በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተካሄደው የወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት ጉዳይ ጥናት ቡድን መሪ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት ሕዝብ ላይ ካለፉት አርባ ሁለት ዓመታት ጀምሮ የደረሱትን ዘርፈብዙ በደሎች አስመልክቶ 21 አባላት ያሉት የጥናት ቡድን በማዋቀር እና በርካታ የመረጃ ምንጮችን በማሰባሰብ ለ15 ወራት የዘለቀ ጥናት ካካሄደ በኋላ የጥናት ውጤቱን በቅርቡ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል። ጥናቱ ሳይንሳዊ የጥናት መስፈርቶችን መሠረት በማድረግ በርካታ ናሙናዎችን በመውሰድ የተከናወነ እንደሆነም የጥናት ቡድኑ ገልፆ ነበር። በጥናቱም በወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት ሕዝብ ላይ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጅምላ ጭፍጨፋዎች መፈጸማቸው ይፋ ተደርጓል። እኛም ይህንን መነሻ በማድረግ በጥናቱ አካሄድና አጠቃላይ የጥናት ሂደት እንዲሁም የተገኙ ዋና ዋና ግኝቶችን በተመለከተ ከጥናት ቡድኑ መሪ ረዳት ፕሮፌሰር ጌታ አስራደ ጋር ቃለምልልስ አድርገን ያጠናቀርነውን እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል፤ መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- በቅድሚያ እስኪ የጥናቱ መነሻ ምን እንደነበር እና ጥናቱን ለማካሄድ የሄዳችሁበትን መንገድ ይግለፁልን።
አቶ ጌታ፡- ዩኒቨርሲቲዎች የተቋቋሙለት ዓላማ አላቸው። ይህም በዋናነት በሦስት አገልግሎቶች ላይ የተመሠረተ ነው። እነዚህም መማር ማስተማር፤ የማኅበረሰብ አገልግሎት እና ጥናትና ምርምር ማድረግ ናቸው። የመምህራንም ድርሻ በነዚህ ላይ ያተኩራል ማለት ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በመማር ማስተማር፤ በማኅበረሰብ አገልግሎት እና በጥናትና ምርምር ሰፊ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል፤ አሁንም እያደረገ ይገኛል።
ጥናትና ምርምር ሲካሄድ ደግሞ ችግር ፈቺ የሆነ፣ የማኅበረሰቡን ችግር ነቅሶ በማውጣት እና መፍትሄውንም ጭምር በማመላከት የመንግሥት እቅድ እና የፖሊሲ ግብአት እንዲሆን ማድረግ ነው።
እንደሚታወቀው በማኅበረሰባችን ውስጥ በተለይ ግብርና መር ኢኮኖሚ ነው እስካሁን ድረስ የሚተገበረው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ጎንደር ዩኒቨርሲቲም አካባቢው በብዛት ያለው አርሶ አደር እንደመሆኑ በግብርና፣ በጤና፣ በምጣኔ ሀብት ዙሪያ በማኅበራዊ ዘርፎች ሁሉ በየጊዜው ጥናትና ምርምር ያደርጋል።
አንድ ጥናት ሲጠና እንዲሁ አይጠናም። መነሻ ምክንያቶች ይኖሩታል። ለጥናቱ ገፊ ምክንያቶች ምንድናቸው የሚለው የመጀመሪያ ወደተግባር ለመግባት የሚያስችል መነሻ ነው።
ዩኒቨርሲቲው በማንኛውም ጉዳይ ላይ ጥናት ለማካሄድ ችግር አለ ወይ፤ ለነዚያ ችግሮችስ መፍትሄ ያስፈልጋቸዋል ወይ፤ የሚለው ነው። ስለዚህ ጥናት ለማካሄድ ድንበር የለውም። ቦታ አይገድበውም። የችግሩ ዓይነት ሊገድበው አይችልም።
ሁላችንም እንደምናውቀው ወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት አካባቢ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጥናት ለማድረግ የተነሳበት ምክንያቶች አሉ። የመጀመሪያው ነገር አካባቢዎቹ እንደሚታወቀው እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ የጎንደር ክፋይ የሆኑ አካባቢዎች ናቸው። ይህም ማለት ለዘመናት የጎንደር እና የትግራይ ክፍላተሃገራት ድንበር የተከዜ ወንዝ ፤ ሁለቱ ሕዝቦች ደግሞ ለረጅም ጊዜ በጥሩ ጉርብትና ምናልባትም ተቀራራቢ ማኅበራዊ ሥነልቦናና ታሪክም ጭምር ያላቸው ናቸው ።
