አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በከፈተው ወረራ ገፈት ቀማሽ ከሆኑት ውስጥ አንዱ ነው። በዚህ ወረራ ቤት ንብረቱን አጥቷል። የንግድ ቤቱን ተዘርፏል። ግፍና መከራም ተፈራርቆበታል። የዛሬውን አያድረገውና ከዛሬ ሀያ ሶስት አመታት በፊት በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት እርሱም የመከላከያ ሰራዊት አባል ነበርና ውትድርናን ጠንቅቆ ያውቃል።
በውስጡ ያለው የአገር ፍቅር ስሜትና አልሸነፍ ባይነት ታዲያ ወራሪው ሃይል ወደ አፋር ጭፍራ ዘልቆ በገባበት ወቅትም ተንፀባርቋል። ምንም እንኳን ነፍጥ ይዞ ወራሪውን ሃይል ፊት ለፊት ገጥሞ ባይፋለምም ለኢትጵያ መከላከያ ሰራዊት ስንቅ በማቀበል፣ ቁስለኞችን በመንከባከብና ህይወታቸው ያለፈውን በክብር በመቅበር እውነተኛ የኢትዮጵያ ባለውለታ መሆኑን አስመስክሯል።
ወራሪው ሃይል ጭፍራን እስኪቆጣጠር ድረስ የሚችለውን ሁሉ አድርጎ በኋላ ላይ የባለቤቱንና ሶስት ልጆቹን ነፍስ ለማዳን ሲል ወደ አማራ ክልል፣ ጃንጀሮ ተብሎ ወደ’ሚጠራ አካባቢ ከሄደም በኋላ ቤተሰቡን ደብቆ ከሕወሓት ሃይል ጋር በሚችለው አቅም ሁሉ ለመፋለም ጥረት አድርጓል። ወራሪው ቡድን በመከላከያ ሰራዊት በደረሰበት ጠንካራ ምት ሙሉ በሙሉ ከአማራና ከአፋር ክልል ተጠራርጎ እስኪወጣም ድረስ እዛው ነበር።
ለፍቶ ያገኘባት፣ ተድሮ ልጅ የወለደባት፣ ነግዶ ያተረፈባት፣ ክፉ ደጉን ወዳ’የባት ጭፍራ ሲመለስ ግን ቤቱ ፈርሶ፣ ንብረቱ ተዘርፎ ጠበቀው። ተስፋ ቆርጦ ሙሉ ቤተሰቡን ይዞ ወደ ተወለደባት አዲስ አበባ በመምጣት በወንድሙ ቤት በጥገኝነት ተጠለለ።
አሁን ጥገኝነቱ አንገሽግሾታል። ባለቤቱም ልጆቹም ተመልሰን ወደ አገራችን እንሂድ እያሉ ሲወተውቱት አይኑ እምባ ያቀራል። እርሱም ቢሆን ብዙ አመት ወደ ኖረበትና ክፉውንም ደጉንም ወዳ’ሳለፈበት አፋር ጭፍራ መሄድ ይፈልጋል። ልጆቹም ያቋረጡትንና የሚወዱትን ትምህርት ለመጀመር ጓጉተዋል።
ይህ ሁሉ መከራና ስቃይ የደረሰበት ቢሆንም ህይወትን እንደ አዲስ ማጣጣም ይፈልጋል። ቤተሰቦቹም እንደዛው። ወደ አፋር ጭፍራ ዳግም ሄዶ ለመኖር ግን እርሱና መሰል ከሌላ አካባቢዎች የመጡና ኑሯቸውን በአፋር ጭፍራ ያደረጉ ሰዎች የመኖር ደህንነት ዋስትና ይፈልጋሉ።
