅ ኢንቨስተሮች ለማፍራት የሚያስችል ተግባር እያከናወነ ይገኛል። ይህ ለትውልድ ራእይ ታላቅ ስንቅ የሰነቀ ተግባር ይደግ ይጎልብት እያልን በተቋሙ የነበረንን ቆይታ አጠናቀናል።
አሥመረት ብሥራት
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20 /2014