ሁለቱ ሕዝቦች በግልጽ ጦርነት ውስጥ የገቡበት ጊዜም የለም። የድንበር ይገባኛል ያነሱበትም ጊዜ የለም። ነገር ግን በ1968 ዓ.ም ወደበረሃ ወርዶ የትጥቅ ትግል የጀመረው ሕወሓት አንድ ማኒፌስቶ ይዞ መጣ። ይህ ማኒፌስቶ ወይም ፍኖተ መርህ አንድ አስደንጋጭ ነጥብ በውስጡ ይዟል። ከዚያ በፊት የሌለ ታሪክ እንደተደረገ ተደርጎ ወጣቱን ሊሰብክ የሚችል በተለይ ደግሞ አብሮ ለዘመናት የኖረውን የአማራና የትግራይ ሕዝብ ጠላት እንደሆኑ ተደርጎ እዚያ ማኒፌስቶ ውስጥ በግልጽ ሰፍሯል። ትግሌ ከአማራ ጋር ነው፤ ዘላለማዊ ጠላቴ አማራ ነው፤ ለትግራይ ሕዝብ መውደቅ ምክንያት አማራ ነው የሚል አስደንጋጭ ሃሳብ ነው ይዞ የመጣው።
ይህ ብቻ ሳይሆን የትግራይ ወሰን ተከዜ ብቻ ሳይሆን እነወልቃይትን፣ እነጠገዴን፣ እነጠለምትን እነራያን፣ በአፋር በኩልም እንዲሁ በርካታ የአፋር አካባቢዎችን፣ እና የጎንደርና የወሎን ግዛት የሚያካትት እንደሆነ አድርጎ ነው ካርታ አዘጋጅቶ የመጣው።
ሕወሓት በደደቢት ላይ በሽፍትነት ከጀመረ በኋላ ማኒፌስቶ አዘጋጅቶ በ1972 ዓ.ም ነሐሴ መጨረሻ አካባቢ ተከዜን ተሻግሮ የጎንደር ክፍለሃገር አካል የሆነውን ወልቃይትን መውረር ጀመረ። ከዚያ አድማሱን እያሰፋ የደርግ መንግሥት በተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ምክንያት አጣብቂኝ ውስጥ በነበረበት ወቅት በሽፍትነት የነበረው ሕወሓት የጎንደርን ክፍለሃገር በተለይ በሰሜን በኩል ያለውን ወልቃይትን፣ ጠገዴን እና ጠለምትን ወደ መውረር ሄደ።
በዚህ ምክንያት የወልቃይት፣ጠገዴና ጠለምት አማራዎች ወረራ ተካሄደባቸው። በጣም ደም አፋሳሽ እና በሂደትም የዚያን አካባቢ ማኅበረሰብ ከፋኝ የሚል የራሱን የትጥቅ ትግል እስከማደራጀት የሄደበት ሁኔታ ነበር። በዚህም ከሕወሓት ጋር ለአስርት አመታት በጦርነት ቆይቷል። ይህ እንግዲህ ከደርግ ጋር ከሚዋጋው ባሻገር ነው ማለት ነው። በሂደት በማኒፌስቶውም እንደተቀመጠው ይህንን አካባቢ ሕወሓት የመንግሥትነት ስልጣን ሲይዝ ወደትግራይ የመጠቅለል ሥራ ሠራ።
ይህን ሲሠራ እንግዲህ ምንም ዓይነት ሕገመንግሥታዊ መሠረት የለውም። ሁለተኛ የአካባቢውን ኅብረተሰብ አላወያዩትም። ያንን የሽግግር ወቅት እና ውዥንብሩን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም እና ስልጣኑን ተገን በማድረግ ወደትግራይ ክልል እንዲካለል ሲያደርግ እዚያ አካባቢ ያለው ኅብረተሰብ ወደነፃነት እንቅስቃሴ እና ትግል በመግባት ብዙ መስዋእትነት ከፍሏል።
በዚህ ምክንያት በመቶ ሺዎች የሚቆጠር የአካባቢው ማኅበረሰብ አካባቢውን ጥሎ እንዲሰደድ ተደርጓል። በእኛ ጥናት ያረጋገጥነው ወረራው የቅኝ ግዛት ወረራ ነው የሚመስለው። ምክንያቱም ቅኝ ግዛት ሲመጣ በጉልበት ተጭኖህ ሊገዛህ ነው የሚመጣው። ሀብትህን ሊዘርፍ ነው የሚመጣው። ሊያሳድድህና ሊገድልህም ጭምር ነው የሚመጣው። ሕወሓትም ይህን ነው የፈጸመው።
ከዚያ በኋላ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ማኅበረሰብ በየትኛውም ዓለም እንዲበተን ሆነ። አሁን እኛ ባገኘነው ጥናት መሠረት ከእያንዳንዱ ቤተሰብ 26 ነጥብ 5 ከመቶ ለስደት ተዳርጓል፤ 19 ነጥብ5 ከመቶ ታፍኖ የት እንደገባ አይታወቅም፣ እንዲሁም 29 ከመቶ ለሞት ተዳርጓል።
ሌላኛው የጥናታችን መነሻ የነበረው በዚህ አማካኝነት ይህንን አቤቱታ በመስጠት እንደነ ልሳነ ግፉአን፣ እንደነ እንደነ ኢሰመጉ፣ እነ ሞረሽ ወገኔ፣ በቅርቡም የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጥናት አካሂደው እዚያ አካባቢ ብዙ ግፍ እንደደረሰ የጥናት መነሻ የሚሆኑ ነገሮች ተቀምጠዋል።
