የዛሬው የፍረዱኝ ዝግጅታችን ወደ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት ልዩ ስሙ ድል በር ተብሎ ወደ ሚጠራው አካባቢ ይወስደናል።አቤቱታ አቅራቢው አቶ ስንታየሁ አየለ ይባላሉ ።በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 ድል በር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ ሲሆኑ ፤ የመኪና እጥበት በማከናወን ኑሮአቸውን የሚመሩ ግለሰብ ናቸው።
የመኪና እጥበት የሚያከናውኑበትን ቦታ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ እንደያዙት አቤቱታ አቅራቢው ይናገራሉ።ይሁን እንጂ መኪና እያጠቡ ቤተሰባቸውን ሲያስተዳድሩበት የነበረውን ቦታ በጉለሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ ሰባት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ውርጭ ፣ ቁር እና ፀሐይ እየተፈራረቀባቸው ያለሙትን የመኪና ማጠቢያ ቦታ እንዲፈርስ በማድረግ ከስምንት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመትን ንብረት ግማሹን በማውደም እና በማበላሸት ፤ ግማሹን ደግሞ በግብር ኃይል ጭኖ በመውሰድ ግፍ እንደሠሩባቸው ይገልጻሉ።
«የሕዝብን ችግር ይፈታሉ ተብለው በተቀመጡት የሥራ አስፈጻሚ ያልተገባ ተግባር ለከፍተኛ የገንዘብ ኪሳራ እና የስነ ልቦና ጫና ስለተዳረኩ የኢትዮጵያ ሕዝብ የደረሰብኝን በደል ተመልክቶ ይፍረደኝ!» ሲሉ አቶ ስንታየሁ አየለ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አቤት ብለዋል።የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ከሰዎች እና ከሰነዶች ያገኛቸውን መረጃዎች ዋቢ በማድረግ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግራ እና ቀኙን በማየት መፍረድ ይችል ዘንድ ዝግጅት ክፍሉ የደረሰበትን ሙሉ የምርመራ ውጤቱን እነሆ ብለናል።መልካም ንባብ።
ከአቤቱታ አቅራቢው አንደበት
አሁን ላይ ውዝግብ የተነሳበት ቦታ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ የመኪና እጥበት የሚያከናውኑበት እና ቤተሰባቸውንም ሲያስተዳድሩበት የቆየ እንደነበር አቤቱታ አቅራቢው ይገልጻሉ። መጀመሪያ ላይ ቦታው አግባብነት ባለው የመንግሥት አካል የተሰጣቸው አልነበረም ።ይሁን እንጂ መኪና የሚያጥቡበት ቦታ በግልጽ የአየር ካርታ ላይ ይታያል። በመሆኑም መንግሥት በ2006 ዓ.ም ከሰነድ አልባ ቦታዎች ጋር ተያይዞ ያወጣውን መመሪያ ተከትሎ በጉለሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 07 ካቢኔ አባላት ተወያይተው እና ገምግመው በ2007 ዓ.ም ቦታው ካርታ እንዲሠራላቸው የሚል ውሳኔ አስተላለፉ።ከውሳኔ በኋላ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የክፍለ ከተማ ባለሙያዎች ቦታውን ለመለካት እና ለመሸንሸን በማሰብ ካርታ እንዲሠራለት ወደተባለው ቦታ በማቅናት ቦታውን ለኩ ።የቦታው ስፋትም 886 ካሬ ሜትር ሆነ ።ነገር ግን ለአንድ ድርጅት መሰጠት የሚችለው ከ5 መቶ ካሬ ሜትር መብለጥ ስለሌለበት ለመኪና ማጣቢያ የሚሆን ከ5 መቶ ካሬ ሜትር ለክተው እና ሸንሽነው ሄዱ።የቦታውን ተከትሎ ካርታውን ለመውሰድ የክፍለ ከተማውን መሬት አስተዳደር መጠባበቅ ያዙ።