የዛሬ የ”እንዲህም ይኖራል” እንግዳችን አቶ አቡበከር መርዕድ ይባላል። እድገትና ውልደቱ እዚሁ አዲስ አበባ፣ ሰሜን ማዘጋጃ አካባቢ ነው። ትምህርቱን እስከ ሰባተኛ ክፍል ድረስ በወይዘሮ ቀለመወርቅ ደበበ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል። በ1990 ዓ.ም የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ሲጀመር የሰራዊቱ አባል ሆኖ ዘመተ። ባድመ ላይ በተደረገው ጦርነትም ተመቶ ለህክምና መጀመሪያ ጎንደር በመቀጠል ደግሞ ወደ አዲስ አበባ ጦር ሃይሎች ሆስፒታል ተላከ።
ህክምናውን ካጠናቀቀ በኋላ ፍቃድ ቢጠይቅም በድጋሚ ወደ ሽሬ ግንባር እንዲሄድ ታዘዘ። ይሁንና የተሰጠው የአስራ አምስት ቀን ፍቃድ ከደረሰበት ጉዳት ሙሉ በሙሉ ለማገገም ስላልበቃው በአዲስ አበባ ለመቆየት ወሰነ። በኋላ ግን ከጦርነቱ የተረፉና የሞቱትን ለመለየት በየቀበሌው ፖሊሶች ፍለጋ ሲያካሂዱ እርሱም ተገኝቶ ከሌሎች ጋር ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወሰደ። ከዚያም ወደ ታጠቅ የወታደር ማሰልጠኛ አመራ።
ማጣሪያ ካደረጉ በኋላ እርሱን ጨምሮ ሰላሳ ወታደሮችን በዛው እለት ምሽት ላይ ለቀቋቸው። እንደገና በማግስቱ ከሰላሳዎቹ ውስጥ ከእርሱ ጋር አስራ አምስቱን ስንፍልጋችሁ ትመጣላችሁ በሚል መርጠው አሰናበቷቸው። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ቤቱ ገብቶ ቀረ። ስራም በቀላሉ ሊያገኝ አልቻለም።
መቼም ሁሌም ቤት መቀመጥ ለአእምሮም ለአካልም ጤና አይሰጥምና አቶ አቡበከር ኑሮን ለማሸነፍ ሲል እዚህ አዲስ አበባ አብሮት በተማረ አንድ ጓደኛው ገፋፊነት ወደ ወልድያ አቀና። ወልድያ ሄዶ ግን በቀላሉ ስራ ማግኘት አልቻለም። ወልድያ እያለ ግን የሰፈሩን ልጅ አገኘ። ስራ እንዳለገኘና ወደ አዲስ አበባ የሚመለስበትን መንገድ እንዲያመቻችለት ጠየቀው። የሰፈሩ ልጅም ችግር የለውም አለው።
በጊዜው ይህ የሰፈር ልጅ ተብዬው የመስኖ ፕሮጀክት ኃላፊ ነበርና ስራ ሊያሰራው ወደ አፋር ወሰደው። በዚህ የመስኖ ፕሮጀክት ውስጥም ከግንበኝነት እስከ አናፂነት ከአናፂነት እስከ ኤሌክትሪክ ሰራተኛነት አገለገለ። ውሃ አጣጩንም ከዛው አግኝቶ አገባ። ቤት በአፋር፣ ጭፍራ ተከራየ። ልጆችም ወለደ። በመስኖ ፕሮጀክት ውስጥ እያለ የቀሰመውን የግንባታ ስራ ሙያ በመጠቀም ያገኘውን የተለያዩ የግንባታ ስራዎችን ይሰራም ጀመር። ቀስ እያለም አነስተኛ የሸቀጣሸቀጥ ሱቅ ደጃፉ ላይ ከፈተ። በዚህ መልኩ ቤተሰቡን እየደጎመ ኑሮን ሲገፋ ቆየ።