ከዚያ በኋላም የወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት ሕዝብ ማንነቴ ይመለስልኝ፣ በጉልበት ያለማንነቴ ወደትግራይ ተካልያለሁ በማለት ጉዳዩን የማንነት አስመላሽ ኮሚቴ በማቋቋም ሕጋዊ በሆነ መንገድ እስከ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ድረስ አድርሶት ላለፉት ስምንት አመታት አካባቢ የተጀመረው የማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ጉዳይ እስካሁን እልባት አላገኘም። ይህ ጉዳይ በመንግሥት በኩል እልባት አለማግኘቱ፣ በቂ የሆነ ምርመራም አለመካሄዱ ለእኛ ለጥናታችን መነሻ ሆኖናል።
ሌላኛው በግልጽ እንደሚታወቀው ከማዕከላዊ መንግሥት ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ የገባው ሕወሓት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን እዝ ላይ በሚያሳዝን ሁኔታ በድንገት ጥቃት ሲፈፅም በስድስተኛው ቀን ማይካድራ ላይ 1644 የአማራ ተወላጆችን ጨፍጭፏል። ይህ በአንድ ቀን ብቻ የተደረገ፣ በተጠና፣ በተደራጀ፣ ስልታዊ በሆነ፣ መዋቅር በተዘረጋለት መልኩ የተሠራ የዘር ማጥፋት ሂደት ነው።
እነዚህ ነገሮች ሁሉ አካባቢው ላይ ሰፊ ጥናት እንድታጠና ያስገድዳሉ። ምክንያቱም ይህ የሰብአዊነት ጉዳይ ነው፤ የሰላም ጉዳይ ነው፤ የፍትህ ጉዳይ ነው፤ ስለዚህ ዩኒቨርሲቲው በነዚህ ጉዳዮች ላይ ጥናት በማጥናት የድርሻውን እንዲወጣ ያስገድደዋል ማለት ነው።
እንዲያውም ወደጥናቱ ገብተን ካየን በኋላ በጣም የዘገየ ጥናት እንደሆነ ነው የተረዳሁት። ይህ ጥናት መጠናት የነበረበት አሁን አልነበረም። ዩኒቨርሲቲዎችም፣ ሌሎች የጥናት ተቋማትም በዚህ ኃላፊነት ነበረባቸው። ምክንያቱም እዚያ አካባቢ ያለ ኅብረተሰብ ተሰዶ፣ ተገድሎ እና ታፍኖ እስከሚያልቅ፣ ማንነቱን እስከሚነጠቅ፣ ቋንቋ እስሚከለከል፣ ባህሉን፣ ወጉንና ልምዱን እንኳን መተግበር እንዳይችል እስከሚደረግ ድረስ መቆየት አልነበረበትም። የመንግሥትም ፍትህ ጭምር የዘገየ ይመስላል። እነዚህ ሁሉ የጥናታችን መነሻዎች ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ከዚያ በኋላ ጥናቱ በምን መልክ ነው የተካሄደው?
አቶ ጌታ፡- አንድ ጥናት ሲካሄድ ቅድመ ሁኔታዎች አሉት። የመጀመሪያው ለጥናት ቅድመ ሁኔታዎች የሆኑ መነሻዎች አሉ ወይ የሚል ነው። ለዚህ መልሱ አዎ የሚል ነው። ሁለተኛው ለዚያ ጥናት የሚሆን ንድፈሃሳብ ይዘጋጃል። ጎንደር ዩኒቨርሲቲም 21 የሚሆኑ የጥናት ቡድን አባላትን አዋቅሮ ዝርዝር ንድፈሃሳብ እንዲዘጋጅ አድርጓል። ምን ዓይነት ስልት መከተል እንዳለበት፤ የጥናቱ ወሰን፣ መቼ ተጀምሮ መቼ ማለቅ እንዳለበት፣ በጀት፣ ተሳታፊዎች እነማናቸው የሚሉ ሃሳቦችን የያዘ ሰነድ ከተዘጋጀ በኋላ መነሻ ሃሳብ ተገመገመ። የጥናት ስነምግባር ደንብ ቦርድም መነሻ ሃሳቡን ገምግሞ አፅድቆታል፤ገለልተኛ የሆኑ በቦርድ የተቋቋሙ ባለሙያዎች ይህንን ከገመገሙ በኋላ ሳይንሳዊ መሆኑን፣ የፖለቲካ ወገንተኝት የሌለው ስለመሆኑ ተገቢ የሆነ ጥናት ነው ተብሎ ከፀደቀ በኋላ ነው በጀት የተለቀቀለት።
ንድፈሃሳቡ ከፀደቀ በኋላ አካባቢውን የመቃኘት ሥራ ነው ቡድኑ የሠራው። ምክንያቱም የጥናቱ አላማ የተደበቀውን ጉዳይ ነው ማውጣት ያለበት። ስለዚህ ዝም ተብሎ ዘው ተብሎ የሚገባበት እና የሚወጣበት አይደለም። ትልልቅ ሰዎችን ቃለመጠይቅ አደረግን፣ የመንግሥት ተቋማትን አየን፣ ሰነዶችን አገላበጥን፣በዚህ ሂደት ውስጥም የጥናት ስልታችንን በዝርዝር አስቀመጥን።