ይህ በእንዲህ እያለ ከፍተኛ የገንዘብ ወጪ የወጣበት ውሃን ሪሳይክል የሚያደርግ መሣሪያ በመኪና ማጠቢያ ቦታቸው ተከሉ።«ሪሳይክል »ማድረጊያው ማሽን አንድ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለን ውሃ ለ37 ጊዜ መጠቀም የሚያስችል ነው ።
ከመኪና ማጠቢያው አጎራባች በአዲስ አበባ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ እና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን የሚተዳደረው ቦታ ይገኛል።ይህን ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ እና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን የሚተዳደረው ቦታ ሪሳይክል በሚደረገው ውሃ አጠቃላይ የሆነ ስነ ምህዳር ለችግር ያደርሳል በሚል እሳቤ የአካባቢ ጥበቃ ኮሚሽኑ የመኪና ማጠቢያው መሬት የኔ ነው የሚል ጥያቄ አነሳ።
ይህን ተከትሎ አቤቱታ አቅራቢው በአዲስ አበባ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ እና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን ጋር ሪሳይክል የሚደረገውን ውሃ ጉዳት መጠን ለመገምግም ያስችል ዘንድ በየጊዜው የሚታደስ ውል ለመግባት ተገደደ።
ውሉ በሠራተኛ ሰውነት እና በመኪናዎች አካል ላይ እንዲሁም በአካባቢው አጠቃላይ ሁኔታ ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ እየታየ እና ሪሳይክል የሚሆነውን ውሀ እየመረመሩ ፈቃዳችን እንዲታደስ የሚል ነው። ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ያለን ግንኙነት ይህ ነው ።
ይሁን እንጂ ከሰባት ዓመት በፊት የአካባቢ ጥበቃ ኮሚሽን መሬቱ የእኔ ነው በማለት ክስ ጀምሮ ነበር።በዚህ ክርክር መሬቱ የእነሱ ስለመሆኑ በፍርድ ቤት ተከራክረው የአካባቢ ጥበቃ ኮሚሽን መሸነፉን አቤቱታ አቅራቢው ይናገራሉ።በ2012 ዓ.ም የተወሰነው ውሳኔ መሬቱ የአቤቱታ አቅራቢው ስለመሆኑ እና የፍርድ ቤት ውሳኔ በእጃቸው እንደሚገኝም ይገልጻሉ ።
በክርክሩ ወቅት እና ከክርክሩ በኋላ የአካባቢ ጥበቃ ኮሚሽን ለንግድ እና ኢንዱስትሪ በጻፈው ደብዳቤ መሠረት የመኪና እጥበቱ ንግድ ፈቃዱ እንዳይታደስ ከለከለ።ለሰባት ዓመት ያህልም የንግድ ፈቃዱ ሳይታደስ እንዲቆይ ተደረገ።ይህ በእንዲህ እንዳለ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ደግሞ ንግድ ፈቃድ ሳይኖርህ መሥራት አትችልም ብሎ ከለከለ።በዚህም ሁከት ይወገድልኝ በማለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን እና የጉለሌ ክፍለ ከተማን የአካባቢ ጥበቃን ኮሚሽን እና የጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት አስተዳደርን በአንድ ላይ አጣምረው ከሰሱ።በመጨረሻም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃን እና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን የመኪና እጥበት የሚካሄድበትን ቦታ የአካባቢ ጥበቃ የማያስተዳድረው « ከግሪን ኤርያ» ውጪ መሆኑን መርምሮ ንግድ ፍቃዱን አድሱለት ብሎ ለንግድ እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ጻፈ።
