የዚህ ሰው ነገር ይገርማል! አስገራሚነቱ ከውልደቱ ይጀምራል። የተወለደው በዕለተ መስቀል መስከረም 17 ቀን 1933 ዓ.ም ነው። ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ደግሞ የፋሲካ በዓል ዕለት ሚያዝያ 11 ቀን 2001 ዓ.ም ነው። የዚያን ዓመት የፋሲካ በዓል በሀዘን ድባብ የተዋጠ እንዲሆን አድርጎታል። በዘፈኑ ደግሞ በዓላትን ሲያደምቅ ኖሯል። በሕያው ሥራው የወደፊት በዓላትንም ያደምቃል። ይህ ሰው የሙዚቃው ንጉሥ የክብር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ነው።
ጥላሁን ገሠሠ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ከ13 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሚያዚያ 11 ቀን 2001 ዓ.ም በፋሲካ በዓል ነው። የፋሲካ በዓል ቀኑ ስለሚቀያየር በዓመቱ ሚያዚያ 11 አይሆንም። የ2001 ዓ.ም የፋሲካ በዓል በጥላሁን ገሠሠ ሞት ሀዘንም ይታወሳል። ያም ሆኖ ግን የጀግና ሞት ሀዘን አይደለምና መገናኛ ብዙኃንን ለአንድ ሳምንት ያህል በአንድ ጉዳይ ብቻ አድምቆ ይዞ ቆይቷል። ሥርዓተ ቀብሩም የተፈጸመው ለሳምንት ያህል ሰፊ ሽፋን ከተሰጠው በኋላ ነው።
የ13ኛ ዓመት የጥላሁን ገሠሠን የሙት ዓመት መታሰቢያ ምክንያት በማድረግ ከሕይወትና ሥራዎቹ ጥቂቶቹን እናስታውስ።
ጥላሁን ገሠሠ ከእናቱ ከወይዘሮ ጌጤ ጉሩሙ እና ከአባቱ ከአቶ ገሠሠ ንጉሤ በአዲስ አበባ ልዩ ስሙ ጠመንጃ ያዥ እየተባለ ከሚጠራው ሰፈር መስከረም 17 ቀን 1933 ዓ.ም የመስቀል ዕለት ተወለደ። ዕድሜው 14 ዓመት እንደሆነ ከአያቱ ጋር እንዲኖር ወደ ወሊሶ ተወሰደ፤ ራስ ጎበና በሚባለው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርት ጀመረ።
በትምህርት ቤት ሳለ፤ ጥላሁን ከፍተኛ የሆነ የሙዚቃ ፍቅር እያሳየ መጣ። አያቱ ግን ትኩረቱን በሙሉ በትምህርቱ ላይ እንዲያደርግ ይመክሩት ነበር። የራስ ጎበና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስተዳዳሪ የነበሩት ሱዳናዊው አቶ ሼዳድ ደግሞ የጥላሁንን የሙዚቃ ፍቅር በማየት ወደ ሱዳን እንዲሄድና በዚያም ሙዚቃ እንዲያጠና ይመክሩት ነበር። ጥላሁን ወደ ሱዳን ባይሄድም ምክራቸውን ግን ትልቅ ቦታ ሰጥቶት ነበር።