ጥናታችን ሁሉንም ዓይነት ስልቶች ያካተተ ነው። ምክንያቱም ጥናት ስታጠና እውነታውን ማግኘት አለብህ። ይህ እዚህ አካባቢ የተፈፀመው ወንጀልም ሆነ ጥፋት ውስብስብ ያለ ሂደትን የተከተለ ነው። አንደኛ ጥፋቱ መንግሥት መር ነው። ሁለተኛ ስልታዊ ነው። ሦስተኛ የተቀናጀ ነው። በርካታ አካላት እጃቸው አለበት። አራተኛ በተቻለ መጠን መረጃዎች እንዳይገኙ ለማድረግ ከፍተኛ ሥራ ተሠርቷል። ስለዚህ ይህ ከሆነ ምንድነው ማድረግ ያለብን በሚል የጥናት ስልታችን ሁሉን ዓይነት ዘዴዎችን እንድንከተል አስገድዶናል። ለምሳሌ አንደኛው የገጠርንም የከተማውንም ኅብረተሰብ ያካተተ አባወራዎችን ቃለመጠይቅ ማድረግ ነው። ታሪኩ፣ ባህሉ፣ ሕወሓት ከገባ በኋላ የነበረው የሕወሓት አስተዳደራዊ ሥርዓት ምን ይመስላል፤ የተፈፀሙ ወንጀሎችና በደሎች ነበሩ ወይ፣ አሁን ማኅበረሰቡ ምን ይፈልጋል፤ ምን ዓይነት ስነልቦና ነው ያለው፤ የሚለውን የሚዳስስ 912 አባወራዎችን የሚያካትት ቃለምልልስ ተደርጓል።
ሌላኛው መንገድ የመስክ ምልከታ ማድረግ ነው። የመስክ ምልከታችን ተቋማትን፣ ቤቶችን፣ በዓላትን፣ የሚያካትት ነው። ለምሳሌ በዓላት ላይ ምን ዓይነት ቋንቋዎችን ይናገራሉ? ምን ዓይነት ባህል ነው ያላቸው? ግንኙነታቸው ምንድነው የሚመስለው? ስነልቦናቸው ምንድነው? የሚመስለው የሚለውን ባካተተ መልኩ የወንጀል አሻራዎችን ተከትለን በማነፍነፍ ምልከታ አካሂደናል።
በሌላ በኩል የቡድን ውይይት ተካሂዷል። የአገር ሽማግሌዎች፣ ታሪክ አዋቂዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች፣ አቤቱታ ሲያቀርቡ የነበሩ ወዘተ፣ ከሙያ ዘርፍም ከሁሉም ሙያ ከሕክምና፣ ከትምህርት፣ ከምጣኔ ሀብት ወዘተ የተካተቱበት ነው።
ሌላኛው ጥልቅ ቃለመጠይቅ ነው። በዚህም አንድ ሰው ያለምንም ገደብ ሃሳቡን በዝርዝር የሚገልጽበት ነው። ከዚህ በተጨማሪ እያንዳንዱ ፎቶ፣ ቃለመጠይቅ እና ውይይት ሲደረግ ሙሉ ፈቃደኝነታቸው ተጠይቆና
ፈቃደኛ ሲሆኑ ብቻ ነው የጥናቱ አካል የሆኑት። የጥናቱ ተሳታፊዎች በራሳቸው ሙሉ ፈቃድ፣ በራሳቸው ነፃነት ተሰምቷቸው ነው። ፈቃደኛ ካልሆኑ አካላት መረጃ አልሰበሰብንም። ጥልቅ ቃለመጠይቅ ታሪክ አዋቂዎችን፣ ሽማግሌዎችን በወቅቱ በስፍራው የነበሩ ሰዎችን ጭምር ያካተተ ነው።
ሌላኛው የሰነድ ማስረጃ ነው። ምንም እንኳ ጥናቱ ስልታዊ ሆኖ ብዙ ሰነዶች ቢጠፉም ወንጀል ሠርቶ ማምለጥ አይቻልምና በርካታ ሰነዶችን ማሰባሰብ ችለናል። እነዚህ አሁንም በመጽሐፍ መልክ የሚወጡ ጭምር ናቸው። ቦታውን ሲወሩ ከመንግሥት ተቋማት ሲፃፉ የነበሩ ደብዳቤዎች፣ የወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት ሕዝብ እንዴት እንደተቀበላቸው፤ ሰዎችን አፍነው ለመውሰድና አማርኛ ቋንቋ እንዳይናገሩ፣ ባህላቸውን እንዳይለማመዱ ለማድረግ ሲሠሩ የነበሩ ተግባራትን በተመለከተ በርካታ ሰነዶችን አግኝተናል። ከተቋማት፤ ከግለሰቦች፣ ከታሪክም ጭምር ማለት ነው።
ሌላኛው ደግሞ ፍንጭን ተከትሎ የመሄድ ስልት /Snow ball technique/ ነው። ይህ ዘዴ አንድ ሰው የሆነ ፍንጭ ሲናገር እሱን በመያዝ ወደሚቀጥለው መሄድና እሱን ተከለትሎ በመሄድ እስከመጨረሻው ምንጩጋ እስከሚደረስ ድረስ የመጓዝ ዘዴ ነው። በዚህ ስልት በተለይ አብዛኞቹን የዘር ፍጅት የተካሄደባቸውን ቦታዎች ለማግኘት በጣም ምስጢራዊ፣ ድብቅ፣ መሬት ውስጥ የተቀበሩ እና ሰው የማይደርስባቸው አካባቢዎች ስለነበሩ፣ ይህንን ስልት ነው የተከተልነው።
በዚህ ሂደት እዚያ አካባቢ ለረጅም ጊዜ ጥያቄ ሲያነሱ የነበሩ ሰዎችን ተጠቅመናል። እያንዳንዷ መረጃ አባወራው ድረስ በመሄድ ዋሻ ውስጥ በመሄድ፤ የተቀበሩትን የጅምላ መቃብሮች፣ አፈላልጎ ማግኘት፣ ሰዎች ወንዝ ውስጥ ሲከተቱ የነበሩ ሰዎችን፣ ለዚህ ምስክር የሚሆኑ ሰዎችን ጭምር በማምጣት እነዚህን ሰዎች በመጠቀም ነው የጅምላ መቃብሮችን ማግኘት የቻልነው።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ ግኝታችሁ ምን ነበር?