ከብዙ የይገባኛል ክርክር በኋላ የንግድ ፈቃዱ እንዲታደስ የሆነበት ዋናው ምክንያት የአዲስ አበባ ከተማ የተቀናጀ የመሬት አስተዳደር መረጃ ማዕከል ቦታው « ከግሪን ኤርያ» ውጪ መሆኑን በማመላከቱ ነው ።
የተቀናጀ የመሬት አስተዳደር ማዕከል የሰጠውን መረጃ ተከትሎ ከደን አስተዳደር ውጭ በመሆኑ የአካባቢ ጥበቃ ኮሚሽን የመሬት ይገባኛል ክሱን ትቶት ነበር ።ሁከት ይወገድልኝ ፍርድ ከተፈረደ አራት ዓመቱ ነው ።
ነገር ግን በ18/4/2014 ዓ.ም የአላሰቡት ነገር ይገጥማቸዋል ።በሌሊት ከመኖሪያ ቤታቸው ተነስተው ወደ መኪና ማጠቢያ ቦታው ያመሩት አቤቱታ አቅራቢው የመሥሪያ ቦታቸው በሰዎች ተሞልቷል። ግማሾቹ የመኪና ማጠቢያ መሣሪያዎችን ይነቃቅላሉ።ግማሾቹ በግቢው የነበሩ የቤቶችን ጣሪያ ያፈርሳሉ።ከፊሉ ደግሞ የቡድን እና የግል የጦር መሣሪያ ይዘው ይታያሉ።
በሌሊት የመኪና ማጠቢያ ቦታቸውን የቡድን መሣሪያ በያዙ በርካታ የፌደራል ፖሊስ አባላት ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ በቁጥር ዘጠኝ እና በርካታ የደንብ ማስከበር ቡድን ተከቦ ሲመለከቱ አቤቱታ አቅራቢው መጀመሪያ ላይ ወቅቱ ሃገሪቱ በተለያዩ የጥፋት ቡድኖች የምትፈተንበት አደገኛ ጊዜ ስለነበር እና ኮማንድ ፖስትም የታወጀበት ወቅት ስለነበር እና የመኪና ማጠቢያው ከጫካ ስር እንደመሆኑ መጠን የጥፋት ኃይሎች በማጠቢያ ቦታ ተደብቀው የተገኙ መስሎአቸው እንደነበር ያስረዳሉ።
ነገር ግን ተጠግተው ጉዳዩን ባጣሩ ጊዜ የቡድን መሣሪያ የታጠቀው የፌደራል ፖሊስ አባላት ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ እና በርካታ የደንብ ማስከበር ቡድን በጉለሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 7 ሥራ አስፈጻሚ የሚመራ የመኪና ማጠቢያ ቦታቸውን የሚያፈርስ ግብረ ኃይል ነበር፡፡ግብረ ኃይሉም ብዛት ንብረት የያዘን ቤት ጣራ በማፍረስ የመኪና ማጠቢያ ቦታውን መውጫ እና መግቢያ ከጣራው ባፈረሱት ቆርቆሮ አጥር ሠርተው ዘጉ ።የሠሩትን አጥርም አሸጉ። የታሸገውን ቤት በራሳቸው ማስጠበቅ ሲገባቸው እነሱ አፍርሰው ሲያበቁ የፈረሰውን ቤት አቤቱታ አቅራቢውን ዘበኛ ቀጥሮ እንዲያስጠበቅ አደረጉ።
አቤቱታ አቅራቢው ለምን የመሥሪያ ቦታቸው እየፈረሰ እንዳለ የግብር ኃይሉን መሪ እና የወረዳ 7 ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ወይዘሮ ደራርቱ ኦላናን ይጠይቃሉ።ወይዘሮ ደራርቱም መሬቱ የመንግሥት እንደሆነ እና ፍርድ ቤትም ይህንኑ ስላረጋገጠ ቦታውን ወደ መንግሥት ይዞታነት ለመመለስ የሚደረግ አስተዳደራዊ እርምጃ መሆኑን ይነግሯቸዋል።
ወረዳው ትክክለኛ የሕግ መሠረት አለን የሚል ከሆነ እና የመኪና ማጠቢያ ቦታው በሕገወጥ መንገድ የያዝነው መሆኑ ካረጋገጠ ሕገወጥ ስለመሆናችን ተነግሮን እና የወረዳው ማህተም ያረፈበት ቁጥር ያለው ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ሊሰጠን ይገባ ነበር ።ማህተምም ሆነ ቁጥር የሌለው ደብዳቤ እንኳን ባይሰጡን በቃል ማስጠንቀቂያ ሊሰጡን ይገባ ነበር ። ነገር ግን ምንም አይነት ማስጠንቀቂያ ባልተሰጠበት ሁኔታ በሃገሪቱ የታወጀውን የኮማንድ ፖስት ሽፋን በማድረግ የቡድን መሣሪያ በታጠቁ ኃይሎች ትብብር በብዙ ሺህ ገንዘብ ወጭ ተደርጎ የተገዙ ንብረቶች እንዲቃጠሉ እና ጉዳት እንዲደርስባቸው ተደርጓል ሲሉ አቤቱ አቅራቢው ይናገራሉ።
