ከልጅነቱ ጀምሮ ጎበዝ ተማሪ ነበር። በ1948 ዓ.ም ከተግባረ ዕድ ትምህርት ቤት ሲመረቅ አንደኛ በመውጣት የከፍተኛ ማዕረግ ተሸላሚ ሆኖ ነው። የከፍተኛ ውጤት ባለቤት በመሆኑ በዚያው በተግባረ ዕድ ትምህርት ቤት መምህር ሆኖ ተቀጠረ።
የውጭ መጻሕፍትንም ያነብ ስለነበር አስተርጓሚ ሆኖም ሰርቷል። ለጋዜጠኝነት ሙያ ልዩ ፍቅር ስለነበረው በተለያዩ ጋዜጦች በጋዜጠኝነት አገልግሏል። የአንጋፋውና ዕለታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ነበር። መምህር፣ ተርጓሚ፣ ጋዜጠኛ እና ደራሲ ብርሃኑ ዘሪሁን!
ብርሃኑ ዘሪሁን በስነ ጽሑፍ ሰዎች ዘንድ ካልሆነ በስተቀር ያተዘመረለት የብዙ ሙያ ባለቤት ነው። ይህን ሰው ያጣነው ከ35 ዓመታት በፊት በዛሬዋ ቀን ሚያዚያ 16 ቀን 1979 ዓ.ም ነው። እነሆ በዋና አዘጋጅነት ሲመራው የነበረው አዲስ ዘመን ጋዜጣ የዛሬ እትም የሳምንቱ በታሪክ አምድ ሕይወቱንና ሥራዎቹን ያስታውሳል።
ብርሃኑ የተወለደው በ1925 ዓ.ም ነው። አባቱ መሪጌታ ዘሪሁን መርሻ የቤተ-ክህነት ሊቅ ስለነበሩ ለልጃቸው ትምህርት የሚጨነቁ ነበሩ። እናም ልጃቸው በቤት ውስጥ በእርሳቸው የሚሰጠውን ጨምሮ የቤተ-ክህነት ትምህርት እንዲማር አድርገዋል።
የኢትዮጵያን ባሕላዊ፣ ታሪካዊና ሐይማኖታዊ ትምህርቶችን በቤተ ክህነት ትምህርት ከተከታተለ በኋላ ዘመናዊ ትምህርት ቤት ገባ። በዘመናዊ ትምህርት ቤትም ለንባብ ያለው ልዩ ፍቅርና የጽሑፍ ችሎታው መገለጥ ጀመረ።
ብርሃኑ ከልጅነቱ ጀምሮ ልዩ የማንበብ ፍቅር እንደነበረው የሚያውቁት ሁሉ ይመሰክሩለታል። መፅሐፍትን የሚያነብ ብቻ ሳይሆን እንደ ምግብም የሚጠቀምባቸው ዓይነት ሰው ነበር ይባላል። ጋዜጠኛና ጸሐፊ ጥበቡ በለጠ ስለብርሃኑ ዘሪሁን በሰንደቅ ጋዜጣ በፃፉት ጽሑፋቸው እንዳብራሩት፤ የብርሃኑን ቀልብ ከሳቡት ድርሳናት መካከል ዋነኞቹ ስለኢትዮጵያ ታሪክ የተፃፉት መጻሕፍት ናቸው።
ከነዚህም መካከል አለቃ ዘነብ የፃፏቸው ታሪኮች ይጠቀሳሉ። አለቃ ዘነብ በዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ቤተ መንግስት የዘመኑ ሊቅ ነበሩ። እርሳቸው የፃፉትና በዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ታሪክ ላይ ያተኮረው መጽሐፍ በብርሃኑ የሚወደድ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ብርሃኑ ‹‹መጽሐፈ ጨዋታ ስጋዊ ወመንፈሳዊ›› የተሰኘችውን፣ ሃይማኖት ላይ መሰረት አድርጋ የተዘጋጀችውንና ከኢትዮጵያ የፍልስፍና ጽሑፎች መካከል አንዷ ተደርጋ የምትቆጠረውን የአለቃ ዘነብን መጽሐፍ በተደጋጋሚ አንብቧታል። የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ፣ የክብር ዶክተር ከበደ ሚካኤል እና የነጋድራስ አፈወርቅ ገብረኢየሱስ መጻሕፍትም ለብርሃኑ የንባብ ፍቅርና እውቀት መሰረት እንደሆኑት ታሪኩ ያስረዳል።