አቶ ጌታ፡- የእኛ ጥናት ታሪክን ያጠናል፤ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ሕዝብ ታሪኩ፤ ባህሉ፤ ልማዱ ወዘተ የሚለውን ያጠናል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የደረሰ የታሪክ፣ የባህልና የቋንቋ ቅየራ መኖሩን አረጋግጠናል። ለውጡንም ጭምር እያነፃፀርን ለማሳየት ሞክረናል። ይህ በዝርዝር በመጽሐፍ መልክ ይወጣል።
ሌላኛው የደረሰ የዘር ማጥፋት ወንጀል አለ። ከላይ እንደተገለፀው 29 ከመቶ የሚሆነው እዚያ አካባቢ ያለው ማኅበረሰብ ሕይወቱ እንዳለፈ አረጋግጠናል። ይህ ሕወሓት ባመጣው ጦስ የደረሰ ነው። ሁለተኛው 26.5 ከመቶ የሚሆኑ ሰዎች አድራሻቸውን እንዲለቁና እንዲበተኑ ተደርጓል። በዚህ የተነሳ የወልቃይት ሕዝብ በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች እና በበርካታ የውጭ አገራት ተበትኖ ይገኛል። ሱዳን፣ ኤርትራ፣ እስራኤል፣ አውሮፓ ወዘተ ተበታትነው ነው ያሉት። እኛ ጥናቱን ካካሄድን በኋላ እነዚህ ሰዎች የት እንደተበተኑ ጭምር ሙሉ መረጃ አሰባስበናል። የት አገር እንደሄዱ፣ መቼ እንደሄዱ ወዘተ ማለት ነው።
ሦስተኛው ታፍነው የሚጠፉ ሰዎች ናቸው። በተለይ ታሪክ አዋቂ፣ ማኅበረሰቡን ያነቃሉ፤ መንግሥትን ይሞግታሉ፤ የሚባሉ ሰዎች ልቅም ተደርገው በጭለማና በብርሃንም ጭምር ታፍነው ተወስደዋል። የሚያሳዝነው እነዚህን ሰዎች ቤተሰቦቻቸው የት ሄደው ነው ብለው ሲጠይቋቸው እንኳ እንዲናገሩ አይፈቀድላቸውም። ስልጠና ወስደናቸዋል ጭምር የሚል ምላሽ ይሰጧቸዋል። እንግዲህ ሃያና ሰላሳ ዓመት የሆናቸው አሉ፤ እነዚህ ሰዎች የት እንደደረሱ እንኳን ማወቅ አይቻልም። ማኅበረሰቡ አንድ ሰው ለምሳሌ ሚስት ባሏ ታፍኖ ሲሄድ የት ሊሄድ ነው ብላ መጠየቅ አትችልም። ይህንን ያህል የስነልቦና ጫና እንዲደረግበት ተደርጓል ማኅበረሰቡ። በዚህ አማካኝነት ሰዎችን ማፈናቀል፤ መግደል አፍኖ መውሰድ ናቸው በዋናነት ከሰብአዊነት አኳያ የተፈፀሙት። ከሕክምና፣ ከግብርና፣ ከኢኮኖሚና ከትምህርት አንጻር የሚያሳዝን ግፍ ነው የተፈፀመው። በነዚህ ውስጥም አንኳር የሆነው ጅምላ ጭፍጨፋ ነው።
በዚህ ሂደት ውስጥ 12 የጅምላ መቃብር ቀጣናዎች ተገኝተዋል። ማይካድራን ጨምሮ በጣም በርካታ ሰዎች የተፈጁበት ቀጣናዎች ተገኝተዋል ማለት ነው። ከነዚህ ውስጥ ስምንቱ የተረጋገጡ ናቸው። ሌሎች 12 የሚሆኑ ተጠርጣሪ ቦታዎችም አሉ።
ማይካድራ ላይ ሲኬድ ስምንት ዋና ዋና የጅምላ መቃብሮች አሉ፤ የሟች ቁጥር 1563 ነው። 81ዱ ደግሞ በሕክምና ጥረት ሕይወታቸው የተረፈ ነው። ለምስክርነት የበቁትም እነሱ ናቸው። ስለዚህ ይህንን ያህል ሰፊ ጅምላ ጭፍጨፋ መካሄዱን ለማረጋገጥ ተችሏል።
እነዚህን ማነው ያደረገው፣ መቼ የሚለውን በተመለከተ ያላለቀ ሥራ አለ። የካርቦን እና የፎረንሲክ ምርመራዎች ይቀራሉ። ዘመናዊ የላቦራቶሪ ምርመራዎችን ለማካሄድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሥራት ላይ እንገኛለን። ነገር ግን መረጃዎቹ ካለው ሰነድ ተነስተን ግልጽ ነው። ጅምላ ጭፍጨፋውን ሕወሓት ስለማካሄዱ ግልጽ ነው። ጭፍጨፋውም በጎንደር አካባቢ ባሉ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት አማራዎች ላይ ስለመፈፀሙ፣ ከበቂ በላይ ማስረጃዎች አሉ።