የፍርድ ቤት አፈጻጸም ነው እየሠራነው ያለው ካሉኝ በደብዳቤ በሰላሳ ደቂቃ ወይም በሰላሳ ቀን ልቀቁ ብሎ ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል።ግን ያን አላደረጉም ። ወረዳው እንደመከራከሪያ ያቀረበው የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሁከት የለም እንጂ የሚለው ቤቱን ሰብራችሁ እና ጣራውን ገንጥላችሁ አጥር በመሥራት አሽጉ አይልም።
ድርጅቱ በወረዳ ሥራ አስፈጻሚዎች ከመውደሙ በፊት 180 ቋሚ እና 20 ደግሞ ኮንትራት ሠራተኞች ነበሩት የሚሉት አቤቱታ አቅራቢው ፤ 180 የሚሆኑት ግብር እና የጡረታ ክፍያ ይከፍሉ የነበሩ እና የቤተሰብ አስተዳዳሪም መሆናቸውን ይገልጻሉ ።
በጉለሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 7 ዋና ሥራ አስፈጻሚ ምላሽ
በጉለሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 7 ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ደራርቱ ኦሊቃ ይባላሉ።የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ከአቶ ስንታየሁ የመኪና ማጠቢያ ቦታ ጋር ተያይዞ ስለተወሰደው እርምጃ ሰነዶችን እና መመሪያዎችን እያጣቀሰ ከወረዳው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ደራረቱ ኦላና ጋር ሰፋ ያሉ ውይይቶችን እና ክርክሮችን አድርጓል።የተደረጉ ውይይቶችን እና ክርክሮችን በጥልቀት አንብቦ የኢትዮጵያ ሕዝብ የራሱን ፍርድ ይስጥ ብለናል።
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል በጉለሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 7 ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑትን ወይዘሮ ደራርቱን ስለጉዳዩ ያውቁ እንደሆነ ጠየቀ።ዋና ሥራ አስፈጻሚዋም ስለጉዳዩ በጥልቀት እንደሚያውቁ ገልጸው፤ አቶ ስንታየሁ አየለ የተባሉት ግለሰብ አንድ መኪናን ለማጠብ የተጠቀሙበትን ውሃን መላልሶ በመጠቀም መኪናን ማጠብ እንደሚችሉ ለጉለሌ ክፍለ ከተማ አካባቢ ጥበቃ እና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን ፕሮፖዛል ያስገባሉ።በዚህም ለጉለሌ ክፍለ ከተማ አካባቢ ጥበቃ እና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን ከሚያስተዳድረው መሬት ሁለት መቶ ካሬ ሜትር የሚሆንን ቦታ በጊዜያዊነት ሰጥቶት እንዲሠሩ ተደርጎ ነበር ።በጊዜያዊነት ማለት ዛሬም ሆነ ነገ ልቀቅ ማለት እንደሚቻል ይታወቃል ።
ይሁን እንጂ ግለሰቡ በጊዜያዊነት ከተሰጠው ቦታ በተጨማሪ ያለ አግባብ መሬቱን በማስፋፋት ያዘ።የአካባቢ ጥበቃ ይህንንም ሕገወጥ መስፋፋት እየተመለከተም ቢሆን በጊዜያዊነት እየተዋዋለ የመኪና ማጠቡን ሥራ እንዲሠራ ፈቅዶለት ቆይቷል።
አቶ ስንታየሁ የተባለው ግለሰብ ከተዋዋለበት መሬት ውጭ በራሱ ፈቃድ የማንንም ፈቃድ ሳይጠይቅ በሕገ ወጥ መልኩ 3274.6 ካሬ ሜትር ላይ አድርሶታል። መሬትን ሕገወጥነት እየወረረ ያለ አግባብ ይዞታውን ሲያስፋፋ ቆይቷል።
ይህ ሆኖ ሳለ የአካባቢ ጥበቃ ለምን ከተፈቀደልህ ውጭ ቦታ አስፋፍተህ ትይዛለህ ብሎ ሲጠይቀው እና የመንግሥትን መሬት ወደ ግሉ ለማዞር የወረዳ አመራሮችን በማጭበርበር ካርታ ፕሮሰስ ለማሠራት ሲሞክር በመታወቁ እና ከድርጊቱ እንዲቆጠብ ሲጠየቅ ግለሰቡ በራሱ ተነሳስቶ በ2011 ዓ.ም ፍርድ ቤት ሄዶ የአካባቢ ጥበቃን ከሰሰ።ክሱ ሁከት ይወገድልኝ የሚል ነበር ።