ብርሃኑ በ1945 ዓ.ም ከተወለደባትና ብዙ እውቀትን ከገበየባት ጎንደር ከተማ ወደ አዲስ አበባ መጣ። በአዲስ አበባ ቆይታውም ተግባረ ዕድ ትምህርት ቤት ገብቶ የሬዲዮ ቴክኒሻንነት ሙያ በመማር በ1948 ዓ.ም ላይ በዲፕሎማ ተመረቀ። የተመረቀውም በትምህርቱ ከፍተኛውን ውጤት አስመዝግቦና አንደኛ ደረጃን በመያዝ ተሸላሚ ሆኖ ነው።
ብርሃኑ የተግባረ ዕድ ትምህርት ቤት ተማሪ በነበረበት ወቅት የታላላቅ የዓለማችንን ደራሲያን ስራዎችን ለማንበብ ዕድሉን አገኘ። የዊሊያም ሼክስፒርን፣ የአሌክሳንደር ዱማስ ፔሬን፣ የቻርልስ ዲከንስን፣ የአሌክሳንደር ፑሽኪንን እና የሌሎችን ስመጥር ደራሲያን መጻሕፍትን አነበበ። በዚህም የንባብ ልምዱን እያጎለበተና እውቀቱንም እያሳደገ መጣ። በዚህ ጊዜ ነበር የማንበብ ብቻ ሳይሆን የመፃፍም ችሎታ ያለው ብርሃኑ በንባብ የተከማቸውን እውቀቱን በጽሑፍ ማውጣት የጀመረው። እዚያው ተግባረ-ዕድ ትምህርት ቤት ሲማር የትምህርት ቤቱ ልሳን የነበረችውና ‹‹ቴክኒ-ኤኮ›› የተሰኘችው መፅሔት አዘጋጅ ሆኖ ሰርቷል።
ብርሃኑ ከተግባረ ዕድ ትምህርት ቤት ሲመረቅ ውጤቱ ከፍተኛ ስለነበር እዚያው በመምህርነት ተቀጠረ። ከማስተማር ስራው ባሻገር ለተለያዩ ጋዜጦች መጻፍ ጀመረ። ከተግባረ ዕድ ትምህርት ቤት በመልቀቅ በወቅቱ አጠራር የጦር ሚኒስቴር (የአሁኑ መከላከያ ሚኒስቴር) በሚባለው መስሪያ ቤት በአስተርጓሚነት ተቀጥሮ መስራት ጀመረ። እዚያም ብዙ ሳይቆይ በ1952 ዓ.ም ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ተዘዋወረ።
በማስታወቂያ ሚኒስቴርም ‹‹የኢትዮጵያ ድምጽ›› ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆነ። በወቅቱም ጋዜጣዋን ታዋቂ ከማድረጉም በላይ በብዙዎች ዘንድ የሚነበቡ መጣጥፎችንና ታሪኮችን በመፃፍ ዝነኛ እየሆነ መጣ። በመቀጠልም የ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆነ። ከዚህ በኋላ የብርሃኑ ስምና ዝና እየገነነ መጣ፤ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ልብም ውስጥ ገባ።
በኢትዮጵያ ስነጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ቦታ ሊሰጣቸው የሚገቡ ስራዎችን ካበረከቱ ደራሲያን አንዱ የሆነው ደራሲ፣ ጸሐፌ ተውኔት እና ጋዜጠኛ ብርሃኑ ዘሪሁን ከ1952 ዓ.ም ጀምሮ ከዚህ ዓለም በሞት እስከተለየበት 1979 ዓ.ም ድረስ 11 ልብወለድ ድርሰቶችንና ሦስት ተውኔቶችን ለተደራሲያኑ ያበረከተ ብዕረኛ ነው።
በ1952 ዓ.ም ‹‹የእንባ ደብዳቤዎች›› በተባለ ድርሰቱን ጉዞውን የጀመረው ብርሃኑ፤ ‹‹ድል ከሞት በኋላ››፣ ‹‹አማኑኤል ደርሶ መልስ››፣ ‹‹የበደል ፍጻሜ››፣ ‹‹ጨረቃ ስትወጣ›› እና ‹‹ብር አምባር ሰበረልዎ›› የተባሉትን ድርሰቶቹን አበርክቷል።