እንደሚታወቀው ሕወሓት ሲመጣ አማራ ጠላቴ ነው ብሎ በወረራ ነው የጀመረው። ስለዚህ ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ የመንግሥት ስልጣን እስከያዘበት ጊዜ ድረስ ይህን አካባቢ ሲቆጣጠር የነበረው ሕወሓት ነው። ሁለተኛ እዚህ አካባቢ ያለው ማኅበረሰብ ሲሰደድ፣ ሲገደል፣ ሲታፈን እንደኖረ በጣም በርካታ ዜጎች ሰሚ አጥተው በታፈነ ሁኔታ ውስጥ እንደነበሩ በርካታ ማኅበሰረብ አባላት ሲጮሁ ነው የቆዩት። ሦስተኛ ከዚህ በፊት የነበሩት የነኢሰመጉም፣ የነሞረሽ ወገኔም፣ የነልሳነ ግፉአን፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ በቅርቡ ደግሞ የማይካድራን ጨምሮ ሕወሓት በግልጽ እዚያ አካባቢ ያሉ አማራዎችን ሲጨፈጭፍ መኖሩን ያሳያል።
ሌላው ደግሞ ማይካድራ ላይ የፈፀመው የአደባባይ ወንጀል ይህንን አይፈፅምም ብለህ እንድትነሳ አያደርግህም። መታወቂያቸውን፣ ሲም ካርዳቸውን፣ ስልክ ቁጥራቸው ለይቶ አማራ የሆኑ ግለሰቦች ላይ ነው ግፉን የፈፀመው።
ሌላው የሕወሓት ከፍተኛ ባለስልጣናት ብዙ ጊዜ ይህንን በአደባባይ ይናገሩት ነበር። ለምሳሌ እነጄኔራል ሳሞራ የኑስ፤ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ ሌሎችም ከፍተኛ አመራሮች በግልጽ ተናግረውታል። በአንድ ወቅት ሁመራ ላይ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ማኅበሰረብ በጣም አቤቱታ ሲያበዛ የአካባቢውን ትላልቅ ሰዎች ሰብስበው ችግራችሁ ምንድነው ብለው አወያዩአቸው። እኛ መሬታችንን በሕወሓት ካድሬዎች ተነጥቀናል፤ እየሞትን ነው፤ እየተሰደድን ነው፤ ፍትህ እንፈልጋለን፤ ወረራ ተካሂዶብናል፤ ስለዚህ ወደአማራ ክልል እንካለል የሚል ጥያቄ ሲያነሱ አቶ መለስ ዜናዊ በአደባባይ እኛ ወደወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት ጨፌ ተጎዝጉዞልን አልመጣንም፤ የመጣነው ደም አፍሰን፣ አጥንት ከስክሰን ነው፤ ከ20 ሺህ በላይ የትግራይ ሰራዊትን መስዋዕት ከፍለን ነው። መሬት ለተወለደበት አትሆንም። ለጉልበተኞች ነው የምትሆነው። ስለዚህ አካባቢውን በጉልበት ይዘነዋል፤ እናንተም ጉልበት ካላችሁ በጉልበት ሞክሩት፤ በሌላ መልኩ ብትሞክሩት ግን አይሳካላችሁም የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው የአካባቢው ሽማግሌዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተውናል። እነ ጄኔራል ሳሞራ የኑስም አማራን አከርካሪውን ሰብረነዋል ብለው በአደባባይ ተናግረዋል። እነዚህ ከራሳቸው የመጣ ምስክርነት ነው።
ሌላው ይህ አካባቢ የተገኘው ጅምላ መቃብር ዛፍ የበቀለበት፤ ፍርስራሽ የወደቀበት፤ እንደሆነ በመስክ ምልከታ ወቅት የታየ ነው። ደጀና፣ ገሃነምና ምንምኔ አካባቢ ያሉት የ20 እና የ30 አመት ፍርስራሾች ስለመሆናቸው በግልጽ ይታወቃል። ይህ አካባቢ የሕወሓት ካምፕ እንደነበርም በግልጽ ይታወቃል። ስለዚህ ወንጀሉን ማን እንደፈፀመው ግልጽ ነው ማለት ነው።
ከዚህም ባሻገር የሟች ቤተሰቦች ከሕወሓት ካድሬዎች ማን እንደገደላቸው ጭምር በግልጽ የተናገሩበት ሁኔታ ነው ያለው። አባቴን የገደለው እከሌ ነው፤ በዚህ ቀን፣ በዚህ ሰዓት፣ በዚህ ቦታ ብለው በግልጽ ይናገራሉ። ያም ሆኖ ግን ጅምላ ጭፍጨፋ ዓለም አቀፍ ወንጀል ስለሆነና ጉዳዩን በዚያ ልክ ከፍ አድርጎ መደምደሚያ ለመስጠት የላቦራቶሪ ምርመራዎቹን ማካሄድ አስፈላጊ ሆኗል።