ሁከት ይወገድልኝ የሚለውን እግድ ሲያመጣ እግዱን የጻፈው ፍርድ ቤት ስለሆነ እና ሕግ መከበር ስላለበት የፍርድ ቤት ውሳኔ እስከሚሰጥበት ድረስ አቶ ስንታየሁ ሥራውን እየሠራበት ቆይቷል።በዚህም ክርክሩ እስከ ሰበር ሂዶ ነበር ።በፍርድ ቤት ክርክሩም የአካባቢ እንክብካቤ ኮሚሽን እንቅስቃሴ ሕግን ለማስከበር እንጂ ሁከት አይደለም ሲል በ2012 ዓ.ም 9ኛ ወር ውሳኔ አስተላልፏል ሲሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚያዋ ያስረዳሉ ።
ይህን ተከትሎ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ሁከት ይወገድልኝ ብሎ መጠየቅ እና በፍርድ ቤት ሁከት የለም በመባሉ መሬቱ የአንተ ስላልሆነ ለቀህ ውጣ ሊያስብል ይችላል? ሲል ዋና ሥራ አስፈጻሚዋን ጠየቀ። ዋና ሥራ አስፈጻሚዋም አዎ! ሁከት የለም ከተባለ መሬቱ የመንግሥት ነው ማለት ነው። ስለሆነም ቦታውን ልቀቅ ማለት እንችላለን ሲሉ መለሱ።
የወረዳችሁ በፕሮሰስ ካውንስል መሬቱ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ እንደተያዘ እና በ2006 ዓ.ም ከሰነድ አልባ መሬት ጋር ተያይዞ በወጣው መመሪያ መሠረት ወረዳው ለአቤቱታ አቅራቢው ካርታ እንዲሠራለት በኮሚቴ ተወስኖለታል ።እዚህ ላይ የአካባቢ ጥበቃ ነው የተዋዋለው ከሚለው ጋር አይጋጭም ? ስለዚህ ላይ ምን ይላሉ ? ሲል የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ዋና ሥራ አስፈጻሚዋን ጠየቀ።ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ እኛ እያስፈጸምን ያለነው የፍርድ ቤት ውሳኔን ነው ።የወረዳውን የፕሮሰስ ካውንስል ውሳኔ አይደለም ።ፍርድ ቤት መሬቱ የአካባቢ ጥበቃ እንደሆነ ወስኗል።እኛ ደግሞ በውሳኔው መሠረት ውሳኔውን እናስፈጽማለን ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ይህን ተከትሎ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል የአካባቢ ጥበቃ የእኔ ነው ሳይል እንዴት የወረዳው ሥራ አስፈጻሚ የአካባቢ ጥበቃ ነው ሊል ቻለ ሲል የአካባቢ ጥበቃ ለአቶ ስንታየሁ የጻፈውን ደብዳቤ ባሳየ ጊዜ የወረዳው ዋና ሥራ አስፈጻሚ መረጃ ከፈለክ እኔ የምልህን አዳምጥ እንጂ አትከራከረኝ ሲሉ መለሱ።እኛም መረጃው እንዳይቋረጥ በማሰብ ክርክሩን አቁመን እርሳቸውም ማዳመጡን ቀጠልን።እኛ ተፈጻሚ እያደረግን ያለነው ፍርድ ቤት ቦታውን ለቆ እንዲወጣ ያዘዘውን ውሳኔ ነው ።የፍርድ ቤት ውሳኔ ተፈጻሚ መደረግ አለበት ።ይህን ተፈጻሚ ለማድረግ ደግሞ ግብር ኃይል በሕግ የተሰጠ መብት አለው ።አሁንም ደግሜ እናገራለሁ ቦታው አሁንም የአካባቢ ጥበቃ ነው ።የአካባቢ ጥበቃም በ2013 ዓ.ም ቦታው በ10 ቀናት ውስጥ ጸድቆ ወደ መንግሥት እንዲመለስ ጠይቀዋል ሲሉ ቀድመውን ሃሳባቸውን ንዴት በተሞላበት አኳኋን ደገሙልን።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ እና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን በቁጥር 203/20-01/2793 በቀን 9/8/2011 ዓ.ም ለአቶ ስንታየሁ በጻፈው ደብዳቤ እንዳመለከተው በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት ድል በር ወደ እግዚአብሄር አብ በሚወስደው መንገድ ወንዝ ዳርቻ አጠገብ በሚገኘው የመኪና እጥበት አገልግሎት እየሠሩ ባለበት ቦታ በውል የተሰጠዎት ፈቃድ መቆረጥ እና የንግድ ምዝገባ ፍቃድ ለጊዜው በመታገዱ ምክንያት ይህ ትዕዛዝ እንዲነሳልዎት በ01/8/2011 ዓ.ም አቤቱታ አቅርበዋል።