ከሀገር ፍቅር ቲያትር ንጋቷ ከልካይ እና ኢዮኤል ዮሐንስ ሌሎችም የሀገር ፍቅር ተዋንያን በትምህርት ቤታቸው ትርኢት ሊያሳዩ በመጡ ጊዜ፤ ይህን እድል በመጠቀም ጥላሁን ለሙዚቃ ያለውን ፍቅር ከኢዮኤል ጋር ባደረገው ውይይት በሙዚቃ መግፋት ከፈለገ ወደ አዲስ አበባ መሄድ እንዳለበት መከሩት። ጥላሁን ትምህርቱን አቋርጦ ጉዞውን ወደ አዲስ አበባ አቀና። ኩብለላውን በእግር የጀመረው ለአያቱ ሳይነግር ስለነበር ከቤት ሲጠፋ አያቱ ለአጎቱ ሁኔታውን በመንገር ጥላሁንን ይጠብቁ ጀመር። ጥላሁንም የአሥራ አምስት ኪሎ ሜትር መንገዱን ጨርሶ ቱሉ ቦሎ ደረሰ፤ ከዚያም ከአክስቱ ከወይዘሮ ተመኔ ባንቱ ቤት አድሮ ወደመጣበት ወደ ወሊሶ አያቱ ዘንድ ተይዞ ተመለሰ።
በሙዚቃ ፍቅር በጣም የተቃጠለው ጥላሁን አያቱ ቤት አንድ ቀን ብቻ በማደር ጉዞውን እንደገና ወደ አዲስ አበባ አቀና፤ በዚህ ጊዜ ግን በጭነት መኪና ላይ በመንጠልጠል ነበር። ጥላሁን አዲስ አበባ እንደገባ በሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ተቀጠረ። በዚያም ጥቂት አመታት ከሰራ በኋላ ወደ ክብር ዘበኛ ባንድ በመቀላቀል እነሆ ታዋቂና ዝነኛ ለመሆን በቃ።
በ1953 ዓ.ም የታኅሣሥ ግርግር ትልቅ ችግር ውስጥ ወድቆ ነበር። ለጥቂት ጊዜም ታስሮ ተፈቷል። ከዚያም ወደ ቀድሞው ሀገር ፍቅር በመመለስ ተወዳጅና ታዋቂ ለመሆን በቅቷል። ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ሀገር ፍቅር ቲያትር ቤትን በጎበኙበት ጊዜ ሦስት ጊዜ ወጥቶ ዘፍኗል፤ ንጉሠ ነገሥቱም ‹‹ጥሩ ድምጽ አለህ፤ እንዳታበላሸው›› የሚል አስተያየትም እንደሰጡት ይነገራል።
ከጥላሁን ዘፈኖች አብዛኞቹ የአማርኛ ሲሆኑ፤ የተወሰኑ ዘፈኖችን ደግሞ በኦሮምኛ እና በሱዳንኛ ዘፍኗል። ጥላሁን ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ላደረገው አስተዋጽኦ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ተሰጥቶታል። ከኢትዮጵያ ኪነጥበብና የብዙሃን መገናኛ ሽልማት ድርጅት የሙሉ ዘመን ሽልማት ተሸላሚ ሆኗል። ጥላሁን በዜማዎቹ ሁሌም የሚታወስ ስለመሆኑ ‹‹ ተቀርጾ ትንፋሼ›› ከተሰኘው ዜማው ግጥሞች የተወሰኑ ስንኞችን ወስዶ መመልከት ይቻላል።
ትንፋሼ ተቀርጾ ይቀመጥ ማልቀሻ
ይህ ነው የሞትኩኝለት የኔ ማስታወሻ
ውበቷን ሳሞግስ የለምለም አገሬን
ማንም አይዘነጋም በጩኸት መኖሬን!
ዜማ እንጉርጉሮዬም የግሌ ቅላጼ
ተቀርጾ ይቀመጥ ታሪኬ ነው ድምጼ
ያስቀየምኩት ቢኖር የጠላኝ በቁሜ
ድምጼን ሰምቶ ያዝናል ለረገፈው አጽሜ
እኔን ለበደሉኝ ሰርዣለሁ ቂሜን
በኔም የከፋችሁ ይቅር በሉት አጽሜን!
ጽሁፉን ስናዘጋጅ ዘካርያ መሀመድ ‹‹ጥላሁን ገሰሰ የሕይወቱ ታሪክና ምስጢር›› በሚል የጻፉትን መጽሐፍና የተለያዩ ድረ ገጾችን በምንጭነት ተጠቅመናል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16 ቀን 2014 ዓ.ም