በግድያው ወቅት ብዙ ዓይነት ስልት ነበር የሚከተሉት። አንዳንዴ አደባባይ ላይ ረሽነው አስከሬንን አደባባይ ላይ ያሰጡ ነበር። ገበያ ላይ ጥለው እንዳይለቀስ ያደርጉም ነበር። ይህ የሰዎችን ስነልቦና ለመጉዳት ነው። ሌላው ደግሞ ገድሎ ገደል ውስጥ መክተት ነው።
አብዛኛው የፈፀሙት ግን እንደነ ገሃነም ዓይነት በመሬት ውስጥ ከተዘጋጁ እስር ቤቶች በምሽት እያወጡ በየቀኑ የሚረሽኑበት ሁኔታ ነበር። ይህን እዚያ እስር ቤት የነበሩና በተዓምር የተረፉ ናቸው የገለፁልን። የአካባቢው ማኅበረሰብም ይህ የዕለት ተዕለት ተግባር እንደነበር ይናገራል። ሌሊት አውጥተው ጉድጓድ ራሳቸውን አስቆፍረው በአውቶማቲክ መሣሪያ በጅምላ የረሸኗቸው ሰዎችም አሉ።
አብዛኞቹን ደግሞ ወንዝ ዳር ነበር የሚቀብሩት። ለምሳሌ ተከዜ ተፋሰስ አካባቢ፣ አድኖ የሚባል ጅምላ መቃብር፣ ገሃነም አካባቢም በቃሌና ወንዝ ተፋሰስ ከወንዙ አምስትና አስር ሜትር ርቀት ላይ ይቀብሯቸው ነበር። ምክንያቱም በክረምት ወንዝ ሲሞላ አስከሬኑን ይዞ እንዲሄድ ለማድረግ ነው።
ወንዝ ዳር ካልሆነ ደግሞ ሰዎችን ገድለው ከቀበሩ በኋላ መሬቱን ልክ እንደ አውድማ ይደመድሙትና ደብዛው እንዳይገኝ ያደርጉ ነበር። ድንጋይ የለውም፣ ምልክት የለውም፣ አንዳንድ ቦታ ደግሞ እንዲታረስም ይደረጋል። በሌላም በኩል አየር ማረፊያዎችን፣ ሆስፒታሎችንና ጤና ጣቢያዎችን ጭምር የመግደያ ቦታ አድርገው ነበር። ይህ የጤና ባለሙያዎች ጭምር ምስክርነት የሰጡበት ነው። ስለዚህ ጥናታችን ይህንን ያካተተ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከነዚህ ጅምላ ጭፍጨፋዎችና ማሳደዶች በስተጀርባ ያለው ፍላጎት ምን ነበር?
አቶ ጌታ፡- ሕወሓት በዚህ አካባቢ በዚህ ልክ የሞት ቀጣና እንዲሆን ካደረገባቸው ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ከመልክዓምድር አንጻር ቁልፍ ቦታ መሆኑ ነው። አካባቢው የእርሻ መሬት ነው። ሰሊጥ፣ ማሽላ፣ ጥጥ፣ የሚመረትበት አካባቢ ነው። የቀንድ ከብት በብዛት የሚረባበት ነው። ወደሱዳንና ኤርትራም ጭምር ኮሪደር የሚሆን ነው። ሕወሓት ካድሬውን ወደ ወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት እንዳመጣ እዚያ አካባቢ ያሉ ገበሬዎችን ገድሎ እና እንዲሰደዱ አድርጎ መሬታቸውን በሙሉ ቀምቷል። በዚህ የተነሳ የሕወሓት ካድሬዎች በጣም ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን በዚያ አካባቢ ይዘዋል። ተወላጁ መሬቱን ተነጥቆ አካባቢው የሕወሓት ካድሬዎች ንብረት እንዲሆን ተደርጓል። በዚህም ለረጅም ጊዜ ሰሊጥ፣ ማሽላና ጥጥ ሲያመርቱበት እንደነበር አይተናል።
በዚያ አካባቢ የወልቃይት ተወላጅ የሆነ የሥራ ዕድል የሚያገኝበት ዕድል ጠባብ ነበር። የወልቃይት የሥራ ማስታወቂያ እንኳን የሚለጠፈው ሽሬና መቀሌ ላይ ነበር። ስለዚህ ዕድሉን የሚያገኙት ሽሬና መቀሌ አካባቢ ያሉ የሕወሓት ደጋፊዎችና ካድሬዎች ናቸው።
በሌላም በኩል በየትኛውም መንገድ በዚያ አካባቢ ያለ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲዳከም ነው የተደረገው። ኢኮኖሚው ባዶ እንዲሆን ተደርጓል። ከብቶቻቸውን ጭምር ለመዝረፍ ሰበብ ነበር የሚፈለግባቸው። ለምሳሌ የወልቃይት ከብት ሄዶ እነሱ ከወልቃይት የነጠቁትን መሬት ከረገጠ ለአንድ የቁም ከብት እስከ 1600 ብር እንዲከፍል ያደርጉ ነበር። እዚያ አካባቢ በርካታ የሕወሓት ሰዎች ሰፋፊ እርሻ እያላቸውና ኢንቨስትመንት ውስጥ ገብተው ሳለ ግብር አይከፍሉም ነበር። እስካሁን ድረስ ሳይመለሱ የቀሩ በርካታ የባንክ ብድሮችንም ይወስዱ ነበር።