ሆኖም መሥሪያ ቤታችን ከተሰጠው ስልጣን እና ኃላፊነት እየሠሩበት ያለው ይዞታ የአረንጓዴ ክልል ውጪ በመሆኑ በይዞታው የማስተዳደርም ሆነ ፈቃድ የመስጠት ስልጣን እና ኃላፊነት የሌለን መሆኑን እያሳወቅን ነገር ግን በጉድጓድ ውሃ እና ለሥራው ከሌላ ቦታ ውሃ በማምጣት ተጠቅመው በድጋሚ በሪሳይክል በማጣራት የሚያከናውኑ ከሆነ ፕሮጀክቱ በአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ (ዒአይ ዔ) በኩል ማለፍ ስላለበት ይህንን አሟልተው ሲመጡ አገልግሎት የምንሰጥዎት መሆኑን እንገልጻለን ።ግልባጭ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ፣ ለጉለሌ ክፍለ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ፣ ለጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ንዑስ አረንጓዴ ልማት ጽሕፈት ቤት እና ለጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት ፍትህ ጽሕፈት ቤት ይላል።ስለዚህ ምን ይላሉ? ስንል ዋና ሥራ አስፈጻሚዋን ጠየቀን ።
ወይዘሮ ደራርቱም ደብዳቤውን ለእኛ ስላልተጻፈልን አናውቀውም ።ግለሰብ ነው የጻፈው ! ግለሰብ የጻፈው ደግሞ ተቀባይነት የለውም ።ግለሰብ ቢጽፈውስ ሕጋዊ የሆነ ማህተም እና ቁጥር እያለው እንዴት ተቀባይነት አይኖረውም? ሲል አዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ጠየቀ። ወይዘሮ ደራርቱም በንዴት ደብዳቤው ለእኛ ስላልተሰጠ እና ስለማናውቀው ተቀባይነት የለውም ሲሉ የቀደመ መልሳቸውን ደገሙ። ይህን ደብዳቤ የጻፈው አካል በሕግ ይጠየቃል ሲሉም አከሉ።
የአካባቢ ጥበቃ በቁጥ196/18-01/2519 በቀን 11/06/ 2012 ዓ.ም በጉለሌ ክፍለ ከተማ ለወረዳ 7 ንግድ እና ኢንዱስትሪ ጽሕፈት ቤት በጻፈው ደብዳቤ እንዳመላከተው የአካባቢ ጥበቃ ላልተወሰነ ጊዜ የአቶ ስንታየሁ የንግድ ፈቃድ እንዳይታደስ እንደከለከለ ነገር ግን ከላይ በተገለጸው ቀን ጀምሮ እንዳይታደስ የሚለው ክልከላ እንዲነሳ መጻፉን ያትታል፡፡ስለዚህ ምን ይላሉ? ሲል አዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል የወረዳውን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጠየቀ።
ወይዘሮ ደራርቱም ከመጀመሪያውም ንግድ ፍቃድ እንዳያድስ አልተከለከለም ሲሉ ይናገራሉ።አንባቢያን እዚህ ላይ ፍርዱን ለእናንተው ትቻለሁ።እኛ የምናውቀው ፍርድ ቤት የወሰነውን ውሳኔ ብቻ ነው ።ይህን ደብዳቤ የጻፈው አካል ራሱ ይጠየቃል ሲሉ ተናገሩ።
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ቤቱን ለማሸግ ስትሄዱ ለምን በሌሊት መሄድ አስፈለገ? ሲል ሥራ አስፈጻሚዋን ጠየቀ ። ዋና ስራ አስፈጻሚዋም በግብር ኃይል ስለሆነ ነው የሚል ምላሽ ሰጡ።
የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም በግብረ ኃይልስ ቢሆን ለምን በሌሊት ሄዳችሁ ታፈርሳላችሁ? ሲል ጥያቄውን ደግሞ ጠየቀ ። ዋና ሥራ አስፈጻሚዋም በግብር ኃይል የሚፈርስ ቤት በማንኛውም ሰዓት መሄድ ይቻላል ሲሉ መለሱ።
