ትውልድና እድገቷ የሽመና ባለሙያዎች ጥበባቸውን ከሚያፈሱበት ሰፈር፤ እጹብ ድንቅ የሆነው የእጅ ሥራዎቻቸው ሞልቶ ከተትረፈረበት ከጥበበኞቹ ደጃፍ ሽሮ ሜዳ ነው። የአገር ባህል አልባሳቱ በአይነት በአይነቱ በሚመረትበት አካባቢ ተወልዳ አድጋለች። ባህር በሆነው የሽመና መንደር ተወልዳ እንደማደጓ የአገር ባህል አልባሳትን ማምረት ባትችልም ተቀራራቢ በሆነው የጋርመንት ሥራ ተሰማርታ ውጤታማ መሆን ችላለች።
በወቅቱ ውጤት ሳይመጣላቸው እንደቀሩት እንደ አብዛኛው ተማሪ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግባት አልቻለችም። በውጤቷ ምክንያት በትምህርቷ ባትገፋም ለዛሬ ማንነቷ መሰረት የጣለላትን የጋርመንት ሥራ ለመሥራት ግን አላገታትም። እንዲያውም ከመቀጠር አልፋ ሌሎችን መቅጠር እንድትችል ሁነኛ ምክንያት ሆኗታል። ቤት ከመቀመጥ ውላ መግባትን ምርጫ በማድረጓ ሥራ ሳትንቅ በአንድ የጋርመንት ድርጅት ውስጥ ከስፌት ሥራ በጣም ቀላሉና ብዙም ልምድ በማይጠይቀው ረዳት ቀንጫቢ በመሆን በግለሰብ ድርጅት ውስጥ ተቀጥራ ሰርታለች። በዚሁ ድርጅት ውስጥ ተቀጥራ መሥራት ለመቻሏም ወላጅ እናቷ ምክንያት ነበሩ። ወላጅ እናቷ የድርጅቱን ባለቤት ያውቁት ኖሯልና ልጃቸውን ቀጥሮ እንዲያሰራት ተማጽነውታል።
ተቀጥራ የመሥራት አጋጣሚውን በማግኘቷ በድርጅት ውስጥ የሚሰሩ የተለያዩ ሥራዎችን በመልመድ ሙያዋን ከጊዜ ወደ ጊዜ አሻሽላለች። እራሷን የመለወጥ ትልቅ ፍላጎት የነበራት በመሆኑም በድርጅቱ የሚመረቱ ምርቶችን ልቅም አድርጋ በማወቅ የራሷን ድርጅት ለመክፈት የሚያስችላትን ሞያና ገንዘብ ለመያዝ ከፍተኛ ጥረት አድርጋለች። ጥረቷም ፍሬ አፍርቶ በአንድ የስፌት መኪና የጀመረችው የልብስ ስፌት ሥራ በአሁን ወቅት ወደ ድርጅት አድጎ ከራሷ አልፋ ለብዙዎች የሥራ ዕድል መፍጠር አስችሏታል።
በአንድ የስፌት መኪና በቤቷ ውስጥ ሥራ የጀመረችውና ዛሬ ላይ ከ160 በላይ የስፌት መኪናዎችን እንዲሁም ለጋርመንት ሥራ አስፈላጊ የሆኑ የተለያዩ ማሽኖችን ማትረፍ የቻለችው የዕለቱ የስኬት እንግዳችን ወይዘሮ ሀረጓ ወንድማገኝ የሀረጓ ጋርመንት ዋና ሥራ አስኪያጅ ናት። ሀረጓ ወደ ሥራው ስትገባ በቀዳሚነት ተቀጥራ ትሰራበት ከነበረበት ድርጅት ጤናማ በሆነ መንገድ በመሰናበቷ ድርጅቱ ያመረታቸውን የተለያዩ ምርቶች በማሻሻጥና አለፍ ሲልም ተመሳሳዩን የማምረት ጥሩ ዕድል ገጥሟታል።
በድርጅቱ በስፋት ይመረት የነበረው የቦቲ ጫማ ገበር መሆኑን ያስታወሰችው ሀረጓ፤ ተመሳሳዩን በማምረት ለገበያ ማቅረብ ቀዳሚ ሥራዋ ነበር። በወቅቱ ሁለት ሰራተኞችን ቀጥራ በመኖሪያ ቤቷ ታሰራ የነበረው የቦቲ ጫማ ገበር ሥራ እንዲሁም ሌሎች የልብስ ስፌት ሥራዎች እየተስፋፋ በመምጣታቸው የመሥሪያ ቦታ እጥረት አጋጥሟታል። በመኖሪያ ቤቷ ግቢ ውስጥ ቆርቆሮ በቆርቆሮ የሰራችው የመስሪያ ቦታ ከጥበቱ በላይ ሙቀቱ ለሥራ ምቹ አልነበረምና ለምትኖርበት ወረዳ ችግሯን አስረድታለች።