በተጨማሪም ‹‹የቴዎድሮስ እንባ›› እና ‹‹የታንጉት ምስጢር›› የተባሉ ሁለት ታሪካዊ ልብ ወለዶችንና በወሎ ክፍለ አገር ተከስቶ የነበረውን ድርቅና የመንግስትን ቢሮክራሲ ህያው አድርጎ የከተበባቸውን ‹‹ማዕበል የአብዮት ዋዜማ››፣ ‹‹ማዕበል የአብዮት መባቻ›› እና ‹‹ማዕበል የአብዮት ማግስት›› የተባሉ ሦስት ልብወለዶችን አስነብቧል። እነዚህ የማዕበል ድርሰቶቹ በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሶስት ተከታታይ የሆኑ መፃሐፍትን በማሳተም ረገድ ብርሃኑ ዘሪሁን በኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ፈር ቀዳጅ ሆኖ እንዲጠቀስ አስችለውታል። ‹‹ጣጠኛው ተዋናይ›› እና ‹‹ባልቻ አባ ነፍሶ›› የተሰኙ ተውኔቶችንም ጽፎ ለመድረክ አብቅቷል።
በ1958 ዓ.ም ያሳተመው ‹‹የቴዎድሮስ እንባ›› የተሰኘው መጽሐፉ የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስን አነሳስና ለኢትዮጵያ የነበራቸውን ራዕይ ብሎም የሕይወታቸውን ፍፃሜ የሚያሳይ ነበር። ብርሃኑ ይህን መጽሐፍ ከመፃፉ አስቀድሞ በነበሩት ጊዜያት ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ በይበልጥ የሚታወቁት በኃይለኛነታቸውና በጭካኔያቸው ስለነበር ውስጣዊ ስብዕናቸውና ሌሎች ባህርዮቻቸው ጎልተው አይነገሩም ነበር። እናም ብርሃኑ ዘሪሁን ያልተነገሩትን የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ባሕርያት ወደ አደባባይ በማውጣት ንጉሰ ነገሥቱ ብሔራዊ ጀግና መሆናቸውን የሚገልፅ ድርሰት ጽፎ በማቅረቡ የበርካቶችን ቀልብ መሳብ ቻለ። ይህ ‹‹የቴዎድሮስ እንባ›› የተሰኘው ታሪክ በኋላ ወደ መድረክ ስራ ተቀይሮ ከታላላቅ ትያትሮች ተርታ መሰለፍ ችሏል።
‹‹ድል ከሞት በኋላ›› የተሰኘው ስራው የሌሎች ሕዝቦችን ታሪክ መተረኩ ከብርሃኑ ስራዎችም ሆነ ከሌሎች በዘመኑና ከእሱም ቀድመው ከታተሙ ልብወለድ ድርሰቶች ልዩ እንደሆነ ይነገርለታል።
ሦስቱ ማዕበሎች እና ‹‹የታንጉት ምስጢር›› መጻሕፍቱ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ተተርከው ለሕዝብ በመቅረባቸው በበርካታ ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ አሉ።
የኢትዮጵያን ደራሲዎች ታሪክ ‹‹Black Lions – The Creative Lives of Modern Ethiopia’s Literary Giants and Pioneers›› በሚል ርዕስ የፃፉት ኖርዌጂያዊው ሩዶልፍ ሞልቬር፤ ብርሃኑ ዘሪሁንን ከኢትዮጵያ ታላላቅ ደራሲያን ተርታ አስቀምጠውታዋል።
አገርን እና ትውልድን በብዕሩ ቀለማት ሲዘክር የኖረው ደራሲና ጋዜጠኛ ብርሃኑ ዘሪሁን ሚያዝያ 16 ቀን 1979 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቶ ስርዓተ ቀብሩ በባለወልድ ቤተ ክርስቲያን ተፈፅሟል። ዘገባውን ስናዘጋጅ ባዩልኝ አያሌው ብርሃኑ ዘሪሁንና ድል ከሞት በኋላ በሚል የጻፉትን መጽሀፍ፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣን በምንጭነት ተጠቅመናል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16 ቀን 2014 ዓ.ም