ይህን ተከትሎ አዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም በፈለጋችሁት ሰዓት ሂዳችሁ ማፍረስ ይችላል የሚል መመሪያ አለ? ሲል ጠየቀ።ወይዘሮ ደራርቱም በከፍተኛ ብስጭት ግብረ ኃይሉ አስተዳደራዊ ለሆነ እርምጃ በማንኛውም ሰዓት መሄድ ይችላል በማለት ገለጹ።
እንደዚህ የሚል መመሪያ ሊያሳዩኝ ይችላሉ ? ሲል የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ዋና ሥራ አስፈጻሚዋን ጠየቀ።
ወይዘሮ ደራርቱም በንዴት በማንኛውም ሰዓት እርምጃ መውሰድ አይቻልም የሚል መመሪያ ታሳየናለህ ሲሉ ጥያቄውን በጥያቄ መለሱ።
አዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም በ2006 ዓ.ም የወጣው አዋጅ መመሪያ እንደሚያሳየው ሕጋዊ የንግድ ፈቃድ ያለውን አንድ አካል ማግኘት እና ማነጋገር የሚፈልግ የመንግሥት አካል ማናገር የፈለገውን ሰው ማናገር የሚችለው በሥራ ሰዓት ብቻ ነው ።ለዚያውም ባጅ አድርጎ ይላል፤ ሲል መለሰ።
ይህን ተከትሎ ወይዘሮ ደራርቱ ከላይ በፈለገን ሰዓት መሄድ እንችላለን የሚለውን አቋማቸውን ትተው እኛ በሥራ ሰዓት ነው የሄድነው የሚል ምላሽ ሰጡን ።እዚህ ላይ ፍርዱን ለሕዝብ ትቸዋለሁ።
ሌላው የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ለሥራ አስፈጻሚያ ያቀረበው ጥያቄ አቶ ስንታየሁ የተባለው ግለሰብ ሕገ ወጥ እንኳን ቢሆን እና እርምጃ ይወሰድ ቢባል የሕገ ወጡን ሰው ቤት ጣራ አፍርሳችሁ አጥር በመሥራት በሠራችሁት አጥር ላይ አሽጋችሁ ሂዱ የሚል መመሪያ አለ? እናንተ ያደረጋችሁት ይሄንን ነው ።ስለዚህ ምን ይላሉ የሚል ጥያቄ ነበር ።
ወይዘሮ ደራርቱም ቦታው በሕገወጥ መልኩ ከተያዘ እና በሕገወጥ መልኩ የያዘው አካል በፍርድ ቤት እንዲለቅ ከተወሰነ ንብረቱን ጭኖ እስከመሄድ እና እስከመውረስ የሚደርስ እርምጃ ይወሰዳል።ይህን ተከትሎ አዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ሕገ ወጥ ከሆነ ቤቱን አፍርሶ እቃውን ጭኖ መውሰድ እንደሚቻል ዝግጅት ክፍሉ ይገነዘባል።የዝግጅት ክፍሉ ጥያቄ ግን ሕገወጥ ከሆነ የሕገወጡን ሰው ንብረት በማፍረስ ጭኖ መውስድ አንድ ነገር ሆኖ እያለ የሰውየውን ጣራ አፍርሳችሁ አጥር በመሥራት አሽጉ የሚል ሕግ አለ ወይ ነው ? ወይዘሮ ደራርቱም ሕገ ወጥ ከሆነ ንብረቱም ይወሰዳል።ጣሪያ ግን አላፈረስንም ሲሉ መለሱ። ወረዳው ጣሪያ አፍርሶ አጥር ማጠሩን ዝግጅት ክፍሉ በአካል ተገኝቶ አረጋግጧል።እዚህ ላይ ፍርዱን ለአንባቢያን ትተነዋል።
ሌላው አዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ለሥራ አስፈጻሚዋ ያቀረበው ጥያቄ የአሸጋችሁበት ደብዳቤ ማህተም የለውም ።እንዲታሸግ የወሰነው አካል እና ሲታሸግ የነበሩ ታዛቢዎችም ስም እና ፊርማ የለበትም ስለዚህ ምን ይላሉ? የሚል ነው። ለዚህ ጥያቄ ወይዘሮ ደራርቱ የታሸገበት ደብዳቤ ማህተም አለው የሚል ምላሽ ሰጥዋል።
ይህን ተከትሎ በማሸጊያ ወረቀቱ ላይ እዚያም እዚህም እንዲሁ ስማቸው ያልተገለጸ ነገር ግን ፊርማቸው ብቻ የተቀመጠ ሰዎች አሉ። ይህ ወረቀቱ ላይ ያለው ፊርማ የእናንተ አይደለም? ሲል ጠየቀ።ወይዘሮ ደራርቱ እሱን እኔ ፎረንሲክ መርማሪ አይደለሁም እሱን ማረጋገጥ አልችልም ሲሉ መልሰዋል።