የአቃቂ ቃሊቲ ወረዳ ሰባት ጽህፈት ቤትም አስፈላጊ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት መቻሏን ካረጋጋጠ በኋላ 160 ካሬ ሜትር የማምረቻ ሼድ አስረክቧታል። በዚህ ጊዜ ታድያ ሀረጓ በስሯ የነበሩ ሁለት ሠራተኞች ላይ 28 ሠራተኞችን ጨምራ በድምሩ 30 ሠራተኞች ነበሯት። 30 ሠራተኞችን ይዛ በ160 ካሬ ሜትር የማምረቻ ሼድ ውስጥ ምርቶቿን ማምረት ቀጠለች። የተለያዩ የህጻናትና የአዋቂ አልባሳትን በጥራት እያመረተች ለገበያ ስታቀርብ ዕለት ዕለት ሥራው ውጤታማ መሆን ቻለ። በዚህ ጊዜ ታድያ 160 ካሬ ሜትር ሼድ አልበቃትምና ማስፋፋያ እየጠየቀች በአሁን ወቅት 408 ካሬ ሜትር የማምረቻ ሼድ ውስጥ 160 ሠራተኞችን ይዛ እየሠራች ትገኛለች።
600 ብር በተገዛች አንዲት ሲንጀር የስፌት መኪና የተጀመረው የሀረጓ ጋርመንት ከአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም ከአምስት ሺ ብር ጀምሮ እስከ አንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺ ብር ድረስ በመበደር ሥራውን ማስፋፋት ችላለች። በአሁን ወቅትም ብድሯን በመመለስ ከማምረቻ ማሽኖች በተጨማሪ ከሶስት ሚሊዮን ካፒታል በላይ ሃብት ማፍራት የቻለችው ሀረጓ፤ እዚህ ደረጃ ለመድረሷ ከፍተኛው ድርሻ የግል ጥረቷ ቢሆንም፤ ሴት ነጋዴዎችን በመደገፍ የተሰማሩበትን የንግድ ሥራ ማስፋፋት እንዲችሉ የገንዘብ ብድር እንዲሁም የተለያዩ ስለልጠናዎችን በመስጠት የሚታወቀው የሴቶች ልማት ፕሮጀክት ከፍተኛ ድርሻ የነበረው መሆኑን አጫውታናለች።
በሀረጓ ጋርመንት የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ሰራተኞች ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሴቶች ሲሆኑ በተለይም ከቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና በዘርፉ የሰለጠኑ ይገኙበታል። በድርጅቱ ከ120 በላይ የስፌት መኪናዎች ያሉ ሲሆን በስፌት መኪናው ከሚሰሩት ባለሙያዎች በተጨማሪ በቆራጭነት፣ በመዘምዘም፣ በረዳትነትና በሌሎች ሥራዎችም የተሰማሩ አሉ። በድርጅቱ ከስፌት መኪናዎች በተጨማሪ በቦታ ጥበት ምክንያት ከሥራ ውጭ ሆነው የተቀመጡ 37 ዘመናዊ ማሽኖች መኖራቸውን የጠቀሰችው ሀረጓ፤ ድርጅቱ አሁን ካረፈበት 408 ካሬ ሜትር ቦታ ተጨማሪ ማግኘት ከቻለ ማሽኖቹን ወደ ሥራ በማስገባት ተጨማሪ የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚቻል ትናግራለች።
ከሥራ ውጭ ሆነው የተቀመጡት 37 ዘመናዊ ማሽኖች ኦቨር ሎክንና ኢንተር ሎክን ጨምሮ ለጋርመንት ሥራ አስፈላጊ የሆኑ ማናቸውንም ሥራዎች መሥራት የሚችሉ ናቸው። ይሁን እንጂ ከዚህ ውጭ ባሉት ከ120 በላይ የስፌት መኪናዎች ግን ማንኛውንም አልባሳት በጥራት በማምረት ለገበያ እያቀረቡ ይገኛሉ። ጅንስን ጨምሮ ገበያው የጠየቀውን ሁሉ ማምረት እንደሚችሉ የገለጸችው ሀረጓ፤ በዋናነት የተለያዩ የሥፖርት ማሊያዎችን፣ ፖሎ ቲሸርቶችን፣ ሱሪ፣ ሸሚዝና ሌሎችን ይመረታሉ። በአብዛኛው ደንበኞች የሚፈልጉትን አልባሳት በሚሰጡት ትዕዛዝ መሰረት የሚያመርቱ ቢሆንም የሀረጓ ጋርመንት መለያ የሆኑ የተለያዩ ቁምጣዎችን አምርቶ ገበያ የሚጠብቅበት ሂደትም አለ።