የሕወሓት ሃይል የመጀመሪያውን ወረራ አፋር ላይ ሲያደርግ በርካቶች ቀያቸውን ለቀው ሲወጡ አቶ አቡበከርም አብሮ ወጥቶ ነበር። ሆኖም የመከላከያ ሰራዊቱ ወራሪውን ሃይል ከአካባቢው ጠራርጎ ሲያወጣ የአካባቢው ነዋሪ ሕወሓት ዳግም አይመለስም በሚል ሙሉ እምነት በፊት ከነበረው በተሻለ ንግዱንም አካባቢውንም ይበልጥ አሙቆት ነበር። እርሱም በጫካ ሸሽጓቸው የነበሩትን ልጆቹን አውጥቶ ዳግም ወደ ነበረው የህይወት እንቅስቃሴው ተመለሰ።
የሕወሓት ቡድን ጭፍራን ጨምሮ ሌሎች የአፋር አካባቢዎችን ዳግም ሲወር ነገሮች ሁሉ ተገለባበጡ። እንደዛ ሞቅ ብላ የነበረችው ጭፍራ በወራሪ ቡድኑ በደረሰባት ከፍተኛ ዝርፊያ እርቃኗን ቀረች። ኑሮን ለማሸነፍ ደፋ ቀና ሲል የነበረው የአቶ አቡበከር ቤት ንብረትም በአንድ ጀምበር ኦና ሆነ። ሱቁንም ተዘረፈ።
ይህ ሁሉ ሆኖ ታዲያ አቶ አቡበከር ቤተሰቡን ወደ ወረባቦ ጀንጀሮ ወደሚባል አካባቢ ካሸሸ በኋላ ከሰራዊቱ መለየት አልፈለገም። እንዲያውም የእርሱን ብቻ ሳይሆን እርሱ የሚኖርበትን አካባቢ ያወደመውን ይህን አረመኔ ቡድን ከሰራዊቱ ጎን በመሆን የመበቀያው ጊዜ ይህ መሆኑን በመረዳት ለሰራዊቱ ደጀን ለመሆን ወሰነ።
ከአካባቢው ሰው ሽሮ፣ በርበሬና እንጀራ እያሰባሰበ ለሰራዊቱ መስጠት ጀመረ። ቁስለኞች ሲያጋጥሙ ሌሎችን በማስተባበር ወደ ሌላ አካባቢ ሄደው እንዲታከሙ አደረገ። የሞቱት ደግሞ ተገቢውን ክብር አግኝተው እንዲቀበሩ ህዝቡን አስተባብሯል። ውሃ በጀሪካን ቀድቶና በጀርባው ተሸክሞ ለሰራዊቱ አቀብሏል።
ወራሪው ቡድን ገፍቶ ወደ ወረባቦ ከመጣም በኋላ አቶ አቡበከር ለሰራዊቱ ያለውን ደጀንነት በብዙ መልኩ አሳይቷል። እንደውም የመከላከያ ሰራዊት አባል የነበረ በመሆኑ መሳሪያ የማግኘት እድል ስለነበረና ቦታውም ለውጊያ አመቺ በመሆኑ በወረባቦ አካባቢ ያለውን ወጣት በማስተባበር እርሱ ከፊት ሆኖ ለመፋለም ዝግጁ የነበረ ቢሆንም የሚከተለው ሰው ግን ሊያገኝ አልቻለም።
ቆስለው በጤና ጣቢያዎች ውስጥ ላሉ የሰራዊቱ አባላትም ምግብ በማምጣት፣ ከባንክ ገንዘብ አውጥቶ በማቀበልና ከራሱም ጭምር ገንዘብ አውጥቶ በመስጠት ከፍተኛ ድጋፍ አድርጓል። ነገሮች ተጠናቀው ወራሪው ቡድን በመከላከያ ሰራዊቱ ተመቶ አካቢውን ከለቀቀ በኋላ መንገዶች ሲከፈቱ አቶ አቡበከርም ሙሉ ቤተሰቡን ይዞ ወደ አዲስ አበባ መጣ።
አዲስ አበባ ከመጣ በኋላም ወረባቦ እያለ ቁስለኞቹ ወደ እርሱ አካውንት ያስገቡትን ገንዘብ ለቤተሰቦቻቸውና ለሚቀርቧቸው በማስረከብ ትክክለኛ ኢትዮጵያዊ ጨዋነቱን አሳይቷል።
ረጅም አመታትን በአፋር ጭፍራ ያሳለፈውና በርሃ የለመደው አቶ አቡበከር ቀን ጥሎት ዛሬ በወንድሙ ቤት አዲስ አበባ ተጠልሏል። ወንድሙን እያስቸገረ ከእርሱ ጋር ተጠግቶ መኖሩ አሳቆታል። እጁ ላይ ምንም ነገር የለም። በዚሁ ጦርነት ጦስ ምክንያት በተለይ ሁለቱ ልጆቹ ያለትምህርት መቀመጣቸው በጣም ያሳስበዋል። ወደ ሁለት ወር እየተጠጋት ያለችው የመጨረሻ ጨቅላ ልጁን ለማሳደግም ዳግም ታች ላይ ማለት እንዳለበትም ያውቃል።