የአካባቢው ተወላጅ ግን ከአቅሙ በላይ ግብር እንዲከፍል በማድረግ ንግዱን እንዲተው ተደርጓል። ትንሽ ምግብ ቤት እንኳን መክፈት የማይችሉበት ሁኔታ ነበር። ስለዚህ ወደ ሥራ መግባት አይችሉም፤ ንግድ ላይ መሰማራት አይችሉም፤ እርሻውን ተነጥቀዋል፤ተምረው እንኳ ሥራ እንዳይዙ ተደርገዋል።
የወልቃይት ተወላጅ የሆነ ሰው ትምህርቱን እንኳን በአግባቡ እንዳይከታተል ይደረግ ነበር። ሴቶችንም አስገድደው ይደፍሩ ነበር። በዚህ የተነሳ ያለዕድሜ ማርገዝና ከትምህርት ማቋረጥና የመሳሰሉ ችግሮች በርካታ ነበሩ። በዚህ የተነሳ በርካታ የወልቃይት ልጆች በተለያዩ የጎረቤትና የአገር ውስጥ አካባቢዎች ተሰደው ነበር። ለምሳሌ በጎንደር ወልቃይት የሚባል ሰፈር አለ።
ከዚህም ባሻገር ከባህል አንጻር የሚሠራው ሴራ ከፍተኛ ነበር። ለምሳሌ መቀሌ አማርኛ እንደልብ ይነገራል። ወልቃይት ላይ ግን አማርኛ መናገር አይቻልም ነበር። ወልቃይት ላይ ምግብ ቤት ላይ በአማርኛ ስም መፃፍ አይቻልም። ብዙ ዋጋ ያስከፍላል።
ወልቃይት ላይ የስፖርት ክለብ ሳይቀር በአማርኛ የተፃፈበት ልብስ መልበስ አይቻልም ነበር። የነፋሲል ከነማን ቲሸርት በአማርኛ ተጽፎበታል ተብሎ እንዳይለብሱ ነው የተደረገው። አዲ ረመጥ ላይ አንድ ትልቅ ሰው ምግብ ቤት ከፍተው በአማርኛ ስም በመጻፋቸው ምግብ ቤቱ እንዲዘጋ ተደርጓል። ግፉ በዚህ ልክ ነው የነበረው።
ከባህልም አንጻር የአካባቢው ሕዝብ በኀዘኑም ሆነ በደስታው ጊዜ የጎንደር አማርኛን ነው የሚጠቀመው። ከሚዲያም አንጻር ላለፉት የሕወሓት ዘመን እኮ ስለወልቃይት ጠገዴና ጠለምት መናገር ወንጀል ነው የነበረው። ጋዜጠኞችንም በዚህ ዙሪያ ስናናግር የወልቃይት ጉዳይ ቀይ መስመር ነው ብለው በግልጽ ነግረውናል።
ማንኛውም ሚዲያ እንዳይዘግበው ነው የተደረገው። ስለዚህ ይህ ስልታዊ፣ የተደራጀ፣ መንግሥት መር የሆነና በማኒፌስቶ የተደገፈ፣ በማንነት ላይ የተፈፀመ ወንጀል ነው። ይህን ወንጀል መንግሥትም ሆነ ሌላው አካል በአደባባይ አውጥቶ ወንጀሉን የሠራውን አካል መጠየቅ፣ ወደፊት ደግሞ ትምህርት እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል።
ከዚህ በኋላ ጉዳዩን መንግሥትም፤ ሰብአዊ መብት ላይ የሚሠሩ አካላትም በባለቤትነት የሚይዙት፣ የፍትህ ተቋማት በሰፊው የሚሠሩበት፣ ፌዴራል ፖሊስና ሌሎች የምርመራ ተቋማትም በዘርፉ ልምድ ያላቸው ሌሎች ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ምሁራን ሊሳተፉበት ይገባል። ጉዳዩን ከፖለቲካ ወገንተኝነት ውጪ ማንኛውም አካል በሰብአዊነት ሊሠራው ይገባል። የዓለም አቀፍ ተቋማትና የሌሎች አገራት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሮፌሰሮችን ጭምር ለማሳተፍ እየሠራን ነው። ስለዚህ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል። እኛም ወደፊት የጥናቱን ግኝት በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ በተለያዩ ቋንቋዎች በማሳተም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደራሽ ለማድረግ እየሠራን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ።
አቶ ጌታ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ወርቁ ማሩ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20 /2014