በሀረጓ ጋርመንት በአብዛኛው ከሚቀጠሩ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ተማሪዎች በተጨማሪ ምንም የማያውቁ ሠራተኞች በቅንጫባና በረዳትነት ገብተው ስፌት ደራጃ ላይ የደረሱ ሠራተኞች ስለመኖራቸው ሀረጓ አጫውታናለች። በተለይም እራሷ ቆማ ያሰለጠነቻቸው ሠራተኞች ዛሬ ላይ እራሳቸውን ችለው የሚሰፉና የሚቆርጡ ስለመሆናቸው ትናገራለች። ለዚህም ዋነኛ ምክንያቷ የሠራተኞቹ ባህሪና ለሥራው ያላቸው ፍላጎትና የማወቅ ጉጉት ሲሆን ደሞዛቸው እየተከፈላቸው የሥራ ላይ ስልጠና ወስደው የሥራና የደምወዝ ዕድገት በማግኘት እየሠሩ ያሉ በርካቶች ናቸው።
‹‹የምናመርታቸውን ምርቶች በጥራት አምርቶ ተወዳዳሪ ለመሆን እየተጋን ነው›› የምትለው ሀረጓ፤ በተለይም ወደ ውጭ የሚላኩ አልባሳትን ማምረት የሚያስችል ደረጃቸውን የጠበቁ የተለያዩ ስልጠናዎችን ያገኘች እንደመሆኗ በአሁን ወቅት ጥራት ያላቸውን ልብሶች በስፋት በማምረት ከአገር ውስጥ አልፎ ወደ ውጭ ገበያ ለማቅረብ ዕቅድ አላት። ለዚህም ሲባል ለሠራተኞቿ የተለያዩ ስልጠናዎችን ማለትም በጥራት፣ በጊዜ ማድረስንና ተወዳዳሪ የሚያደርጉ ልምዶችን ለማካፈል ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር እየሰራች ትገኛለች።
በአገር ውስጥ የሚመረቱ አልባሳት ከውጭ አገር ከሚገባው ጋር ሲነጻጸር ብዙም ልዩነት የሌለውና አንዳንድ ጊዜ የአገር ውስጥ ምርት የሚበልጥበትንና የአገር ውስጥ ምርት በውጭው ዓለም ገበያ ላይ እንደሚገኝ አጋጣሚዋን ስታጫውተን፤ ከዱባይ አገር ተገዝተው ወደ አገር ቤት ከመጡ አልባሳት መካከል በኢትዮጵያ የተመረተ የሚል መለያ ያለው ልብስ ያጋጠማት ጓደኛዋ መኖሯን አስታውሳ ማህበረሰቡ በአገር ውስጥ ምርት እንዲኮራ ጥሪ አቅርባለች። በአገር ውስጥ መጠቀም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው ያለችው ሀረጓ፤ የሚመረቱት ምርቶችም ጥራት ያላቸውና ከውጭው የሚተናነሱ አለመሆናቸውንና ማህበረሰቡም ግንዛቤ የሌለው እንደሆነ አንስታለች።
ደንበኛው እንዲሰራለት የሚያዘው የልብስ አይነት በብዛት የውጭ አገር አልባሳት ሲሆን ለአብነትም በውጭ አገር የተመረተ አንድ ቲሸርት በማምጣት አስመስለው እንዲሰሩ ይጠየቃሉ። በተጠየቁት መሰረትም ምንም አይነት ልዩነት ሳይኖረው አምርተው እንደሚያስረክቡ የገለጸችው ሀረጓ፤ እንዲያውም የጎደለውን በመሙላት በተሻለ ጥራት የሚመረት መሆኑን ትናገራለች። በተለይም ከቻይና ታሽገው የሚመጡ የህጻናት አልባሳትን በምሳሌነት በማንሳት በጥራት የማይመረት እንደሆነና እጁ አልያም አንገቱ የሚጠብበትና እጅግ በጣም የሚሰፋበት አጋጣሚ እንዳለም ጠቁማለች።