አፋር ጭፍራ ያለው ሁኔታ ከተስተካከለና ለመኖር አመቺ ሁኔታ ካለ አቶ አቡበከር አሁንም ቢሆን ተመልሶ ለመሄድ ዝግጁ ነው። እንኳን እሱ ይቅርና ባለቤቱና ልጆቹም ወደ አገራችን እንመለስ እያሉ ይወተውቱታል።
በአፋር ጭፍራ አቶ አቡበከርን መሰል በርካታ ከሌሎች አካባቢ መጥተው የእለት ጉርሳቸውን ለማግኘት የሚፍጨረጨሩ ብዙ ናቸው። እነዚህ ሰዎች በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለዋል። ሆኖም በአሁኑ ወቅት እነዚህ ሰዎች ወደ ቄያቸው ተመልሰዋል።
ልክ እንደነዚህ ሰዎች ሁሉ አቶ አቡበከርም ወደ ጭፍራ ተመልሶ የቀድሞ ህይወቱን ዳግም መጀመር ይፈልጋል። ነገር ግን ይህን ለማድረግ መንግስት ለነዚህ ሰዎች በበቂ ሁኔታ እርዳታ ሊያደርስ ይገባል ባይ ነው። ኑሯቸውን ሳይሳቀቁ እንዲገፉና ሰርተው እንዲበሉ መንግስት የመኖር ዋስትናቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅበታልም ነው የሚለው።
‹‹ይህን ሁሉ ድጋፍ ለመከላከያ ሰራዊቱ ያደረኩት የኢትዮጵያዊ ዜግነት ግዴታ ስላለብኝና ለአላህ ብዬ›› ነው የሚለው አቶ አቡበከር የወታደርን ህይወት እኔም ወታደር ሆኜ አውቀዋለው፤ ስለዚህ መከላከያውን ረዳሁ ሲል ይገልፃል። ይህን ሁሉ ነገር ሳደርግ ግን ለቤተሰቤና ለኑሮዬ ቅድሚያ መስጠት አቅቶኝ አይደለም፤ የአገር ፍቅር ህሊናዬ ይዞኝ እንጂ” ሲል እምባ እየተናነቀው ይናገራል።
እንደ አቶ አቡበከር ሁሉ በርካታ ያልተነገረላቸውና በዚህ ጦርነት ለአገራቸው ቅድሚያ ሰጥተው ሰራዊቱን ያገዙ፣ አብረው የተዋጉና ያዋጉ ህይወታቸውንም የገበሩ በርካቶች ናቸው። ግን ማን ያውራላቸው? ማን ይናገርላቸው? በእኛ ባህል ሁሌም ጀብዱ የሚነገርለት ከፊት ያለው ብቻ ነው።
‹‹የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ›› ነውና ተረቱ አቶ አቡበከርን የመሰሉና በጦርነት የኋላ ደጀን ሆነው ለአገራቸው ውለታ የዋሉ ሰዎች ሊመሰገኑና ሊሸለሙ ይገባል። አሁን ያሉበት የህይወት ሁኔታ ታይቶም በመንግስትም ሆነ በህብረተሰቡ በተለያየ መልኩ ድጋፍና እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል፤ የእለቱ መልእክታችን ነው። ሰላም!!
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15 /2014