አዲስ ዘመን በፕሮሰስ ካውንስል የተወሰነው ውሳኔ ስህተት ነው ይላሉ? ሲል ወይዘሮ ደራርቱን ጠይቆ ነበር ።ወይዘሮ ደራርቱም ወረዳ ወይስ ክፍለ ከተማ ፕሮሰስ ካውንስል ሲሉ ጥያቄን በጥያቄ መለሱ ።የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም በወረዳው የታየውን ሲል መለሰ።ይህን ተከትሎ ወይዘሮ ደራርቱ ስለመሬቱ በወረዳው የፕሮሰስ ካውንስል አልታየም ሲሉ መለሱ።አዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም በቀን 16/07/2007 ዓ.ም በወረዳ ደረጃ አስራ አንድ የወረዳ አመራሮች የወሰኑትን ውሳኔ አያውቁትም ? ሲል ጠየቀ።ወይዘሮ ደራርቱም እኛ የወረዳውን እና የክፍለ ከተማ ፕሮሰስ ካውንስል የወሰነውን አልመረመርንም።እኛ የምናስፈጽመው የፍርድ ቤትን ውሳኔ ነው በማለት መለሱ።
ፍርድ ቤት ሲወስን የፕሮሰስ ካውንስል የሥራ ክንውኖችንም መሠረት ማድረጉ የማይቀር ነው ። ስለዚህ ምን ይላሉ ሲል የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል የጠየቃቸው ወይዘሮ ደራርቱ ፤ ከፍርድ ቤት ውሳኔ ውጭ ስለፕሮሰስ ካውንስሉ አይመለከተንም።እኛ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ብቻ ነው ተፈጻሚ የምናደርገው ሲሉ መለሱ።
በመጨረሻም የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል የሚጠይቃቸው ጥያቄች ያበሳጫቸው ወይዘሮ ደራርቱ የጋዜጠኛውን የድምጽ መቅጃ ወረወሩ።መረጃ የሰጠንህ እኛ ቀና ሰለሆንን ነው ! የሚል ንዴት የተሞላበት ቃል ተናገሩ።ነገር ግን ቅን ስለሆኑ ሳይሆን መረጃ መስጠት ስላለባቸው እንደሆነ ሊገነዘቡ ይገባል፡፡
ጥያቄ መጠየቃቸው ያንገበገባቸው ወይዘሮ ደራርቱ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል በጠየቃቸው በበነጋታው አጥር ሠርተው አሽገውት የነበረውን የአቤቱታ አቅራቢ ሙሉ እቃ በፌደራል ፖሊስ ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ እንዲሁም ደንብ ማስከበር ታግዘው ጭነው ሲወስዱ በቦታው በመገኘት የፎቶ ምስል ማስቀረት ችሏል።
ይህንን ጉዳይ በተመለከተ መረጃ እንዲሰጡን የጉለሌ ክፍለከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚን በደብዳቤ ጠይቀን በሰጡን የደብዳቤ ምላሽ ቅሬታ አቅራቢው ከገቡት ቃል ውጪ የአካባቢውን ምህዳር በመቀየርና ባልተገባ መንገድ ከመንግሥት በጊዜያዊነት ለሥራ የተሰጣቸውን ቦታ በግል ይዞታነት በሥማቸው ካርታ ለማውጣት ባደረጉት ጥረት ከሕገወጥ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ቢነገራቸውም ከመታረም ይልቅ ሁከት ተፈጠረብኝ በማለት በአስተዳደሩ ላይ ክስ ቢመሰርቱም የፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 237477 በቀን 15/05/2011 ዓ/ም የከፍተኛ ፍርድቤት በመዝገብ ቁጥር 230647 በቀን 6/08/2011 ዓ/ም የሰበር ሰሚ ፍርድቤት በሰበር ሰሚ መዝገብ 176497 በቀን 28/08/2014 ዓ/ም በአስተዳደሩ የተፈጠረ ሁከት የለም ሲል ውሳኔ በመስጠቱ ይግባኝ ሰሚው ፍርድቤትም ሆነ የሰበር ሰሚው ውሳኔ ይሄንን በማጽናቱ እንዲሁም የተሰጠው የእግድ ትዕዛዝ በመነሳቱ የወረዳው አስተዳደር ርምጃ መውሰዱን የሚገልጽ ምላሽ ሰጥተዋል።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 19 /2014