ታድያ እንዲህ ያሉ ምርቶችን ስንመለከት በአገር ውስጥ የሚመረቱ አልባሳት ጥራት ያላቸው ለመሆናቸው ምስክሮች ነን የምትለው ሀረጓ፤ ደንበኞች ለማሳያነት የሚያመጡትን ልብስ ሳይቀር ጥራት ጨምረው የሚያመርቱ መሆናቸውን ትናገራለች። ምርቶቹን ለማምረት አስፈላጊ የሆነው ግብአትም በዋናነት ክር ሲሆን ክሩ የሚገኘው ከነጋዴ እንደመሆኑ ዋጋው በየጊዜው ይቀያየራል። ይሁን እንጂ አሉ የተባሉ ችግሮችን በመቋቋም ሀረጓ ጋርመንት ተወዳዳሪ ሆኖ መቀጠል እንዲችል ምርቶቹን በብዛትና በጥራት እያመረተ ይገኛል።
በጥራትና በብዛት የሚመረቱት የሀረጓ ጋርመንት ምርቶች የገበያ መዳረሻቸው በዋናት መርካቶና ኮልፌ ገበያ ላይ የሚገኙ ነጋዴዎች ናቸው። ጅምላ ነጋዴዎቹ የፈለጉትን የአልባሳት አይነት በሚፈልጉት መጠን ያዛሉ። ምርቱን ተረክበውም በችርቻሮ ለገበያ የሚያቀርቡ ሲሆን ከጅምላ ነጋዴዎች ተረክበውም በየአካባቢው የሚሸጡ ነጋዴዎች አሉ።
ቤት ከመዋል ወጣ ገባ ማለት መልካም ነው ብላ የጀመረችው የቅንጨባ ሥራ ሙያ እንድትማር ዕድል ከፍቶላታል። የቀሰመችውን ሙያም በተግባር ለመዋልና ተጠቅማ ሌሎችን ለመጥቀም ጊዜ አላጠፋችምና የጋርመንት ሥራዋን በቤቷ ውስጥ ከጀመረች ከአስር ዓመታት በላይ አስቆጥራለች። ከጊዜ ወደ ጊዜም ሥራዋን እያሻሻለችና እያስፋፋች ከሁለት ሶስት፤ ከአስር ሃያ ሰላሳ እያለች ለ160 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለችው ሀረጓ፤ ለሥራው ጥልቅ ፍቅር ያላት መሆኑን በመግለጽ በዘርፉ በርካታ ችግሮችን ተጋፍጣ ማለፍ መቻሏንም ትናገራች።
ወደ ድርጅቷ የምታቀናው ገና በማለዳ ሠራተኞች ሳይገቡ ሲሆን ሠራተኞች ከገቡ በኋላ አርፍዳ ስትገባ እንኳን ምቾት የማይሰማት ሀረጓ፤ ለሥራዋ የተለየ ፍላጎትና አክብሮት ያላት መሆኑን በመግለጽ፤ ውጤታማ መሆን የቻለችውም በዚሁ ምክንያት እንደሆነ ታምናለች። ማንኛውም ሰው ሥራውን ወዶትና ፈልጎት መሥራት አለበትም ትላለች።
ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻር በወረዳዋ የተለያዩ ድጋፎችን በተለይም ችግረኛ ለሆኑ ህጻናትና ሴቶች የአቅሟን ታደርጋለች። አገራዊ በሆኑ ማንኛውም ጥሪዎችም እንዲሁ ምላሽ በመስጠት ኃላፊነቷን ትወጣለች። በቀጣይም ባላት አቅም ሁሉ ማህበረሰቧን የማገልገልና አገራዊ ለሆኑ ጥሪዎች ምላሽ ለመስጠት ወደኋላ የማትል መሆኗን አረጋግጣልናለች።
በመጨረሻም ሰዎች በማንኛውም የሥራ ዘርፍ ውጤታማ መሆን ከፈለጉ ከትንሹ ሊጀምሩ ይገባል። የምትለው ሀረጓ፤ ከትንሽ መነሳት ትልቁ ያደርሳል በማለት በተለይም ወጣቱ፤ ፍላጎቱንና ውስጡ ያለውን ክህሎት በመረዳት ራዕይ ሰንቆ ሊንቀሳቀስ እንደሚገባና ሥራን ሳይንቅ እንዲሠራና እንዲለወጥ ትመክራለች። ታድያ በየትኛውም መንገድ ሲጓዙ ብዙ ተስፋ አስቆራጭ የሆኑ ነገሮች ቢገጥሙም ጥርስን ነክሶ ማለፍ የግድ መሆኑን አስረግጣ በመናገር ከሁሉ አስቀድሞ ግን ወጣቱ ራዕዩን ሊያስቀምጥ ይገባል ትላለች። ራዕይ ያለው ሰው ራዕዩን ተከትሎ በሚወደው ሙያ በመሰማራት ውጤታማ መሆን ይቻለዋል። በማለት ለወጣቱ ባስተላለፈችው መልዕክት አበቃን።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15 /2014